Thursday, August 15, 2013

መንግስት እምነትን ከእምነት የማጋጨት ጥረቱን ገፍቶበታል! (ድምፃችን ይሰማ)


ሐሙስ ነሐሴ 9/2005

ግጭት ቀስቃሽ በራሪ ወረቀቶች በመንግስት ሰዎች እየተበተኑ ነው!

መንግስት የተነሳበትን ተቃውሞ ከእምነት አክራሪነትና አሻባሪነት ጋር በማቆራኘት፣ እንዲሁም ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ግጭት እንዲፈጠር በማነሳሳት ተግባር ላይ ተጠምዷል፡፡ መንግስት ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ያቀረበለትን ሰላማዊ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ የተለያዩ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም ሙስሊሙን ህብረተሰብ ለከፍተኛ ችግር ሲዳርግ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ላለፈው አንድ አመት ከመንፈቅ ያህል ጊዜ በሙስሊሙ ላይ ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይ የረመዳን ወር ከገባበት ወቅት ጀምሮ መንግስት ሲሰራቸው የነበሩ ሁሉን አቀፍ ዘመቻዎች ብዙ ግብ ለማሳካት የታለሙ ነበሩ፡፡ በዒድ የሚደረገውን ተቃውሞ ለማኮላሸትም እቅድ ነበረው፡፡ ሆኖም ሁሉም ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡ 

በኢድ ቀን ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከነሙሉ ቤተሰቡ ነቅሎ በመውጣት አዲስ አበባ ስታዲየምና አካባቢውን ሞልቶት የተገኘው የመንግስት የሚዲያ ፉከራ እና ሽንገላ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለማሳየት ጭምር ነበር፡፡ ‹‹ከሰላም ወዳዱ ሙስሊም ማህበረሰብ ጋር በመተባበር›› የሚለው የመንግስት የተደጋገመ የሹፈት ቃልና ተራ የመቀባባት ፖሊሲ ትርጉም የሌለው መሆኑን ለማሳየት የዒድ እለቱ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ምላሽ አመርቂ እና የማያወላዳ ነበር፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በየመስጂዱና በየአካባቢው እየተፈጸመበት ያለውን በደል ከማንም በላይ የሚያውቅና የሚረዳ በመሆኑ በመንግስት ባዶ ሽንገላ ፈጽሞ ሊሸወድ እንደማይችል ባለፈው አንድ ወር የነበረውን የመንግስት የግዳጅ ሰልፍ ኢንቨስትመንት፣ የጋዜጣዊ መግለጫ ኢንቨስትመንት፣ የስብሰባ ኢንቨስትመንት እና የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ኢንቨስትመንት ያከሰረ የዒድ ትእይንት መፈጠሩ የምንደሰትበትም የምንኮራበትም ታሪካችን ሆኗል፡፡ 

የሚዲያ እና ሰልፍ ኢንቨስትመንቱ ዋነኛ ዓላማ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ካልሆነው ኢትዮጵያዊ ህብረተሰብ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዳይኖረንና በመሀከላችን አለመግባባት እና ግጭት እንዲነግስ ነው፡፡ በዚህ ምድብ ‹‹ጂሀዳዊ ሐረካት››ን የመሳሰሉ የመንግስት ድራማዎችን ጨምሮ በርካታ አሳፋሪ ውንጀላዎች ሙስሊሙ ላይ ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፡፡ ‹‹ሙስሊሙ በኢትዮጵያ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ይሻል›› የሚል ያለተጨበጠ እና ፍጹም ሊታሰብ የማይችል እንዲሁም የራሱ የመንግስት ፍ/ቤት ውድቅ ያደረገውን ውንጀላ በመሰንዘር በተለይም አብዛኛውን የክርስትና እምነት ተከታይ ፍርሃት ውስጥ ለመክተት እና በአጸፋውም ከሙስሊሙ ጋር የእምነት ግጭት ውስጥ እንዲገባ እየሰራ ይገኛል፡፡

መንግስት ምንም እንኳ ተደጋጋሚ ውዥንብር የመፍጠርና በአምነቶች መካከል አለመተማመን፣ ከዛም አልፎ ግጭት እንዲነገስ ይህ ቀረሽ የማይባል ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳያመጣለት ቀርቷል፡፡ የዚህ ዋናው ዓላማ ለተጠየቀው ሕጋዊ ጥያቄዎች ማምለጫ በር ለማግኘት መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ መንግስት በሚሰራቸው እና ከፍተኛ ወጪ ከሚያወጣባቸው የሚዲያ ኢንቨስትመንቶች የክርስትና እምነት ተከታዮችን ድጋፍ ማግኘት ዋነኛ አላማው እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ሊሳካ አልቻለም፡፡ ክርስቲያን ወንድሞችና እኅቶቻችን የሙስሊም ኢትዮያውያን እንቅስቃሴ ፍፁም ሰላማዊ እንደሆነና ያነሳናቸውም ሕጋዊ ጥያቄዎች መመሆናቸውን ከመረዳት ባለፈ የሚደርሱብንን በደሎች በእለት ተእለት ሕይወታቸው ባለፉት ሁለት ዐመታት በደንብ ያስተዋሉት በመሆኑ በመንግስት ይህን መሰሉ አረመኔያዊ ሴራ እንደማይሸነፉ እርግኞችኛ ነን።

አሁን ደግሞ መንግስት ፍጹም ተስፋ መቁረጡን በሚያመላክት መልኩ በየመንገዱ በራሪ ወረቀቶችን መበተን ጀምሯል፡፡ ከትናንት ወዲያ ጀምሮ በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ‹‹ለክርስቲያን ወገኖች›› በሚል ርእስ ከክርስትና እምነት ተከታዮች የተለላፈ መልእክት በማስመሰል ‹‹ሙስሊሞች እስላማዊ መንግስት ሊመሰርቱ ነው›› እና መሰል መያዣ መጨበጫ የሌላቸውን ውንጀላዎችን በማስፈር ‹‹ሙስሊሞችን እንታገል›› በሚል በግልጽ የእምነት ግጭት እንዲከሰት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ተበተነው ወረቀት መንግስት ከሰሞኑ ይህንኑ የእርስ በእርስ ጥላቻ የሚነዙ ኮንፈረንሶች በማዘጋጀቱና ለእሱም መንደርደሪያና ማመቻቻ እነዲጠቅመው በመፈለጉ መሆኑም ታውቋል፡፡ ወረቀቶቹ ሕግ አስከባሪ ፖሊሶች ባሉባቸው በዋና ዋና ጎዳናዎች ጭምር በመበተን ላይ የሚገኙ መሆናቸው ደግሞ መንግስት ምን ያህል ከመስመር ያለፈ ተግባር ውስጥ መዘፈቁን አመላካች ነው፡፡

ምንም እንኳ መሰል ቅስቀሳዎችና ጥሪዎች አብረው ለሺ አመታት በኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚሳካላቸው ባይሆንም፣ አገርን እመራለሁ በሚል መንግስታዊ አካል ይህን መሰል ጸያፍ ድርጊት መፈጸሙ ግን እጅግ አሳሳሳቢም አሳፋሪም ነው፡፡ መንግስት እያካሄደ ያለው ሃይማኖቶችን እርስ በእርስ የማጋጨት ፍላጎት ዘመቻ ሃገራችንን በሌሎች አገሮች ያየናቸው አይነት ማብቂያ የሌላቸው የእርስ በርስ ጦርነቶችና ጭፍጨፋዎች የሚያመራ በመሆኑ ለኢትዮጵያ መረጋጋት የሚያስቡ ወገኖች ሁሉ ሊያወግዙትና ይህን ጥረት ሊያከሽፉ ይገባል፡፡ ህገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄያችንን ለመመለስ የተቸገረው መንግስት በእምነቶች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚሸርበው ሴራ በታሪክም በትውልድም ተወቃሽ ከመሆን እንደማያድነው በመገንዘብ ከዚህ አይነት ድርጊቱ እንዲታቀብ በተደጋጋሚ ጊዜያት መልእክቶችን አስተላልፈናል፡፡ አሁንም የሙስሊሙን ህብረተሰብ ህገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄ ምላሽ በመንፈግ በአቋራጭ በእምነቶች መካከል ግጭትን መፍጠር በዛሬዋ ኢትዮጵያ ፈጽሞ እንደማሳካ አስረግጠን መናገር እንሻለን፡፡

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment