Thursday, July 18, 2013

አክራሪነት በኢትዮጵያ – ጥያቄዎች ለሃጂ ናጂብ

ከማከብራቸው የዲሞክራሲ አክቲቪስት መካከል አንዱ የሆኑት፣ አቶ ተድላ አስፋዉ፣ አቶ ጃዋር መሃመድ ለተናገራቸው አንዳንድ አባባሎች የሰጡትን ምላሽ አነበብኩ። አቶ ጃዋር የተወለደው በአርሲና በሃረርጌ ድንበር አካባቢ ነዉ። በዚያ አካባቢ ነዉ አርባ ጉጉ (ምእራብ አርሲ) እና በደኖ (ምስራቅ ሃረርጌ) የሚገኙት። ወያኔ/ኢሕአዴግና ኦነግ ስልጣን በጨበጡ ጊዜ፣ በአርባ ጉጉና በደኖ የተፈጸሙትን ሁላችንም የምናወቀዉ ነዉ። አካባቢዉን ከክርስቲያኖችና ከ«አማራዎች» ለማጽዳት ፣ ብዙዎች በቤታቸው ተቆልፎባቸው ተቃጥለዋል። ብዙዎች፣ ነፍሰ ጡር እህቶቻችን ሳይቀሩ፣ ጥልቅ በሆነ ጉድጓድ ዉስጥ፣ አይኖችቸው በጨርቅ ታስረዉ፣ በሕይወት ተወርውረዋል። አርባ ጉጉን ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ፣ በደኖን ደግሞ ኦነግ ነበር የሚያስተዳድሩት። በዚያን ወቅት ከፍተኛ ፀረ-አማራና ፀረ-ክርስቲያን የጥላቻ ዘመቻ ይደረግ ነበር። ብዙ ያልተማረው ሕዝብ፣ ተማሪዎች፣ ልጆች ፣ የዚህ ጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ሰላባዎች እንዲሆኑ፣ ይህን አይነት የጥላቻና የአክራሪነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ተደርጓል።

አቶ ጃዋር መሃመድ የዚህ ዉጤት ናቸው። አሁን የሚያንጸባርቁት፣ ያኔ በልጅነታቸው ከኦሕዴድና ኦነግ አክራሪዎች የተማሩት ነዉ። ይህ አይነቱ የጥላቻና የአክራሪነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ ዉስጥ ቦታ ሊኖረው የማይገባ፣ ለአገር ትልቅ ጠንቅ የሆነ ፖለቲካ ነዉ። አቶ ተድላም በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜያቸዉን ወስደው አክራሪነትን እና ጥላቻን ለማጋለጥ ላደረጉት አስተዋጾ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።



በቅድሚያ አክራሪነት ላይ ትንሽ ልበል። በአለማችን የሙስሊም አክራሪዎች በርካታ ጥፋቶች እየፈጸሙ እንደሆነ ሁላችንም የምናወቀዉ ነው። እነዚህ አክራሪዎች ዋሃቢስት ወይንም ሳላፊስት ይባላሉ። አላማቸው ሰው ሁሉ ሙስሊም እንዲሆን ነዉ። «ከሙስሊም (ይሄ ሱፊዎችና ሺያዎችን አይጨምርም) ውጭ ያሉ በሙሉ፣ እዉነተኛ ሙስሊም መሆን አለባቸው። አሊያም መጥፋት ይኖርባቸዋል» የሚል እምነት ነዉ ያላቸው። ሁሉንም በፍቃደኝነት ሆነ በሃይል ካሰለሙ በኋላ፣ በአንድ ከሊፋ የሚመራ፣ የሽሪያ እስላማዊ መንግስት ማቋቋም ነዉ አላማቸው።

የግብጹ ሙስሊም ወንድማማቾችን እንመልከት። አካባቢዉን ሁሉ (ግብጽ፣ ሶሪያ፣ ሳዉዲ አረቢያ፣ ዮርዳኖስ ፣ ሊባኖስ …) በሙሉ ተቆጣጥሮ፣ ዋና ከተማዉን ኢየሩሳሌም አድርጎ ፣ አካባቢዉን ሙስሊም ካልሆኖት ቃፊሮች አጽድቶ፣ አንድ ታላቅ እስላማዊ የከሊፋ ግዛት ለሟቋቋም ነዉ ሲሰሩ የነበሩት። በየቦታዉ፣ ዉስጥ ዉስጡን የተደራጁ ናቸው። ከሰማኒያ አመታት በኋላ ፣ የግብጽ ወጣቶች በቀሰቀሱት አብዮት ላይ ተረማምደው በግርግር ስልጣን ጨበጡ። የክርስቲያኖችን እና አክራሪ ያልሆኑ ሙስሊሞች ጥያቄ ወደ ጎን አደረጉ። እስላማዊ ሕገ መንግስት አጸደቁ።

አላማቸው ሕዝቡን በሙሉ ማገልገል፣ ግብጽን ማሳደግ ቢሆን ኖሮ፣ የሁሉንም መብት የሚያስከበር ሕግ መንግስት እንዲኖር ያደርጉ ነበር። ነገር ግን አላማቸው አገራዊ ሳይሆን አክራሪነት በመሆኑ፣ የማታ ማታ ከሕዝባቸው ጋር ተጋጩ። ሞርሲ ከስልጣን ወረዱ። ይኸው ግብጽም በነዚህ አክራሪዎች ምክንያት እየታመሰች ነዉ።

አንድ ነገር አንርሳ። እነ ሞርሲ ለምርጫ ይወዳደሩ በነበረበት ወቅት፣ ስዉር አላማቸውን ደብቀዉት ነበር። ስልጣን ከያዙ በኋላ ነዉ እዉነተኛ ማንነታቸው የተጋለጠው።

ኢትዮጵያ ዉስጥም አክራሪዎች አሉ። ለጊዜው ማንነታቸውን ደብቀዉ፣ ኃይላቸዉን እስኪያፈረጥሙና ስልጣን እስኪጨብጡ ድረስ ሞደሬቶች ሊመስሉን ይችላሉ። የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበረ፣ አንድ አክራሪ የኢሕአዴግ ባለስልጣን ሙስሊም ነበር። (በዚህ አጋጣሚ ኢሕአዴግ እራሱ በአክራሪዎች የተሞላ ድርጅት መሆኑን የሚያሳይ ነው) አብያተ ከርስቲያናት እንዳይገነቡ እየከለከለ፣ መስኪዶች እንዲገነቡ ይፈቅድ ነበር። መስኪዶች መሰራታቸው ችግር ባይኖረዉም፣ ቤተ ክርስቲያናት እንዳይሰሩ እያከላከሉ መስኪድ እንዲሰራ መፍቀድ ግን፣ ሌሎች እምነቶችን ለማዳከምና ለማጥፋት የሚደረግ አክራሪነት ነዉ።

እነ ጃዋር መሃምድ፣ እስላማዊ ኦሮሚያን፣ ብሎም እስላማዊ ኢትዮጵያን ለማቋቋም አላማቸው አድርገዉ ሲንቀሳቀሱ፣ ብዙ ልንደነቅ አይገባም። እነዚህ ከአለምአቀፉ የሙስሊም ወንድማማች ጋር እየተመካከሩ፣ እጅና ጓንት ሆነው የሚሰሩ ናቸው። ወጣት ጃዋር መሃምድ፣ ቸኩሎ የረጅም ርቀት አላማቸዉን አጋለጠባቸው እንጂ፣ በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛዉ፣ ሰላማዊ፣ ሞደሬት ፣ ከሁሉም ጋር መስራት እንደሚፈልጉ፣ አድርገዉ ነዉ እራሳቸውን የሚያቀርቡት። በአሁኑ ጊዜ ትኩረታቸው ሙስሊም ያልሆነው ክርስቲያኑ ላይ ሳይሆን፣ ሞደሬት ሙስሊሞች ላይ ነዉ። ከዋሃቢዝም ዉስጥ የተሳሰተ እስልምና የሚከተሉ የሚሏቸውን ማጥራት፣ ለዚህ ዘመቻም መሰናክል የሚሆኑትን፣ ታላላቅ የሙስሊም አባቶችን፣ ማስወገድ ዋና አላማቸው ነዉ።
ይሄንን ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ከወዲሁ ማገናዘብ ያለብን ይመስለኛል። ጉግል እያደረግን ትንሽ ጥናት ብናደርግ ብዙ የአክራሪዎችን ታክቲኮች እንረድለን።

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፣ ለዜጎች መብት መከበር፣ ለእምነት ነጻነት፣ ለዴሞክራሲ ያለዉን ቁርጠኝነት እያሳየ የሚገኝበት ወቅት ነዉ። እነ ኡስታዝ አቡበከር፣ ከመታሰራቸው በፊት ሲያስተምሩት በነበሩ ትምህርቶች ላይ ተቃዉሞ የሚኖርን ብዙ አለን። ነገር ግን የሚያስተምሩትን ብንቃወምም፣ ትምህርታቸውን በትምህርት መመክት ሲቻል፣ ሃሳባቸውን በነጻነት የመግልጽ መብታቸው ተረግጦ፣ አንዲት ጠጠር ሳይወረዉሩ ሽብርተኛ ተብለዉ፣ አሳፋሪ በሆነ መንገድ፣ በኢቲቪ ስብእናቸውና ክብራቸው ተዋርዶ ማየታችን እንደ ሰው፣ እንደ ኢትዮጵያዊ አሳዝኖናል። በነርሱም ላይ የደረሰው ግፍ ፣ የሃይማኖት ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በመሆኑም፣ ከነእስክንድር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ ጋር፣ የነአቡበከርንም መፈታት ሕዝቡ እየጠየቀ ነዉ።

በእስረኞች መፈታት፣ በእምነት ነጻነት፣ በሰብዓዊ መብት መከበር፣ በሕግ የበላይነት ዙሪያ፣ በአንድ ድምጽ መናገር እንደጀመርነዉም፣ በአክራሪነት ዙሪያም አንድ ድምጽ መናገር አለብን። በጋራ ሁላችንም ዋሃቢዝም አክራሪነትን መቃወም ይኖርብናል።

የመጀመሪያው ከጂራ ፋንዉንዴሽን መሪ ለሆኑት ለሃጂ ነጂብ መሃመድ አቶ ተድላ በጻፉት ደብዳቤ «It is unfortunate you did not condemn Jawar Mohamed hateful speech » ብለዋል። ሃጂ ነጂብ መሃመድ፣ በተለያዩ የዳያስፖራ ኢትዮጵያዉያን ጉባዔዎች ላይ ሙስሊም ማሀብረሰቡን ወክለው የሚናገሩ ናቸው። በርግጥም እነ አቶ ጃዋርና መሰሎቻቸው የሚያራግቡትን አክራሪነት አለማውገዛቸው ተገቢ አይደለም። «ምናልባት ሃጂ ነጂብ ከላይ ሞደሬት ከዉስጥ ግን እንደ ጃዋር አክርራሪ ይሆኑ ይሆን ?» የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላል።

የሳዉዲ ታላቅ ሙፍቲ (የዋሃቢስቶች ፓትሪያርክ እንደማለት ነዉ) ፣ ሼክ አብዱል አዚዝ ቢን አብደላ፣ ያለፈው አመት፣ በአካባቢዉ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲጠፉ ጥሪ አቅርበዉ ነበር። አንድ ተራ አክራሪ ይሄን አይነት አስተያየት ቢሰጥ፣ ብዙ ትኩረት ላይሰጠው ይችላል። ነገር ግን እኝህ ሰው ዋና መሪ ሆነው ነዉ፣ በነጃዋር የተንጸባረቀዉን አክራሪነት በይፋ ሲያወጁ የምንሰማዉ።

http://rt.com/news/peninsula-saudi-grand-mufti-701/

እንግዲህ ለሃጂ ነጂብ ያሉኝ ጥያቄዎች «እርሳቸውና የሚመሩት የሃይማኖት ተቋም ፣ ይሄንን አክራሪነት ለምን በይፋ አይቃወም ? ዋሃቢዝምን ለምን አያወግዝም ? በርግጥ ዋሃቢዝምና አክራሪነት የሚቃወሙ ከሆነ ደግሞ አክራሪነትን ለመወጋት በተግባር አስተምህሮ ይሰጣሉ ወይ ? » የሚሉት ይሆናል።

ለነዚህ ጥያቄዎች ግልጽ ምላሽ ባልተገኘበት ሁኔታ፣ ከነዚህ ሰዎች ጋር መንቀሳቀስ በተዘዋዋሪ መንገድ አክራሪነትን ማጠናከር ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል። የሃይማኖት ነጻነትን በማስከበር ስም፣ አክራሪነትን በማስፋፋት የሃይማኖት ነጻነትን እንዲገፈፍ መስራት የለብንም።

እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ላድርግ። ዜጎች የፈለጉትን የመሆን መብት አላቸዉ። እምነታቸውን የማስፋፋት፣ ክርስቲያኖችን አስተምሮና አሳምኖ ሙስሊም የማድረግ፣ መስኪድ የመከፈት ሙሉ መብት አላቸው። ክርስቲያኖችም ፣ ቤተ ክርስቲያን የመክፈት፣ ሙስሊሙን ክርስቲያን የማድረግ፣ ወንጌልን በሁሉም ቦታ የማስተማር ሙሉ መብት እንዳለቸው መረጋገጥ አለበት። ሙስሊሞች ክርስቲያን በመሆናቸው የሞት ፍርድ ሊፈረድባቸው አይገባም።

እንግዲህ አብረን እንድንሰራ ከተፈለገ «ሃይማኖት የግል አገር የጋራ» በሚለው መርህ ተስማምተን፣ አገራችንን እንደ አንድ ሕዝብ እያሳደግን፣ በፊናችን ደግሞ የምናምንበትን እምነት በሰላም ማስተማር፣ የምንከተለዉን ሃይማኖት ይዘን በሰላም መቀጠል ያስፈልጋል። ሰው የመረጠዉን የወደደዉን ሃይማኖት ይያዝ።

በአክራሪነት ላይ ይሄን ካልኩ ይበቃል። በጠባባ ብሄረተኝነት ላይ ያተኮረዉን ክፍል ሁለት በሚቀጥለው ጊዜ ይዤ እቀርባለሁ። ያኔም ጃዋር «ኢትዮጵያዉያን ከኦርሚያ ይዉጡ» ያለው አባባል በክልል ሕገ መንግስቶች በሰነድ የተንጸባረቀ መሆኑን ለማሳየት እሞክራለሁ።

Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/

በአማኑኤል ዘሰላም
amanuelzeselam@gmail.com

No comments:

Post a Comment