Wednesday, August 7, 2013

አገር አቀፉ የዒድ ተቃውሞ ዝርዝር መርሐ ግብር! (ድምፃችን ይሰማ)






ይህ መርሐግብር በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ የኢድ ተቃውሞዎች ሁሉ የሚያገለግል ነው፡፡

የረመዳን ዒደል - ፊጥር ቀን የተቃውሞ ውሎ ሁለት ንኡስ ክፍሎች አሉት፡፡

1. የዒድ ሰላት ከመሰገዶ አስቀድሞ እና
2. የዒድ ሰላት ከተሰገደ በኋላ እና

1. የዒድ ሰላት ከመሰገዱ አስቀድሞ

ይህ ክፍለ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ስታዲየም ከደረስን ከማለዳው 12 ሠዓት ጀምሮ በክፍለ ሀገር ደግሞ እንደ አከባቢው ሠዓት ሁኔታ ለዒድ ሶላት እስከምንቆምበት ያለውን ጊዜ ያካትታል፡፡

* ሁላችንም ከማለዳው 12 ሠዓት ላይ ተጠናቀን በስታዲየም እንገኛለን፣
* ሥርዓት ያለው ተቃውሞ ለማካሄድ እንዲረዳን ስታዲየም እንደደረስን ቦታችንን እንይዛለን፣
* መከራና ስቃይ ቢደራረብብንም ዛሬም ሠላማዊነታችንን ለማስመስከር ከመድረክ የሚባለውን ተክቢራ በጋራ እያልን የያዝነውን ነጭ ወረቀት/ጥምጣም ቀጥ አድርገን እንይዛለን፣
* ከመድረክ አካባቢ በመጅሊስ ሹመኞች ምንም ዓይነት ንግግር ከተሠማ በተክቢራ እናስቆማለን፣
* የመንግስት ባለስልጣን ተጋባዥ እንግዳ ካለ በእስር፣ በግፍና በእንግልት ላይ መሆናችንን በሚያንፀባርቅ መልኩ ጆሮዎቻችንን በመዳፎቻችን በመያዝ ‹‹ድምፃችን ይሰማ!›› የሚል መፈክር ንግግሩን አቋርጦ መድረኩን ለቅቆ እስከሚወርድ ድረስ እናሰማለን፡፡
* የዒድ ሰላትን በጋራ እንሰግዳለን፡፡

2. የዒድ ሰላት ከተሰገደ በኋላ 

ይህ ክፍለ ጊዜ የዒድ ሶላት እንዳበቃ የሚጀምርና ተቃውሞ ጀምረን እስከምናጠናቅቅ ያለውን አጭር ክፍለ ጊዜ ያካትታል፡፡

* ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ባለንበት ሳንንቀሳቀስ እንቆማለን፡፡ ይህ ለረብሻና ግርግር የመጡትን ኃይሎች በቀላሉ ለመቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ ተቃውሟችን አንድነቱንና ስርዓቱን በጠበቀ ሁኔታ እንዲካሄድ ያግዘናል፡፡
* ባለንበት ምንም እንቅስቃሴ ሳናደርግ አዘጋጅተን የመጣነውንና ‹‹ሹመኞችን..አውርደናል›› የሚለውን ወረቀት ለ 3 ደቂቃ በማሳየት የመንግስት የመጅሊስ ሹመኞች ከእንግዲህ በይፋ መውረዳቸውን እናውጃለን፡፡
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹አላሁ አክበር!›› እንላለን
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹ድምፃችን ይሰማ››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹ጥያቄው ይመለስ!››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹የታሰሩት ይፈቱ!››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹በአቋማችን እንፀናለን!››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹በእምነታችን - ጣልቃ አትግቡ!››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹ሀስቡን አላህ - ወኒዕመል ወኪል!››
* ለ 3 ደቂቃ ‹‹ድራማው ይብቃ!›› እንልና እንጨርሳለን፡፡



ከላይ የተቀመጡት መርሐግብሮች እንደተጠናቀቁ ሕገ መንግስቱ የሰጠን ሃይማኖታዊ መብታችን ተጥሶና ሰብአዊ መብታችን ተረግጦ በመስከረም 27 በቀበሌ የተቀናበረው የመጅሊስ ሹመት ላይ ተምሳሌታዊ ስርአተ ቀብር ቀጥሎ የሚፈጸም ይሆናል፡፡ይህም ግለሰቦች በተናጥል ወረቀት ላይ በመጻፍም ሆነ ትንሽ ጨርቅ በመጠቅለል ሊፈጽሙት የሚችል ሆኖ ተምሳሌታዊነቱን የሚያሳይና የጋራ ማሳያዎች ያሉት ስርአተ ቀብርም ይካሄዳል፡፡

ይህ አንደተካሄደም የዒድ አልፊጥር አገር አቀፍ ሠላማዊ ተቃውሟችን ይጠናቀቃል ማለት ነው፡፡

ማስታወሻ!

1. ሁላችንም ‹‹ሹመኞችን..አውርደናል!›› የሚል መፈክር በወረቀት ላይ ፅፈን ይዘን እንመጣለን፡፡

2. መንግስትና መጅሊስ የሚያደራጇቸው ቡድኖች እኛን ወደ ሁከት ለመቀስቀስ ቢጥሩ እንደከዚህ ቀደሙ በምንም መልኩ ምላሽ ባለመስጠት እና ስራቸውን በማጋለጥ ዓላማቸውን እናከሽፍባቸዋለን፡፡

3. በማንኛውም ቦታ ኹከት ቢፈጥሩ(በሴቱም በወንዱም በኩል) በምንም ዓይነት ሁኔታ ሳንደናገጥ ባለንበት ቦታ ረግተን ቆመንና እጅ ለእጅ ተያይዘን ግርግራቸውን እናከሽፋለን፡፡

4. መሃላችን ገብተው ህዝቡን ‹‹ሰልፍ እናድርግ›› ከተጠቀሰው ሰዓት ውጪ ‹‹እንቆይ›› ብለው የሚቀሰቅሱ ካሉ እናጋልጣቸዋለን፡፡

5. ዝናብ ቢኖር አንኳ ከዚህ በፊት እንዳሳየነው ሁሉ ፀንተን ድምፃችንን ከማሰማት አይገድብንም፡፡

6. ከኢማሙ አቅጣጫ ድምጽ የማይሰማበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ከፊት ያለን ሰዎች የኢማሙን ድምፅ ወደ ኋላ ላሉት እናስተጋባለን፡፡

7. በተለይም በአዲስ አበባ ተቃውሟችንን በእስታዲየምና አካባቢው በሚኖረን ቆይታ ካጠናቀቅን በኋላ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በኩል በምናልፍበት አጋጣሚ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች!

ከላይ የተቀመጠውን የተቃውሞ ሂደት ብቻ ሙሉ በሙሉ በመተግበር ቁጣችንን እንገልፃለን! በዲናችን ላይ እየተደረገ ያለውን የእጅ ጥምዘዛ፣ እስር ድብደባና የህይወት ማጥፋት ወንጀል እንቃወማለን! በዳዮች ለፍርድ እንዲቆሙም እንጠይቃለን! ኮሚቴዎቻችን፣ ዱዓቶች፣ ወንድምና በእህቶች ያለ
ምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱልን እንላለን! በዚህ አንድነታችንን አናሳያቸዋለን! እኛ ሚሊዮኖች መሆናችንን በተግባር እናረጋግጥላቸዋለን፡፡ ዲናችንን ለድርድር እንደማናቀርብ በዓይናቸው አንዲመለከቱ እናደርጋለን!

ይህ የኢድ ተቃውሞአችን ከተጠናቀቀ በኋላ የጁምአ ተቃውሞዎች ላልተወሰኑ ጊዜያት የማይካሄዱ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ በዚህ የኢድ ተቃውሞአችን ለሌላ ተጨማሪ ጊዜ ለመንግስት እና ለሚመለከተው አካላት መልእክታችንን በማድረስ የመንግስትን ተግባራዊ ምላሽ ለመጠበቅ ስንል የጁምአ ተቃውሞዎችን ላልተወሰኑ ጊዜያት የምናካሄድ አይሆንም፡፡ በተለይም በመስከረም 27 የተካሄደው የመጅሊስ የቀበሌ ሹመት በእለቱ ተምሳሌታዊ ስርአተ ቀብር ስለሚፈጸምለት ይህ ነው ተብሎ የሚወጣ አካል ባለመኖሩ መንግስት የጥሞና ጊዜ ወስዶ ሕዝብ ለጠየቃቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሹን እንዲሰጥ የጁምአ ተቃውሞዎች ላልተወሰኑ ጊዜያት ይቆማሉ፡፡

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment