Monday, July 1, 2013

የአሜሪካ አዲስ ፖሊሲ በአፍሪካ ላይ …

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በነደፉት የአሜሪካና የአፍሪካ ግንኙነቶች የሚመሠረቱበት አዲስ አቅጣጫና አካሄድ ከፍ ያሉ የምጣኔ ኃብት ዕድሎችን፣ ዴሞክራሲንና አፍሪካ መር የሆኑ የፀጥታ መፍትሔዎችን መደገፍና ማበረታታት እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡

በሦስት የአፍሪካ ሃገሮች ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኬፕ ታውን ላይ ትናንት ንግግር አድርገዋል፡፡

የሚስተር ኦባማ የኬፕ ታውን ንግግር የአሜሪካና የአፍሪካ መጭ ግንኙነቶች መሠረቶች ናቸው የተባሉ ግቦችን ያሣየ ስፋት ያለው ሥዕል ነው ተብሏል፡፡

ይህ የዩኤስ-አፍሪካ ፖሊሲ ድጋፍን ወይም እርዳታን፣ ንግድና መዋዕለ-ነዋይን፣ ጤናና የፀጥታ ትብብር አካባቢዎችን የሚሸፍን እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

በፕሬዚዳንቱ አባባል የንግግራቸው ማዕቀፍ የተዋቀረው የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ለአህጉሪቱ ትሩፋት እንዲሆን ባኖሯቸው እሴቶች ላይ ነው፡፡

ከመሬት ለመነሣት እየተንደረደረ ባሉት አህጉር ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ ከአዲስ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አማራጮች ጋር በመንቀሣቀስ የንግድ እገዳዎችና መሠናክሎችን በማስወገድ ተሣትፎዋን እንደምታሣድግ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ ከድኅነት መካከለኛ ገቢ ወዳለው ሕዝብነት እየተሸጋገረች ብትሆንም፣ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ምክንያት እየሞተ ያለው ሰው ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም “የሙስና ብስባሽ እና ግጭቶች” ሥጋቶችን እንዳጠሉባት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

“ዩናይትድ ስቴትስ ኢንቨስት ማድረግ የምትፈልገው ጠንካራ በሚባሉ ሰዎች ወይም መሪዎች ላይ አይደለም፤ በጠንካራ ተቋማት ላይ እንጂ” ብለዋል ሚስተር ኦባማ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ቀጥለውም “ግልፅና ተጠያቂ መንግሥታትን፣ ነፃ የፍትሕና የፍርድ አካላትን፣ የሴቶችን የወሣኝነት አቅም የሚያበለፅጉና ውሣኔ ሰጭነትን የሚያጎናፅፉ ተቋማትን ትደግፋለች” ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ ንግግራቸው በፊት ኔልሰን ማንዴላ ከሃያ ሰበት ዓመቱ የአፓርታይድ አገዛዝ ዘመን የወኅኒ ሕይወታቸው ሁለት አሠርት የሚሆኑትን ያሣለፉበትን አሥር ቤትና ክፍል ሮቢን ደሴት ላይ ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ፕሬዚዳንት ኦባማ ከትናንት በስተያ - ቅዳሜ ንግግር ባደረጉበት የሶዌቶ አዳራሽ ውጭ ተገኝተው የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብር የአሜሪካ መንግሥት ጫና እንዲያሣድር ጠይቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዚዳንት በአሁኑ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ የሚያደርጋቸው ምክንያት እንደሌለ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምሕር ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ የአፍሪካ ጉዟቸው የመጨረሻ ክፍል ለሆነው ጉብኝት ዛሬ - ሰኞ፣ ሰኔ 24/2013 ዓ.ም ታንዛኒያ ገብተዋል፡፡

ምንጭ፡ VOA 

No comments:

Post a Comment