Thursday, November 5, 2015

ረሃብ የመንግሰት ፖሊሲ ብልሹነት እንጂ የዝናብ እጥረት ዉጤት አይደለም!

ኤፍሬም ማዴቦ- ከአርበኞች መንደር !!

ደርግ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሤን ስርዐት ከደመሰሰ በኋላ ወሎ፤ ትግራይና ሰሜን ሸዋ ዉስጥ ህዝብ እንደ ቅጠል ሲረግፍ እሳቸዉ የልደት በዐላቸዉን ለማክበር ከዉጭ አገር ኬክ ያስመጣሉ ብሎ ነበር ንጉሰ ነገስቱንና ስርዐታቸዉን የከሰሰዉ። በአስራ ሰባቱ የደርግ ዘመን ሁለት ግዜ ከባድ ረሃብ ተነስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን አልቀዋል። በተለይ በ1977 ዓም ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከሰተዉና የአለምን ህዝብ ያስደነገጠዉ ረሃብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን እንደ ቅጠል ሲያረግፍ ደርግ የስብሰባ አዳራሽ ለመስራትና የኢሠፓን ምስረታ ለማክበር ብዙ ሚሊዮን ዶላር እንዳባከነ ይታወሳል። ህወሃት የደርግን ስርዐት ሲዋጋ የኢትዮጵያን ህዘብ ከጎኑ ለማሰለፍ ከተጠቀመባቸዉ ዋና ዋና የፕሮፓጋንዳ ስራዎች ዉስጥ አንዱ ይህንኑ ረሃብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸንን ሲገድል ደርግና ባለሟሎቹ የፓርቲ ምስረታ ለማክበርና አዳራሽ ለማሰራት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያባክናሉ የሚል ፕሮፓጋንዳ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ዉስጥ ለደረሰዉ ረሃብ ዋናዉ ምክንያት የዝናብ እጥረት ሳይሆን የደርግ የተበላሸ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ፖሊሲ ነዉ ብሎ ደጋግሞ ደርግን መክሰሱ አይረሳም። ህወሃት ኢትዮጵያን በመራባቸዉ ባለፉት ሃያ አራት አመታት ዉስጥ የዘንድሮዉን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ሦስት ግዜ ለረሃብ አደጋ ተጋልጧል። የዘንድሮዉ ረሃብ ደግሞ ስፋቱና ጥልቀቱ እጅግ በጣም አደገኛ መሆኑ በአለም አቀፍ የመገናኛ አዉታሮች እየተነገረ ነዉ።

ዛሬ ኢትዮጵያ በየአመቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የዉጭ ዕርዳታ ታገኛለች፤ በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ትበደራለች፤ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የዉጭ ምንዛሪ በዉጭ አገር ከሚገኙ ዜጎቿ ታገኛለች። ኢትዮጵያ ዉስጥ ከፍተኛ የልማት ሰራዎች እንደሚሰሩ ይነገራል። ግድቦች፤ መንገዶች፤ ህንጻዎችና የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ይገነባሉ እየተባለ ይነገራል። የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በአመት ከ10% በላይ እንደሚያድግ ይነገራል። ይህ ሁሉ ሆኖ ረሃብ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል። ለምን? ከህወሃት በፊት የነበሩት ሁለት መንግስታት በስልጣን ላይ በነበሩበት ግዜ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለደረሰዉ ረሃብና በረሃብ ላለቁ ወገኖቻችን ተጠያቂዎች ነበሩ። ደርግና የቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ ስርዐት የተከተሏቸዉ ብልሹ የሆኑ የኤኮኖሚ ፖሊሲዎችና ጎታች የመሬት ይዞታ አስተዳደር በሁለቱ ስርዐቶች ዉስጥ ለደረሰዉ ረሃብ አይነተኛ ምክንያቶች ነበሩ። ዛሬስ የሃያ ሚሊዮን ወገኖቻችንን ህይወት አደጋ ላይ ለጣለዉ ረሃብ ምክንያቱ ምንድነዉ? ተጠያቂዉስ ማነዉ? በነገራችን ላይ ህወሃት ሠላም አነገስኩባት በሚለዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ረሃብተኛ ቁጥር ላለፉት አምስት አመታት በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰዉ ሦሪያ ዉስጥ ካለዉ ረሃብተኛ ቁጥር ይበልጣል።

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ህዝብ በአጭር ግዜ ዉስጥ በቀን ሦስት ግዜ የመብላት ዋስትና ይኖረዋል ብለዉ ባዶ ተስፋ ከቀለቡን በኋላ የዘንድሮዉን አመት ጨምሮ እኛ ትዮጵያዉያን ሦስት ግዜ የረሃብ አደጋ ላይ ወድቀናል። ለመሆኑ ምን ይሆን ባለ ራዕዩ መሪ ያዩልን ራዕይ? በቀን ሦስት ግዜ መብላታችንን ወይስ ረሃብ ሦስት ግዜ እንደሚጎበኘን? ከአንድ አመት በፊት ክረምቱ መገባደጃ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያ ዉስጥ 6.5 ሚሊዮን ህዝብ የረሃብ አደጋ ይጠብቀዋል ብሎ ባስጠነቀቀ ማግስት ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በምግብ ምርት እራሷን የቻለች አገር ሆናለች ብለዉ ለአለም አወጁ። እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በሰኔ 2015 ዓም እኚሁ ሰዉ ኢትዮጵያ ረሃብን በግማሽ እንደምትቀንስና በአመቱ ማለቂያ ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለረሃብ የሚጋለጠዉ ህዝብ ከ5% በታች እንደሚሆን አረጋገጡ። በተመድና በብዙ ለጋሽ አገሮች ጥናት መሠረት በ2015 ማለቂያ ላይ ከኢትዮጵያ ህዝብ 21% የሚሆነዉ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ካላገኘ ከፍተኛ አደጋ ይጠብቀዋል። ለምንድነዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሪ ነን ተብዬዎች የኢትዮጵያን ህዝብ የማይጨበጥ ባዶ ተስፋ የሚቀልቡት? ለምንድነዉ ፈጣኑና ታዳጊዉ የአፍሪካ ኤኮኖሚ ለዜጎቹ የስራ ዕድል መፍጠር ተስኖት ወጣት ኢትዮጵያዉያን አገራቸዉን እየጣሉ የሚሰደዱት? ለምንድነዉ በቀን ሦስቴ ትበላላችሁ ተብለን አንዱም ያረረብን? ለምንድነዉ በምግብ እህል እራሳችንን ችለናል ተብሎ ተነግሮን መንፈቅ ሳይሞላ ረሃብ የሚጨፈጭፈን? ለምንድነዉ? . . . ለምንድነዉ? . . . ለምንድነዉ?

በቅርቡ CNN እና ኒዮርክ ታይምስን ጨምሮ አያሌ ታዋቂ የአለማችን መገናኛ አዉታሮች ኢትዮጵያ ዉስጥ እየመጣ ያለዉን አስፈሪ የድርቅ አደጋ መዘገብ ሲጀምሩ ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ድርቅ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አዉስትራሊያንና አሜሪካንን ጭምር እንዳስቸገረ ገልጸዉ ነበር። ይባስ ብለዉም “ኤልኒኖ” የተባለዉን የተፈጥሮ ክስተት ኢትዮጵያ ዉስጥ ለተከሰተዉ ድርቅ ተጠያቂ አድርገዋል። የሚገርመዉ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝና መንግስታቸዉ ዛሬ ምግብ ካልሰጣችሁን በረሃብ ልናልቅ ነዉ እያሉ የሚወተዉቱት እንደ ኢትዮጵያ እነሱንም ድርቅ መቷቸዋል ያሉትን አሜሪካንና አዉስትራሊያን ነዉ። በነገራችን ላይ ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ትክክል ናቸዉ – ድርቅ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደገባ ሁሉ አሜሪካና አዉስትራሊያ ዉስጥም ገብቷል፤ ኤልኒኖም ኢትዮጵያ ዉስጥ በተከሰተዉ የአየር ጸባይ መዛባት ላይ ተፅዕኖ ነበረዉ። ሆኖም እሳቸዉ ስራ ስለሚበዛባቸዉ ረስተዉ ሳይጠቅሱት ቀረ እንጂ ድርቅ ጎረቤት አገር ኬንያ፤ ሱዳንና ኤርትራ ዉስጥም ገብቷል። ጠ/ሚኒስትሩ የኮነኑት ኤልኒኖም ቢሆን ኤርትራንና ኬንያን ዘልሎ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ አልመጣም። ድርቅ ማለት ደግሞ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠዉ በቀር የዝናብ እጥረት ማለት ነዉ። ዝናብ በተከታታይ ካልዘነበ ዬትም አገር ዉስጥ ድርቅ ይከሰታል። ነገር ግን ድርቅ ሁሉም አገር ዉስጥ ወደ ረሃብ አይለወጥም። ድርቅን አስመልክቶ በአገሮች መካከል ያለዉ ትልቁ ልዩነትም እዚህ ላይ ነዉ። አንዳንድ አገሮች ድርቅን በሩቁ ያዩና ዝግጅት አድርገዉ ረሃብን ይከላከላሉ፤ እንደ ኢትዮጵያ አይነቶቹ በልመና የተካኑ አገሮች ደግሞ ድርቁ ወደ ረሃብ እስኪለወጥ እጃቸዉን አጣጥፈዉ ይጠብቁና ህዝቡ ሲራብ አለም አቀፉን ህብረተሰብ “ስለ ማሪያም” ማለት ይጀምራሉ።


በቅርቡ ፕሮፌሰር መስፍን በግልጽ እንደተናገሩት አገራችን ኢትዮጵያ ክብሯንና ኩራቷን ለምዕራባዉያን አሳልፋ የሸጠች አገር ሆናለች። ምዕራባዉያንም በተለይ አሜሪካና ታላቋ ቢሪታኒያ ለዚህ በርካሽ ዋጋ ለገዙት ክብርና ልዕልና ሲሉ ኢትዮጵያን እንደ በኩር ልጃቸዉ በአንቀልባ ታቅፈዉ እሹሩሩ ሲሉ ከርመዋል፤ አሁንም እያሏት ነዉ። የአሜሪካዉ ባራክ ኦባማና የእንግሊዙ ዴቭድ ካምርን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያን ሲጠቅሱ ተአምረኛዉ ኤኮኖሚ፤ በድርብ አኃዝ የሚያድገዉ ኤኮኖሚ ወይም የአፍሪካ ፈጣኑ ኤኮኖሚ እያሉ ነዉ። የህወሃት አገዛዝም ጧትና ማታ ስራዬ ብሎ የሚደክመዉ “ተዳጊዉ ኤኮኖሚ” ለመባል ነዉ እንጂ የ96 ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያንን ህይወት ለመለወጥ አይደለም። ለዚህም ነዉ 15 አመት ሙሉ ፈጣን ዕድገት፤ ህዳሴ፤ ትራንስፎርሜሺን እየተባለ በተዘፈነባት አገር ዉስጥ ከ30 ሚሊዮን በላይ ዜጎች (ከጠቅላላዉ ህዝብ 1/3ኛዉ) በቀን የተመድ የድህነት መመዘኛ ከሆነዉ ከ$1.25 በታች እያገኘ በድህነት የሚማቅቀዉ።ግሎባል ፖስት የተባለ የዜና ማዕከል በቅርቡ ኢትዮጵያ በ30 አመት ዉስጥ ታይቶ የማይታወቅ የረሃብ አደጋ ዉስጥ ወድቃለች ካለ በኋላ ለመሆኑ ይንንን አደጋ የኢትዮጵያ መንግስት መቋቋም ይችላል ወይ ሲል ጠይቋል። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግስት ቅድሚያ የሚሰጠዉ ለምንድነዉ የሚለዉን ጥያቄ መመለሱ የሚበቃ ይመስለኛል። የህወሃት አገዛዝ አይን ላወጣ ዘረፋና ለሜዲያ ፍጆታ በሚያመቹ ፕሮጅክቶች ላይ ካማተኮሩ በፊት ቅድሚያ የሚሰጠዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ክብር ለመጠበቅ፤ የኢትዮጵያን ህዘብ ልመና ይዞት ከሚመጣዉ ዉርደትና የሂሊና ዝቅጠት ለማዉጣትና ረሃብን ከአገራችን ምድር ለማጥፋት ቢሆን ኖሮ ረሃብ ከኢትዮጵያ የሚጠፋዉ ዛሬ ሳይሆን ህወሃት የኢትዮጵያን በትረ ስልጣን በተቆጣጠረባቸዉ በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ዉስጥ ይሆን ነበር።

The Famine Early Warning Systems Network (FEWS Net) የተባለ ድርጅት ኢትዮጵያ ዉስጥ የምግብ እህል ምርት ከሚጠበቀዉ በታች መሆኑን ወይም ይመረታል ተብሎ የሚጠበቀዉ ምርት አገሪቱ ከሚያስፈልጋት የምርት መጠን እጅግ በጣም ያነሰ መሆኑን በግዜ አስጠንቅቆ ነበር። ለመሆኑ ለዚህ ማስጠንቀቂያ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠዉ ምላሽ ምን ነበር? እርግጠኛ ነኝ FEWS Net ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአካባቢዉ ድርቅ ለሚያዘወትርባቸዉ አገሮች መንግስታትም የድርቅ አደጋን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ሌሎች መንግስታት ለዚህ ማስጠንቀቂያ የሰጡት ምላሽ ምን ይሆን? የኢትዮጵያ መንግስትስ በራሱም ቢሆን እንዲህ አይነቱን በዝናብ እጥረትና በአየር ሁኔታ መለዋወጥ የተነሳ ሊከሰት የሚችለዉን የምግብ እጥረት ከግምት ዉስጥ ያስገባ ጥናት በየአመቱ ማካሄድ አይገባዉም ነበር?

በ1977 ዓም በአገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ረሃብ ትግራይ፤ ወሎና ሰሜን ሸዋ ዉስጥ የሰዉን ልጅ እንደ ቅጠል ሲያረግፍ የዚህ ጸሁፍ ፀሀፊ የሰሜን ኢትዮጵያ ፕላን ቀጣና ጽ/ቤትን ወክሎ ትግራይ ዉስጥ ይሰራ ነበር። በወቅቱ የትግራይ ጎረቤት ክፍለሀገር በነበረችዉ ኤርትራ ዉስጥ ድርቅ ቢኖርም ረሃብ የሚባል ነገር አልነበረም። ዛሬ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለት የተለያዩ አገሮች ከሆኑ ሩብ ምዕተ አመት ሊሆን በወራት የሚቆጠር ግዜ ነዉ የሚቀረዉ። አንድ ነገር ግን ዛሬም አልተለወጠም። ኢትዮጵያና ኤርትራ ዉስጥ ዛሬም ድርቅ አለ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ድርቁ ዛሬም ወደ ረሃብ ተለዉጦ የሚሊዮኖችን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል። ኤርትራ ዉስጥ ግን ድርቅ ቢኖርም ድርቁ ወደ ረሃብ አልተለወጠም፤ ወይም የኤርትራ መንግስት እንደ ኢትዮጵያ መንግሰት ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ የምግብ ያለህ የሚል የልመና ጥሪ አላቀረበም። ለምን?

ኤርትራ የምዕራቡ አለም በተለይ የአሜሪካ መንግስት የማይገባ ማዕቀብ ጥሎባት ከዉጭ አገር ቤሳ ቤስቲን የማታገኝ አገር ናት። ኢትዮጳያ ግን በጥቁር አለም ዉስጥ ከፍተኛዉን የዉጭ ዕርዳታ የምታገኛ አገር ናት። የኤርትራ ኤኮኖሚ የራሱ በሆነ መንገድ እያደገ ቢሆንም በአሜሪካ የሚመራዉ የምዕራቡ አለም ይህንን ዕድገት መመስከር አይፈልግም። የኤርትራ መንግስትም ቢሆን እንደ ወያኔ በነጋ በጠባ አደግን እያለ ጥሩምባ አይነፋም። ኤርትራ አንድም አመቱን ሙሉ የሚፈስ ወንዝ የሌለባት አገር ናት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የወንዞች ማማ ተብላ የምትጠራ አገር ናት። ኤርትራ ዉስጥ አንድም ሐይቅ የለም፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን የሀይቁን ብዛት መቁጠር ያዳግታል። ኢትዮጵያ ያላት የእርሻ መሬት ስፋቱ ከጠቅላላዉ ኤርትራ የቆዳ ስፋት እጅግ በጣም ይበልጣል። የቀድሞዉ የወያኔዉ ጠ/ሚኒስቴር በቀን ሦስቴ እንበላለን ብሎ ትንቢት ነግሮን ነበር፤ ይህ ትንቢት ሳይፈጸም ነበር እሱን የተካዉ ሰዉ ከዛሬ ወዲህ በምግብ እህል እራሳችንን ችለናል ብሎ ለአለም ህዝብ ያወጀዉ። የኤርትራ መንግስት በእንደነዚህ አይነት ተራ የሜዲያ ፍጆታዎች ግዜዉን ሲያጠፋ አናይም። ለአገሩ ህዝብ የሚያስፈልገዉን የምግብ ፍጆታ አሟልቶ አገሩን ከረሃብ አደጋ ሲከላከል የምናየዉ ግን የኤርትራ መንግስት ነዉ። እነዚህን በሁለቱ አገሮች መካካል የሚታዩትን ልዩነቶች ያነበበ ሰዉ ሁሉ አንድ ሊገነዘበዉ የሚገባ ትልቅ ሀቅ አለ። እሱም ኢትዮጵያ ዉስጥ በመንግስት ብልሹ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ፖሊሲ የተነሳ ድርቁ ወደ ረሃብ ተለዉጦ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል። የኤርትራ መንግስት ግን የድርቁን መምጣት አስቀድሞ ስለተገነዘበ እርምጃ በመዉሰዱ ኤርትራ ዉስጥ የገባዉ ድርቅ ወደ ረሃብ አልተለወጠም። በመሆኑም ዛሬ ኤርትራ ዉስጥ ረሃብ የለም። ኤርትራ ዉስጥ ድርቁ ወደ ረሃብ አለመለወጡ የሚያሳየን ኤርትራዉያን ልዩ ፍጡሮቸ መሆናቸዉን ሳይሆን የሁለቱ አገር መንግስታት ቅድሚያ የሚሰጡት ለምን እንደሆነና በሁለቱ መንግስታት መካክል ያለዉን ከፍተኛ የፖሊሲ ልዩነት ነዉ። ወያኔ የሚያጮኸዉ የድርብ አኃዝ ዕድገትና የህዳሴ ጩኸት ከቅርብም ከሩቅም ይሰማል። በኤርትራና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል በምግብ ራስን መቻልን አስመልክቶ የሚታየዉ ከፍተኛ የፖሊሲ ልዩነት ግን በቀላሉ አይታይም። ኤርትራ ላይ የተጣለዉ ማዕቀብ እንዳይነሳ የሚፈልጉት አሜሪካኖችማ በተለይ እነ ሱዛን ራይስን የመሳሰሉ የአዕምሮ አይነስዉራን ይህንን ልዩነት ቢታይም ማየት አይፈልጉም።

ድርቅ ድንበር አይልም፤የፖለቲካ ስርዐት አይልም፤ ደሃና ሀብታም አይለይም- አገር ከአገር ህዝብ ከህዝብ አይለይም። ድርቅ በዬትም አገር ዉስጥ በማንኛዉም ግዜ ሊከሰት የሚችል የተፈጥሮ ክስተት ነዉ። የሰዉ ልጅ ድርቅ ይዟቸዉ ሊመጣ የሚችለዉን አደጋዎች ነዉ መቆጣጠር የሚችለዉ እንጂ ድርቅን እራሱን መቆጣጠር አይችልም። ዝናብ በተከታታይ ከጠፋ ድርቅ መምጣቱ አይቀሬ ነዉ። በ2007 ዓም ኢትዮጵያ ዉስጥ የገባዉ ድርቅ ኤርትራ ዉስጥም ገብቷል። ሁለቱ አገሮች የዝናቡ እጥረት ወደ ድርቅ ከመለወጡ በፊትና በኋላ የወሰዷቸዉ እርምጃዎች ግን የሰማይና የምድርን ያክል የተራራቁ ናቸዉ። እነዚህ ሁለቱ አገሮች የወሰዷቸዉ የተለያዩ እርምጃዎች ናቸዉ ዛሬ ኢትዮጵያን የምግብ ለማኝ ኤርትራን ደግሞ በራሷ የምትተማመን አገር ያደረገዉ።

የኢትዮጵያ መንግስት ድርቅ እየመጣብህ ነዉ ተብሎ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠዉ ትኩረት የሰጠዉ እየመጣ ላለዉ ረሃብ ሳይሆን ለ“እዩኝ እዩኝ” ፕሮጅክቶች ነዉ። ፕሮጀክቶች አያስፈልጉንም ማለቴ አይደለም። ያስፈልጉናል፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ በረሃብ እያለቀ ደርግ አዳራሽ ይሰራል ብሎ የወነጀለ አካል የሱም ትኩረት በመጀመሪያ የህዝብን የምግብ ፍላጎት መሟላት እንጂ ህዘብ በረሃብ እያለቀ ሌላ ሌላ ፕሮጀክት ላይ ማተኮር አልነበረበትም። የኤርትራ መንግስት የ2007 ዓም ዝናብ መጠን የእህል አምራች በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች አስተማማኝ አለመሆኑን ሲረዳ ገና ከጧቱ ነበር ከተለያዩ ምንጮች የምግብ እህል በግዢ በማሰባሰብ የአገሪቱን የምግብ ፍላጎት ማሟላት የጀመረዉ። ዛሬ የኤርትራ ህዝብ ስሙ በረሃብ የማይነሳዉ ኤርትራ ዉስጥ ድርቅ ስላልገባ አይደለም። የኤርትራ መሪዎች ድርቁ ወደ ረሃብ ከመለወጡ በፊት ቀድመዉ የወሰዱት እርምጃ አገራቸዉን ከረሃብ አደጋ ስላዳነዉ ነዉ። የኛ መንግስታት ግን ንጉሱም ሆኑ፤ ደርግ ወይም ወያኔ ድርቅ ወደ ረሃብ ተለዉጦ ህዝብን ሲጨርስ ምግብ መለመን ነዉ እንጂ ዛሬ ትንሿ አገር ኤርትራ እንዳደረገችዉ የድርቅን መምጣት አይተዉ ረሃብን ተከላክለዉ አያዉቁም። ለዚህ ነዉ መሰለኝ ኢትዮጵያ ዉስጥ በድርቅና በረሃብ መካከል ልዩነት ያለም አይመስልም።

እዉነትን ማሞጋገስና በዉሸት አለቆች ሰትደፈጠጥ ደጋግፎ ማቆም እስትንፋሴ እስካለች ድረስ በፍጹም የማልተወዉ ቋሚ ስራዬ ቢሆንም የዚህ ጽሁፍ አላማ ግን የኤርትራን መንግስት ማሞጋገስ አይደለም። እሱ የኤርትራዉያን ስራ ነዉ። የዚህ ጽሁፍ ብቸኛ አላማ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዛሬ የ20 ሚሊዮን ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ የጣለዉ ረሃብ መንስኤዉ የዝናብ እጥረት ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት ቅደም ተከተሎች ያላስተዋለ ብልሹ የመንግስት ፖሊሲ ዉጤት መሆኑን ለማሳየት ነዉ። ይህና ይህ ብቻ ነዉ የዚህ ጽሁፍ አላማ። ቸር ይግጠመን።

ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር ebini23@yahoo.com

No comments:

Post a Comment