Thursday, April 30, 2015
በኮምፒተር የኤሌትሪክ ገመድ የሚገርፍ አገዛዝ - ግርማ ካሳ
የኢትዮጵያ መንግስት ለሕግ የሚቆረቆር መንግስት እንደሆነ ብዙ ጊዜ ሲናገር ይደመጣል። የተባበሩት መንግስታት አባል ድርጅት እንደመሆኗም፣ ኢትዮጵያ፣ የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን ድንጋጌን የማክበር ግዴታ አለባት። እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1976 የተደረገው፣ ቃልኪዳን ለሰብአዊና ፖለቲካ መብቶች ፣ The International Covenant on Civil and Political Rights (ICCPR) ዉል/ስምምንት ፈራሚ አገር ናት።
የ ICCPR ዉል አንቀጽ ሰባት እንዲሁም የተባበሩት መንግስት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ አምስት፣ በግልጽ እንዳስቀመጡት ፣ ማን ሰው በአካሉ ላይ ድብደባ፣ ጉዳት፣ ቶርቸርና ክብሩ የሚነኩ ተግባራት ሊፈጸሙበት እንደማይገባ ይደነግጋሉ። «No one shall be subjected to torture or to cruel, inhuman or degrading treatment or punishment» ይላሉ አንቀጾቹ።
በአገራችን ኢትዮጵያ ወዳሉት ሕጎች ስንመጣ ደግሞ፣ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ መንግስቱ እንጂ ከጥቂት የሕወሃት የደህንነት አባላት የሚመጣ መመሪያ እንዳለሆነ በግልጽ ተቀምጧል። የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 21 « በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰባአዊ ክብራቸውን በሚተበቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው» ይላል።
ሆኖም በተለያዩ ጊዜያት ተቃዋሞ የሚያሰሙ ወገኖች ሕግ መንግስቱ ወረቀት ብቻ እንደሚሉት፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ለአገሪቷ ሕግ ደንታ እንደሌለው፣ የአለም አቀፍ ሕግጋቶችን የሚጥስ ፣ አደገኛው አሸባሪና የሕግ አፍራሽ እንደሆነ በግልጽ እያሳየ ነው።
ለሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ለሚባል ድርጅት ፣በማእከላዊ እሥር ቤት ስለደረሰባቸው ሁኔታ ዞን ዘጠኞች የተናገሩትን ላነበበ፣ በርግጥም ምን ያህል አገራችን በሕግ የማትተዳደር እንደሆነ መደምደም አያቅተውም።
«ከወንበሬ አንድነሳ አዘዙኝ፡። ከዚያም በቆምኩበት ግራ ብብቴን እና እጄን በአንድ እጁ አንዳልወድቅ ወጥሮ ይዞ በእግሩ ጭኔን በሃይል ደበደበኝ። ከድብደባው በማስከተል ደግሞ እግሬ መሃል እግሩን በማስገባት ወደግራ እና ወደቀኝ በመምታት ተዘርጥጬ እንድቆይ በማድረግ እጄን ወደላይ አድርጌ እግሬ ግራና ቀኝ ተዘርጥጦ ( በተለምዶ ስፕሊት በሚባለው) በግራ እና ከቀኝ በመደብደብ እጄን ወደላይ አድርጌ እነድመረመር ተደርጌያለሁ። ከዚህ ምርመራ በኋላ ለሁለት ቀን እያነከሰኩ ነበር» ሲል ነበር በፋቃዱ ሃይሎ ሰቆቃዉን የገለጸው።
አቤል ዋበላ በተራው የደረሰበትን ግፍ ሲያስረዳ «ድብደባውም ጨለማ ክፍል ውስጥ በማስገባት አፌ ውስጥ ካልሲ በመወተፍ እግሮቼን ከላይ፣ ውስጥ እግሬን እና ከውስጥ ባቴን ታፋዬን እንዲሁም ጀርባዬን በእንጨትና በኮምፒውተር ገመድ ገርፈውኛል። የምርመራ ክፍሉ ወለል ላይ በደረቴ አንዲሁም በጀርባዬ እያገላበጡ በማስተኛት መላ ሰውነቴን ረግጠው ተራምደውብኛል፡። አፌን ሳይቀር ረግጠውታል» ነበር ያለው።
ናትናኤል ፈለቀ በበኩሉ «ጫማዬን አውልቄ በባዶ እግሬ አንድቆም ከተደረኩ በኋላ እግሮቼ ጣቶች ላይ መርማሪዎቹ በጫማቸው በሃይል በመርገጥ እግሬ ላይ ከባድ ድብደባ አድርሰውብኛል» ሲል አጥፋን ብርሃኔ ደግሞ «ከግድግዳ ጋር እያጋጨ ደብድቦኛል» ሲል በማእከላዊ የነበረዉን ሰቅጣጭ ቶርቾር አጋልጠዋል።
በማእከላዊ የሚታየው ቶርቸር፣ ከዋናዉ የደህንነት ሃላፊዎች አዎንታ ያገኘ የተለመደ አሰራ እንደሆነ የታወቀ ነው። በሕወሃት/ኢሕአዴግ ዉስጥ ያለው ባህል፣ ፓለቲካን አሰራር የፍቅር፣ የሰብአዊነት፣ የመቻቻል፣ የሰለጠነ፣ የፍቅር ሳይሆን የጫካ፣ የአዉሬ፣ የጭካኔ፣ የኢሰባአዊነት አረሜኔያዊ ፖለቲካን አሰራር ነው።
ይህ ባህል፣ ይህ ፖለቲካ፣ እስካልተቀየረ ድረስ ዛረ በነ በፍቃዱ ላይ የሆነው ነገ በሌሎችም ላይ መድረሱ አይቀርም። ዛሬ ዞን ዘጠኞችን ያንኳኳ፣ ነገ የኛን በር ማንኳኳቱ አይቀርም። በመሆኑም ይሄንን ለአዲሱ ትዉልድ የማይመጥን፣ ያረጀ፣ ኋላ ቀር፣ ዘረኛ፣ ፍጹም አረመኔያዊ የሆነ ስርዓት ለመቀየር እያንዳንዳችን ከመቼዉም ጊዜ በላይ መነሳት አለብን። ከዚህ በላይ ዉርደት፣ ከዚህ በላይ ሞት የለም። ወገን፣ በነጻነትና በክብር እንድንኖር በእግዚባሄር አምሳል የተፈጠርን ሰዎች እንጂ እንስሶች አይደለም። በቃ የምንለበት ጊዜ ነው። እነርሱ ለጊዜው ሜዲያዉን ይዘው ፣ ዲስኩር በማስማት ያስፈራሩ ይሆናል። እነርሱ በጥቅም በገዟቸው ጉጄል ፌዴራሎችን አጋዚዎች ይመኩ ይሆናል። «አንመካም በጉልበታችን፣ እግዚአብሄር ነው የኛ ኃይላችን» እንዳሉት የአዲስ አበባ ሰልፈኞች እኛ የምንመካው በእግዚአብሄር ነው። በፈጣሪ እርዳታ፣ በፍቅርና በአንድነት ተያይዘን ከቆምን፣ ጥቂቶች በምንም ሂሳብ ሚሊዮኖችን ሊያሸንፉ አይችሉም።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment