Wednesday, June 18, 2014

ለጊዜ ቀጠሮዉ ሌላ ጊዜ ቀጠሮ


ፍቃዱ አንዳርጌ

በአንድ ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር የዋለን ሰዉ የያዘዉ አካል ወዲያዉኑ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ፍርድ ቤት የመቅረቡ ዋና አብይ ጉዳይ የእስሩን ህጋዊነት ለማረጋገጥ ከመሆኑም በተጨማሪ ቀጣዩን ሂደት ለአቅጣጫ ለማስያዝ ነዉ፡፡ ተጠርጣሪዉ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ጉዳዩ የምርመራ ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ሲያምን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ የጊዜ ቀጠሮ መሰረተ ሃሳብ የሚጀምረዉ ከዚህ ደረጃ ላይ ነዉ፡፡ የጊዜ ቀጠሮ ቀጥተኛ ትርጉም በህጉ ተገልፆ የማናገኘዉ ሲሆን በተለምዶ ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎች ለምርመራ የሚቆዩበትን ተጨማሪ ጊዜ በተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ እያልን እንጠቀምበታለን፡፡

የኢፌዲሪ ህግ መንግስት አንቀፅ 19(4) የተያዙ ሰዎች ስላለቸዉ መብት ፍርድ ቤት የተያዙ ሰዎች በጥበቃ ስር እንዲቆዩ ወይም ምርመራ ለማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ ሲጠየቅ አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ ሊፈቅድ እንደሚችል ይናገራል፡፡ ይህ የህገ መንግስት ድንጋጌ ጊዜ ቀጠሮ ሊፈቀድ የሚገባዉ አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ ነዉ በማለት ሲያስቀምጥ የተጠየቀዉን ሁሉ ስለተጠየቀ ብቻ መፍቀድ በተያዘዉ ሰዉ መብት ተቃራኒ መቆም መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የምርመራ ጊዜ ፈቃድ አሰጣጥ አሁን ባለዉ የህግ ስርዓት በሁለት መልኩ ከፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን በተሻሻለዉ የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ የሚታዩ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግን መሰረት አድርገዉ እና በፀረ-ሽብርተኝነት የሚታዩ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡በሁለቱም ህጎች ጊዜ ቀጠሮን የሚሰጡት በማረፊያ ቤት ለምርመራ የሚቆይበት ጊዜ በማለት ነዉ፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጉ ለአንድ ጊዜ ምርመራ አስራ አራት ቀን ጊዜ ያለገደብ የተቀመጠ ምርመራዉ እስካላለቀ ድረስ ጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ መኖርን የሚፈቀድ ነዉ፡፡ በፀረ-ሽብርተኝነት ህግ የአንድ ቀጠሮ የምርመራ ጊዜ ሃያ ስምንት ቀን ሆኖ በአራት ወር የተገደበ ነዉ፡፡


ዋናዉ ፍሬ ነገር በጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤቶቻችን ምን ዓይነት ሚና ይኖራቸዋል የሚለዉ ነዉ፡፡ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 13(1) የዳኝነት አካሎች በህገ መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተመለከቱት መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የማክበርና የማስከበር ሃላፊነትና ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡ ስለተያዙ ሰዎች ምርመራም የህገ መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት አንቀፅ 19(4) ጊዜ ቀጠሮን አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ ፍቀዱ በማለት ፍርድ ቤቶችን አሳስቧል፡፡ መርማሪ ሺህ ጊዜ ቢጠይቅ የሚሰጠዉን ተጨማሪ ጊዜ ሊወስን የሚችለዉ ፍርድ ቤቱ ነዉ እንደማለት ነዉ፡፡ ቀደም ሲል ያየነዉ የህገ መንግስቱ ድንጋጌ ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮ መሰጠት ያለበት አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ እንደሆነ ነዉ፡፡ “አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ” የሚለዉን ሃረግ ልንመለከተዉ የሚገባ እንደ ጉዳዩ እየታየ የሚወሰን በሚል ነዉ፡፡ ”ሀ” ለተጠረጠረበት ጉዳይ ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ለ”ለ” ላንስጠዉ እንችላለን፡፡ ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮን ቀን የሚወስነዉ መርማሪዉ በተሰጠዉ ጊዜ ያከናወናቸዉን ስራዎች በመመልከት፣ ማስረጃዎች ሊገኙ የሚችሉበትን ሁኔታ ርቀት፣ ከጉዳዩ ዉስብስበነት ወይም ቅለት እንዲሁም የተመርማሪዎች አደገኛነት ሁኔታ በመመልከት ነዉ፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይኖር እያንዳንዷ የጊዜ ቀጠሮ በአግባቡ እየተመረመረ መወሰን ከፍርድ ቤቱ የሚጠበቅ ነዉ፡፡
በተጨማሪም መርማሪዉ አካል በተሰጠዉ የጊዜ ገደብ ምርመራዉን በማጠናቀቅ በአፋጣኝ ለፍርድ ቤቱ ዉጤቱን ማስታወቅ ይጠበቅበታል፡፡ በአብዛኛዉ የወንጀል መርማሪወዎች ምርመራዉን ከራሳቸዉ ሁኔታ ብቻ በመመልከት ሰፋ ያለ ጊዜ የሚጠይቁበት ጊዜ የበዛ ነዉ፡፡

በስራ አጋጣሚ ከታዘብኳቸዉ መርማሪዎች ሁሉም ማለት ይቻላል አስራ አራት ቀን በታች ጠይቀዉ የማያዉቁ ናቸዉ፡፡ የአንድ ቀን ምርመራ ለሚያስፈልገዉ ጉዳይ አስራ አራት ቀን መጠየቅ ማለት ከአስራ አራቱ ቀን በአንዱ ቀን ምርመራዉን አጠናቅቃለሁ በማለት እንደመቀለድ ነዉ፡፡ ለምርመራ ሰፊ ጊዜ መስጠት መርማሪዎችን ገና ሰፊ ጊዜ አለ በሚል እሳቤ ለምርመራዉ ትኩረት እንዳይሰጡ እና እንዲዘናጉ በማድረግ የተመርማሪዎች መብት ጥያቄ ዉስጥ እንዲወድቅ ከማድረጉም በተጨማሪ ተመርማሪዉን በህግ ሽፋን ህግን እንደ ዱላ በመጠቀም መቀጥቀጥ ነዉ፡፡ ለዚህም ይመስላል ፍርድ ቤቶች ጊዜ ቀጠሮዉን ከመወሰናቸዉ በፊት መርማሪዎች ቀደም በተሰጡት ጊዜ ያከናወኑትን ምርመራ መዝገቡን አስቀርበዉ ሊመለቱ ይገባቸዋል የሚባለዉ፡፡ የሃያ ስምንት ቀን ተሰጥቶት የአንድን ምስክር ብቻ ቃል የተቀበለ ዘገምተኛ መርማሪ ተጨማሪ ሃያ ስምንት ቀን መፍቀድ ማለት በግልፅ ተኝተህ ክረም የሚል ትዕዛዝ ከመስጠት የማይተናነስ ነዉ፡፡ የጊዜን ጥቅም ሊያወቅ የሚቻለዉ ጊዜ ያጠረዉ መርማሪ ነዉ፡፡ ጊዜ በገፍ ከተሰጠዉ መርማሪ የጊዜን ጥቅም የሚያወቀዉ ሃያ ሰባቱን ቀን ተኝቶ በሃያ ስምንተኛዉ ቀን ምርመራዉን እንዳለጠናቀቀ ሲረዳ ነዉ፡፡ ፍርድ ቤቶች የመርማሪዎችን የምርመራ መዝገብ ተቀብለዉ መገምገም በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ማከናወን ያለባቸዉ ግዴታ ቢሆንም በአብዛኛዉ ጊዜ ይህንን ሲያደርጉ አይታይም፡፡ የተለመደዉ አሰራር በቀጠሮዉ ቀን መርማሪ ምርመራህን ከምን አደረስክ ብሎ መጠየቅ ነዉ፡፡ መዝገቡ የማይታይበት መርማሪ ብዛት ያለቸዉን ምስክሮች ቃል ተቀብያለሁ፤ ቀሪዎቹ ምስክሮችና ተጠርጣሪዎች ወደ ክፍለ ሃገር ስለሄዱ እንዲሁም የትርጉም ስራ ስላለቀ የሚል መሽሎኪያ ሃሳብ በማቅረብ ጊዜ ቀጠሮዉን በገፍ አስፈቅዶ ይወጣል፡፡ ሃምሳ ሁለት ቀን ከዚህ ግባ የሚባል ማስረጃ ያለገኘ መርማሪን በተጨማሪዉ ሃያ ስምንት ቀን አስረጅ ማስረጃ ያገኛል ብሎ ጊዜ መፍቀድ ትንሽ ፈገግ ያሰኛል፡፡

ሌላዉ ከጊዜ ቀጠሮ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለዉ የተጠርጣሪዎችን የመደመጥ መብት በተመለከተ ነዉ፡፡ ጊዜ ቀጠሮ ራሱን የቻለ በፍርድ ቤት የሚደረግ የስነ ስርዓት ሂደት በመሆኑ እኩል የመደመጥ ይጠይቃል፡፡ መርማሪዉ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ በማለት በሚያቀርብበት ጊዜ ለተጠርጣሪዉም ከመርማሪዉ ሃሳብ ላይ አስተያቱን እንዲሰጥ ማድረግ ከፍርድ ቤቱ ይጠበቃል፡፡ ተጠርጣሪዉ አስተያየቱን መስጠቱ አስፈላጊ የሚሆነዉ በተጠርጣሪዉ ላይ ሲደረግ የነበረዉን ምርመራ በማረጋገጥ ወደ ፊት ሊሰጥ የሚችለዉን ጊዜ ለመወሰን ጠቃሚነት ሊኖረዉ ስለሚችል ነዉ፡፡ እኩል የመደመጡ መብት ሃሳብን በመግለፅ ብቻ የሚገደብ ሳይሆን የምርመራዉን ሂደት መሊኪያ እስከማድረስ የሚጠይቅ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በሁለተኛዉ ጊዜ ቀጠሮ ጋዜጠኛ አስማማዉ ፍርድ ቤቱ በፈቀደዉ የጊዜ ቀጠሮ በተደጋጋሚ ሌሊት እየተጠራዉ የዞን 9 አባል መሆንክን እምን ከመባል ዉጪ ሌላ የተደረገ ምርመራ የለም በማለት ያሳሰበዉን መርማሪዎች ካቀረቡት ሃሳብ ጋር እኩል ዋጋ መሰጠት የነበረበትና እንዲሁም ፖሊስ በምርመራ ዉጤቱ አዲስ ነገርና ተጨባጭ ማስረጃ ሳያቀርብ ሌሎች ተጠርጣሪዎች እየሸሹብኝ ነዉ፣ምስክሮቼ በግበረ አበሮች ማስፈራሪያ እየደረሳቸዉ ነዉ ያለዉን በመመለከት ሊሰጥ የሚችለዉን የጊዜ ቀጠሮ ቀን ለመወሰን በአንፃራዊ መሊያነት ሊወሰድ ይገባዉ ነበር፡፡

በአጠቃላይ ዞን 9 ጋር ተያይዞ የሚሰጠዉ ጊዜ ቀጠሮ ስለተጠየቀ ብቻ በገፍ መፈቀዱ፣ በሰተጠዉ ጊዜ ቀጠሮ ማከናወን ያለበትን ተግባር ያለከናወነ መርማሪ በዝምታ መተላፉ እንዲሁም ህገ መንግስቱ በተቀመጠዉ ድንጋጌ መሰረት ጊዜ ቀጠሮዉ እየተሰጠ ያለዉ አስፈላጊ በሆነዉ መጠን ብቻ አለመሆኑ ለጊዜ ቀጠሮዉና ሰጩ አካል ሌላ ጊዜ ቀጠሮ ሳያስፈልገዉ አይቀርም፡፡

‪#‎FreeZone9bloggers‬ ‪#‎FreeEdom‬ ‪#‎FreeTesfalem‬ ‪#‎FreeAsemamaw‬ ‪#‎Ethiopia‬

No comments:

Post a Comment