Saturday, August 22, 2015

ነጻነታችን በእጃችን፣ ህወሃት ካልተገረሰሰ እስሩም ግድያውም ይቀጥላል!

ተስፋዬ ነጋ (ዋሽንግተን፣ ዲሲ)

ዛሬ እነሆ እነ ሀምታሙ አያሌው፣ ዳኤል ሽበሺ፣ አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋና፣ አብርሃም ሰለሞን በነፃ እንዲለቀቁ የወያኔ ፍርድ ቤት ወስኗል የሚል ዜና ሰማሁ። እንኳንም በውሸት ክስ የታሰሩት ወደየቤተሰቦቻቸው በሰላም ተቀላቀሉ። ከሚወዱት ቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እጅግ ደስ የሚል ስሜት ይፈጥራል። የቤተሰቦቻቸውን ናፍቆታቸውን በአግባቡ እንዲያጣጥሙ ምኞቴ ነው። እውነት መጨረሻ ላይ እውነት ሆና መውጣቷ አይቀርም፣ ይኸው እውነት ነጻ አወጣቻቸው።

የሆኖው ሆኖ እነዚህ ወጣቶች ከመጀመሪያውም መታሰር አልነበረባቸውም። በወንጀል ደም ተጨማልቀው የሚዋዥቁ አረመኔዎች አልነበሩም። ለአገራቸውና ለህዝባቸው ከፍተኛ ራዕይ የሰነቁ ንጹህ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፣ አሁንም ንጹሃን ናቸው። ወያኔዎች ሰላማዊ ዜጎችን በማሰር የፖለቲካ ትርፍ እናገኛለን ብለው ቢያስቡም፣ የእነአብርሃ ደስታ መታሰር የህወሃትን ድንቁርና ከማጋለጥ ውጭ በተቃዋሚው ወገን ላይ ያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ የለም። እንዲያውም ተቃዋሚዎች የትግሉን ዳራ በጥልቅ እንዲመረምሩና የወደፊቱን የትግል አቅጣጫ በጥንቃቄ እንዲቀይሱ አደረጋቸው እንጂ! የታሳሪዎችን ንጹህነት ደግሞ ህወሃቶችም (እዉነትና ውሸት የማያገናዝቡ ሆዳም ካድሬዎችም ጭምር) በሚገባ የሚመሰክሩ ይመስለኛል፣ ያው የሞት ሽረት ነገር ሆኖባቸው ቢያስሯቸውም! የህወሃት ሰዎች ለስልጣናቸው የሚያሰጋቸውን ሁሉ በሃሰት ክስ ከመወንጀል ተቆጥበው አያውቁም፣ እነዚሁ ፖለቲከኛ ወጣቶች በምሳሌነት ሊቀርቡ ይችላሉ፣ የእስሩ ገፈት ቀማሾች ዞን 9ኞችም ሌሎች ሰለባዎች ናቸው። ተመስገን ደሳለኝ፣ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት አለሙ፣ ውብሸት ታዬ የፈሪው ህወሃት የሃሰት ፍርድ በትር ተጎጂዎች ናቸው። የህወሃት መንግስት በውሸት የተካነ፣ የፈጠራ ክስ ጸሃፈ-ተውኔት እንደሆነ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። ህወሃቶች ተቃዋሚ የመሰላቸውን ሁሉ በፈለጉ ጊዜ ሲያስሩ፣ በፈለጉ ጊዜ ሲፈቱ ኖረዋል፣ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሲመጣ ከመግደል ወደኋላ አይመለሱም። ህወሃት በ1996 ዓም ሰላማዊ ሰልፈኞችንና ህጻናትን ሳይቀር በጠራራ ጸሃይ በካሊበር ጥይት በሳስቶ ገሏቸዋል። ወደፊትም የፈጠራ ክስ ማቀናበር፣ ማሰር፣ መፍታት፣ መግደል፣ ስራቸው ሆኖ ይቀጥላል።

ሕወሃት ሁለት መገለጫዎች አሉት። የመጀመሪያው የጦር ሃይሉን በመተማመን፣ በጉልበት ስልጣን ላይ እንደተቆናጠጠ ዘላለም እገዛለሁ ብሎ ማሰቡ ነው። የመሳሪያ ባለቤት በመሆኑ፣ የተቃወመኝን እያሰርኩ፣ ጠላቴን እየገደልኩ፣ እንዲሁም ከተቃውሞ የማይታቀበውን እያስፈራራሁ ለረጅም ጊዜ እኖራለሁ ብሎ ያምናል። እዉነትም ህወሃት በከፊል ትክክል ነበር፣ በጉልበት እያስፈራራ፣ እያሰረ፣ እየገደለ ለ25 አመታት ያለምንም ችግር ዘልቋል። ከራሱ ከህወሃት የተፈጠሩ የጦር መኮንኖችን ብቻ ስልጣን ላይ አስቀምጦ፣ በሙስና እንዲዘፈቁ በማበረታታትና፣ የሚያማልል ስጦታ በመስጠት፣ እንዲሁም እነዚሁን የጦር መኮንኖች የወንጀል ተባባሪና መሪ በማድረግ የ”አብረን እንዝለቅ” ጨዋታ ተክኖበታል። ሁሉንም የጦር መኮንኖች ከአንድ ብሄር ብቻ በመሾም፣ ለተቃዋሚ እንዳያደሉ “ከካዳችሁን በጦር ወንጀለኝነት ትፈለጋላችሁ፣ የትግራይን ህዝብ ታስጨርሳላችሁ” በሚል ሰንካላ ማስፈራሪያ ከሌላው የኢትዮጵያዊ ጋር እንዳይነናኙና እንዳይተባበሩ አድርገዋቸዋል።

ሁለተኛው የህወሃት መገለጫ ደግሞ ከመንግስት ባለስልጣናት ያውም ከሚኒስትሮች የማይጠበቁ ዘረኝነት፣ ስግብግብነት፣ ውሸትና፣ የሞራል ዝቅጠት ነው። አብዛኞቹ ባለስልጣናት በዘረኝነት ዛር የሰከሩ ወፈፌዎች ናቸው። የራሳቸውን ብሄር “ወርቅ” በማለት የሚያሞካሹ፣ ሌላውን ብሄረሰብ ግን “ትምክህተኛ፣ አክራሪ፣ ብሄርተኛ” የሚል ታፔላ በመለጠፍ በጅምላ የሚሳደቡ [የራሳቸውን ቃል ልጠቀምና] “ወራዳ” ናቸው። በተለይም ለአማራና ለኦሮሞ ብሄረሰቦች ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸውና በካድሬዎቻቸው አማካኝነት እስከዛሬ ድረስ አርሶ አደር ገበሬዎችን በማፈናቀል የተካኑ በክፋት ሃሴት የሚዝናኑ ናቸው።

አቶ መለስና የህወሃት ባለስልጣናት ዋና ዋና መስሪያ ቤቶችን፣ ወታደራዊ ተቋማትን፣ የገንዘብ ተቋማትን፣ የፖለቲካ ተቋማትን፣ የማህበራዊ አገልግሎት ድርጅቶችን በብቸኝነት በመቆጣጠር ለግላቸው ስልጣን ማስረዘሚያና ኪስ ማድለቢያ ማድረጋቸው አሌ የማይባል ሃቅ ነው። ዛሬም የአየር መንገድን፣ የኮንስትራክሽንና የንግድ ድርጅቶችን፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንን፣ የውጭ ንግድንና የአገር ውስጥ ገቢን፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን፣ ብሄራዊ ባንክን መብራት ሃይልንና ቴሌኮም የመሳሰሉትን ዋና ዋና ተቋማትን ምንም ሃፍረት ሳይሰማቸው ከአንድ ብሄር በተውጣጡ ቡድኖች ቁጥጥር ስር በማድረግ፣ ወይም ደግሞ “ታኮ” ከመጋረጃ ጀርባ በማስቀመጥ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል። ከላይ እንደተገለጸው የትግራይ ተወላጅ ሃላፊዎችን በሙስና እንዲዘፈቁ በማድረግ፣ ወይም ሙስና ውስጥ ሲዘፈቁ አይቶ እንዳላዩ ሆኖ በማለፍ፣ በመፍቀድና፣ በማበረታታት የመንግስት ለውጥ ቢታሰብ እንኳን ከተቃዋሚው ጋር ተባባሪ እንዳይሆኑ የማስፈራሪያ ሪሞት ኮንትሮል ገጥመውላቸዋል። ይህ ስግብግብ ባህርያቸው እንቆረቆርለታለን ለሚሉት ለትግራይ ህዝብም እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው የሚሰማው። በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ህዝብ እነዚህን ግፈኞችን የደገፋቸው ታጋዮቹ እንዲህ አይነት የግለኝነት እና የአምባገነንነት ባህርይ ይኖራቸዋል ብሎ ሳይገነዘብ ነበር። የትግራይ ህዝብ የህወሃት ባለስልጣናት በጊዜው የደገፋቸው ዛሬ ለራሳቸው እልል ያለ ቪላ ቤት እንዲሰሩ፣ ለራሳቸው እጅግ ውብና ውድ መኪና እንዲገዙ፣ ከድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ጉሮሮ በመንጠቅና በውጭ አገር በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለግላቸው እንዲያስቀምጡ አልነበረም። ለስልጣናቸው ሲሉ የሃውዜንን ምስኪን ህዝብ በአውሮፕላን ያስጨፈጨፉ እጅግ እኩይ ሰዎች ናቸው። አቶ መለስ ሞት ባይገላግላቸው ኖሮ ከ22 አመት በኋላም ቢሆን ስልጣናቸውን ለመልቀቅ፣ ተተኪም ለማዘጋጀት ፈቃደኛ አልነበሩም።


የህወሃት ባለስልጣናት የራሳቸው ኪስ ስለደለበ ብቻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የደላው ስለሚመስላቸው የውሸት የእድገት ቁጥር ጨዋታ ያቀርባሉ። እነሱ እንደሚሉት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ከ22 አመታት በኋላም ቢሆን ከችግር፣ ረሃብና፣ እርዛት ኣልተላቀቀም። የህወሃት ባለስልጣናት ግን ገንዘብ ተርፏቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደ ውጭ አገር እያሸሹ እንደሆነ አለም የሚያውቀው ሃቅ ነው። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ይኸው ከ 24 አመት የስልጣን ጊዜ በኋላም ከ24 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን እርዳታ ይፈልጋሉ። የህወሃት ሰዎች ግን ሌላ መልስ አላቸው። ኢትዮጵያ፣ ከካሊፎርኒያ፣ ወይም ከአውስትራሊያ በተለየ መልኩ ድርቅ አልጎዳትም።

እኔ ግን ለእነዚህ ሰዎች ጥያቄ አለኝ። በየትኛው ስሌት ነው የካሊፎርኒያና የአውስትራልያ ድርቅ ከኢትዮጵያ ድርቅ ጋር የሚወዳደረው? በካሊፎርኒያ በድርቅ ሳቢያ የተራበ ሰው የለም። አውስትራሊያም ቢሆን በድርቅ የተነሳ እርዳታ የሚቀበል ሰው የለም። እኛም ጋ በድርቅ ሳቢያ የተራበ ሰው የለም ሊሉን ይሆን? ካሊፎርኒያም ይሁን አውስትራሊያ በድርቅ ምክንያት የቤት እንስሳት አልሞቱም፥ አዝርዕት አልተበላሸም። ቢሆንም በቂ ክምችት አላቸው። የእኛስ? በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ አርብቶ አደር ወይም ገበሬ ነው፥ ያውም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ምርት የሚያመርት ወይም ከእንስሳት ተዋጽኦ ተጠቃሚ። አዝርዕቱ ከደረቀ፣ ከብቶቹ ከሞቱበት ምን ይሆናል? አቶ ሃይለማሪያም የህወሃት የትሮይ ፈረስ ሆነው እንጂ ይህንን ከመናገራቸው በፊት ሊያስቡበት ይገባ ነበር። ውድድሩን ከማድረጋቸው በፊት የካሊፎርኒያስ ድርቅ ምን ይመስላል? የአውስትራሊያስ? የውሃ አጠቃቀማችንስ እንዴት ነው? የቁም እንስሳት አያያዛችንስ ምን ይመስላል? የሚለውን ሃሳብ እንኳን የማያገናዝቡ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በጭብጨባ በታጀበ መግለጫ አፋቸውን ሞልተው ሶስቱን አገሮች (?) በአንድ ሚዛን ሲለኩ ሰማሁ። የህወሃት የትሮይ ፈረስ ማለት እኚህ ናቸው። ህወሃቶች የሚፈልጉትን ሁሉ በእሳቸው ተመስለው የሚፈልጉትን መልዕክት ያስተላልፋሉ፣ እውነታው ግን ሌላ ነው። አቶ ሬድዋንም ቢሆኑ ያው “አርብቶአደሮቹ በጊዜው ውሃ ስላላጠጧቸው ነው ከብቶቹ ያለቁት” አሉ። አጃኢብ ነው! ከባለቤቱ በላይ ያወቀ ቡዳ ነው ይባል የለ! ጋዜጣዊ መግለጫውን የባዮሎጂ ክፍለጊዜ አስመሰሉት እኮ!

የህወሃት አሽከሮችና ጭፍሮቻቸው በምግብ ራሳችንን ችለናል የሚል ልፈፋ ሲያሰሙ ከርመው ነበር። የታል ታዲያ? እርግጥ ነው የህወሃት ባለስልጣናት ኪስ በ11 ሚሊዮን % አድጓል። የህዝቡ ኑሮ ግን 1% እንኳን ከፍ አላላም። እርግጥ ነው በህወሃት መንደር እና ሎሌዎቻቸው ቤት ምግብ ተትረፍርፏል፣ በሱማሌ፣ በአፋርና፣ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች፣ የገበሬዎች የቤት እንስሳትና የቀንድ ከብቶች ተረፍርፈዋል።

በጣም የሚገርመው የህወሃት ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም አይነት የፖለቲካ ግንዛቤ የለውም ብለው ማሰባቸው ነው። ያኔ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ አቶ ስዩም መስፍን ባድመ ለኢትዮጵያ ተሰጠች ብለው አስጨፈሩን፣ በኋላ ስንሰማ ግን የጨፈርነው በሞት ለገበርናቸው ወንድሞቻችን ደም ላይ ነበር!

ሌላው ህወሃት ኢትዮጵያ ውስጥ በማህበረሰባችን በነውርነት የሚታወቀው የውሸት ልማድ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው። ትውልድ ከእነዚህ መሃይማን ምን ይማራል? የህወሃት ቁልፍ የበላይ ሃላፊዎች ድርጀቱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀመሮ በሸፍጥ፣ በመግደል፣ በማሳደድ፣ በማሰር፣ በማሸማቀቅ እዚህ ለመድረስ በቅተዋል። በህልማቸው እንኳን አስበውት የማያውቁትን ሃብት አካብተዋል፣ አቅማቸው የማይፈቅድላቸውን ስራ ሰርተዋል፣ በማይመጥናቸው ወንበር ተቀምጠዋል፣ ታዛዥ መሆን ሲኖርባቸው በተገላቢጦሽ አዛዥ ሆነዋል። ከሁሉም በላይ ይቅርታ የማያስደርግ ወንጀል ውስጥ ተዘፍቀዋል። 100% የፓርላማና የአካባቢ ምርጫ አሸነፍን ብለዋል። ከህወሃት በላይ ጀግና የለም፣ አገሪቷን ከፈለግን እንደዶሮ ብልት ገነጣጥለን እንሄዳለን ብለዋል፥ አፍርሰን እንሰራለንም ብለዋል… ሌላም ሌላም።

የህወሃት ሰዎች የተከበሩ ተቋማትን አዋርደዋል። በአገራችን ውስጥ ለረጅም ጊዜ የተከበረው ሽምግልና በነፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ አማካኝነት ፈሩን ስቶ ገደል ገብቷል። ፍርድ ቤቶች የህወሃት የፖለቲካ መሳሪያ በመሆን በንጽሃን ላይ የውሸት ክስ በመመስረት ታሪክ ይቅር የማይለውን ፍርድ አስተላልፈዋል። በተለይም ወጣቶቹ የሚሰሩበትን የወጣትነት ጊዜያቸውን በግፍ በወህኒ ቤትና እንዲያሳልፉ በውሸት ክስ ከአሸባሪዎች ጋር በማያያዝ አስረዋቸው፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፈተዋቸዋል። ለምሳሌ የዞን 9 ጦማሪያን በአሸባሪነት ክስ ተከሰው በወህኒ ቤት ከአንድ አመት በላይ ሲማቅቁ ቆይተው ፕሬዚደንት ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ያለምንም የፍርድ ቤት ሂደት ፈተዋቸዋል። እንግዲህ ህወሃቶች ለስልጣናቸው ሊያሰጋቸው የሚችል ሰው ባይሆንም እንኳን ለሆድ የማይደለል ተቃዋሚ ወይም ጋዜጠኛ ባጋጠማቸው ቁጥር በመጀመሪያ ማስፈራራትና ማሰር፣ ካልሆነም መግደል ለአስርተ-አመታት የተካኑበት አሳዛኝ ድራማ ነው። እናም በኢትዮጵያ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ በውሸት ፖለቲካዊ ክስ ተፈርዶባቸው የሚማቅቁ ኢትዮጵያውያንን ማዕካላዊ፣ ቂሊንጦ፣ ዝዋይ፣ ሸዋሮቢት፣ እና ስማቸው የማይታወቁት የጨለማ እስርቤቶች ይቁጠሯቸው!

እንግዲህ ምርጫ በመጣ ቁጥር ተቃዋሚዎችን እያደኑ ማሰር ምርጫው ካለፈ በኋላ እንደገና መልሶ መፍታት የተነቃበት የህወሃት ታክቲክ ከሆነ ሰነባብቷል። የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ጋዜጠኞችን ሰሞኑን የተፈቱበት ሁኔታም ይኸው ነው። ወቅቱ ስለተቀየረ፣ ተፈተዋል። በሌላ ወቅት ደግሞ እነሱን ብቻም ሳይሆኑ ሌሎች ወጣቶች እንዲሁ ዘብጥያ መውረዳቸው አይቀርም። ሀብታሙ አያሌው፣ ዳኤል ሽበሽ፣ አብርሃ ደስታ፣ የሸዋስ አሰፋ፣ አብሃም ሰለሞን ሲፈቱ ሌሎች ባለሳምንት ደግሞ በቅርቡ ይገባሉ። እነዚህ ፖለቲከኞች አሁን የተፈቱበት ምክንያት የጦዘውን ፖለቲካዊ ተቃውሞ ለማቀዝቀዝ ይሆናል። ሰሞኑን ህወሃት ከባድ ፈተና ገጥሞታል።

በአንድ በኩል ከልዕለ-ሃያላን ከፍተኛ ወቀሳ ደርሶታል። በሌላ መልኩ ደግሞ ህወሃት ለማድረግ የፈለገው አንድ ነገር ይኖራል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት ድል ገንኖ መውጣት የመጀመሪያው ሲሆን፣ በኤርትራ በኩል የሚመጣውን ማንኛውንም ሃይል ለመምታት ያኮረፈውን የኢትዮጵያ ህዝብ “5 የፖለቲካ እስረኞችን” በመፍታት መካስ ይፈልጋል። በመሆኑም እነዚህን የተፈቱት የፖለቲካ እስረኞች ለኢትዮጵያ ህዝብ የቀረቡ የእርቅ ገጸበረከቶች መሆናቸው ነው።

በአሁኑ ሰአት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይህ የህወሃት መንግስት በሰላማዊ መንገድ ስልጣን እንደማይለቅ በጥብቅ ያምናል። በሌላ በኩል በጉልበት ስልጣን ላይ የወጣ እና በሙስና በአንድ ዘር የበላይነት የነገሰ “መንግስት” በምንም መልኩ አሁን ያለውን ጥቅሙንና ክብሩን ለመልቀቅ አይፈልግም። የራሱን ህልውና ሊያጠፋ የሚችል ነገር በምንም መልክ ይሆን ማዳፈን የመጀመሪያ ስራው ነው። በመሆኑም ትናንሽ መደለያዎችን በማቅረብ ህዝቡን ለማታለል መሞከር ከፍተኛ ጅልነት ነው። አቶ ሃይለማሪያም እንዳሉት፣ “የኢትዮጵያ ህዝብን ፈቃድ ጠይቀን ከኤርትራ ጋር ጦርነት እንገጥማለን” የሚል ጨዋታ ከዚህ በኋላ ሰሚ ጆሮ የለውም። ኣንደከዚህ በፊቱ ህዝቡ ሆ ብሎ ሻዕቢያን (አሁን ደግሞ አርበኞች ግንቦት ሰባትን) ለመደምሰስ በነቂስ ይወጣል ብለው ማሰባቸው ምን ያክል ህዝቡን እንደናቁት ያሳያል።

አሁን የጨዋታው ህግ ተቀይሯል። እንደከዚህ በፊቱ ሆ የሚወጣላቸው ተቃዋሚ ወይም ህዝብ አይኖርም። ህወሃሃት የራሷን አባላት ይዛ መዝመት ተችላለች። የአባላቱ ቁጥር ስንት ነበር? 7 ሚሊዮን? አዎ ሰባት ሚሊዮን አባል ለዘመቻ ብቻ ሳይሆን አገር ለመመስረትም በቂ ነው። 85 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብን ግን ይተውት!

አይሆንም! ህዝቡ ጠላቶቹና አሸባሪዎቹ እነማን እንደሆኑ አብጠርጥሮ ስለሚያውቅ ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ሲያሸብሩ የኖሩ ወያኔዎች ላይ አፈሙዙን ማዞሩ አይቀርም። አዎ! ህወሃት የአየር ሰአቷን አሟጥጣ ጨርሳለች። የተወሰኑ ሰዎችን በመፍታት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘትና ስልጣናቸውን በጦርነት ለማስረዘም መሞከር በፊት አዋጥቷቸው ይሆናል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ግን አያዋጣም። ህዝቡ ነቄ ብሏል፥ ህወሃት እስረኞችን ስለፈታች ተለውጣለች ማለት እንዳይደለ በደንብ ተገንዝቧል። ነገ ደግሞ ሌሎችን ማሰሯ እንደማይቀር ከልምድ የተማረው ህዝብ የህወሃትን ልብና ኩላሊት በደንብ መርምሯል።

ስለዚህ መቀየር ያለበት የህወሃት ሶፍትዌር ነው። አርጅቷል። በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት የዘረኝነት፣ የአምባገነንነት፣ የማን አለብኝ ባይነት፣ አድሏዊና የቂመኝነት አስተሳሰብ ይዞ አገርን የሚያክል ግዙፍ ነገር መምራት አይቻልም። ስለሆነም በአዲስ አሰተሳሰብ መቀየር አለበት። ከአርባ አመት ከፊት በነበረ ሶፍትዌር አሁንም አገር እየመሩ ያሉ ቡድኖች መፍረስ አለባቸው። ያ የሚሆነ ደግሞ የህወሃት ዘረኞችን ከስልጣን በማባረር ነው። ትግል መደረግ ያለበት ከሻቢያ ወይም ከግንቦት ሰባት ጋር አይደለም ፣ ከወያኔ ጋር ነው። ወያኔ ከተለወጠ ዘላቂ ሰላም ያመጣል፣ የሚገደል፣ በውሸት ክስ የሚታሰር አይኖርም። ከሁሉም በላይ ውሸት የሚፈበርክ ተቋም አይኖርም!

No comments:

Post a Comment