Wednesday, September 25, 2013

የሙስሊሞች ጉዳይ መፍትሔ ይሻል!!!

በአብርሃ ደስታ

የናይሮቢው የዌስትጌት ሞል ጥቃት አሰቃቂ ነው። ግን ጥቃቱ ለኛ ኢትዮዽያውያን ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረ? “የተለያየ ስሜት” እንበለው ላለመሳሳት። በዚህ ጉዳይ ኬንያና ኢትዮዽያ ይመሳሰላሉ እንዴ?

በኬንያ ግለሰቦች ንፁሃን ሰለማዊ ዜጎችን በገበያ ማእከል ያግዳሉ፣ ያሰቃያሉ፣ ይገድላሉ። በኢትዮዽያ ደግሞ የገዢው ፓርቲ ፖሊሶች ንፁሃን ሰለማዊ ዜጎችን በመስጂዶች ያግዳሉ፣ ያሰቃያሉ፣ ይገድላሉ። ስለዚህ በኬንያና በኢትዮዽያ ዉስጥ የሚፈፀሙ ድርጊቶች የሚመሳሰሉበት ነጥብ በሁለቱም ተጠቂዎቹ ሰለማዊና ንፁሃን ዜጎች መሆናቸው ነው። የሚለያዩበት ደግሞ በኬንያ ጥቃት የሚፈፅሙ ግለሰቦች ሲሆኑ በኢትዮዽያ ግን የመንግስት ሃይሎች ናቸው።

ይቅርታ!

በሁለቱም ሀገሮች የሚፈፀሙ ጥቃቶች ይመሳሰላሉ። በኬንያ ለተፈፀመ ድርጊት ሓላፊነት የወሰደ አልሸባብ አይደለምን? ስለዚህ በናይሮቢ የሽብር ተግባር የፈፀሙ ሃይሎች ግለሰቦች ሳይሆኑ ድርጅት ነው። ምክንያቱም ጥቃቱ የፈፀመው አልሸባብ ነው። አልሸባብ ደግሞ ድርጅት ነው። በኢትዮዽያ የሚፈፀመውም በገዢው ፓርቲ ነው። ገዢው ፓርቲ ድርጅት ነው። ስለዚህ በሁለቱም ሀገሮች የሚፈፀሙ ጥቃቶች በድርጅቶች የትፈፀሙ ናቸው። ስለዚህ ይመሳሰላሉ።

እንደገና ይቅርታ!

በሌላ ነጥብ ደግሞ ይለያያሉ። አልሸባብ ስልጣን ያልያዘ፣ የህዝብ ሓላፊነት ያልተሸከመ፣ በግልፅ የተወገዘ ቡድን ነው። የኢህአዴግ መንግስት ግን ስልጣንና የህዝብ ሓላፊነት አለበት። ሌላ ደግሞ አልሸባብ ጥቃቱ የፈፀመው በሌላ ሀገር ህዝቦች ነው (ለመበቀል)። ኢህአዴግ ግን በራሱ ህዝብ ላይ ነው የሚፈፅመው (በስልጣን ለመቆየት)።

ጥቃት ይፈፀማል፤ የሚፈፀመው ግን ተስፋ በቆረጡ ሃይሎች ነው። የግል (ወይ የድርጅት) ዓላማቸው ለማሳካት በሰለማዊ ህዝብ ላይ የሽብር ጥቃት የሚሰነዝሩ አሉ። እነ አልሸባብና ቦኮ ሃራም የሚጠቀሱ ናቸው። ግን የአልሸባቦችና የቦኮ ሃራሞች ተግባር በማጣቀስ የኢትዮዽያውያን ሙስሊሞች ጥያቄ ለማድበስበስ መሞከር ተገቢ አይደለም። የኢትዮዽያ ሙስሊሞች ሕጋዊ ጥያቄና ሰለማዊ ተቃውሞ ከነ አልሸባብ የሽብር ተግባር ጋር ምን አገናኘው?

ጥያቄያቸው በሰላማዊ መንገድ የሚገልፁና በህዝቦች ላይ ጥቃት የሚፈፅሙ እንዴት ይገናኛሉ? ስለዚህ የኢትዮዽያ ሙስሊሞች ጥያቄ ላለመመለስ ጉዳያቸው ከቦኮ ሃራሞች ተግባር ማመሳሰል ተገቢ አይደለም። 

የኢትዮዽያ ሙስሊሞች ጥያቄ አላቸው። ጥያቄያቸውም በሰለማዊ መንገድ እያሰሙ ነው። ጥያቄያቸው ምን ይሁን ምን መልስ ያስፈልገዋል። የዜጎችን ጥያቄ መመለስና በግዛቲቱ ለሚነሱ ማናቸውም ችግሮች መፍትሔ ማፈላለግ የመንግስት ግዴታ ነው። መንግስት ለችግሩ መንፍትሔ ካላመጣ ግዴታው በአግባቡ እየተወጣ አይደለም ማለት ነው። ግዴታው መወጣት ካልቻለ ስልጣኑ (የህዝብ ሓላፊነቱ) ለህዝብ መልሶ ማስረከብ አለበት፤ ምክንያቱም ሊሰራበት አልቻለማ።

የአብዛኞቹ ሙስሊሞች ጥያቄ ሃይማኖታዊ ነው ብዬ አስባለሁ። ግን የተወሰኑ ግለሰቦች የራሳቸው ሌላ ዓላማ ሊኖራቸው (ወይ ላይኖራቸው) ይችላል። ሁሉም ሙስሊሞች የተለያዩ ሰዎች እስከሆኑ ድረስ ተመሳሳይ ሃይማኖት ስላላቸው ብቻ ተመሳሳይ ሓሳብና ፍላጎት ይኖራቸዋል ማለት አይቻልም። ግን አንድ ግልፅና ለሁሉም ሙስሊሞች የጋራ ነጥብ የሆነ ጥያቄ አላቸው፤ “መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ አይግባብን” የሚል። ሌላ ተጨማሪ ጥያቄም ቢኖር መብታቸው ነው። የመንግስት ግዴታ ጥያቄያቸው ማፈንና ማጥላላት ሳይሆን የመፍትሔ መልስ መስጠት ብቻ ነው።

የኢትዮዽያ መንግስት ግን ለሙስሊሞቹ ጉዳይ መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ ጥያቄያቸውን ማጥላላት ይዟል። ጥያቄያቸው በሰለማዊ ሰልፍ ለሚገልፁ የኢትዮዽያ ሙስሊሞች ዓላማቸው በሃይል ማስፈፀም ከሚፈልጉ አልሸባቦችና ቦኮሃራሞች ጋር ማመሳሰል?

የኢትዮዽያ መንግስት እየተከተለው ያለው ስትራተጂ አደገኛ ነው። ዜጎች ሰለማዊ ሰልፍ ሲወጡ በፖሊስ ከተደበደቡ አማራጫቸው ምን ሊሆን ነው? መንግስት ምን ዓይነት መልእክት እያደረሳቸው ነው? “በሰለማዊ መንገድ ስለማይሳካ ሌላ የዓመፅ መንገድ ብትሞክሩ ይሻላችሃል” እያላቸው ነው? ወይስ ምንድነው? ሙስሊሞቹ ከአንድ ዓመት በላይ ጥያቄያቸው በሰለማዊ መንገድ ሲገልፁ ቆይተዋል። እስካሁን ተስፋ አልቆረጡም (ተስፋ ባለመቁረጣቸው አደንቃቸዋለሁ)።


በመንግስት ተስፋ ቢቆርጡስ? ጥሩ አይደለም። ሳይፈልጉት (ተስፋ ከቆረጡ) ወደ ሃይል እርምጃ ሊገቡ ይችላሉ። የኢህአዴግ መንግስት ግን የኢትዮዽያ ሙስሊሞች ዓመፅ ቢጀምሩ የሚደሰት ይመስለኛል። የሙስሊሞች ዓመፅ ከተጀመረ ኢህአዴግ “አላልኩም ወይ !? ዓላማቸው ዓመፅ መቀስቀስ ነው!” ሳይለን አይቀርም። ግን ሙስሊሞቹ ለጥያቄያቸው መልስ የሚሰጣቸው አካል (መንግስት) ካጡ ሌላ ጥያቄያቸው ሊመልስላቸው የሚችል ስርዓት ለመመስረት ቢታገሉ አግባብነት የለውም ማለት አንችልም።

ኢህአዴግ የሙስሊሞች ሰለማዊ ተቃውሞ ስላስጨነቀው ዓመፅ ቢያነሱለትና የሃይል እርምጃ ቢወስድባቸው የሚመርጥ ይመስለኛል (ሙስሊሞቹ ግን አያደርጉትም ብዬ ተስፋ ላድርግ)። ስለ ኢህአዴግ ስትራተጂ አንድ ምሳሌ ልስጥ። 

ሁለት ልጆች ያሏት እናት ነበረች። የመጀምርያው ልጅ ዓመፀኛ ነው። ለታናሽ ወንድሙ ዘወትር ይደበድበዋል። 
ታናሹ እየጮኸ (እያለቀሰ) ወደ እናቱ ይሄዳል።
እናት ደግሞ ለልጇ “አትደብድበው” ብላ ትቆጣለች። 
ታላቁ ለናቱ እንዲህ ይላታል፣ “እኔ’ኮ የምደበድበው እየጮኸ ስለሚረብሸኝ ነው። ባይጮኽ ኑሮ አልደበድበውም ነበር።” 
እናት ለታናሹ “በል አትጩኽ፣ ወንድምህን አትረብሸው” ትለዋለች። 
ታናሹም “እኔ’ኮ አልጨኽኩም፣ እመኚኝ እማዬ” ይላታል። 
እናትም ለታላቁ “ለምን ታድያ ሳይጮኽ ትደበድበዋለህ?” አለች። 

ታላቁም ታናሹ እንደሚጮህ ለናቱ ለማሰማት መልሶ ይደበድበው ያዘ። ታናሹም ስለተደበደበ አለቀሰ (ጮኸ)። በመጨረሻም “ልጁ የተደበደበው ስለጮኸ ነው” ተባለ። (ያስጮኸው ግን ዱላ ነበር። በፍትሕ እጦት ምክንያት ደግሞ ዉጤቱም ዱላ ሆነ)። ግን ልጁ የጮኸው ስለተደበደበ ነበር። ድብደባ ከዛ ጩኾት። ዓመፀኛው ልጅ ግን ሂደቱ … ጩኾት ከዛ ድብደባ እንደሆነ ለናቱ ለማሳመን መኮረ ልክ እንደ ኢህአዴግ። የኢህ አዴግ ስትራተጂም ይሄ ነው። ራሱ በፈጠረው ችግር ሌሎችን ይከሳል።

መንግስት ማንኛውም ጥያቄ የመመለስ ግዴታ አለበት። ካልሆነ ግን ለጥያቄ ተገቢ መልስ መስጠት ለሚችል የፖለቲካ ድርጅት ስልጣኑን ማስረከብ ይኖርበታል። መንግስት የዜጎች ጉዳይ ከመፍታት ይልቅ ራሱ በጉዳዩ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን ችግሩ የማባባስ መብት የለውም።

ፈጣሪ ኢትዮዽያን ይባርክ።

No comments:

Post a Comment