Tuesday, December 23, 2014

ሞትን ሸሽቶ ተራ ሞት ከመሞት ከገዳዮች ጋር ተፋልሞ በክብር መሞት የኢትዮጵያዊነት ምልክት ነዉ

ወጣቱ ትዉልድ በየትኛዉም አገር ወይም ህብረተሰብ ዉስጥ በአገር ልማት’፤ በመሰረታዊ ተቋሞች ግንባታና አገርን በመከላከል ስራዎች ላይ የተሸከመዉ ኃላፊነት ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የበለጠ ነዉ። እንደ ኢትዮጵያ አይነት ዘረኛ አምባገነኖች በነገሱበት አገር ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱት አገራዊ አደራና ሀላፊነቶች በተጨማሪ ወጣቱ ትዉልድ እራሱንና ወገኖቹን ከዘረተኝነትና ከአምባገነንነት አላቅቆ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ ስርዐት የመገነባት ተጨማሪ ሀላፊነት አለበት። ወጣቱ ትዉልድ የኢትዮጵያን አገራዊ ራዕይ የተሸከመ ደከመኝን የማያዉቅ ተከታታይነት ያለዉ የማይነጥፍ የህይወት ምንጭ ነዉ። በእርግጥም ወጣትነት የህይወት ህልምና ፊቺዉ አብረዉ የሚገለጹበት የእድሜ ክልል ነዉ። ወጣቱ ደግሞ ራዕይ ተሸካሚ ብቻ ሳይሆን የተሸከመዉን ራዕይ እዉን ሆኖ ለማየትና ለማሳየት ብቃቱ፤ ችሎታዉና ፍላጎቱ ያለዉ መበአካሉም በመንፈሱን ጠንካራ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ነዉ።

አገራችን ኢትዮጵያ በአለም ታሪክ ዉስጥ እንደ አገር ተመዝግባ በኖረችባቸዉ ረጂም አመታት ዉስጥ የየዘመኑ ወጣት ለእናት አገሩ ሠላም፤ ብልጽግናና የግዛት አንድነት መከበር ይህ ነዉ ተብሎ በቃላት ሊነገር የማይችል ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል ዛሬም እየከፈለ ነዉ። ትናንት በአባቶቻችን ዘመን የአገራቸዉን ዳር ድንበር በጠላት አናስደፍርም ብለዉ ጫካዉንና ዱሩን ቤታቸዉ ያደረጉ በላይ ዘለቀን፤ አብዲሳ አጋንና ጃገማ ኬሎን የመሳሰሉ ወጣቶች ነበሩን። በ1970ዎቹ ደግሞ ሰዉ በላዉን የደርግ ስርዐት ፊት ለፊት ተጋፍጠዉ ለእናት አገራቸዉ ኢትዮጵያ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ነበሩ። ዛሬም ዘረኛዉን የወያኔ ስርዐት ለማስወገድና አገራቸዉ ኢትዮጵያን የእኩሎች አገር ለማድረግ በየቀኑ የአካልና የሕይወት መስዋዕትነት የሚከፍሉ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ለምሳሌ በ1997 ዓም የህዝብ ድምጽ ይከበር ብለዉ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ያቀረቡ ከሁለት መቶ በላይ ወጣቶች የጦር ሜዳ መሳሪያ ከታጠቁ አግዓዚ ነብሰ ገዳዮች ጋር ባዶ እጃቸዉን ተጋፍጠዉ በክብር ተሰዉተዋል።

ከላይ ከፍ ሲል አጽንኦት ሰጠተን እንደገለጽነዉ ወጣቱ ትዉልድ የህብረተሰብ አንቀሳቃሽ ሞተር ነዉ። ሀኖም ሞተር ከራሱ ዉጭ ሌሎችን ማንቀሳቀስ የሚችለዉ መጀመሪያ እሱ እራሱ መንቀሳቀስ ሲችል ነዉ። የኢትዮጵያም ሆነ የማንኛዉም አገር ወጣት ሞተር ሆኖ የሚኖርበትን ህብረተሰብ ማንቀሳቀስ እንዲችል ከፍተኛ የመንግስትና የሁሉም ህብረተሰብ ያላሰለሰ ድጋፍ ያስፈልገዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ወጣቱ በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችልበት የፖለቲካ፤የማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ድባብ ያስፈልገዋል። እዚህ ላይ አንድ እጅግ በጣም የሚያሳዝነንና የሚያሳስበን ጉዳይ አለ፤ እሱም የኢትዮጵያ ወጣት የእድገት ሞተር ሆኖ አገሩን የሚያንቀሳቅስበት ቀርቶ እሱ እራሱም የነጻነት አየር የተነፈሰበት አንድም የታሪክ አጋጣሚ የለም። በተለይ በወያኔ ስርዐት ዉስጥ ከልጅነት ወደ ወጣትነት የተሸጋገረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገር፤ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ከሚባሉ ትልላቅ ብሄራዊ እሴቶች ጋር እንዳይተዋወቅ ተደርጎ ያደገ ወጣት ነዉ።

የዛሬዉ ዘመን ኢትዮጵያዊ ወጣት በጻፈ ቁጥር የሚደበደብ፤ ባነበበ ቁጥር የሚጋዝ፤ ተናግሮ ሀሳቡን በገለጸ ቁጥር ደግሞ ከየመንገዱ እየተለቀመ የት እንደደረሰ እንኳን ሳይታወቅ ደብዛዉ የሚጠፋ ቀን የጨለመበት ወጣት ነዉ። ባጠቃላይ ወያኔ ስልጣን ይዞ በቆየባቸዉ ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት ዉስጥ የኢትዮጵያ ወጣት የአባቶቹን ታሪክ እንዳያዉቅና ከዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ ጋር ሳይተዋወቅ ድቅድቅ ጨለማ ዉስጥ እንዲኖር ተደርጓል። የኢትዮጵያ ወጣት ከመረጃ ቴክኖሎጂ ጋር ተዋዉቆ እራሱን ካደራጀና ከጓደኞቹ ጋር ባሰኘዉ ግዜ ሁሉ ከተገናኘ በአገሩ የፖለተካና ማህበራዊ መድረኮች ላይ የሚጫወተዉን ሚና ወያኔ ስለሚረዳ የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ከወሰዳቸዉ እርምጃዎች አንዱና ዋነኛዉ ወጣቱ ህብረተሰብ ከመረጃ ቴክኖሎጂ ጋር ያለዉን የቅርብ ግኑኝነት መስበር ነዉ። ይህ ፀረ አገርና ፀረ ዕድገት እርምጃ ደግሞ ወጣቱን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ አገራችን ኢትዮጵያ በመረጃ ቴክኖሎጂ ዕድገትና ስርጭት የአለማችን የመጨረሻዋ ጭራ አገር እንድትሆን አድርጓታል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን ወጣት አማራጭ አሳጥቶ ከዚህ ቀደም ታይቶም ተሰምቶም በማያዉቅ ፍጥነትና ብዛት አገሩን እየጣለ እንዲሰደድ አድርጎታል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎችም አለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች ያደረጉት ጥናት በግልጽ እንደሚያመለክተዉ ምሁሩና ወጣቱ ትዉልድ በከፍተኛ ቁጥር ከሚሰደድባቸዉ አገሮች ዉስጥ ኢትዮጵያ በዓለዉ ዉስጥ ቀዳሚዉን ቦታ የያዘች አገር ናት። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የኢትዮጵያን አኮኖሚ የአፍሪካ የዕድገት ምልክት አድርገነዋል እያሉ ቢፏልሉም ይህ አሳደግነዉ የሚሉት ኤኮኖሚ ስራ አልባ ኤኮኖሚ በመሆኑ የራሱን አገር መገንባት የነበረበት ኢትዮጵያዊ ወጣት ወንድ ሴት ሳይል እጅግ በጣም በሚያስፈራ ፍጥነት አገሩን እየለቀቀ በመዉጣት ላይ ነዉ።

ዛሬ በዘለም ዙሪያ ከደቡብ ኮሪያ እስከ አዉስትራሊያ፤ ከሳዑዲ አረቢያ እስከ ካናዳ በየአህጉሩ፤ በየአገሩና በየደሴቱ ላይ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች የሌሉበት አገር የለም። በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የደርግን ጭፍጨፋ እየሸሸ ከአገሩ መሰደድ የጀመረዉ ኢትዮጵያዊ ወጣት ዛሬም ከ37 አመታት በኋላ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ አገዛዝ የለየለት ነብሰ ገዳይ አገፈዛዝ በመሆኑ የኢትዮጵያ ወጣት አሁንም አገሩን እየለቀቀ በመዉጣት ላይ ነዉ። የስደት ጉዞ ብርድና ቁር፤ ሀሩርና ንዳድ፤ እንዲሁም ህመም፤ ቁስልና ሞት የተቀላቀሉት ለወገንም ለባዳም የማይመኙት እጅግ በጣም አደገኛ ጉዞ ነዉ። ስደት ጉዞዉ ብቻ ሳይሆን ስደተኞች በስደት የሚኖሩበት አገርም ቢሆን ለአካልም ለመንፈስም የማይመች ቦታ ነዉ። ሴቶች እህቶቸቻችን በየቀኑ ወደ አረብ አገር የሚጎርፉት አካለቸዉ ላይ የፈላ ዉኃ እንደሚደፋ፤ ከፎቅ ላይ እንደሚወረወሩና በአረብ ጎረምሳ በየቀኑ እንደሚደፈሩ እያወቁ ነዉ ከወያኔ ጋር ከመኖር ስደት ይሻላል ብለዉ አገራቸዉን ለቅቀዉ የሚሰደዱት። ወንዶች ወንድሞፐቻችንም ቢሆኑ የሰሃራን በረሃና የቀይ ባህርን የመከራ ጉዞ ቆርጠዉ የሚገበቡበት ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ ብለዉ ነዉ እንጂ በየበረሃዉና በየባህሩ ላይ እንደወጣ የቀረዉ ኢትዮጵያዊ ቁጥር እጅግ በጣም ብዙ እንደሆነ ሳያዉቁት ቀርተዉ አይለደም። ለመሆኑ ኢትዮጵያዉያን ይህንነ ሁሉ ቸግርና ጣጣ እያወቁ ወነድ፤ሴት፤ ወጣት አዛዉንት፤ ሳራተኛና ገበሬ ሳይል ሁሉም በጅምላ እትብታቸዉ የተቀበረበትን አገር እየለቀቁ የሚሰደዱት ለምንድነዉ?

ኢትዮጵያዉያን የሚሰደዱት ወያኔን እየጠሉ ነዉ ወይም የወየኔ ዘረኝነት፤ ከፋትና ጥላቻ እንገፍግፏቸዉ ነዉ ብለዉ የሚገምቱ ብዙ ኢትዮጵያዉያን ሰዎች ሊኖሩ ይቻላል። በጥቅሉ ሲታይ ግምታቸዉ ትክክለኛ ግምት ነዉ፤ የወያኔ ዘረኝነትና ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ብዙ ኢትዮጵዉያንን አንገፍግፏል፤ አበሳጭቷል ወይም አስቆጥቷል። ሆኖም ሰዎች ስለተቆጡና ስለተንገፈገፉ ብቻ እንደ ምፅአት አገራቸዉን እየለቀቁ አይወጡም። ኢትዮጵያዉያን አገራቸዉን እየለቀቁ የሚወጡት ከወያኔ እስር፤ ድብደባና ግድያ ለማምለጥ ነዉ ብለን መገመትም እንችላለን። ትክክለለኛ ግምት ነዉ። ግን ስንቱ ኢትዮጵያዊ ነዉ ኬንያ፤ ማላዊ፤ ሞዛምቢክ፤ ግብፅ’ የመንና ሊቢያ ድረስ ሲንከራተት በየመንገዱ እየሞተ ለቀብር እንኳን የማይበቃዉ? ደግሞም የሰዉ ልጅ ባህሪይ የሚያሳድደዉንና የሚገድለዉን እየገደለ መሞት ነዉ እንጂ ሞትን እየሸሰ ጣረ ሞት ዉስጥ መግባት አይደለም። እዉነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ ወጣት አገሩን በገፍ እየለቀቀ የሚሰደደዉ የወያኔ ዘረኞች ተስፋዉን ስለገደሉበትና የወደፊቱን ስላጨለሙበት ነዉ።

ተስፋ የሰዉ ልጆች የመኖር ዋስትና ነዉ። እኛ ሰዎች እየከፋንም ቢሆን ደስ እንዳለዉ ሰዉ የምንኖረዉ ይኖረናል፤ ይመቸናል ወይም ክፉዉ ቀን አልፎ መልካም ቀን ይመጣል በሚል ተስፋ ነዉ።ተስፋ የሞተ ቀን ለምን እንደምንኖር ስለማናዉቅ አገር ጥለን መሰደድ ብቻ ሳይሆን ከዚህም የከፋ ብዙ ነገር ማድረግ እንችላለን። ወያኔ ስልጣን ይዞ የቆየባቸዉን ያለፉት ሓያ ሦስት አመታትን ትተን ከ2000 እስከ 2007 ያሉትን ሰባት አመታት ብቻ ስንመለከት ማላዊ ሀይቅ ወስጥ፤ ሰሃራ በረሃ ዉስጥ፤ ኤደን ባህረ ሰላጠና ባቢኤል መንደብ ዉስጥ እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ኢትዮጵያዊ የአዉሬ ስራት ሆኖ ቀርቷል። ነፃነትና የተሻለ ኑሮ እናገኛለን ብለዉ በኮንቴነር ተጭነዉ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይጓዙ የኘበሩ ከ50 በላይ ኢትዮጵያዉያን በእግራቸዉ እየተራመዱ ከገቡበት ኮነቴነር እሬሳቸዉ እየተጎተተ ወጥቷል።

ስደትንና እየተሰደደ ደብዛዉ የሚጠፋዉን ኢትዮጵያዊ በተመለከተ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ለጆሮ የሚከብዱ ዜናዎችን ሰምቷል። ባፈዉ ህዳር ወር ማለቂያ ላይ ከወደ የመን የተሰማዉ ዜና ግን ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ብቻ ሳይሆን ለምን ኢትዮጵያዊ ሆኜ ተፈጠርኩ የሚያሰኝ ነዉ። አገራቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ወያኔ ተስፋቸዉን ያጨለመባቸዉ አያሌ ኢትዮጵያዉያን እንደ ዜጋ የሚመለከታቸዉና የት ገቡ ወይም የት ደረሱ የሚል መንግስት ስለሌላቸዉ ለቀበር እንኳን ሳይበቁ ቀይ ባህር ዉጧቸዉ ቀርቷል። ለወትሮዉ ለኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ብዙም ግድ የሌለዉ የየመን መንግስት እንኳን ሰብዓዊነት ቆርቁሮት ቀይ ባህር እንደዋጠ ያስቀራችዉን ኢትዮጵያዉያን አስከሬን ፍለጋ ጀልባና መርከብ ሲያሰማራ፤ 99 በመቶ ኢትዮጵያዉያን መረጡኝ የሚለዉ የወያኔ አገዛዝ ግን የራሱ ዜጎች ሞት የተመቸዉ ይመስል ሰምቶ እንዳልሰማ ተመልካች መሆኑ አልበቃ ብሎት በተላላኪዉ ጠ/ሚኒስተር በኃ/ማሪያም ደሳለኝ አማካይነት ጭራሽ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ስደተኞችን ሲዘልፍና ሲያጥላላ ከርሟል። አሜሪካ፤ አዉሮፓና መካከለኛዉ ምስራቅ ዉስጥ በየጋዜጣዉ በየቴሌቪዥኑና በማህበራዉ ሜድያዉ የአንድ ሳምንት የመወያያ አርዕስት ሆኖ የከረመዉ የኢትዮጵያዉያኑ እልቀት አገራቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን ለይስሙላ እንኳን ስማቸዉ አልተነሳም።

አዎ እኛ ኢትዮጵያዉያን የትም እንኑር የት በህይወታችን ቆመንም ሆነ ሞተን ዜጎቼ ብሎ የሚቆረቆረልንና ለወገንና ለአገር ልጅ የሚደረገዉን ልዩ እንክብካቤ የሚየደርግልን መነሰግስ/ት የለንም። አልፎ አልፎ የወያኔ ባለስልጣኖች አዉሮፓና አሜሪካ ሲመጡ በየኤምባሲዉና በሚስጢር በሚያዙ ሆቴሎች ለዉይይት የሚጋብዙት ታማኝ ሎሌዎቻቸዉንና የአንድ አካባቢ ተወላጅ የሆኑ ሰዎችን ነዉ እንጂ ብዛት ያለዉን ሌላዉን ኢትዮጵያዊ የት ወደቀ ብለዉ እንኳን አይጠይቁም። እንዲያዉም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ ሁሉም የወያኔ ባለስልጣኖች በዉጭ አገሮች የሚኖረዉን ኢትዮጵያዊ እንደ ባዕድ መመልከና መዝለፍ ጀምረዋል። ይህ ሁሉ የሚያሳየን አገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ አገሮች እኛ ኢትዮጵያዉያን ተገናኝተን እርስ በርስ ካልመከርንና ችግሮቻችንን በጋራ እኛዉ ካልፋታን እንደ ዜጋ የሚንከባከብልን ቀርቶ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር የሚመለከተንም እንደሌለን ነዉ። ይህንን ደግሞ ባለፈዉ አመት ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ አሁን በቀርቡ ደግሞ የመን ዉስጥ በግልጽ አይተናል። ወገኖፐቻችን የሆኑ ኢትዮጵያዉያን የመን እንገባለን ብለዉ ቀይ ባህር ዉስጥ የአሳ ሲሳይ ሆነዉ ሲቀሩ በጠ/ሚኒስቴርነት ስም የወያኔ ተላላኪ የሆነዉ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ጭራሽ በአለም ዙሪያ የሱን እርግጫ፤ እስርና የጅምላ ግድያ ሸሽተዉ የተሰደዱ ሲትዮጵያዉያንን እጅግ በጣም አስነዋሪና አስጸያፊ በሆነ መለኩ ሲዘልፋቸዉ ተሰምቷል። የሚገርመዉ ባለፈዉ ህዳር ወር ማለቂያ ላይ ቀይ ባህር ዉስጥ ሰጥመዉ ካለቁት ከሰባ በላይ ወገኖቻችን ዉስጥ ገሚሶቹ ባለፈዉ አመት ከሳዑዲ ተባርረዉ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱና እነ ቴዎድሮስ አድሃኖም ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የማታደርጉወ ምንም ነገር የለም ብለዉ የተናገሩላቸዉ ሰዎች ናቸዉ።

ባጠቃላይ እኛ ኢትዮጵያዉያን አገራችን ዉስጥ ተዋርደናል፤ በስደት በምንኖርባቸዉ አገሮች ዉስጥም ተዋርደናል። አገር ዉስጥ ወያኔ እንዳሻዉ ያስረናል፤ ይደበድበናል ይገድለናል። ይህንን ጠልተን ከአገራችን ስንሰደድ ደግሞ በየበረሃዉና በየባህሩ ላይ ክብርና ወግ ላለዉ ቀብር እንኳን ሳንበቃ እንደወጣን እንቀራል። ካሁን በኋላ እንደ ህዝብ መብታችንና ነጻነታችን ተከብሮ አንደ አገር ደግሞ አንድነታችንና ዳር ድንበራችን ተጠብቆ ለመኖር የምንፈልግ ከሆነ አማራጩ አገራችንን አንደ ምጽዐት ለቅቀን መዉጣት ሳይሆን ለዚህ ሁሉ ዉርደትና መከራ ከዳረጉን ዘረኞች ጋር ፊት ለፊት መግጠምና ይለየለት ማለት ብቻ ነዉ። ወያኔ የሚፈጽምብን ሰቆቃ እንዲቆም፤ አስርና ግድያዉ አክትሞ ስደት እንዲያበቃ ብቸኛዉ አማራጭ እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ መግለጫ ማዉጣትና ከንፈር መምጠጥ ብቻ ሳይሆን የችግሮቻችንን ምንጭ ማድረቅ ነዉ፤ ወይም ዘረኛዉን የወያኔ አገዛዝና እሱ የገነባዉን ዘረኛ ስርዐት ነቃቅለን ማስወገድ ብቻ ነዉ። በዜግነታችን ተከብረንና በገዛ አገራችን ኮርተን መኖር የምንችለዉ ይህንን ስናደርግ ብቻ ነዉ።

No comments:

Post a Comment