v መድረክን ወደ ጥምረት /ቅንጅት ማውረድ አይጠቅምም
v መድረክን ወደ ውህድ ፓርቲ መግፋቱ ጠቀሜታው አልታየኝም
በዘሪሁን ሙሉጌታ
የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በመድረክና አንድነት መካከል ስላለው ግንኙነት ለመጀመሪያ ጊዜ የግል አቋማቸውን ይፋ አደረጉ። ዶ/ር ነጋሶ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ በላኩት ፅሁፍ መድረክን በተመለከተ የተለየ አቋም መያዛቸውን አረጋግጠዋል።
ዶ/ር ነጋሶ “የግንባርነት መስፈርትና መድረክ” በሚል ርዕስ ለሰንደቅ በላኩት ፅሑፍ መድረክን ወደ ጥምረት/ ቅንጅት ማውረድ እንደማይጠቅም እንዲሁም መድረክን ወደ ውህድ ፓርቲ መግፋቱ ጠቀሜታው አልታየኝም ሲሉ የግል አስተያየታቸውን ገልጸዋል።
የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት በቅርቡ “የአንድነት /መድረክ የፖለቲካ ግንኙነት እና የጋራ እንቅስቃሴ ከመቀናጀት እስከ ግንባር ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ግምገማ” በሚል ባቀረበው የግምገማ ሰነድ ላይ መድረክ “ግንባር” የሆነበት አካሄድና ውሳኔ በአግባቡ ያልተመከረበት መሆኑን በመጥቀስ እንደገና ውይይት እንዲደረግ ከጠየቀባቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
በግምገማ ሰነዱ ላይ መድረክ የአባል ፓርቲዎችን ፕሮግራም በማቀራረብ አንድ ወጥ የሆኑ ፓርቲ ሆነው የሚወጡበትን ዕድል መፍጠር ካልቻለ ትርጉም ያለው ስብስብ ይሆናል ተብሎ እንደማይጠበቅ መግለፁ አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ ዶ/ር ነጋሶ መድረክ ሰፊ (Broad) ግንባር መሆኑን፣ በምርጫ ኢህአዴግ ቢሸነፍ እንኳ ኢህአዴግን ጨምሮ ከሌሎች ፓርላሜንታዊ ፓርቲዎች ጋር ብሔራዊ አንድነት መንግስት ለማቋቋም መወሰኑን ጠቅሰዋል።
በተያያዘ የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት ቀደም ሲል በቀረበው ሰነድ ላይ የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ከሶስት ወር በኋላ የደረሰበትን ሁኔታ እንዲያሳውቅ ባዘዘው መሠረት በቀጣይ ቀናት በጉዳዩ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልፀዋል።
የአንድነት/መድረክ ግንኙነት በመስከረም ወር በሚካሄደው የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በስፋት ከሚነሱ አጀንዳዎች ግንባር ቀደም ሊሆን እንደሚችልም ይጠበቃል።(ከዶ/ር ነጋሶ ጋር የተደረገው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል)
የግንባርነት መስፈርትና መድረክ
በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
የግል አስተያየት
በግንቦት ወር በአንድነትና በመድረክ መካከል ይፋዊ ውይይት ተከፍቷል፤ ቀጥለውበታልም። በዚህ ውይይት ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ አስተያየት አልሰጠሁም። በአንድነት ውስጥ ግን በግሌ ያለኝን አቋም፣ አመለካከትና አስተያየቶችን ማንፀባረቄ አልቀረም። በግሌ ሳንፀባርቃቸው የነበርኳቸውን አቋሞች፣ አመለካከቶችና አስተያየቶችን በጽሑፍም ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።
አንድ በሰኔ ወር ያጠናቀቅሁት ጽሑፍ “በመድረክ ዙሪያ የተጀመረው ውይይት መድረክን ህዝባዊ ድርጅት ያደርገዋል ወይስ ይጎዳዋል? ዝምታዬ ስምምነት እንዳይመስልብኝ” የሚል ርዕስ አለው። ይህ ጽሑፍ ዛሬ በሙሉ ይፋ ማድረግ አልፈለግሁም። ይልቁንም ከጽሑፉ አንዲት ክፍል ብቻ ቀንጭቤ አቅርቤአለሁ። ይህችም ያቀረብኳት አጭር ጽሑፍ ስለ መድረክ ግንባርነት ነው። የቀሩትን ክፍሎች እንዳስፈላጊነቱ እያየሁ ለአንባቢያን አቀርባለሁ።
መጀመሪያ ግን ለመሆኑ “ግንባር” ምንድው? የሚለውን ጥያቄ ባለኝ ትንሽ ዕውቀትና ተሞክሮ ላይ በመመርኮዝ ኀሳቤን ለማቅረብ እሞክራለሁ፤
የግንባር ቃለ አመጣጥ ከሰውነታችን ክፍሎች ከፊታችን ወጣ ብሎ የሚታየው የአካል ክፍል ነው፤ የፊት ለፊት ዘርፍ ነው ማለት ነው። በውጊያ ጊዜ ኃይል የሚከማችበት የሠራዊት የፊት መስመር ነው። ለምሳሌ የቡሬ ግንባር፣ የባድመ ግንባር፣ የዛላንበሳ ግንባር፣ የከረን ግንባር ሲባል እንደነበረው።
ከታሪክ አንፃር ስናየው በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የፖለቲካ ግንባሮች እንደተፈጠሩ እናስታውሳለን። ለምሳሌ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የኮሙኒስቶችና የፀረ-ኮሚኒስቶች ግንባሮች ተፈጥረው ነበር። የሠራተኛ ማኅበራት፣ የሶሻሊስት ፓርቲዎች፣ የነሱም ሕዝባዊ አደረጃጀቶች በርዕዮተ ዓለም መቀራረብ ላይ የተመሠረተ የአንድነት ግንባሮች ሲመሠረቱ ነበር። በአሜሪካና በአውሮፓ ለእስራኤል ድጋፍ ሰብሳቢ ግንባሮች ተመስርተው እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል።
የግንባር መሠረተ ሃሳብ የጋራ አጀንዳ ያላቸው፣ ግን የተለያዩ ፍላጎት ሊኖራቸው የሚችሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ቡድኖች (የግራ ዘመም፣ የመሀልና የሊብራል ቡድኖች ሊሆኑ ይችላሉ) የጋራን አጀንዳ ለማራመድና ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ያላቸው ድርጅቶች፣ ወይም የተለያዩ ርዕዮተ ዓለም ያላቸው ድርጅቶች ሰፋ ያለ (Broad) አንድነት የሚፈጥሩበት አደረጃጀት ነው።
የግንባር ዓላማና መርህ ሲፈተሽ የሚከተሉት ባህሪያት አላቸው። የጋራ ጠላትን በጋራ ለመዋጋት፣ የጋራ ተቃዋሚን በጋራ ለመከላከል፣ የጋራ ተፃራሪን በጋራ ለመጋፈጥና የጋራ ዓላማን በጋራ ለማራመድ የሚፈጠር የአንድነት አደረጃጀት ነው። የግንባር አባል ድርጅቶች ኃይል ለመፍጠርና ውጤታማ ለመሆን “አንድነት ኃይል ነው” የሚለውን መርህ ይከተላሉ። አንድ ፓርቲ ብቻውን መንግሥት መያዝ አይችልም፣ ትክክልም አይደለም ይላሉ። አንድ ፓርቲ ብቻውን መንግሥትን አጠቃልሎ መያዙ ጥሩ አይደለም የሚል እምነት በመያዛቸው በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ አቅጣጫን ይከተላሉ።
ግንባርና ጥምረቶች (ቅንጅቶች) ይለያያሉ። ጥምረት /ቅንጅት ለተወሰነ ዓላማ ብቻና ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል የአንድነት አደረጃጀት ነው። የጥምረት /ቅንጅት ዓላማ በምርጫ ገዢውን ፓርቲ ለማሸነፍና ለአንድነት የምርጫ ዘመን የጋራ መንግሥት (coalition government) ለማቋቋም የሚመሠረት ጊዜያዊ አንድነት ነው።
ግንባር ግን የረጅም ጊዜ ዓላማ ያለው ስትራቴጂአዊ አንድነት ነው። በረጅም ጊዜ ወይም በዘላቂ ስትራቴጂካዊ እቅድ ውስጥ ወደ ዓላማውና ወደ ግቡ የሚያደርሱ በየደረጃው የሚፈፀሙ የአጭር ጊዜ ስትራቴጂዎች አሉ።
በግንባር አንድነት አደረጃጀት ውስጥ የሚታቀፉ ድርጅቶች አንድ ወይም የተለያየ ርዕዮተ ዓለም ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፡- እንደ ኢህአዴግ በቋንቋና በአካባቢ ላይ የተመሠረቱ ፓርቲዎች ቢኖሩበትም ድርጅቶቹ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ አብዮታዊ ዴሞክራት አባሎች የተሰበሰቡበት ድርጅት ነው። የዚህ ዓይነት በአንድ ወጥ ርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረቱ የላብ አደሩና የኮሙኒስት ሶሻሊስት አደረጃጀቶች በዓለም ላይ ሲፈጠሩ አዲስ አይደለም። በርዕዮተ ዓለም ባይስማሙም የጋራ አጀንዳ ያላቸው፣ የጋራ ጠላት፣ ተቃዋሚ ወይም ተፃራሪ አቋም ያላቸው ኃይሎች በፈቃደኝነት ተስማምተው ገብተው አንድ የጋራ ፕሮግራም ነድፈው ለረጅም ጊዜ አብሮ ለመስራት የሚቋቋሙ የግንባር አደረጃጀቶችም ሊፈጠሩ ችለዋል። ይችላሉም ከዚህ አኳያና የአገሪቱ ሕግ በደነገገው መሠረት መድረክ ግንባር ሆኖ ተመዝግቧል።
የመድረክ ግንባርነት ባህሪይን ስንመለከት ግንባርነቱ የተመሠረተው በሰፊ (Broad) አንድነት ላይ ነው እንጂ በርዕዮተ ዓለም አንድነት ላይ የተመሠረተ አይደለም። ከመድረክ ሰነዶች እንደሚታየው በምርጫ ጊዜ በአንድ የምርጫ ምልክትና በአንድ ማኒፌስቶ በመወዳደርና በፕሮግራሙ የተቀመጠን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዓላማዎችን መድረክ በምርጫ ካሸነፈ በሚቋቀመው መንግሥት በኩል በዚያ የምርጫ ዘመን ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ቢያልምም የረጅም ጊዜ ወይም ስትራቴጂአዊ ዓላማውና ግቡ፡-
1. የኢትዮጵያ ህዝብ በዘላቂነት የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ለማድረግ፣
2. ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ፍትህ የሰፈነበትና የበለፀገች አገር ለመገንባት፣
3. ከተጨባጭ የኢትዮጵያ ሁኔታ በመነሳት በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያን መገንባት፣
4. የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚል ነው።
የግንባሩ አባል ድርጅቶች ይህን የረጅም ጊዜ (ስትራቴጂያዊ) ዓላማና ግብ በመያዝ በጋራ ተግባራዊ ለማድረግም በልዩ ሁኔታ ተስማምተዋል። እነዚህም ስምምነቶች እንደሚከተሉት ናቸው።
1. የኢትዮጵያ አንድነት፣ ነፃነትና ሉዓላዊነትን ለማስከበር ለማስጠበቅ በጋራ መስራት፣
2. ኢፍትሓዊና አድሎአዊ አሠራሮች የተወገዱባት ኢትዮጵያን መገንባት፣
3. በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲጠናከር በጽናት መቆም፣
4. የግለሰቦች፣ የብሔር ብሔረሰቦች፣ ህዝቦችና የቡድን መብቶች እኩል እንዲከበሩ ሳይታክቱ አብሮ መሥራት፣
5. ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ የሰፈነባት የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት የሚሉ ናቸው።
መድረክ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚከተለው የትግል ስልት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡-
1. ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ለማክበርና ለማስከበር ይሰራል፣ የአገሪቱን ሕጎች ያከብራል፤
2. በሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮች በቀጣይነት ውይይት እንዲካሄድ ይሰራል፣ ሕገ-መንግሥቱ በሕገ-መንግሥታዊ መንገድ፣ በሕዝበ ውሳኔ ጭምር፣ የሚሻሻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ይታገላል፤
3. በሰላማዊ ትግል ያምናል፣ ሠላማዊ ትግል ለማጠናከር ሳይታክት ይሰራል፣
4. ምርጫ ሠላማዊ፣ ነፃና ፍትሓዊ እንዲሆን የፖለቲካ ምህዳሩ ለሁሉም እኩል የተመቻቸ እንዲሆን እንደሚታገል ገልጿል።
በእነዚህ የመድረክ ግንባርነት ባህሪይና የትግል ስልት አንፃር ሲታይ መድረክ ወይ የመድረክ አባል ድርጅቶች በርዕዮተ ዓለም አንድነት ላይ የተመሠረተ ውህድ ፓርቲ መሆን አለበት፣ ያለበለዚያ በቅንጅትነት (ጥምረትነት) ደረጃ መንቀሳቀስ አለበት የሚሉ ሰዎች ምክንያታቸውን የበለጠ ቢያብራሩ አስተማሪነቱ የሚናቅ አይደለም። በእኔ ትንሽ ዕውቀትና የዕድሜ ተሞክሮ የሚነግረኝ ግን መድረክ የግንባርነት መስፈርት ማሟላቱ የሚያጠራጥር አይደለም። ሆኖም ግን ከግንባር ደረጃ ሲታይ መድረክ የሰፊ ግንባር (Broad Front) መስፈርትን እንጂ የጠበበ (Narrow or Limited Front) ግንባር ደረጃ ላይ የደረሰ ነው ለማለት አያስደፍርም።
ይህን ለመረዳት እንዲረዳን የፀረ-ደርግ ትግል ጊዜ አንድ ክስተትን ማስታወሱ ጥሩ ነው። ልክ እንደዛሬው የኢህአዴግ ተቃዋሚ የሆኑ ብዙ ፓርቲዎች እንዳሉ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜም ኢህአዴግንና ኦነግን ጨምሮ ብዙ ፀረ-ደርግ የፖለቲካ ድርጅቶች ነበሩ። በዚያን ጊዜም የጋራ ጠላትን ለማስወገድ ቀላል ይሆን ዘንድ የተቃዋሚ ድርጅቶች መሰባሰብ አስፈላጊ ነበር። በመሆኑም፣ ለምሳሌ ሕወሓት ከኦነግ ጋር ግንባር ለመፍጠር ብዙ ጥረት ሲያደርግ ነበር። ሆኖም ግን ሕወሓት የነበረው አቋም ከኦነግ አቋም የተለየ ነበር። ሕወሓት ፍላጐቱ ደርግ ከተወገደ በኋላ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነበር። ማኅበረ-ኢኮኖሚና የፖለቲካ ፍላጐቱ ደግሞ የሶሻሊስት ኢትዮጵያ ግንባታ ሁኔታን ማመቻቸት ነበር። ለዚህም እንዲረዳው አብዮታዊ ዴሞክራሲን ማስፈን ይፈልግ ነበር። ከውጭ ግንኙነት አንፃር ያኔ የነበረውን ሶቪየት ኅብረትን እንደ ሶሻል ኢምፔሪያሊስት ያይ ነበር። የምኒልክን እንቅስቃሴ ደግሞ እንደፊውዳል ተስፋፊነት ይመለከት ነበር።
በአንፃሩ ግን፣ ኦነግ የሚኒልክን እንቅስቃሴ እንደ ቅኝ ግዛት መስፋፋት ያይ ስለነበር የፀረ-ኮሎኒያሊዝም ትግል በማካሄድ ነፃ የኦሮሚያን ሪፐብሊክ ለመመስረት ይታገል ነበር። ከማኅበረ-ኢኮኖሚ-ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አንፃር ደግሞ የማኦን አዲሱ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ይከተል ነበር። ሶቪየት ኅብረትን ግን እንደ ኢምፔሪያሊስት ኃይል አይወስደውም ነበር።
ግንባር የመፍጠር አስፈላጊነት ላይ ሁለቱም ያምኑ ነበር። ችግሩ ግን የነበረው ምን ዓይነት ግንባር እንፍጠር በሚለው ላይ ነበር። ከዚህም የተነሳ ህወሓት ሁለት አማራጮችን አቀረበ። አንደኛው አማራጭ፣ ኦነግ አቋሙን ቀይሮ የሕወሓትን አቋም በመከተል ሁለቱ “ዴሞክራሲያዊ ግንባር” መፍጠር የሚል ነበር። ይህ የጠበበ (Narrow or Limited) ግንባር የምንለው ዓይነት ነው። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ደርግን ለመጣል ያለመ አንድነትን መፍጠር ነው። ይህ ሰፊ ግንባር (Broad Front) የምንለው ነው።
የዚህ ግንባር ዓላማ ደርግን መጣልና ከዚያ በኋላ በሚፈጠረው የኃይል ሚዛን ጉልበተኛ የሆነው ቡድን ሌላውን አስወግዶ የቆመለትን ዓላማ ተግባራዊ ማድረግ ነበር። ኦነግ የመጀመሪያውን አማራጭ አልፈለገም። በ1983 በነበረው የኃይል ሚዛን ኦነግ በጉልበት ተመጣጣኝ ስላልነበረ ደርግ ከወደቀ በኋላ ሕወሓት ያጠፋኛል ብሎ ስለፈራ ሁለተኛውም ዓይነት ግንባር ውስጥ ለመግባት አልፈለገም። በመሆኑም የተፈጠረው ሁኔታ ከብዙ ውስብስብ ሁኔታዎችና ችግሮች ጋር የታጨቀ ሰፊ ትብብር ነበር። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነበር የሽግግር መንግሥት የተመሠረተው።
ወደ አሁኑ ሁኔታ ስንመለስ መድረክ ሰፊ (Broad) ግንባር ነው። ሆኖም ግን በምርጫ ኢህአዴግ ከተሸነፈ በኋላ ኢህአዴግን ጨምሮ (ኢህአዴግ በፓርላማ ወንበር ካገኘ) ከሌሎች የፓርላሜንታዊ ፓርቲዎች ጋር የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለማቋቋም ይፈልጋል። በዚያን ወቅት ሆነ ከዚያም በኋላ አንድነትዋ፣ ነፃነትዋና ሉዓላዊነትዋ የተጠበቀች፣ ሁሉም የግለሰቦችና የቡድኖች መብቶች እኩል የተከበሩባት፣ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ይታገላል ብሎ የመድረክ ግንባር ቃል ገብቷል። ስለሆነም የመድረክ ግንባርነት፣ ከርዕዮተ ዓለም አንድነት በመለስ ከኢህአዴግ ሰፊ ግንባርነት (Broad Front) ከፍ ያለ ነው። ስለሆነም መድረክ በዚያው ደረጃ ቢቆይ ይሻላል እንጂ ወደ ጥምረት /ቅንጅት ደረጃ እንዲወርድ መፈለጉም ሆነ ወደ ውህድ ፓርቲ መግፋት መፈለጉ በአሁኑ ወቅት ጠቀሜታው አልታየኝም። ያም ሆነ ይህ ዋናው ቁም ነገር ለአንድ ዓይነት ዓላማ በጋራ መስራት ጠቃሚ የመሆኑ ጉዳይ ነው።
ይህ በግንባር ዙሪያ የሚካሄደውን ውይይት ለከፈተው አንድነት ፓርቲ፣ ለመድረክ፣ ለ33 ፓርቲዎች ስብስብና ለሌሎችም በአገር ቤት በውጭ ላሉ ተናጠልና ስብስብ ፓርቲዎች በኀሳቡ (Concept) ላይ ግልጽነት እንዲኖረን ከሚረዳን በላይ ለምናደርገው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ድክመትና ጥንካሬ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ስለሚችል ውይይቱ ይቀጥል። በሌላ በኩል ግን ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ተረስተው በዚህ ርዕስ ላይ ተጠምደን ጊዜ ማባከኑ ትክክል እንዳልሆነ ኀሳቤን እየሰጠሁ፣ የምናደርገው ውይይት ግን ገንቢ እንጂ አፍራሽ እንዳይሆን አደራ እላለሁ።
(ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 411 ሀምሌ 17/2005)
No comments:
Post a Comment