Saturday, June 28, 2014

ትንሽ ስለ እስክንድር ............

በቅዱስ ዮሃንስ

ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆነው እስክንድር ነጋ ገድል ከነፃው ፕሬስ ውልደት ጀምሮ አሁን የመጨረሻው አፋፍ ላይ እስከ ደረሰበት ጊዜ የሚዘልቅ ነው። ብዙዎች ከእስክንድር ጋር ረጅሙን ጉዞ የጀመሩ ዛሬ አጠገቡ የሉም፡፡ ያ! እንደ እሳት የሚፋጀው የብእር ትሩፋታቸው ከአንባቢ ማእድ ከራቀ ዘጠኝ አመት ሞላው፡፡ አንዳንድ የብእር ገበሬዎች እስር ቤት ባፈራዉ ህመም ምክንያት መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ብዙዎቹ የሚወዷት ሀገራቸውን ጥለው ተሠደዋል፡፡ ለምሳሌ ጋዜጠኛ ቅዱስሀብት በላቸው፣ ፋሲል የኔያለም፣ የነፃው ፕሬስ ፊት አውራሪ የነበሩት አቶ ክፍሌ ሙላት፣ ከፍያለው ማሞ ይጠቀሳሉ፡፡ እስክንድርስ?

እስክንድር ግን ፍፁም ለየት ያለ ባህሪ ያለው ሠው መስሎ ታየኝ፡፡ ከመልካም ቤተሰብ ፍቅርን ሲመገብ ያደገው ይህ ልበ ሙሉ ጋዜጠኛ የምቾትና የተንደላቀቀ ኑሮውን በመተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት ሲል ከአሁኑ እስር በፊት እንኳ ከሰባት ጊዜያት በላይ ወደ ወህኔ አምባ ተወርውሯል፣ አንድ ባልታደለች ማለዳ ላይ ደግሞ ባልታወቁ ሠዎች ተደብድቦ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ እስክንድር በእውቀት የመጠቀ ብቻ ሣይሆን የመልካም ባህሪ ባለቤትም ነው፡፡ ለዚህም ነው እንደ ጥጃ እያሠሩ የሚፈቱትን፣ በጋዜጠኝነት ሙያ እንዳይሰማራ ያገዱትንና የአይምሮው ጭማቂ የነበረውን መጽሀፍ ማሳተም አትችልም ያሉትን የዘመናችንን ፈርኦኖቹን አንድም ጊዜ በጥላቻ አይን ያላየው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምስክሮቹ በጋዜጣ አሊያም በድረ-ገጽ ይጽፋቸው የነበረው በሣል ትችቶች ናቸው፡፡ እርግጥ ነው ይህን የለየለት የአመባገነን ሥርዓት በሠላ ሂስ በርካታ ጊዜ ሸንቁጦታል፡፡ ይህ ደግሞ ለእናት ኢትዮጵያ መፃኢ እድል ከመጨነቅና ከመጠበብ የተነሳ ነው፡፡ ‹‹አካፋን አካፋ›› ማለት ከአድርባይና ከባንዳ ጋዜጠኛ አይጠበቅም፡፡ እስክንድር ግን የእናት ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ እንቅልፍ የነሳው በመሆኑ የወያኔን የእውር ድንብር ጉዞን በተባ ብእሩ ኮንኗል፣ ሥርዓቱ በትክክለኛው ሀዲድ እንዲጓዝ ሞክሯል፡፡ ዘክሯል፡፡ ምላሹ ግን ከሥራ ማገድ፤ በመጨረሻም የከፋ የእስር ወሳኔ ተላልፎበታል፡፡ ሰውየው ጀግናው እስክንድር ነጋ ሆነ እንጂ ገዢዎቻችን በህይወት የመኖር መብቱን ገፈውታል፡፡ ይኼ ሁሉ ግን ከዓላማው አላዛነፈውም፤ ራሱን ለአገሩ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያን ከምለቅ ሞቴን ብሎ ጨቋኙን አገዛዝ በመጋፈጡ ለከፋ እስር ተዳርጓል። ይህ ጀግና አሁን ላለው ትውልድ የዓላማ ጽናት ተምሳሌ ነው፡፡


በመጨረሻም ባለፈው ሳምንት በዓለም የጋዜጠኞች እና የዜና አታሚዎች ማኅበር የዓመቱ የወርቅ ብዕር የ “pen Golden of freedom 2014″ ተሻላሚ በመሆኑ ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› ለማለት ኬክ አስጋግረን ወደቃሊቲ አምርተው ነበር። በነበራቸው አጭር ቆይታም እስክንድር ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን ከሰላማዊ ምክሮች ጋር እንደለገሳቸውና ለኢትዮጵያ ህዝብም አድሩስልኝ ያላቸውን መልዕክት በተለያዩ ሚዲያዎች አስተላልፈው ተመለከትኩኝ። መልዕክቷ እንዲህ ትነበባለች፡

''ሀገር ስትወረር ወይም ጠላት በሀገር ላይ ጦርነት ሲያውጅ ሁሉም ኢትዮጵዊ በአንድነት ‹‹ሆ!›› በማለት የተቃጣውን ወረራም ሆነ ጦርነት ለመመከት እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ሁላችንም ዴሞክራሲ ያሻናል፡፡ ሁላችንም ሀገር ሲወረርብን እና ጦርነት ሲታወጅብን በአንድነት እንደምንቆመው ሁሉ ይህንን ያጣነውን ዴሞክራሲ ለመጎናጸፍ፣ ሁላችንም በሰላማዊ መንገድ አጅ ለእጅ ተያይዘን እና አንድ ሆነን መታገል ይኖርብናል፡፡ ከትግሉም በኋላ ለውጥ ይመጣል፡፡ ያኔ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን ስለሚፈጠር ሁሉም በየመንገዱ ይጓዛል፡፡ ለምሳሌ እኔ፣ ምንም የምፈልገው ሥልጣን የለም፡፡ ፍላጎቴም አይደለም! የሕይወት መስመሬ ጋዜጠኝነት ነው፡፡ ያኔ በምወደው የጋዜጠኝነት ሙያ እየሰራሁ እቀጥላለሁ፡፡ የህይወት መስመሩ ፖለቲከኝነት የሆነም ሰው በዚያው ይቀጥላል፡፡ ምሁሩም አካዳሚካዊ ነጻነት ስለሚያገኝ ወደሚወደው የትምህርት፣ የምርምርና ጥናት ዘርፍ ላይ በነጻነት ይሰማራል – ሌላውም በመንገዱ፡፡ ይህ እንዲፈጠር ግን ዛሬ ላይ በጋራ መታገል የግድ ይለናል!''

መልዕክቷን ተግባራዊ እንዳርግ ዘንድ ይሁን!

No comments:

Post a Comment