Tuesday, December 23, 2014

ትግሉን ወደፊት ከመግፋት ውጭ አማራጭ የለም!

በፋሲል የኔያለም (የኢሳት ጋዜጠኛ)

ባለፉት 6 ወራት ብቻ 11 አብራሪዎች አገዛዙን ጥለው ጠፍተዋል። አንድን አብራሪ ለማሰልጠን ረጅም ጊዜ ይወስዳል፤ አብራሪዎች የጤና ሰራዊት፣ የልማት ሰራዊት እየተባሉ በሳምንት ውስጥ እንደሚፈለፈሉት ካድሬዎች አይደሉም። ለምሳሌ ሻለቃ አክሊሉ መዘነ አየር ሃይልን ጥሎ ከመጥፋቱ በፊት ለ15 አመታት በአየር ላይ በሯል። ሌሎችም እንዲሁ ከ7-15 ዓመታት የበረራ ልምድ ነበራቸው ። እነዚህን ሰዎች ማጣት ባገዛዙ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። እውነተኛው ትግል ሲጀመር አብራሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ጄኔራሎችም እስከነ ወታደሮቻቸው የነጻነት ትግሉን እንደሚቀላቀሉ የሚጠራጠር ካለ ኢህአዴግ ውስጥ ስላለው ትርምስ በቂ መረጃ የሌለው ሰው ብቻ ነው።

ትግሉን ሞቦቱ ሴሴሴኮ በወረደበት ፍጥነት ማጠናቀቅ እንደማይቻል አምናለሁ። ነገር ግን በምድር ላይ ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ማለትም የህዝቡን የለውጥ ፍላጎትና የስርአቱን መበስበስ ግምት ውስጥ ስናስገባ፣ ህወሃት ደርግን ለመጣል የወሰደበትን ሩብ ያክል ጊዜ ላይወስድ እንደሚችልም እገምታለሁ። ገና ብዙ ስራዎች ይቀራሉ ። ብዙ መጥራት ያሉባቸው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች አሉ። ህዝቡን በአንድ ልብ እንዳይነሳ የሚያደርጉትን ስጋቶች መርምሮ በቶሎ እልባት መስጠት ለነገ የሚተው ስራ አይደለም፤ ለውጡ ኢትዮጵያዊ እንዲሆን በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው መስክ መሰራት ያሉባቸው በርካታ ስራዎች ከለውጡ በፊት ቀድመው ማለቅ አለባቸው። ዞሮ ዞሮ የትግሉ አላማ እጅግ ነጻ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት መገንባት ነውና ዜጎች ለነጻነታቸው መረጋገጥ እንቅፋት ይሆናሉ ብለው የሚሰጉባቸውን ጉቶዎች ለይቶ በመንቀል፣ መንገዱ አስጊ አለመሆኑን ማሳየት ግንባር ቀደም ሆነው ከተሰለፉት የፖለቲካ ድርጅቶች ይጠበቃል። በተለይ በሃይል መንግስትን ለማስወገድ የሚታገሉ ሃይሎች፣ የሃይል አማራጭን ሆነ ሃይሉ የሚመጣበትን በሃይልም ይሁን በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ሃይሎች፣ የመጨረሻ ግባቸው ለራሳቸው ስልጣን ለመያዝ አለመሆኑን፣ አገዛዙን ጥለው የሚመሰርቱት የሽግግር መንግስትም ሁሉንም በእኩል የሚያስተናግድ መሆኑን ቃል ከመግባት ባሻገር በተግባር ማረጋገጥ አለባቸው።

ከፖለቲካ ድርጅቶች ተጽኖ ነጻ የሆኑ የሲቪክ ተቋማት በብዛት ቢመሰረቱ በሁዋላ ላይ ለሚመሰረተው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የጀርባ አጥንት ይሆናሉ። የሲቪክ ተቋማቱ ነጻነትንና ዲሞክራሲን የተመለከቱ ማቴሬያሎችን በማዘጋጀት፣ ለነጻነት ለሚፋለሙ ሃይሎች መሬት ድረስ በመውረድ በማስተማር ለነጻነት የሚደረገው ትግል ፈሩን እንዳይስት ሊያግዙ ይችላሉ። የፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ ግልጽ የሆነ ስርዓተ ትምህርት አዘጋጅተው ለሚመጡ የሲቪክ ተቋማት በራቸውን ክፍት አድርገው ታጋዮቻቸውን እንዲያስተምሩ ሊፈቅዱላቸው ይገባል። ሚዲያውም በተመሳሳይ ታጋዩ የሚታገልለለትን አላማ በውል እንዲገነዘብ በየጊዜው የማስተማር ሃላፊነት
አለበት። ታጋዮች የነጻነትና የዲሞክራሲ ስንቅ በጀርባቸው እስካዘሉ ድረስ የሚያሰጋ ነገር አይኖርም። የዚህ ትግል መዳረሻ አንድን ወገን ወደ ስልጣን ለማምጣት ሳይሆን ሁሉም ወገኖች ወደ ስልጣን የሚመጡበትን መሰላል መስራት በመሆኑ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ተሳትፎ ሊያደርግ ግድ ይለዋል። ዞሮ ዞሮ አገራችን በነጻነት ብትመራ ተጠቃሚው ሁሉም በመሆኑ ( የታገለውም ያልታገለውም)፣ በዚህ ትግል ውስጥ የራስን ድርሻ ለመወጣት ተሳትፎ ማድረጉ የሚሰጠው እርካታም ወደር አይገኝለትም።

አገዛዙ የሻእቢያ ተላላኪ ባላቸው ላይ የሃይል እርምጃ እንደሚወስድ ዝቷል። አገዛዙ ያለው ወታደራዊ ቁመና ሲታይ የሃይል እርምጃ ለመውሰድ አያስችለውም ፤ ለምሳሌ አየር ሃይሉ በባድሜ ጦርነት ወቅት ከነበረበት በባሰ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፤ ያን ጊዜም ቢሆን አየር ሃይልን ነፍስ የዘሩበት የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ሃይል አባላትና ቅጥረኛ ሩሲያዎች ነበሩ። እገረኛ ወታደሩም በየጊዜው ጥሎ እየጠፋ ነው። ደጀን የሚሆነው ህዝብም ትግሉ መቼ ተጀምሮልን በማለት ላይ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ህወሃት ጦርነት ይጀምራል ብሎ ማሰብ ባይቻልም፣ አንዳንድ የህወሃት አመራሮች እድላችንን እንሞክር ብለው ቃታ ሊስቡ ይችላሉ፤ የለኮሱት እሳት ራሳቸውን መልሶ እንደሚበላቸው ግን አያጠራጥርም። እድሜ ከሰጠን ሁሉንም በሂደት እናየዋለን። እንበርታ!

No comments:

Post a Comment