Friday, December 12, 2014

የቅሊንጦ አንበሶች!

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ቅሊንጦ የሚባል ጫካ አለ እዚያ ጫካ ውስጥ በርካታ ጥቁር አንበሶች አሉ፡፡ ለጥቂት ቀናት እዚያ ጫካ ውስጥ ከትቸ ነበር፡፡ በገባሁ በዐሥረኛ ቀኔ ትቻቸው ወጣሁ፡፡ እዚያ በነበርኩበት ወቅት ካገኘኋቸው አናብስት የሁለቱን ታሪክ ብቻ በአጭር በጭሩ ላጫውታቹህ፡፡

አንደኛው አበበ ካሴ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው ጎንደር ነው፡፡ አምና 2006ዓ.ም. ጥር 12 ቀን ነበር የተያዘው፡፡ ወደዚህ ጫካ ከመምጣቱ በፊት በተለያዩ ሀገሪቱ ውስጥ ባሉ የማሰቃያ ቦታዎች ሰቆቃ ሲፈጸምበት ቆይቶ በመጨረሻ ነው እዚህ ጫካ ውስጥ የታሰረው፡፡ አበበ ካሴ የግንቦት 7 ቆራጥ ታጋይ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ከ1981-1993ዓ.ም. ድረስ የቀድሞው ኢሕዴን የአሁኑ ብአዴን ታጋይ ሆኖ ለ12 ዓመታት አገልግሏል፡፡ ከዚያ በኋላ እሱና ጓዶቹ ታግለው ለዚህ ያበቋቸው መሪዎቹ ከዚህ በስተቀር የማይባል ሁለንተናዊ ድጋፍ እየሰጠ ባበቃቸው ሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት ገደብ የለሽ ግፍና በደል አንጀቱን ሲቆርጥበት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የፍትሕ ጥያቄ የመመለስ ብቃቱ ወኔው ፍላጎቱ ጽናቱ እንደሌላቸው ባረጋገጠ ጊዜ ጥሏቸው በረሀ ገባ፡፡ በረሀ ሆኖ ለሦስት ዓመታት ያህል በግሉ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ በኋላ እንደሱ የከፋቸው ቢጤዎቹህ ተቀላቀለ ከዚያም ወደ ግንቦት 7 ተቀላቅሎ ድርጅቱ ላዘዘው ተልእኮ አምና ጎንደር ላይ እስከተያዘበት ቀን ድረስ ለ9 ዓመታት ያህል ነፍጥ አንሥተው ከሚታገሉ ወገኖች ጋራ ሲታገል ቆይቷል፡፡

ለአበበ ካሴ አምና ጥር 12 ገደኛ ቀን አልነበረችም፡፡ ያች ቀን የተሰጠውን ወታደራዊ ተልእኮ (mission) በዚህ አገዛዝ ባለሥልጣናት ላይ የሚፈጽምባት ቀን ነበረች፡፡ ለዚህ ለሚወስደው እርምጃ ከአጋሩ ጋራ ቅድመ ዝግጅት በሚያደርጉበት ሰዓት በጥቆማ ተያዙ፡፡

አበበ ጎንደር ከመግባቱ በፊት ከሁለት ጓዶቹ ጋራ ሆኖ ሙሉ ትጥቃቸውን እንደያዙ ከኤርትራ ተነሥተው የሱዳንን በረሀ ለ13 ቀናት በእግራቸው ተጉዘዋል፡፡ ወደ ሀገራቸው ምድር ገብተው እየገሰገሱ እንዳሉ ከወያኔ ካምፕ በቅርብ ርቀት ላይ በሆኑበት ሰዓት ከሁለቱ ጓዶቹ አንደኛው መሬት ላይ በመቀመጥ እንደደከመውና መንቀሳቀስ እንደማይችል ተናገረ፡፡ አበበም እንደ አለቃነቱ ያሉበት ቦታ ከወያኔ ወታደሮች ካምፕ ቅርብ ርቀት በመሆኑ አደገኛ መሆኑን አስገንዝቦ እንደምንም ተጠናክሮ ቦታውን ከመልቀቅ ውጭ ምንም አማራጭ እንደሌለውና እንዲነሣ አዘዘው፡፡ ጓዱ ግን ጨርሶ መንቀሳቀስ እንደማይችል ተናገረ፡፡ ይሄኔ ነበር አበበ ይህ ባልደረባው በእርግጥም የወያኔ ሰላይ እንደነበረ አልነሣም ያለውም ስለደከመው ሳይሆን ሆን ብሎ እንደነበር ያረጋገጠው፡፡

አበበ በዚህ ልጅ ላይ ጥርጣሬ አድሮበት የነበረው ሱዳን በረሀ ላይ እንዳሉ ያሉበትን ሁሌታ ለአለቆቹ ለማስታወቅ ከሁለቱም ነጠል ብሎ ስልክ ለመደወል በሚሞክርበት ሰዓት ድንገት ወደጓዶቹ ዞር ሲል ይህ አሁን ተቀምጦ አልንቀሳቀስም ያለው ጓዱ መሣሪያውን የማቀባበል እንቅስቃሴ ሲያደርግ ያየው ይመስለውና ስልኩን አቋርጦ ይመለስና መሣሪያውን ተቀብሎ ሲመለከተው በእርግጥም ተቀባብሎ አገኘው፡፡ ማን አዞት ለምን እንዳቀባበለው ሲጠይቀው “ሰው ከርቀት ያየሁ መስሎኝ ነው” ይለዋል ከዚያ በኋላ አበበ ይሄንን ልጅ በጥርጣሬና በጥንቃቄ ነበር የሚመለከተው፡፡ ሁኔታውን ለአለቆቹ ለማሳወቅ ስልክ ለመደወል በተደጋጋሚ ሞክሮ ሊሳካለት አልቻለም በግሉ ወስኖም ርምጃ መውሰድ አልፈለገም፡፡ ይህ ልጅ መሣሪያውን ያቀባበለው የነበረው እነ አበበን ለመግደል አስቦ ነበር፡፡

አበበ ይህ ጓዱ አልነሣም እንዳለው መሣሪያውን ይቀበለውና ሰላይነቱን እንዳወቀበትና ሊያደርግ የሚፈልገውንም ነገር ማድረግ እንዲችል ወደፈለገበት ቦታ እንዲሄድ ይፈቅድለታል፡፡ ይሄኔ ልጁ ይደናገጥና እንዲገለው አበበን ይጠይቀዋል፡፡ አበበም “እኔም ሆንኩ ድርጅቴ ሰው የመግደል ዓላማ የለንም አንተን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕና ነጻነት እራሳችንን መሥዋዕት ማድረግ እንጅ” የሚል መልስ ይሰጠውና ልጁን እንዲሔድ ያዘዋል ልጁ ከአሁን አሁን ተኩሶ ገደለኝ በሚል ጥርጣሬ ዐሥሬ እየዞረ በመመልከት ወደ ካምፑ አቅጣጫ ተጓዘ፡፡ አበበ እነኝህ አብረውት ያሉት ሁለቱ ጓዶቹ የተሰጣቸው ወታደራዊ ተልእኮና የትና ምን እንደሆነም ስለማያውቁ የዚህ ልጅ ከእነሱ መለየትና ሔዶ ለወያኔ ስለነሱ መናገሩ አላሳሰበውም፡፡ አበበና አንዱ ጓዱም በተቻለ ፍጥነት አካባቢውን ከለቀቁ በኋላ ሌሊት ሌሊት እየተጓዙ ጎንደር ከተማ ገቡ፡፡ ጎንደር እንደገቡም ሰዓቱ ሲደርስ ለጓዱ የሚወስዱት እርምጃ ምን እንደሆነና በማን ላይ እንደሆነም ከነገረው በኋላ በቦታው ላይ ቅድመ ዝግጅት በሚያደርጉበት ሰዓት ይሄ ከአበበ ጋር ያለው ጓዱ ቀደም ሲል ኤርትራ እያሉ አብሯቸው ለመታገል ግንቦት ሰባትን ተቀላቅሎ ከነበረ በኋላ ግን ድንገት ከተሰወረ ሰው ጋር ፊት ለፊት ዐይን ለዐይን ይጋጠማሉ፡፡ ይህ ሰው የሬዲዮ መገናኛ ይዟል ልጁ ተደናገጠ መለስ በማለት ቀጥ ብሎ አበበ ወዳለበት ቦታ ሔደ ይሄንን ሁኔታ ለአበበ እየነገረ ባለበት ቅጽበት አካባቢው በሦስት ካሚዮኖች በመጣ የፌዴራል ፖሊስ ተወረረ እነ አበበም በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡


ይህ እነ አበበን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሰው የወያኔ ደኅንነት ነው፡፡ ኤርትራ ሔዶ የአንድነት ፓርቲ አባል ነኝ በማለት ስሙ ተስፋዬ እንደሚባል ሁለት ዲግሪ እንዳለው አውርቶ የበረሀ ስሙን ታይሰን በሚል ሰይሞ እዚያ ታይሰን በሚባል ስም እየተጠራ ታማኝነት አግኝቶ ከተማ ድረስ እየተላከ ድንገት ተሰውሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በድርጅቱ ውስጥ የነበረ ሰው ነው፡፡

አበበ ከዚያች ቀን ጀምሮ ወደዚህ ወደ ቅሊንጦ እስከወረደበት ጊዜ ድረስ አስቀድሞ በጎንደር በኋላም እዚህ አዲስ አበባ በማእከላዊ የግንቦት 7ን አንዳንድ ምስጢሮችና እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉ የግንቦት 7 የስለላ መዋቅር ሰንሰለትና አባላትን፣ እጃቸው ላይ የተገኙትን ሊወስዱት አስበውት ለነበረው እርምጃ የሚያገለግሉ ሰነዶችን ማን እንደሰጣቸው እንዴት እንዳገኙት እንዲናገር ተጠይቆ ለመናገር ፈጽሞ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የሰው ልጅ የጭካኔ ደረጃ የተለካበት ሰቆቃ (ቶርቸር) ሲፈጸምበት ነበር የቆየው፡፡ የመጀመሪያዋና ቀላሏ እራቁቱን እጅና እግሩን አስረው የጉንዳን አሸን ላይ ነበር የጣሉት በዚህ አልሆን ሲላቸው እያገላበጡ አንጠልጥለው ገረፉት አሁንም አልሆነላቸውን ሰቆቃውን እያከበዱት መጡ ውኃ የተሞላ የፕላስቲክ ጠርሙዝ ብልቱ ላይ አንጠለጠሉበት በዚህ ሁሉ መከራ ወይ ፍንክች ያለው አበበ ደረቱላይና ውስጥ እግሩ ላይ ኤሌክትሪክ አያይዘው አቃጠሉት አበበ ግደሉኝ እንጅ ምንም ዓይነት ኢሰብአዊ የጭካኔ ድርጊት አይበግረኝም ብሎ እንቅጩን ነገራቸው፡፡ ርሕራሔ ያልፈጠረባቸው አውሬዎቹ የአበበን የእጆቹንና የእግሮቹን ጣቶች ጥፍሮች እያንዳንዳቸውን በተራ በተራ እየገሸለጡ እየቦጨቁ እየፈነቀሉ ጣሏቸው ቆራጡ ጨካኙ ጀግናው አበበ ግን ጽናቱ ወደር አልነበረውምና ጨርሶ ሊፈታላቸው አልቻለም፡፡ አውሬዎቹ ተስፋ ቆረጡ ከአበበ ምንም እንደማያገኙ ሲገባቸው ማእከላዊ ጨለማ ክፍል ውስጥ ወርውረውት ከቆዩ በኋላ ከዚያ አውጥተው እሱን ወዳገኘሁበት ቦታ ወደ ቅሊንጦ አመጡት ከዚህ በኋላ የሚቀራቸው እሱን ለመበቀል መግደል ብቻ ነው፡፡ እስከአሁን ይሄንን አላደረጉም፡፡ ሲመስለኝ ይሄንን እንዳያደርጉ ያደረጋቸው ይህ ሥርዓት ሰቆቃ (ቶርቸር) በዜጎች ላይ እንደማይፈጽም በኢትዮጵያ ውስጥ ይደረግ የነበረው ሰቆቃ በደርግ ሥርዓት እንደቀረ ለሰብአዊ መብት ድርጅቶችና ለምዕራባዊያን መንግሥታት ሳያሰልስ ስለሚደሰኩር አበበ ደግሞ በእነዚህ አካላት በወያኔ እጅ እንዳለ መታወቁ ይኔንን የመጨረሻ እርምጃ እንዳይወስዱ አድርጓቸዋል፡፡

አሁን አበበ ከሌሎች ወንድሞችና እኅቶች ጋር የግንቦት ሰባት አመራር ተብሎ ክስ ተመሥርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ነው፡፡ በዚህ አገዛዝ ሳንባ የሚተነፍሰውና የሀገርንና የሕዝብን ጥቅሞች ሳይሆን ከሀገርና ሕዝብ ጥቅሞች ጋራ የማይጣጣመውን የሥርዓቱን ጥቅም ለማስጠበቅ ከሚሠራ “ፍርድ ቤት”፤ የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ሳይሆን የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ተጎድቶ የቡድን ጥቅም በሚጠበቅበት በሚከበርበት በወያኔ ፓርላማ ሰላማዊ አማራጮች ፈጽሞ ስለተዘጋባቸውና የዜግነት ግዴታቸው የታሪክ አደራ አላሳርፍ ብሏቸው ለሀገርና ሕዝብ ፍትሕ ነጻነትና እኩልነት በመታገላቸው፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከግፍ አገዛዝ ነጻ አውጥተው የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ ይህ አገዛዝ የተወላቸውን ብቸኛ አማራጭ በመጠቀማቸው በዚሁ ምንም ዓይነት የሕዝብ ውክልና በሌላቸው በወያኔ ቡድን ስብስብ ፓርላማ ተብየ በወጣ ሰብአዊ መብቶችን ዓለማቀፋዊ ድንጋጌዎችንና የገዛ ሕገ መንግሥታቸውን በቀጥታ በሚጻረር ሕግ አላግባብ አሸባሪዎች ስለተባሉ ብቻ ግንቦት ሰባትንና የአርበኞች ግንባርን አሸባሪ ናቸው ብሎ ከሚያምንና ከተቀበለ ፍርድ ቤት ፍትሕ ባይጠበቅም ፍርድ ቤት አቅርበዋቸዋል፡፡

አበበና ሌሎች ወገኖች ፍርድቤት በቀረቡ ጊዜ በተለይም በአበበ ካሴ ላይ የተፈጸመበትን ኢሰብአዊ የግፍ ዓይነቶች ለፍርድ ቤቱ በሚያስረዱበት ጊዜ ዳኛው እሱ ራሱ ይናገር እናንተ ምንድን ናቹህ? በማለቱ በሰው ተደግፎ የቆመው ቆፍጣናው ጎንደሬ አበበ ካሴ ዳኛው ያልጠበቀውን መብረቃዊ ቃላቶች በዳኛው ላይ አወረደበት ዳኛው ደነገጠ “ነገሩህ እኮ!” አለ አበበ “ምኑን ነው የምነግርህ?” ሲልም ጠየቀ “ለመሆኑ አንተ ዳኛ ነህ? ዳኛ ነኝ ብለህስ ራስህን ትቆጥራለህ? ለዜጎች የፍትሕ ጥያቄ ፍትሕ የመስጠት ነጻነቱና ብቃቱስ አለህ? ለመሆኑ በዚህች ሀገር ፍርድ ቤት አለ? የማናውቅ መሰለህ አንተ ዳኛ ሳትሆን ካድሬ ነህ፡፡ ቀን ቀን ዳኛ ነኝ ብለህ ካባ ደርበህ ትውላለህ ሌት ሌት ፋቲክ ለብሰህ ሕዝብ ስታሰቃይ ስትቀጠቅጥ የምታድር የሕዝብ ጠላት ነህ” አለ አበበ፡፡ አበበ ወኔውና ጽናቱ ዳርቻ የለውም፡፡

ይሄንን የአበበን ታሪክ መጀመሪያ ከሌሎች በኋላም ከራሱ ስሰማ ትውስ ያለኝ የነ አቶ መለስ ጀግና አሞራው ነበር፡፡ በእርግጥ አሞራው በአበበ ዐይን ሲታይ ትንኝ ነው፡፡ የሰማይና የምድር ርቀት አላቸው፡፡ ይሄም ልዩነታቸው መሰለኝ እንዳስታውሰው ያደረገኝ፡፡ ለነአቶ መለስ ግን አሞራው የጀግናና የጽናት ምሳሌ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከአሞራው ጋራ ያደረገውን ቃለ ምልልስ ዐይታቹህታል፡፡ በቃለ ምልልሱ አሞራው ምንም እንኳን ደርግ እንዲናገርለት የፈለገውን ነገር ባይናገርለትም አቀራረቡ ግን ምን ያህል የተለሳለሰ እንደነበር ታስታውሳላቹህ፡፡ “ሕወሀት ደርግ ከያዛቹህ እንዲህ ያደርጋቹሀል እንዲህ ያደርጋቹሀል” እያለ የሕወሀት ካድሬዎች ምን እያሉ እንደሚሰብኳቸው ተንትኗል፡፡ ያውም እንግዲህ ይሄ የቀረበው አሞራውን ለትዝብት ሊዳርጉ የሚችሉ ብዙ ነገሮች ከመሀሉ ተቆራርጦ እንደቀረበ የቀረበው ቪዲዮ (ምስለ ትዕይንት) ያረጋግጣል፡፡

ቆፍጣናው አቤ ግን ቀድሞ ነገር መቸ ፊት ሰጣቸውና እንኳን እንደ አሞራው እንዲህ ነው እንዲህ እያለ ሊቀበጣጥር ይቅርና! ለምርመራ በመጡበት ቁጥር ተናግሮት የማያልቀውን እንደ መብረቅ የሚያነዱ ካላቶቹን ያዘንብባቸዋል፡፡ የምርመራ ሥራቸውን ለመሥራት ዕድል ባይሰጣቸው ከሱ ጋራ ስድብና ብሽሽቅ መግጠሙን ሥራ አድርገው ይዘውት ነበር፡፡

ከዚያ ሁሉ መከራው በኋላ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች የቪዲዮ ካሜራቸውን (መቅረጸ ምስለ ትዕይንታቸውን) ተሸክመው አበበ እንደማያውቃቸው ሁሉ ልክ ነጻና ተቆርቋሪ ጋዜጠኛ በመሰለ አቀራረብ ቀርበውት ነበር አልተሳካላቸውም፡፡ እነሱም ቅመሱ ብሏቸው አይደል ሲያከለፈልፍ ያመጣቸው? አጠጣቸዋ እስኪበቃቸው! ፀረ ኢትጵያነታቸውን ፀረ ሕዝብነታቸውን እየዘከዘከ አንባረቀባቸው፡፡ ካልደመሰሱት ወያኔ አሞራውን እንዳሳየ ሁሉ ነገ ሀገር ነጻ ስትወጣ አበበን ዕናይ ይሆናል፡፡ የዛ ሰው ይበለንና ፈጣሪ፡፡

ዛሬ አበበ በዛ በተፈጸመበት ዘግናኝና አረመኔያዊ ጭካኔ የተሞላበት የግፍና ሰቆቃ ዓይነቶች የተነሣ ከጭንቅላቱ እስከ እግሩ ድረስ የግራ ጎን ሰውነቱ በድን ሆኖ ደርቋል፡፡ ብልቱ ያዣል ፈሳሽ አለው ጥፍሮቹ ግን እንደገና በቅለዋል፡፡ በእነዚህ ህመሞች እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ቀይ መስቀል መጥቶ በጎበኘው ሰዓት በራሱ ወጪ ሙሉ ሕክምና እንዲያደርግለት አገዛዙን ፈቃድ ሚጠይቅም አገዛዙ ሊፈቀድለት አልቻለም፡፡

አቤ በውጭ ጋዜጠኞችም ተጎብኝቷል ቃለ መጠይቅም አድርገውለታል ቆፍጣናው መብረቁ አቤ ለነሱስ ቢሆን መቸ ተመለሰ? ለዚህች ሀገር ውድቀት ለዚህ ሕዝብ ስቃይና መከራ መንግሥቶቻቸው ተጠያቂዎች መሆናቸውን እስኪደነግጡ ድረስ ነግሯቸዋል፡፡ ወንድሜ አበበ ካሴ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ባለህበት ይጠብቅህ፡፡ አበበ አንዱ ምሳሌ ነው ገድሎቻቸውን ሰው ሳያውቅላቸው ሳይሰማ ሳያይላቸው ከዓላማቸው ፈቀቅ አንልም እያሉ ከሀቃቸው ጋር በመጽናት፤ አጨካከናቸው ግድል አድርገው ሊገላግሏቸው እየቻሉ በሰቆቃ ብዛት ነፍሳቸው ሳይወጣ በወደቁበት ገምተው ተልተው ተጠራሙተው እንዲሞቱ ያደረጓቸው በርካታ ዕንቁ ጀግና አንበሳ ዜጎች እንዳለፉ በእነዚህ የማሰቃያ የምድር ሲዖል ቦታዎች ለቶርቸር (ለሰቆቃ) ገብተው ከወጡ ሰዎች የዐይን ምስክሮች ተረድቻለሁ፡፡

አንድ የገረመኝ ነገር ቢኖር እነኝህ ጀግኖች ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ከገበሬው ማኅበረሰባችን የወጡ መሆናቸው ነው፡፡ በእርግጥ አንድ ግልጽ ነገር አለ የሀገር ፍቅር ስሜት ከከተማ ሰው ይልቅ በገጠር ሰው ይጠናል፡፡ የዚህም ምክንያቱ የሚመስለኝ ሀገር ማለት በድንበር ተከልሎ ያለው መሬትና በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ ማለት ነውና የገጠር ሰው ደግሞ ሕይዎቱ የተመሠረተው በግብርና ስለሆነና ከአፈሯ ከውኃዋ ከእጽዋቷ ከአዕዋፋቷ ከእንስሳቷ ከሁለመናዋ ጋር ያለው ግኑኝነት ቅርብና ቀጥተኛ በመሆኑ የመሬቷ የውኃዋ የሌሎች ሀብቶቿ ዋጋ ስለሚገባው ጋራ ሸንተረሯን በእግሩ ስለሚወጣ ስለሚወርድባት ወዙ ከወዟ ላቡ ከላቧ ጋር ስለሚሞጋሞግ ስለሚሻተት ስለሚቀዳ በክረምቱ ከመኸሩ በበጋው በጸደዩ የተለያየ ዓይነት ማራኪ ውበት ገጽታዋ በዐይነ ሥጋውና በዐይነ ሕሊናው ላይ ታትሞ ስለሚቀረጽበትና በእነዚህ ምክንያቶች ፍቅሯ የግዱን በልቡ እንዲያድርበት ስለሚያደርገው ይመስለኛል፡፡

የከተማ ሰው ግን ግፋ ቢል የበዓልና የበዓል ግርግሩ ካልሆነ በስተቀር እንደ ገጠሩ ሰው ስለሀገሩ በተለየ እንዲያስታውስ እንዲናፍቅ የሚያደርገው ጠንካራ ትስስር ስለሌለው የሀገር ነገር ብዙም የሚደንቀው አይደለም፡፡ ይሄንን ነገር ምሁራን በሚባሉትና ባልተማሩት ወገኖች መሀከል ብናየውም ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ምሁራን የሚባሉት የፈለገ ነገር ቢሆን ግፋ ቢል “የተጠየቀውን በመጠኑ ለመቀነስ” ወይም “ሁሉንም ከማጣት ጥቂት ለማግኘት” እንደራደር ይላሉ እንጅ ያልተማረው እንደሚለው “እሞታለሁ እሠዋለሁ እንጅ የሀገሬን ጥቅምማ አሳልፌ አልሰጥም” አይሉም፡፡ ምሁራን ነፍሳቸውን ይወዳሉ ጥቅመኛም ናቸው ለሚጨበጠው ለቁሳዊ ነገሮች ያላቸው ግምትና ዋጋ ከፍተኛ ነው ለማይጨበጠው ለመንፈሳዊ ሀብቶች ግድ የላቸውም፡፡ እንደ መሥዋዕትነት የሚፈሩት ነገር የለም በተቻላቸው መጠን መሥዋዕትነትን በሚጠይቅ ጉዳይ ዙሪያ አይደርሱም፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የዜግነት ግዴታቸውና መማራቸው የጣለባቸው ኃላፊነት ሆኖ እያለ መሥዋዕትነት በሚጠይቅ ቦታ ሁሉ ላይ ምሁራኖቻችንን የማታዩዋቸው፡፡ በፖለቲካው(በእምነተ አሥተዳደሩ) ብቻ ሳይሆን በሰብአዊ መብቶች ጥበቃና ግንዛቤ ፈጠራ ዙሪያ በሚሠሩ ድርጅቶችም በመሳተፍ ሲሠሩ የማታዩዋቸው፡፡

ሳይበላ ሳይጠጣ ሳይለብስ ሳይጫማ ሳይማር ግብሩን ከፍሎ ለዚህ ያበቃቸውን ወገንና ሀገር ውለታቸው አለብኝ ዕዳ አለብኝ ብለው ቅንጣትም እንኳን የባለዕዳነት ስሜት ሳይሰማቸው የግል ቁሳዊ ጥቅማቸውን ብቻ በማሰብ ሀገር አስተዋጽኦዎቻቸውን እጅግ እየፈለገች እያለች “ስትፈልጊ ለኔ ስትይ አራት እግርሽን ንቀይ!” እያሉ እየጣሏት የሚሔዱት፡፡ ያልተማረ ገበሬ ብለን የምንንቃቸው ግን በሀገር ጥቅምና ክብር በመጣ ነገር ያለማወላወል ዐይናቸውን ሳያሹ አንዲት ነፍሳቸውን ለመስጠት ሲሰለፉ ነፍሳቸው መተኪያ የሌላት እንደሆነች እንኳን አያስመስሏትም፡፡ ይህ ከሕዝባችን ቁጥር 85 % ይይዛል የሚባለው የገጠር ሰው ባይኖር ኖሮ እኮ እንደከተሜውና ምሁር ተብየው አስተሳሰብ ቢሆንማ ይህች ሀገር ዛሬ ላይ በታሪክ እንደሁ እንጅ በእውን ባልተገኘች ነበር፡፡

ወደ ሁለተኛው አንበሳ አጭር ታሪክ ልለፍ ኦኬሎ አኳዬ ኡቸላ ያባላል የጋምቤላ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሆኖ እያገለገለ እያለ 1996ዓ.ም. ይህ የአገዛዝ ሥርዓት በአኙዋክ ጎሳ ላይ የፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያጋለጠ ጀግና ነው፡፡ ኦኬሎ እንደነገረኝ ያ የዘር ማጥፋት ወንጀል በተፈጸመበት ወቅት መጀመሪያ ላይ 550 የአኙዋክ ተወላጆች ነበሩ እንዲጨፈጨፉ ትእዛዙን ላስፈጸመው በወቅቱ የክልሉ የጸትታና የደኅንነት ክፍል ኃላፊ ለነበረው ከአቶ ኦኬሎ በኋላ ደግሞ ርእሰ መሥተዳድር ሆኖ የቆየውና በኋላ ላይ አገዛዙ ይሄንን በአኙዋኮች ላይ የፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰውየው እንዳስፈጸመው አድርጎ ሲወነጅለው “እኔ የታዘዝኩትን ነው የፈጸምኩ ትእዛዙን ያዘዙኝ አቶ መለስ ናቸው እኔ የምጠየቅ ከሆነ ይህ ክስ በቅድሚያ እሳቸውን ተጠያቂ ያድርግ” ላለው ለአቶ ኡመድ ኡቦንግ የስም ዝርዝራቸው ተሰጥቶት የነበረው፡፡ ቀጥሎና በሁለተኛው ዙር ደግሞ የ250 ሰዎች ዝርዝር መጣ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ እኔ ነበርኩ ይላል አቶ ኦኬሎ፡፡

አቶ ኦኬሎ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ (ዶቸቬሌ) ጋዜጠኛ የነበረችውን ወ/ሮ አሰገደች በርታን አመስግኗት አይጠግብም፡፡ ነፍሴን ያተረፈችልኝ እሷናት ይላል፡፡ አቶ ኦኬሎ ምንም በማያውቀው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሐሰተኛ ዜና ለቆ ምንጩንም አቶ ኦኬሎን አድርጎ ስለነበር አንጋፋዋ በሳል ጋዜጠኛ ወ/ሮ አሰገደች በርታ ወደ አቶ ኦኬሎ ደውላ የዜናውን ትክክለኝነት ስትጠይቅ አቶ ኦኬሎ ፈጽሞ ሐሰት እንደሆነና ግጭቱ በአኙዋክና ኑዌር ጎሳዎች መሀከል የተፈጸመ ሳይሆን የመከላከያ ሠራዊቱ በአኙዋኮች ላይ የፈጸመው እንደሆነ ስለነገራት ወ/ሮ አሰገደች ይሄንን ዘገባ በጀርመን ድምፅ ራዲዮ ለቀቀችው፡፡ ያ ዜና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲለቀቅ አቶ ኦኬሎን ምሽቱን ሁሉ በስብሰባ ወጥረውት ስለ ነበረ አላየውም ነበር፡፡

ይህ ትክክለኛ ዜና በጀርመን ድምፅ ራዲዮ እንደተሰማ በማግስቱ አገዛዙ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ጋዜጠኞች አምጥቶ ለጀርመን ራዲዮ የሰጠኸውን ቃል አስተባብልና መግለጫ ስጥ ይሉታል፡፡ እሱም የተናገረው ያየውንና የሚያውቀውን እንደሆነ በመግለጽ ይሄንን እንደማያደርግ ሲናገር በቅርብ ክትትል ስር አድርገውት እያለ ባገኛት ክፍተት ተጠቅሞ ወደ ሱዳን ተሰደደ ለ6 ቀናት በእግሩ ተጉዞም ሱዳን ድንበር ላይ ደረሰ ሱዳን ገብቶ ከዲፕሎማቲክ አካላት ጋራ ግንኙነት በማድረግ ወደ ኖርዌይ ወጣ ብዙም ሳይቆይ የኖርዌይ ዜግነትን ያዘ ባለቤቱንና ልጆቹንም አወጣ፡፡ አቶ ኦኬሎ እነኝህን ነገሮች ማሳካት ቢችልም አገዛዙ አርፎ አልተኛለትም ነበር፡፡ አቶ ኦኬሎ እንደነገረኝ ለአደጋ የሚዳርጋቸውን ከባድ ምስጢር ይዞባቸው እንደወጣ የተረዱት አቶ መለስ ዜናዊ አቶ ኦኬሎን እዚያ በሚኖርበት ሀገር ለአንዲት የዩኒሴፍ ሠራተኛ 10.5 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል ሊያስገድሉት ሞክረው እንደነበር ይናገራል፡፡ ይህ ሙከራ ከከሸፈ በኋላም ወ/ሮ አዜብ መስፍን ለማፍያ ቡድን 6 ሚሊዮን ዶላር ከፍለው ልጀንና ሚስቴን ሊያስገድሉብኝ ሞክረው ነበር በማለት ይሄም እንደከሸፈ ይናገራል አቶ ኦኬሎ፡፡

አቶ ኦኬሎ በወገኖቹ ላይ በ21 መቶ ክ/ዘ በጠራራ ፀሐይ የተፈጸመው ግፍ እረፍት ስለነሳው ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ሆኖ በ2004ዓ.ም. GDM (Gambella Democratic Movement) የተሰኘ ፓርቲ አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ እያለ ሌሎቹ የፓርቲው አባላት ዓላማችን መገንጠል ነው በማለታቸውና እሱ ደግሞ መገንጠልን ባለመፈለጉና መፍትሔም አይሆንም ብሎ በማመኑ በተፈጠረ የዓላማ ልዩነት ምክንያት ትቶ በመውጣት አምና ሊያዝ አካባቢ GDAM (Gambella Democratic Alliance Movement) የሚልፓርቲ መሥርቷል የኦኬሎ ሕልም ራስገዝ (self determination) ማለትም ወያኔ እያደረገው እንዳለው የውሸት ፌዴራሊዝም ሳይሆን ትክክለኛ ፌዴራላዊ አወቃቀር ያላት ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡ መገንጠል መፍትሔ እንዳልሆነ ጠንቅቆ ያውቃል እነ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራን እየጠቀሰም ያስረዳል፡፡ የፌዴራሉ የክልል መንግሥታት የክልል አወቃቀር የብሔረሰቦችን አሰፋፈር መሠረት ማድረጉ ችግር ይኖረዋል ብሎ ስለሚያስብ ብሔረሰቦች እራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እስከቻሉ ጊዜ ድረስ የክልል አቀወቃቀሩ የደርግ ዘመኑ ክፍላተ ሀገራት ቢሆን ችግር እንደሌለበትና ድንበርን መንስኤ አድርጎ ዘወትር የሚቀሰቀሰውን አሰልቺ የብሔረሰቦችንና የጎሳዎችን ግጭቶችን እንደሚያስወግድና ግጭቶቻችን ለማስወገድ መፍትሔ እንደሚሆንም ያምናል፡፡ 80 ብሔረሰች አሉ ተብሎ 80 ድንበር ያላቸው የክልል መንግሥታት ይኑሩ ማለት የማይታሰብና ሊተገበር የማይችል እንደሆነም በሚገባ ይረዳል፡፡ ከዚህም የተነሣ ነው ከከሸፈውና ወያኔም በአፉ ከማውራት በስተቀር አስተካክሎ ሊፈጽመው ካልቻለው ብሔርን መሠረት ያደረገ ከሚለው የወያኔ 9 የክልል መንግሥታት አወቃቀር ይልቅ ታሪክንና መልክአምድርን መሠረት ያደረገው 14ቱ ክፍላተ ሀገራት ጥሩ መፍትሔ ነው የሚለው፡፡

አቶ ኦኬሎ ፓርቲውን ከመሠረተ በኋላ ሱዳንና ኬንያ እየተዘዋወረ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ባገኘው አጋጣሚና መድረክ ሁሉ እያጋለጠ ፓርቲውንም እያስተዋወቀ ሲንቀሳቀስ እንዳለ አምና 2006ዓ.ም. ደቡብ ሱዳን በነበረበት ወቅት የደቡብ ሱዳን የደኅንነት ሰዎች በቁጥጥር ስር አዋሉት፡፡ የደቡብ ሱዳን የደኅንነት ሰዎች እኔንና ላገኛቸው እየፈለኳቸው የነበሩትን አራት ሰዎች እንዲሁም ሌሎች ሦስት ወያኔ የሚፈልጋቸውን አኙዋኮች አድርገው ለወያኔ በ23 ሚሊዮን ዶላር ሸጡን፡፡ የወያኔ ደኅንነቶች ወዲያውኑ ባዘጋጁት የጭነት አውሮፕላን (በረርት) ጭነው ጋንቤላ ከጋምቤላም ደብረ ዘይት አመጡንና ለመግደል ዝግጁ አድርገው እኔን ለብቻየ ሌሎቹን ሰባቱን አንድ ክፍል አሰሩንና ሄዱ፡፡ ከሰዓታት በኋላ አንድ የደኅንነት ሰው መጥቶ አቶ ኦኬሎ ስሕተት ሰርተናል የኖርዌይ ዜጋ መሆንህንም አናውቅም ነበር በማለት ከጓዶቹ ጋር ወደ ማዕከላዊ እንዲዛወር አደረጉት፡፡

እነ ኦኬሎን እግዚአብሔር ትረፉ ሲላቸው የደቡብ ሱዳን የደኅንነት ሰዎችና የወያኔ የደኅንነት ሰዎች ሸጠዋቸው አውሮፕላኑ ላይ ሲቀባበሏቸው ፎቶ ያነሡ ሰዎች ስለነበሩ ፎቷቸው (ምስለአካላቸው) ወዲያውኑ በተለያዩ መካነ ድሮች ተለቆ ስለነበርና ጉዳዩን ዓለም ስላወቀው እንዳሰቡት በስውር ገድለው ሊጥሉን ሳይችሉ ቀሩ በማለት ይናገራል ታጋይ ኦኬሎ፡፡ አቶ ኦኬሎ በማዕከላዊ ቆይታው ሦስቱንም ማጎሪያዎች አይቷል ለ17 ቀናት ጨለማ ክፍል ብቻውን ታስሯል ከዚያም ወደ ሳይቤሪያ ከሳይቤሪያም ወደ ሸራቶን ከሸራተንም አሁን እሱን ወዳገኘሁበት ቦታ ወደ ቅሊንጦ አዛውረውታል፡፡

አስቀድሞ ከሌሎች እስረኞች በኋላም ከራሱ እንዳረጋገጥኩት አንዴ ምን ሆነ መሰላቹህ የወሕኒ ቤቱ ኃላፊዎች እስረኞቹን ስለ ሽብርተኛነት ለማወያየት ሰብስቦ በነበረበት ወቅት የወሕኒ ቤቱ ኃላፊዎች ስለ ሽብርተኛነት ገለጻ ሲያደርጉ አንበሳው ኦኬሎ ይነሣና “ሽብርተኛ እናንተ ብቻ ናቹህ! ከእናን በስተቀር በዚህች ሀገር ሌላ ሽብርተኛ የለም! ጨፍጫፊም እናንተ ናቹህ!” እያለ በኃይል በስሜት ሲናገር እስረኛውም አብሮት በመጮህ ኦኬሎን በመደገፉ የወሕኒ ቤቱ ኃላፊዎች ጥለው እንዲወጡ አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ ያቄሙት የወሕኒ ቤቱ ኃላፊዎች ኦኬሎን ወስደው እንደ እባብ ቀጥቅጠውታል በድብደባው ምክንያትም ሁለቱ ጣቶቹ እንደማይንቀሳቀሱ ስብራት እንደደረሰባቸው አሳይቶኛል፡፡ እኔ የታሰርኩት የነበረው እነኝህ ሁለት አንበሶች ባሉበት ክፍል ነው፡፡ ነገሩ ሆን ተብሎ ለተንኮል ይሁን ያጋጣሚ አላውቅም ሆን ተብሎ “ቢንጎ” ለማለት ከሆነም ለወያኔ ደኅንነቶች እሱውላቹህ ደስ ይበላቹህ ልላቸው እወዳለሁ፡፡

የዋና ዋናዎቹህ አናብስት ላጫውታቹህ ብየ ነው እንጅ ቅሊንጦ ጫካ ውስጥ ስንት ጀግኖች ስንት አንበሶች አሉ መሰላቹህ! ባሉበት አምላክ በሰላም በጤና ይጠብቃቸው፡፡ ጨለማው ነግቶ ለብርሃኑ እንዲያበቃቸው በጸሎታቹህ አስቧቸው፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

No comments:

Post a Comment