ጋሻው ገብሬ
እጅግ በጣም ደማቅ የአርበኞች ግንቦት 7 ድጋፍ ዝግጅት በቬጋስ ተከናውኖ በማየቴ እድለኛ ነኝ። ቬጋሶችን “እንኳን ደስ ያላችሁ” ማለት በጣም ይገባል። የድጋፍ ማሰባሰቡ ከ70 ሺ ዶላር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል።
እኔ በስደት ወደ አሜሪካ የመጣሁት እአአ 1981 ዓም ነበር።አሜሪካ የመማርና የመስራት እድል የሰጠኝ የተመሰገነ ሰው መርዳት የሚወዱ ሰዎች ያሉበት አገር ነው።ልክ እንደኔ በስደትም በሌላ ምክንያትም የመጣችሁ ይህን የኔን አባባል ትደግፋላችሁ ብዬ አምናለሁ።ላስ ቬጋስም በተለያዩ ምክንያት የመጡ ኢትዮጵያውያንን አገኘሁ። ወደ ቬጋስ ሄጄ ስለ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንድናገር እድል በማግኘቴ ነው አየሩም የወገን ፍቅሩም ሞቅ ያለውን ከተማ አይቼው መጣሁት።
ህብረታቸው ፤ድርጅታቸው፤ዝግጅታቸው እጅጉን የሚያስደስት፤ከቶም የማይረሳ ነው።አበው የሆኑ የተከበሩ አገር ወዳዶች ወጣት ከሆኑት ጋር እጅና ጓንት ሆነው ይሰራሉ።ሴት ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው የትም እንደሆነው ሁሉ ጥቂት ቢሆንም ነብሮች ናቸው።ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር ለአርበኞች ግንቦት 7 ያላቸው ግምትም ትልቅ ነው።
ስብሰባውን ስካፈል ከሌሎች ቦታዎች ለየት ያሉ አስተያየቶችን ነው ያሰማሁት።ሌሎች ቦታዎች ለምሳሌ በኤርትራ የምትታገሉት ምን ተማምናችሁ ነው?ሰላማዊ ትግል መቸ ውጤቱ ጨርሶ ታየ?በተቃዋሚዎች መካከል ያለው ልዩነት ሊጠብ አይችልም። የኢትዮጵያውያዊነት፤የዜግነት፤ የፍትህ፤ የእልነት፤ ጥያቄ እንደዝሆን ገዝፎ ቆሞ። የተለያዩ በጎን ያሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። በየላስ ቬጋስ ለየት ያለ ነው።ቁርጥ ያለ ግልጥ ያለ ነው አስተያየቱ። አገራችን ተበድላለች።በዳዮችዋን እናውቃለን ሊያድንዋት ለተነሱት ተገን ነን።ግጠሟቸው።ደጀናችሁ ነን።በቃ።
አንዱ ላገኘው እድል የገጠመኝ የቀድሞው የኢትዮጵያውያ ጦር አባል ከጀግናም ጀግና የላቀ ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ነው። ብዙ እንደሱ ያሉ ወገኖቸ እንዳሉ ሀቅ ነው።በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት የጀግንነቱ ታሪክ እንዲህ እንዳገኘሁት ወንድሜ ባለ ሲነገር ደስ ይላል።እሱ ልክ የጀግና ነው ንግግሩ። በጠላቱም ቢሆን የተፈጸመውን ጀብድ ይናገራል።ብዙ በተወራበት “ጦርነት መስራት እንችላላን” ድንፋታ በተሰማበት የላቀ ጀግናው የጀግና ታሪክ ያስገርማል።እራሱ ይተርከው ዘንድ እተወዋለሁ። እኔ በህወሀት ያዘንኩበትን ልናገር።ይህ የላቀው ጀግና ከሰራዊቱ በክብር ተሰናብቶ ትዳር ይዞ ልጆች ይወልዳል።ልጆቹ ለትምህርት እድሜአቸው ይደርሳል።በነመለስ የክልል ድንጋጌ ትምህርት በአንዱ አካባቢ ቋንቋ ብቻ ይባላሉ።ይህ አባትና ሌሎች ወላጆች ለምን ልጆቻች በቋንቋቸው ኦፊሴል በሆነው አይማሩም ብለው የወያኔ ካድሬዋችን ይሞግታሉ። አዳራሽ ሞልቶ ክርክር ይሆናል።የላቀው ጀግና ይህ ዓለም ያወቀው መብታችን ነው ብሎ ተከራከረ።ወደ አዳራሹ ክላሸን ቦምብ ይዘው ነበር ለውይይቱ የደረሱት የወያኔ ካድሬዋች።በሰላም የተረቱበት ክርክር ቢሆንም አንዱ የህወሃት ካድሬ ጀግናውን “አንተ ይህን ስትል ትግራይ ብትሆን ትሞት ነበር” ይለዋል።ስብሰባው ያልቅና ጀግናው ጓደኘቹ ካሉበት ከጨዋታ አምሽቶ ወደ መኖሪያው ለመሄድ አስቦ ጓደኞቹ ካሉበት ይሄዳል። ይህ ሁሉ ሲሆን ካድሬዎቹና የቀጠሯቸው ወሮበሎች ሲከታተሉት ቆይተዋል።አምሽቶ ጀግናው ወደቤቱ ሲነሳ ጭለማ ለብሰው እኒህ ፈሪዎች ተረባረቡበት።ጀግናውን ቀጠቀጡት።ሰባበሩት።በደረቱ መሳብ ብቻ እንዲችል አደረጉት፡ፈሪዎች ጀግናውን። አንደኛው ህወሀት “ልጨርሰው” ሲል ሌላኛው “እዚህ እኮ ጅብ አለ” ብሎ ተናገረ።የላቀው ጀግና በሰሜን ኢትዮጵያ ወታደራዊ ህይወቱ ትግርኛን የሚሰማ ነው:: ቬጋስ ያገኘሁት ጀግና ከዚህ በደል አምላክ ትረፍና ተናገር ያለው ነው።አርበኞች ግንቦት 7 ን መደገፉ ይህ ግፍ ይቁም። አገር የጋራ ትሁን። ዜግነት ይከበር የሚል ነው።የማልረሳው ወገኔን በቬጋስ አገኘሁት።ጀግናው ተደላድሎ የልጅ ልጆች አይቶ በቬጋስ ይኖራል። ቀን ሲወጣ ከልጆቹ ጋር ውድ አገሩን ያገለገላትን የተዋደቀላትን ጔዶቹን ያጣባትን መልሶ እንዲያይ እመኝለታለሁ።
ህወሃት መሩ መንግስት ብዙ በደል አድርሷል።በአዳራሹ ተነሰቶ የሚናገረው ሁሉ የየራሱ በደል አለው። “ንግዴን ቀሙኝ።”አከሰሩኝ” አሉ። አንዱ የድሜ ባለጠጋ ያገሬ ሰው። ከሁለት መቶ በላይ ሰው ቀጥሬ የማሰራበት ንግድ ነበረኝ። “አፈረሱት” አሉ ምርር ብለው። “ይሄው እኔ እዚህ አልባሌ ሥራ ሰራለሁ” አሉ።የጣት ቀለበታቸው ሳይቀር ለአርበኞች ግንቦት 7 ለገሱ።ኋላ ትሁት የሆኑት የአርበኞች ግንቦት 7 አስተባባሪዎች”ለዛሬ እርዳታ በቂ አግኝተናል” ብለው ቀለበታቸውን እንደ መለሱላቸው ሰምቻለሁ።እንዲህ ያሉት አዛውንቶች በመጦሪያቸው አገራቸውን፤ ህይወታቸውን ለምን ያጣሉ? ህወሃት መሩ ጥርቃሞ የሚደርስበት ተቃውሞ ከተቃዋሚ በጅምላ ሳይሆን እንዲህ ከሚመሰክሩ ሰዎች ነው።ተቃውሞው ከሕዝቡ ነው። ህወሃትን የጠላው ሕዝብ ነው።
ሌላ ትዝ የሚለኝ የበቃ ሙያ ያለው በቬጋስ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ያለው ነው።”ህወሃት እንደወራሪ ኅይል ያለ ነው”። አለ።”በሚቻለው መንገድ ሁሉ ታግሎ ማስወገድ ነው” “ወራሪ ኅይል” የሚለውን አገላለጥ ሌሎችም ቢጠቀሙበትም ይህ ባለሙያ በቀድሞ የትግል ሕይወቱ ህወሃትን የሚያውቅ መሆኑን በስሜት ሲናገረው “ወራሪ ኅይል” አድርጎ ቢመለከታቸው የረጅም ጊዜ ልምዱ ያሳየው ነው ብየ ደመደምኩ።እንደ ህወሃት አርሶ አደሩን የናቀ የበደለ የለም። በመሆኑም ነው ስምሪቱ ከትልቅ አስተትንሽ ስርቆት የሆነው።
ለነጻነት፤ ለውብ አገራችን ግጥሞችን ያሰሙትን ገጣሚም ላገኝ እድል አግኝቻለሁ።የማልረሳው ስጦታም ስላደረጉልኝ እድሜና ጤና ይስጣቸው እላለሁ።
ከማንም በላይ ወጣቶች በተግባር ለታዘብኩት ቅንብር ሁሉ የጀርባ አጥንት ናቸው።የኢትዮጵያ ህዝብ የፍትህ፤የነጻነት፤የእኩልነት ትግል ወሳኙ ወጣቱ ነው። የቬጋስ መንገዴ ዳያስፖራ ያሉ ወጣቶችና በግንባር በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉት እንዴት እንደሚናበቡ ማየት አስቻሎኛል።
ትግሉ አንድ ወሳኝ ደረጃ መድረሱን አመላካች የሆነው የእርዳታ ማሰባሰቢያ በታየው ትልቅ ውጤት መከናወኑ ወያኔን በተግባር ለመፈተን ህዝባዊ ሀይሎች
ማምረራቸውን በግልጽ አመልካች ነው።ይህ በሁሉም የአሜሪካ ከተሞችም መሆኑ ደስ ይላል። ቬጋስ ባገር ፍቅር የሞቀ ነው።አጋርነቱን ያስመሰከረ ዝግጁ የጀግና ስብስብ ያለበት ከተማ። በያለንበት የኢትዮጵያ አምላክ ያበርታን ።
እኔ የትግሉ አጋር ነኝ! እኔም ባለሁበት ዘማች ነኝ!
ከፍ ያለ ክብር ለአርበኞቻችን!
አንዳርጋቸው ጽጌ ይፈታ!
ያገራችን የእስልምና መሪዎች ይፈቱ!
ጀግና ጋዜጠኞቻችን ይፈቱ!
ኢትዮጵያ በሰላም ተከብራ በዜጎቿ ሁሉ አንድነት ለዘለዓለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment