Thursday, July 30, 2015

ወያኔዎች የአንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ለምን ያስጨንቃቸዋል?

ሽብሬ ደሳለኝ

ባለፉት 24 ዓመታት ወያኔዎች በሃገር ውስጥ (በሰላማዊ መንገድ) ለውጥ ለማምጣት የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ድርጅቶች እና ፖለቲከኞች ከማዳከም አልፈው በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ተጽኖ መፍጠር እንዳይችሉ አድርገዋቸዋል።

አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች የወያኔ አፈና ሲበረታ ከማምረር ይልቅ ፖለቲካውን እርግፍ አድርገው ይተውታል ወይንም ደግሞ ስደት ይወጡና ቀደም ሲል የተሰደደውን የኢትዮጵያ ስደተኛ ተቀላቅለው እንደ አብዛኛው ስደተኛ ቤተሰቦቻቸውን እና እራሳቸውን በኢኮኖሚ የማሻሻል ተግባር ላይ አተኩረው ይቀራሉ። ይህ እየተለመደ የመጣ አካሄድ ወያኔዎቹን ተመችቷቸው ኖረዋል፣ እነ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የጨዋታውን ህግ እስከቀየሩት ድረስ።

በርግጥም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ጓዶቹ ወደ ፖለቲካው ሜዳ ያመጡት አዲስ የጫወታ ህግ ሰርቷል!

ወያኔ አዲሱን የጨዋታ ህግ ከጅምሩ አልወደደውም፣ ከሚቆጣጠረው ግዛት ውጪ የሚደረጉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ኋይት ሃውስ ፊት ለፊት ሻማ ከማብራት ያለፉ እንዳይሆኑ ምኞቱ ነበር። ይህ አልሆነም።

አቶ አንዳርጋቸው እና ጓዶቹ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካን ወይንም የእንግሊዝን መንግስት በመለመን ነጻነታቸውን እንደማይቀናጁ ይልቁንም ብረት አንስተው ወያኔን በሚገባው ቋንቋ የማነጋገር አስፈላጊነትን አስተማሩ፣ ወተወቱ፣ የመውጪያ መግቢያ ቀዳዳዎችንም አመላከቱ… ኤርትራ!

ወያኔ በሃገር ውስጥ (በሰላማዊ መንገድ) የሚደረጉ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ሲያዳፍን፣ ለውጥ ፈላጊው ትውልድ የሃይል አማራጮችን እንደሚያማትር አልጠፋውም፣ ወያኔዎች የለውጥ ፈላጊው ትውልድ የሃይል አማራጮችን በስራ ላይ ለማዋል ተባባሪ/ፈቃደኛ የጎረቤት ሃገሮች እንደሚያስፈልጉት ቀደም ብሎ መተንበዩ አልቀረም (ወያኔ ከደርግ መንግስት ጋር ባደረገው የሃይል ትግል ወቅት ሱዳን እና ሶማሊያ ዋንኞቹ መጠለያው ነበሩ)። ከሃገር ጥቅም ይልቅ ለመንበረ ስልጣኑ ቅድሚያ የሚሰጠው ወያኔ ለኢትዮጵያ አጎራባች ሃገሮች ሁሉ የሚጠይቁትን እየሰጠ (ለምሳሌ ሱዳን ከሃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ ይገባኛል የምትለውን የኢትዮጵያ መሬት ከወያኔ ተቀብላለች) በምላሹም ተቃዋሚዎቹን እንዳያስጠልሉ፣ አልፎ ተርፎም ተቃዋሚዎቹን እያደኑ እንዲያስተላልፉለት አግባባቸው። ይሁንና ይህ አካሄድ በጎረቤት ኤርትራ ሊሰራለት አልቻለም።

አንዳርጋቸው ጽጌ እና ጓዶቹ አውርተው አልቀሩም፣ ከኤርትራ መንግስት ጋር የተሳካ ግንኙነት ፈጠሩ፣ ጦርም ማደራጀት ቻሉ፣ ቀደም ሲል ጀምሮ በኤርትራ መሬት ይንቀሳቀሱ በነበሩት ሃይሎች መካከልም መልካም እና መተማመን የሰፈነበት ግንኙነት እንዲኖር አስቻሉ።

ወያኔ ከሚቆጣጠረው ግዛት ውጪ የሚደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ እየበረታ መሄዱን በመገንዘብ እንቅስቃሴውን በእንጭጩ ለማስቀረት መንቀሳቀሱ አልቀረም፣ ይህንን ወያኔን እንቅልፍ የነሳ እንቅስቃሴ ወደ ተግባራዊነት እየቀየሩ ባሉት የግንቦት 7 አመራሮች ላይ አነጣጥሮ በተገዙና የተቃዋሚ ካባ በደረቡ ግለሰቦች አማካኝነት አመራሮቹን ከህዝብ ለመነጠል ከፍተኛ ሙከራ ቢያደርግም ውጤቱ አመርቂ አልሆነም። ወያኔ ከዚህ በኋላ ነበር አማተር ሰላዮቹን ወደ ኤርትራ በመላክ አርበኛውን አንዳርጋቸው ጽጌን ለመግደል ሙከራ ያደረገው ይህም አልተሳካም እንደውም ከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ ደረሰበት (ብዙዎች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጠንቅቀው የማያውቁት ሳይቀሩ የአንዳርጋቸውን ማንነት ለመገንዘብ ቻሉ)።


ወያኔ በመጨረሻ ያደረገው ሙከራ ተሳክቶለት አቶ አንዳርጋቸውን ከየመን አፍኖ ወደ አዲስ አበባ መውሰድ ቻለ።

ለጊዜው ወያኔዎች ከፍተኛ የድል አድራጊነት ሰሜት ተሰምቷቸው ጮቤ ረገጡ ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ደስታቸው እንደጉም በኖ እስካሁን በሚያቃዣቸው ስጋት ውስጥ እንዲዘፈቁ ሆነ። ጀግናቸው (አንዳርጋቸው ጽጌ) በወያኔ እጅ መውደቁን የሰሙ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከጫፍ ተነቃነቁ፣ አንዳርጋቸው የጀመረውን የትግል ጉዞ ከግብ ለማድረስም ቁርጠኝነትቸውን አሳዩ፣ የአንዳርጋቸው ቤተሰቦች ሴት ከወንድ ሳይባል በአንዳርጋቸው ጽጌ እግር ተተክተው አንዳርጋቸው ያቀጣጠለውን ችቦ ተረከቡ።

የግንቦት 7 ንቅናቄ አመራሮችና የአንዳርጋቸው የትግል ጓዶች ዙሩን አከረሩት፣ በተደጋጋሚ ከወያኔ ጋር ባካሄዳቸው የሽምቅ ውጊያዎች ልምድ ካካበተውና የሰሜኑን የኢትዮጵያ ግዛቶች መግቢያ መውጫ ጠንቅቆ ከሚያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ጋር ውህደትን ፈጠሩ፣ በውጤቱም አርበኞች ግንቦት 7 ተወለደ።

በለስ ቀንቷቸው አቶ አንዳርጋቸውን በእጃቸው ያስገቡት ወያኔዎች ከሚቆጣጠሩት ግዛት ውጪ እየተካሄ ያለው እንቅስቃሴ በአንዳርጋቸው መያዝ ምክንያት መባባሱን ተረድተዋል። የእንቅስቃሴውን ፍጥነት ለመግታት በቁጥጥራቸው ስር ያለውን አንዳርጋቸው ጽጌን ለመጠቀም በማሰብ እየቆረጡ እና እየቀጠሉ የሚለቋቸው የአዳርጋቸው ጽጌ ቪዲዮዎች ምንም ውጤት አላመጡም፣ ይልቁንም በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ ከፍተኛ ቁጭትን እየጫሩ አንዳርጋቸው ጽጌ የጀመረውን ትግል ከግብ ለማድረስ ቃላቸውን እንዲያድሱ አድርጓቸዋል።

ለዚህም ይመስላል አንዳርጋቸው ጽጌን የስፖርት ቱታ በማልበስ ሰው በሌለበት ጎዳና ላይ ፎቶ አንስተው “ተመልከቱ እባካችሁ አንዳርጋቸው ሰላም ነው” በማለት ኢትዮጵያውያኑን ለማረጋጋት የሞከሩት።

አርበኞች ግንቦት 7 ጥቃት መፈጸም ከጀመረና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ኤርትራ ገብቶ በአንዳርጋቸው እግር መተካቱ ከተሰማ በኋላ ደግሞ ወያኔዎች የአንዳርጋቸው ጉዳይ ፍም እሳት ሆኖባቸው የሚያደርጉትን አሳጥቷቸዋል፣ ለዚህም ምልክቱ ቴድሮስ አድሃኖም በቪኦኤ ላይ የተናገረው ነው “አንዳርጋቸው ላፕ ቶፕ ተሰጥቶት መጽሃፍ ጽፎ ጨርሷል፣ አንዳርጋቸው የሃገሪቱን ልማት ማየት ፈልጎ እያዟዟርን አሳይተነዋል ወዘተ…”

እውነታው ግን አንዳርጋቸው ጽጌን የት እንዳሰሩት አይናገሩም፣ አንዳርጋቸውን ቤተሰብም ሆነ ማንኛውም ሰው አይጎበኘውም። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ወያኔዎች በአንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የሚያውቁትን የማሰቃያ መንገዶች ሁሉ በመጠቀም አንዳርጋቸው እነርሱ የሚፈልጉትን አይነት መልእት እንዲያስተላልፍ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። ይሁንና ጀግናው አንዳርጋቸው ጽጌ እስካሁን የሚፈልጉትን አልሰጣቸውም (ይህንንም ለማረጋገጥ በአቶ አንዳርጋቸው ላይ ስቃይ እየፈጸሙ ቀርጸው የሚያሰራጯቸውን ቪዲዮዎችን መመልከት ይበቃል)።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በአካል ተገኝቶ ትግሉን መምራት ባይችልም መንፈሱ ግን ትግሉን በማቀጣጠል ላይ ይገኛል። እንግዲህ ወያኔዎች የአንዳርጋቸው ጽጌን ለመቆጣጠር ነው ቁጭ ብድግ በመስራት ላይ ያሉት፣ ይሳካላቸው ይሆን? ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል።

No comments:

Post a Comment