Friday, August 9, 2013

ከታሳሪዎቹ መካከል ያየናቸው አብዛኛዎቹ ሴቶች ሲሆኑ መጎተትና መመናጨቃቸው አንገት ያስደፋ ነበር፡፡


የሶሊያና ትዝብት

የኢድ ጠዋት ውሎ ከሃያ ሁለት እስከ መስቀል አደባባይ

ኢድ ጠዋትን የሙስሊም ወገኖች ውሎ ለማየት ተቀጣጥረን የሄድነው እኔና ሶስት ወዳጆቼ መሃል ላይ ሌሎች ሁለት ወገኖች ተቀላቅለውን መጨረሻ ላይ በተለያየ አቅጣጫም ቢሆን ውደ ቤት ተመልሰናል፡፡

እኔ ከነበርኩበት ሃያ ሁለት ማዞሪያ ከውሃ ልማት ጀምሮ መንገድ ዝግ የነበረ ሲሆን ሁሉም ሰው በእግሩ ነው መስቀል አደባባይ ድረስ የተጓዘው፡፡ ሁለት ፍተሻዎችን ያለፍን ሲሆን የመጀመሪያው ኡራኤል ተሻግሮ ሲሆን ሁለተኛው እስጢፋኖስ መብራት ላይ ነበር፡፡ ፍተሸዎቹ ላይ ምንምወረቀት የማያልፍ ሲሆን ባንዲራ የያዙም ለፖሊስ አስረክበው ያልፉ ነበር፡፡ ፓሶቹ የአዲስ አበባ ፓሊስ ሲሆኑ ምንም አይነት ፌደራል ፓሊስ መንገዱ ላይ አላየሁም፡፡ አንድ ሰው ወረቀት አልሰጥም ብሎ እሰጥ አገባ ከመፈጠሩ በስተቀርና በፍተሻው ብዛት ሰዎች ከመማረራቸው በስተቀር ሁሉም ነገር ሰላም ነበር፡፡

መስቀል አደባባይ ላይ ፌደራል ፓሊሶች በግራና በቀኝ በአንድ ሜትር ርቀት ቢሰለፉም ምንም ሳይፈጠር ስነስርአቱ ተጀመረ፡፡ ከስታዲየም የሚመጣውን ድምጽ መስማት ከባድ ነበር፡፡ ምክንያቱም አላህ ዋክበርና ድምጻችን ይሰማ በሚሉ ድምጾች ስለሚዋጥ፡፡ ፓሊስም ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳያደርግ ስግደሩ በሰላም ተጠናቀቀ፡፡ ከስግደቱ በሁዋላ ሰዎ ወደቤት መመለስ ሲጀምሩ ወደተለያየ የከተማው አቅጣጫ ተበተኑ፡፡ ኮሚቶዎቹ ይፈቱ፣ ድምጻችን ይሰማ፣ አሸባሪ አይደለንም፣ ኢቲቪ ሌባ መብትን መጠየቅ አሸባሪነት አይደለም የሚሉ መፈክሮች የነበሩ ሲሆን መንዙማና ጭፈራ ላይ የነበሩ ወጣቶችም ነበሩ፡፡ ፌደራል ፓሊሶች መንገዱን ግራና ቀኝ ይዘው መንገድ ከማሳየት ውጪ ምንም እርምጃ ሳይወስዱ መንገዳችንን ወደ ኡራኤል አደረግን፡፡ ከመካላቸው አንዱ ምንድነው የሚሉት ብሎ ሲጠይቅ ይፈቱ ነው ብሎ ሌላው ፌደራል ሲመልስለት አስተውለናል፡፡ ይሰማ ይላሉ የምን ድምጽ ነው የሚሰማው ሲባባሉ ሰምተን በፈገግታ አለፍን፡፡

በጭፈራውና በመፈክሩ መሃል አንዲት ሴት አዲስ የተወለደ የወራት ልጅዋን ይዛ አሸባሪዎች አይደለንም ስትል አይተናት በመደነቅ ተያየን፡፡ ከወዳጆች ጋርም ስልከ እየተደዋወልን በጣም ሰላማዊ ነው ፣ ወደ ቤት እየሄድን ነው ተባባልን፡፡ ልክ ፍትህ ሚኒስተር ጋር ስንደርስ ከፍ ብሎ ዋናው የኡራኤል ዳገት ላይ ሙሉ ለሙሉ የታጠቁ አድማ በታኝ ፓሊሶች አስፓልቱነ ሲያቋርጡ አየን፡፡ የድንጋጤ ሩጫ ተከተለ፣ ሰዎች እርስ በርሳቸው ችግር የለም ለማስፈራራት ነው እንጂ አይነኩንም አትሩጡ እያሉ ወደፌት ቀጠሉ፡፡ መንዙማውም መፈክሩም ቀጠለ፡፡ ዳር ይዘው ቆመው የነበሩት ፓሊሶ ግን ድንገት አስፓልቱን ቆርጠው ከፌት ያለውን ሰው መደብደብ ጀመሩ፡፡ በመሃል ከተከበቡት ውስጥ እኛም ተገኘን፡፡ አብዛኛዎቹ የተያዙት ሴቶች ሲሆኑ የወለቀ ጫማቸውን እያሽቀነጠረ መሬት እንቀመጡ አዘዛቸው፡፡ እኛም ከትእዛዙ ተቀላቀሉ ተብለን ስንጠብቅ አለባበሳችን ታይቶ( ሱሪና ጸጉር ያልሸፈኑ) ዳር ላይ እንድንጠለል ተፈቀደልን፡፡ አቅራቢያችን የተያዙት አብዛኛዎቹ ሙስሊም ሴቶች ወደ ፍትህ ሚኒስትር ጊቢ እየተመነጫጨቁ እየተመቱና እየተጎተቱ ገቡ፡፡ አብሮን ሆኖ ድንገት የጠፋብን ወዳጃችን ካሳንቺዝ ድረስ ሮጦ ራሱን አተረፈ፡፡

ከፈጥኖ ደራሾቹ ፓሊሶች መካከል መሪ የሚመስለው ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ተከተሉኝ፣እኔ ያዙ የምላችሁን ትይዛላችሁ ተሰማሩ ብሎ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ( ግንቡ ስር እነደቆምን የጠላት ወራሪ የመጣባቸው የሚመስሉት አድማ በታኞች ሲሰማሩ አየን) ጥቂት ቆይቶ አስፓልቱን መሻገር ተፈቅዶልን ብንሄድም ሶስት ዙር ወደ ፍትህ ሚኒስተር የተያዙ ሰዎች ሲገቡ አየን፡፡ በዚያ ሰአት ወዳጃችን በአድናቆት ያየናት የልጆች እናት ታስራ ስትጎተት እንዳየና ብዙ እናቶች ሲመቱ መመልከቱን ነገረን፡፡ ከታሳሪዎቹ መካከል ያየናቸው አብዛኛዎቹ ሴቶች ሲሆኑ መጎተትና መመናጨቃቸው አንገት ያስደፋ ነበር፡፡ ከሰአታት በሁዋላ መንገዱ ተከፍቶ መንቀሳቀስ ሲጀመር ብዙ ቤተሰቦች ተሰብስበው የታሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ዜና እየጠበቁ ሲላቀሱ አየን፡፡

የገረመኝ አድማ በታኝ ፓሊሶቹ መሃል ላይ ሲገቡ ያለምንም መስፈርት የእድል ጉዳይ ብቻ የነበረ ሲሆን ሲያዝም ሆነ ሲደበደብ ድንጋይ ያነሳ እና በጉልበት የመለሰ ማንም ሰው አላየሁም፡፡ የተጎዳ ንብረትም ሆነ የተሰበረ መስኮት አልነበረም፡፡ ብዙ ህጻናት ይህንን ድብደባ በአይናቸው አይተዋል፡፡ 

መጽናናቱን ይስጠን!! አሜን!

No comments:

Post a Comment