ልማት እንጀራ መጋገር ብቻ አይደለም፤ የጋገሩትን እንጀራ የመብላትንም መብት ያጠቃልላል። ማን ምን ያህሉ ቁራጭ ደረሰው የሚለውም ይታሰባል። ከዚህም አልፎ ነገ እንጀራ የማግኘት ተስፋንም አሻግሮ ይመለከታል። ልማት በቁሳዊ ሃብቶች ብቻ ሳይሆን ቁሳዊ ባልሆኑ ሃብቶችም ጭምር ይለካል። ልማት የዛሬ ነፃነትንና የነገንም ተስፋ ያጠቃልላል።
ገዢው መንግስት እስከዛሬ ከነበሩ አፋኝ ሥርዓቶች ሁሉ የባሰ ፀረ-ልማት ኃይል መሆኑን ግልፅ ስለሚያደርግ ይኸንን የተሟላ የልማት ትርጉም ከመዝገበ ቃላታችን መፋቅ ይሻል። በተቻለው መጠንም ዓይኖቻችን ግዑዝ ነገሮች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና ስለ መንፈሳዊ ሃብቶቻችን፣ ስብዕናችን፣ ክብራችን፣ አንድነታችን፣ አገራችን፣ ድንበራችን፣ ነፃነታችን እንዳናስብ ይሻል። ነገር ግን ልማት ሲባል ሁሉን አቀፍ መሆን እንዳለበት በፅኑ ይታመናል፤ ቁሳዊ እና የመንፈሳዊ ሃብቶች መዳበር።
የወያኔ የነጋ ጠባ “ልማታችን፣ ልማታችን” የደንቆሮ ጩኸት እንዲህ ሃቅን ለማድበስበስ ታስበው በተፈበረኩ ቁጥሮች እና በጥቂት የታይታ ሥራዎች የቆመ የእንቧይ ካብ ነው። ሃቁ ግን የተገላቢጦሽ መሆኑን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። ኢትዮጵያችን ውስጥ ዛሬ ድህነትና ሥራ አጥነት በዝቷል፤ ፍትህና ነፃነት የለም፤ የህዝቡ ክብርና ስብዕና ተረግጧል፤ የትምህርት ጥራት አሳፋሪ ደረጃ ላይ ወድቋል፤ ስደት ተሰምቶ ወደማይታወቅ ደረጃ ደርሷል፤ ሙስና ተቀባይነት ያለው አሠራር ሆኗል። በመብቶች ረገድ ደግሞ ኢትዮጵያ ጥቂት ወንበዴዎች ሕዝቦቿን ያገቱባት ትልቅ እስር ቤት ሆናለች። ይባስ ብሎ ወያኔ ከኔ የተሻለ መንግስት አታገኙም እያለ በህዝብ ማሾፍን ተያይዟል፤ ይሳለቃልም።
ስለዚህ በእኔ እምነት በወያኔ የአፈና ሥርዓት ውስጥ ስለልማት ማውራት ቧልት ብቻ ሳይሆን ህዝብን ለማታለልና የስልጣን ቆይታ እድሜን ለማስረዘም መሆኑንም አስረግጨ መናገር እፈልጋለሁ።
ኢትዮጵያችን በክብር ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment