
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ቀድሞ የተደረጉት ጥረቶች የተጠበቀውን ውጤት አለማስገኘት ተስፋ ሳያቆርጠን ከእያንዳንዱ ጥረት ልምድ እየወሰደን የኢትዮጵያዊያን አንድነት እስኪረጋገጥ ድረስ አዳዲስ የትብብር ጥረቶችን ማድረግ ያለብን መሆኑ ያምናል። በዚህም መሠረት የትብብር መርህ ነድፎ ትግል ውስጥ ካሉ ሁሉም የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር ሲነጋገር እና ሲደራደር ቆይቷል። እንደሚታወቀው የንቅናቄዓችን አበይት የትብብር መርሆች ሁለት ናቸው። መርህ አንድ፣ ለውጥ እንዲመጣ የምንታገለው ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ መሆኑ ማመን ነው። መርህ ሁለት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም እርከኖች የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የሚገባው በሕዝብ ነፃ ምርጫ ብቻ መሆኑን መቀበል ናቸው።
በምድር ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ኃይሎች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ ሁለቱንም መርሆዎች የሚያሟሉ ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ከንቅናቄዓችን የተለየ አቋም የላቸውም። በአለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅቶቹ ተቀራርበው እንዲሠሩ በመደረጉ ከአመራር አልፎ አባላት መካከል መልካም ወዳጅነት መመሥረት ተችሏል። የነፃነት ትግላችን የደረሰበት ደረጃ እና የድርጅቶቹም ቅርርብ በመገምገም ሶስቱ ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር፣ የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄና እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ መዋሃዳቸው ትግሉን ያራምዳል ተብሎ ታምኖበታል። በዚህም መሠረት ሶስቱ ድርጅቶች ለመዋሃድ ተስማምተን ስምምነታቸንን ይፋ አድርገናል። ድርጅቶቹን የማዋሃድ ዝርዝር ሥራም ተጀምሯል።