Monday, July 29, 2013

‹ኦሮሞ ፈርስት› ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ህመም!

(በመልካምሰው  አባተ ተፃፈ)

ሰሞኑን አንድ ንፁህ ኦሮሞ ነኝ የሚል ወንድማችን ‹ኦሮሞ ፈርስት› የሚል ጣጣ አምጥቶ ጥቂቶቻችን አኩርቶ ብዙዎቻችን ጣጣ ውስጥ አስገብቶ ከፊሎቻችን አበሳጭቶ እሱ በህይወት አለ፡፡ ነገሩ ካበሳጫቸው ሰዎች መካከል እኔና ሃኪም ገዝሙ በዋናነት እንጠቀሳለን፡፡ ምክንያቱም እኔና ሃኪም ገዝሙ የብሄር ክልሶች ነን፡፡ የቀበሌ መታወቂያ የሌለን ለዚህ ነው፤ ብሔር ከሚለው ጎን የሚፃፍ ብሄር ጠፍቶ፡፡ ….ጋሽ ገዝሙስ የቀበሌ መታወቂያ ባይኖራቸው ክሊኒክ አላቸው፤ እኔ ነኝ እንጂ ክሊንክ የለኝ፤ መታወቂያ የለኝ፤ ብሔር የለኝ፤ ብሄረሰብ የለኝ፤ ለነገሩ እኔ ራሴ አለሁ እንዴ? ያያችሁኝ ካላችሁ ንገሩኝ እስቲ….

መቼም ዘረ - ንፁህ ነን የሚሉትስ ኦሮሞ ፈርስት፤ አማራ ፈርስት፤ ጉራጌ ፈርስት፤ ትግሬ ፈርስት…… ምናምን ፈርስት ብለው ጎረሩብን፤ ፎከሩብን፤ አቅራሩብን፤…..እኔና ሃኪም ገዝሙ ማን ፈርስት እንበል? በውነቱ ህገመንግስቱ ፈርስት የምንለው ነገር ይሰጠን ዘንድ በንዴት እንጠይቃለን፤ ህገ መንግስቱ ብዙ ፈርስቶች ስላሉት እኔና ጋሽ ገዝሙን ማስደሰት አያቅተውም መቼም፡፡ በዚህ አጋጣሚ የህገመንግስቱን ፈርስቶች ጠቀስ ጠቀስ ባደርጋቸው ደስ ይለኝ ነበር ደሞ፤ የምጠቅሳቸው በአይኔ ነው ታዲያ፤ ይሞታል እንዴ ታዲያ?!....

 ….የጋሽ ገዝሙ ክሊኒክ ሰሞኑን ስራ በዝቶበታል፤ ገበያው ደርቷል፤ ይሄን ጊዜ ነበር ጋሽ ገዝሙን ማዬት፤ የማይስቅ የአካል ክፍል የላቸውም፡፡ ገዳም ሰፈር በተባለው ምርጥ ሰፈር ከኔ ቪላ ቤት ጥቂት ወረድ ብሎ ይገኛል የሃኪም ገዝሙ ክሊኒክ፡፡ (መቼም ያገሬ ሰው ደግ ነው የኔ ቪላ ቤት ስል አምኖኝ ይሆናል፡፡ እንኳንም አመነኝ፡፡ ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ካለማመን ማመን ሳይሻል አይቀርም፡፡…….)

የጋሽ ገዝሙ ክሊኒክ ሰሞኑን ለምን ገበያው ደራለት ብለው አንዳንድ ወገኖች ፌስቡክ አድርገውልኛል፡፡ እኔም የጥያቄውን ተገቢነት በመረዳት ጉዳዩን አጣርቻለሁ፡፡….ሃኪም ገዝሙ በገበያ ጥናታቸው በደረሱበት መሰረት እና ሾላ በድፍን በተባለው የንግግር ዘዴ እንደገለጹልኝ ከሆነ የክሊኒካቸው ገበያ የመድራቱ ምስጢር ‹ኦሮሞ ፈርስት› የተባለ እንደ ኤች አይቪ ቫይረስ መልኩን የሚለውጥ አዲስ ቫይረስ በመከሰቱ ነው፡፡…..ይህን ቫይረስ ከኤች. አይ. ቪ. ቫይረስ ጋር የሚያመሳስለው ሌላ ነገርም አለ፤ እሱም ምንድን ነው ቫይረሱ ከወደ አሜሪካ መምጣቱ ነው፤ እናት አገር ተማሩልኝ ተመራመሩልኝ ብላ የላከቻቸው የኛ ልጆች ናቸው አሉ ፖለቲካ ሳይንስ ላቦራቶሪ ውስጥ ሲመራመሩ ቫይረሱን ድንገት የፈጠሩት፡፡ ይህን ጉዳይ የሰሙ አንድ የአርሲ ክፍለሃገር ባላባት እንዲህ ብለው ፈጣሪን አመሰገኑ አሉ፤
እኔን ያንተ ምንዱባን
እንኳንም አረከኝ መሃን
ቆፍሬ ዘር የማልተክል
ትል ወልጄ ከእበት ጋር ከምተካከል!


***
ወንድም እና እህት የሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት መልስ ወደ ቤት ሲያዘግሙ ‹እግረመንገዳችን ለምን ኢንተርኔት ካፌ ገብተን ኢንተርኔት ምናምን አናይም› አሉ፡፡ የኢንተርኔት መጀመሪያው ፌስቡክ በመሆኑ ሁለቱም ፌስቡክ ሲከፍቱ አንድ አይነት ወሬ ይመለከታሉ፤ ኦሮሞ ፈርስት፤ ኢትዮጵያ ፈርስት፤ በሜንጫ አንገቱን በለው፤ አትበለው፤ እናትክን፤ አባትክን ምናምን የሚሉ ንትርኮች፡፡ ልጆቹ ግራ ይገባቸዋል፡፡ ግራ እንደገባቸው ከፌስቡክ ወጥተው ወደ ቤት ማዝገም ቀጠሉ፡፡ ሆኖም ወንድምዬው (ማለትም በቤት ስሙ ቤቢ) ጭንቅላት ውስጥ ‹ኦሮሞ ፈርስት› የምትለው እንግዳ ነገር ተቀምጣ እየጎረበጠችው ኖሯል፡፡ ቤቢ ‹ኦሮሞ ፈረስት› ምን ማለት እንደሆነ አልገባውም፤ የምርጫ ጉዳይ መሆኑን ግን አላጣውም፡፡ እናም ነገሩን ወደ ቤት ጣጣ አመጣው እና አባዬ ፈርስት ወይስ እማዬ ፈርስት? ሲል መፈላሰፍ ጀመረ፡፡ ተፈላስፎም አልቀረ እህቱ ኪኪን በጥያቄ ሊወጥራት ፈለገ፤…..
‹‹ኪኪ?››
‹‹ወይ?››
‹‹Dadi first? Or Mamy first?››
ኪኪ አላመነታችም ‹‹Dadi first› አለች በኩራት፡፡

ቤቢ ደግሞ የእናቱ ነገር ሞቱ ነው፡፡ ተናደደ፡፡ ‹ቆይ ለእማዬ ባልነግርልሽ› ይልና ይዝታል፡፡ ዝቶም አልቀረ እቤት ሲደርሱ ነገሩን ለእማዬ አቃጠረ፡፡ እናት ነገሩ አበሳጭቷቸው ኖሮ ኪኪን አስረው ሲገርፉ አባት ደረሱ፡፡ ‹ምን አድርጋ ነው?› ብለው ሲጠይቁ ቀልቃላው ቤቢ ‹አባዬ ፈርስት!› ብላ ነው ይላል፡፡ አባትም ፌስቡክ ላይ ኖሮ የዋሉት ነገሩ ወዲያው ተገልጦላቸው ‹‹አንተ እማዬ ፈርስት ስላልክ ነው የማትገረፈው?›› ይሉና ቤቢን መቀጥቀጥ ይጀምራሉ፤ በቀበቶ፡፡ ድንገት የቀበቶው ብረት የቤቢን ግራ አይን ታገኛለች፡፡ ቤቢ ራሱን ስቶ መሬት ላይ ይዘረራል፡፡ እሪታው ይቀልጣል፡፡ ቤተሰብ እና ጎረቤት እየጮኸ ቤቢን ይዞ ወደ ገዝሙ ክሊኒክ፡፡ ቤቢ እስካሁን ከክሊኒክ አልወጣም፤ አንድ አይኑም እስካሁን ድረስ እንደተከደነ ነው ብለውኛል ሀኪም ገዝሙ፡፡ …..

***
ወደ ሚቀጥለው የሃኪም ገዝሙ ጥናታዊ ምሳሌ ከመሄዴ በፊት የድምፃዊ መልካሙ ተበጀን ‹ሪሚክስ› ልጋብዣችሁ እና አብረን እንዝፈን እስቲ፡፡ ጨዋታችን ሞቅ ሞቅ እንዲል፡፡ የዘፈኑን ዜማ የማታውቁ ግን አርፋችሁ ተቀመጡ፤ እንዝፈንበት……..ያዙ እንግዲህ፤……
ማታ ማታ ከስራ በኋላ፤
ያስፈልጋል አንድ አንድ ካቲካላ!
ካቲ ካቲ……… ካቲ ካቲ….

***
ከሀኪም ገዝሙ ክሊኒክ ትንሽ ወረድ ብሎ ይገኝ የነበረው ዝነኛው ዝናሽ ካቲካላ ቤት ወደ ጠጅ ቤት መለወጡ የሰሞኑ የሰፈራችን ወሬ ነው፡፡ የጠጅ ቤቱ ስም ‹‹የፌስቡኳ ዝናሽ ጠጅ ቤት!›› ይባላል፡፡ የጠጅ ቤቱ ባለቤት ወ/ሮ ዝናሽ በፋና ኤፍ. ኤም. 20 ደቂቃችን ፕሮግራም ላይ ቀርባ እንደተናገረችው ከሆነ ጠጅ ቤቱን የከፈተችው በፌስቡክ ቆይታዋ ያገኘችውን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም ነው፡፡ እንደ ዝናሽ ትዝብት ከሆነ በፌስቡክ ከተማ ውስጥ ብዙ ተናዳጅ እና አናዳጅ ኢትዮጵያውያን አሉ፤ ከዚህ አንፃር የነኚህን ብስጩ ወገኖቻችን ንዴት ሊያስረሳ የሚችል ሃይል ጠጅና ጠጅ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ነው ጠጅ ቤቱን የከፈተችው፡፡ ዝናሽ አክላ ስትገልፅ  ጠጅ ቤቱን የከፈተችበት ሌላ ምክንያት ህገመንግስቱ በአንቀፅ 39 ያሰፈረላትን መብቷን ለመጠቀም ሲሆን የሷን ጠጅ ቤት ከሌሎች ጠጅ ቤቶች ለዬት የሚያደርገው ደግሞ ሰካራሞች ሲረብሹ በወይራ ቆመጥ ጣ! ጣ! አድርገው የሚያጋድሙ ጠረንገሎዎችን ከላሎምድር እና በጌምድር በማስመጣት ለወገኖቿ የስራ ዕድል በመፍጠሯ ነው፡፡ ዝናሽን ኢንተርቪው ያደረጋት ጋዜጠኛውም ሁላችንም የዝናሽን አርዓያ ብንከተል በመጠጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ መንግስት ያስቀመጠውን ግብ መምታት ባንችል እንኳ ጥሩ የግብ ሙከራ እናደርጋለን ብሎ የመከረ ሲሆን ይህን የሰሙ የጠጅ ቤቱ ጠጭዎችም ተጨማሪ ብርሌዎችን አዘዋል፡፡ …….ቺ   ር   ስ   !

ይህ በእንዲህ እንዳለ በክረምቱ ብርድ ምክንያት ስራ የቀዘቀዘበት ደላላው አሰግድ ፌስቡክ ላይ ተጎልቶ ትንሽ የባለጌ ልጆችን ስድቦች ከተመለከተ እና በትውልዱ ካዘነ በኋላ ‹እስቲ እንዳው ዝናሽዬ ቤት አራት ለመንገድ ልበል› ይልና የ‹ፌስቡኳ ዝናሽ ጠጅ ቤት› ዘው ይላል፡፡ ጠጅ ቤቱ ውስጥም አናጢው ዳምጤን ያገኘዋል፤ ዝናሽን እያሽኮረመመ፡፡ አሰግድ ብልጭ አለበት፡፡ ዝናሽ ከእሱ ውጭ የሌላ መሆኗን አስቦት አልሞት ገምቶት ጠርጥሮት አንጥሮት አብጠርጥሮት አንጠርጥሮት ዘርዝሮት መንዝሮት አበጥሮት አስበጥሮት አስነጥሮት…. አያውቅም፤ በፍፁም!  

‹‹ምን ትሰራለህ እዚህ?›› ሲል ይጠይቃል አሰግድ ብርሌ ጠጅ ከማዘዙ በፊት
‹‹ሰው የሚሰራውን!›› ይመልሳል አናጢው ዳምጤ
‹‹ከዝናሽ ጋር የምታደርገውን ጠጋ ጠጋ ብትተው አይሻልህም?›› ሲል ያስፈራራል አሰግድ
‹‹አገርና ሴት የጋራ ናቸው ወንድሜ!›› ይመልሳል ዳምጤ
‹‹ይቺን ይወዳል አሴ!›› አሰግድ ጥርሱን ነከሰ፡፡ ንዴቱን ለመርሳት ይህን ጠጅ በላይ በላዩ፤ በታች በታቹ ይለዋል፤ ይጠጣል፤ ይሸናል፡፡ ይሸናል፤ ይጠጣል፡፡ ‹አራት ለመንገድ› ልበል ብሎ የገባውን ‹አስራ ኣራት› ብርሌ አደረሰው፡፡ አስራ አምስተኛ አዘዘ፡፡ ዳምጤም በብርሌ ቁጥር ብልጫ ዝናሽን ከአሰግድ የቀማ መስሎት አንድ ብርሌ በሰከንድ ይጨልጣል፡፡ በርግጥም ዳምጤ 18 ብርሌ ለ15 ብርሌ እየመራ ነበር፡፡ ዝናሽ ደግሞ ዳምጤን ጠጋ ጠጋ አበዛች፡፡ አይ የሰው ነገር፤ ሰሞኑን አሰግድ እንደመቸሰት ስላደረገው እኮ ነው፤ ለምን እንደሁ እንጃ ክረምት ክረምት የድለላ ስራ ይቀዘቅዛል፡፡ ዝናሽ ደግሞ ክረምት ክረምት ሲሆን አሰግድን ጣል ጣል ታደርገዋለች፡፡ አሰግድ ፌሚኒስት ባይሆን ኖሮ ‹አይ ሴቶች!› ብሎ የሴቱን ዓለም ባጣጣለ ነበር፡፡ …..ይሁንና የዝናሽ ሁኔታ አሰግድን አለቅጥ ማናደዱ አልቀረም፡፡ ድንገት ‹‹ዝናሽ!›› ሲል ጮሆ ተጣራ፤ ጉሮሮው በጩኸት ከአስራ አስር ተሰንጥቆ ባይገኝ ምን አለ በሉኝ፡፡

‹‹አቤት›› አለች ዝናሽ የጠጅ ማንቆርቆሪያውን እንደያዘች ቆማ፡፡
‹‹አሰግድ ፈርስት ወይስ ዳምጤ ፈርስት!?›› ሲል ጠዬቀ አሰግድ አይኖቹን ጎልጉሎ
‹‹ዳምጤ ፈርስት!›› ብላ መለሰች ዝናች ኮስተር ኮስተርተር ብላ፡፡ ዳምጤ ከማዶ በደስታ ውቅያኖስ ሰምጦ ሃሴት ሲያደርግ ይታያል፡፡ እውነቱን ነው፤ ዝናሽን በመሰለች ደርባባ ወይዘሮ መመረጥን የመሰለ አስደሳች ነገር ምን አለ?!
ብስጭት እና ጠጅ አናቱ ላይ የወጡበት አሰግድ ወደ ዝናሽ ተንደረደረ፡፡ መንገድ ላይ ዳምጤ ያዘው፡፡ ግብ ግብ ገጠሙ፡፡ ወደቁ፡፡ ጠጁ ወለሉ ላይ ተደፋ፤ ብርሌው ተሰበረ፤ ማንቆርቆሪያ ተጨረማመተ፡፡  ዝናሽ እሪታውን አቀለጠችው፡፡ አንዴ አሰግድ፤  አንዴ ደግሞ ዳምጤ እየተገለባበጡ ተለጣለጡ፤ በቡጢ፤ በክርን፤ በቴስታ፡፡ የተጣሉ ሴቶች ሲሰዳደቡ፤ የተጣሉ ወንዶች ሲደባደቡ ቆሞ ማዬት እንዴት ደስ ይላልኮ!
ዝናሽ ድንገት እሪታዋን አቁማ ዘነዘና አነሳች፡፡ ለአሰግድ ወገብ ወረወረችው፤ ዳምጤ ግንባር ላይ አለፈ፡፡  የዝናሽ ወለል በደም ጎርፍ ተጥለቀለቀ፡፡ ሰፈርተኛ ዳምጤን ተሸክሞ ወደ ሀኪም ገዝሙ ክሊኒክ ሩጫ፡፡

ሃኪም ገዝሙ እንደነገሩኝ ዳምጤ እስካሁን ነፍስያውን አላወቀም አሉ፤ አሰግድም እስር ቤት ገብቷል፡፡ ጉዳዩን ለማዬት ፍርድ ቤቱ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ለነሃሴ 20፤ 2008 ዓ.ም.ቀጥሮታል አሉ፤ ፍርድ ቤት እንዲህ ወረፋ ይብዛበት በናታችሁ?!
ጋሽ ገዝሙ በሰሞኑ ገበያ መድራት እየተደሰቱ ዳምጤና አሰግድ የተጣሉበትን፤ ዝናሽ ለዳምጤ ያገዘችበትን ምክንያት ከስር መሰረቱ እየነገሩኝ ባሉበት ሁኔታ የሰፈራችን ጎረምሶች አናቱ በድንጋይ የተበረቀሰ ጓደኛቸውን እያንዘላዘሉ ወደ ክሊኒኩ ገቡ፡፡ ሃኪም ገዝሙ ቶሎ ብለው ነጭ ጋውናቸውን ለብሰው መራወጥ እና ማራወጥ ጀመሩ፡፡ እኔም በምን ምክንያት ይሆን ጠቡ? የሰውን አናት እንዲህ አለት ላይ የወደ ቅል የሚያስመስሉ በ’ውነት ምን አይነት ሰዎች ናቸው?….እያልኩ ሳስብ…..‹‹ማንቼ ፈርስት! ብሎ ነው አሉ አንዱ ብስጩ አርሴናሌ አናቱን የበረቀሰው፤ ከደጃፌ ላይ የሰው ነፍስ አጥፍተውብኝ ነበር እኮ፤ ሆ ሆ…….ወይ ጣጣ…….›› አሉ አፈር ከዱቄት እየደባለቁ እንጀራ ጋግረው ይሸጣሉ ተብለው የሚታሙት ወይዘሮ ስፍራሽ፡፡
‹‹እሱ የሊቨርፑል ደጋፊ፤ ከማንቼ እና አርሴ ቦለቲካ ምን አገባው እስቲ?›› አሉ አንድ ሽማግሌ በተጎጂው ላይ እየፈረዱ፤ የአርሰናል ደጋፊ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡
‹‹ምን አባቴ አውቄ እቴ?›› የወይዘሮ ስፍራሽ መልስ ነበር

***
ይህ በሆነ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይመስለኛል ቅዳሜ ማታ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ሸገር 102.1 የተባለ ኤፍ.ኤም. ጣቢያ ከፍቼ ቀልድ አዋቂው ቀንደኛ ጋዜጠኛ የጀኒፈር ሎፔዝ ዳሌ እያነሰ የሄደበትን ምክንያት ለአድማጮች ሲተነትን፤ እኔም በትንታኔው ድንገት ትን እንዳይለኝ ሰግቼ ፖፖዬን እየፈለኩ ሳለሁ ሃኪም ገዝሙ ደወሉልኝ፤
‹አቤት ጋሽ ገዝሙ?››
‹‹የምስራች!››
‹‹ምስር ብሉ፤ ምን ተገኘ?!››
‹‹አዲሱ ቅርንጫፍ ክሊንኬ ጠዋት ይመረቃል፤ ምን ይዤ ሳትል መጥተህ እንድትመርቅ!››
‹‹እንዴት አልነገሩኝም ቀደም ብለው?››
‹‹ሰርፕራይዝ ላድርግህ ብዬ ነው!››
ጋሽ ገዝሙ ለራሳቸው ጉዳይ እኔን የምስራች ማለታቸው እየገረመኝ እሁዱን ጠዋት ራስ ደስታ ፊት ለፊት የሚገኘውን አዲሱን ክሊንካቸውን ልመርቅላቸው ሄድኩ፤ ‹ቦታው ይጠፋኝ ይሆን?›  እያልኩ ስጨነቅ ከቅርብ ርቀት ጉልድበርግን የሚያካከሉ ፊደላት ነጭ አቡጀዴ ላይ አየር ላይ ተንጠልጥለው አየሁ፤ በአንድ ላይ እንዲህ እየተነበቡ፤..

‹ገዝሙ ፈርስት› ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ክሊንክ - የገዝሙ ክሊኒክ እህት ኩባንያ…….ስራ ጀመረ!
የምንሰጣቸው አገልግሎቶች፤
ለኦሮሞ ፈርስት
ለአማራ ፈርስት
ለትግሬ ፈርስት
ፈርስት ለተጠናወታቸው ሁሉ
.
.
.
ይምጡ፤ ይታከሙ፤ ይዳኑ፤ ይፈወሱ! በገዝሙ ፈርስት ክሊንክ!!!

No comments:

Post a Comment