Saturday, July 27, 2013

ምርጫው ከጠረጴዛው ላይ ነው! (ከድምፃችን ይሰማ)

ትናንት በአለም አቀፍ ደረጃ የተካሄደው ልዩና አስደማሚ ተቃውሞ መቼም ቢሆን ከልባችን የሚጠፋ አይሆንም፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ከቤቱና አካባቢው ነቅሎ በመውጣት ፍትህን ሲጣራ የዋለበት የትላንቱ ጁምአ በእርግጥም ደማቅና ልዩ ነበር፡፡ ከተቃውሞው ድምቀት እና ማማር ጋር ሙስሊሙ ሀህብረተሰብ ማድረስ የሚፈልገውን መልእክት በሚገባና በተብራራ ሁኔታ አድርሷል፡፡ እውን ለዜጎች ፍላጎትና መሻት የሚጨነቅ አካል ካለ ምርጫው ከጠረጴዛው ላይ ነው፡፡ እውን ለሕገ የበላይነት መከበር፣ ለሕገ መንግስቱ መከበር፣ ለአገር እድገትና ልማት የሚገደው መንግስት ካለ ምርጫው ከጠረጴዛው ላይ ነው፡፡ ሕዝቡ በጁምአው ትዕይንት መልእክቱን ትናንትም አድርሷል፡፡


የህዝበ ሙስሊሙ ፍላጎት የሚንጸባረቀው በጁምአ ሰላት ተቃውሞዎች ብቻ አይደለም። በስራ እና በአቅም ማነስ፣ እንዲሁም በተለያዩ አለመመቻቸቶች ምክንያት ተቃውሞ በሚደረግባቸው መስጂዶች መስገድ ያልቻሉ በርካታ ሚሊዮኖች በየከተማው አሉ። የመንግስት ጭቆና ጫፍ በደረሰባቸው ከተሞች ደግሞ ተቃውሞ ማድረግ እየፈለጉ አጋርነታቸውን በዱአና ተሰብስቦ በአንድ መስጂድ በመስገድ ብቻ ለመወሰን የተገደዱ ከተሞች በርካታ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ግን የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ የሚጋሩና በመንግስት ጭቆናም እኩል የተማረሩ ናቸው። የመስጂድ ነጠቃውና መድረሳ እሸጋው በቀጥታ እየነካቸው ያሉ ናቸው። ልጆቻቸው በየሳምንቱ ለእስርና ድብደባ እየተጋለጡባቸው ያሉ ናቸው። 


መንግስት በበርካታ አጋጣሚዎች ተቃውሞው የህዝበ ሙስሊሙ በሙሉ እንጂ የጥቂቶች አለመሆኑን ማረጋገጥ ችሏል። አስቀድሞ በየወረዳና በየቀበሌው ባደረጋቸው ስብሰባዎች ሀዝቡ ተቃውሞውን እስከጥግ አሰምቷል፤ ችግሩን ተናግሯል። ካድሬዎችና የወጣት ሊግ አባሎችን ብቻ በጠራባቸው ስብሰባዎችም አባላት መንግስት እየተከተለ ባለው አቅጣጫ ደስተኛ አለመሆናቸውን በግልጽ አንጸባርቀዋል። በአንዳንድ ቦታዎች የኢህአዴግ አባልነት መታወቂያቸውን አውጥተው ‹‹እንኩ ተቀበሉን አንፈልግም!›› ያሉ አባላት ታይተዋል። ሁሉንም ግን ‹‹የራሳችሁ ጉዳይ›› የሚል አመለካከት የሚያራምድ የሚመስለው መንግስት በአስገራሚ ሁኔታ ችላ ብሏቸዋል።



ባለፈው አመት መንግስት በጉልበተኝነት በቀበሌዎች አካሂደዋለሁ ያለውን የመጅሊስ ቅርጫ ድራማ ህዝበ ሙስሊሙ ሙሉ በሙሉ ገፍቶ በመተው ድምጹ አንድ መሆኑን አሳይቷል። የቅርጫ ጣቢያዎች ባዶ ሆነውባቸው የተቸገሩት ካድሬዎች ወደ አስፋልት እየወጡ ያገኙትን ሙስሊም እየጎተቱ ሲያስገቡ ለከፍተኛ ትዝብት ተጋልጠው ነበር። የደረሰባቸውን ሀፍረት መቋቋም ባለመቻላቸው ዜና ላይ ‹‹7 ሚሊዮን ሙስሊም በነቂስ ወጥቶ መረጠ!›› የሚል አስቂኝ ዜና ለማስነገር ተገደው ነበር።

መንግስት ይህ ሁሉ ሚሊዮን ሙስሊም የሚቃወመውንና ‹‹አይወክለኝም!›› የሚለውን መጅሊስ ይዞ ምን ሊያደርግ እንዳሰበ ለብዙዎች ግራ ነው። ከዚህ ሁሉ ህዝብ ጋር የተጣላና የሚጠላ መጅሊስ እቅዶቹን የሚያስፈጽመው እንዴት አድርጎ ይሆን? መንግስት መጅሊሱ ህዝቡን እንዲቆጣጠርለት ይፈልጋል፤ ኹጥባ እንኳ ከመጅሊሱ እጅ እንዳይወጣ መፈለጋቸውን ግልጽ አድርገዋል። ሚሊዮኖች እየተቃወሙት ግን ሙስሊሙን የማስቆጣት እንጂ የመቆጣጠር ስራ ሊሰራ እንደማይችል ግልጽ ነው። በአጭሩ አቅም የለውም፤ ህዝብ አንቅሮ ተፍቶታልና! ታዲያ መንግስት እንዲህ አይነቱን አቅመ ቢስ መጅሊስ ከሚስቀምጥ ህዝቡ በትክክል የሚያምናቸውን መሪዎች መርጦ ከነሱ ጋር መደራደር አይሻለውም ኖሯልን?


በአፈሙዝ ታጅቦ የመጣው የአህባሽ አመለካከት በህዝቡ አንቅሮ ተተፍቷል። በሁለት እግሩ ተደላድሎ ሊቆም የሚችልበትም እድል የለውም። የሚሊዮኖች ጆሮ የሚጠየፈውን ነገር በግድ ልጫን ቢባልም ህዝቡ በግልጽ ‹‹እምቢ!›› ብሏል። ሃይማኖት በሰዎች ልብ ውስጥ የሚኖር ከሆነ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አህባሽን በልባችን ቦታ ነፍገነዋል። ታዲያ ልባችን ዝግ ከሆነ የትኛው ቦታ ላይ ይሆን መቅደሱን የሚያንጹለት?

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እንደህዝብ አቋማችንን ግልጽ አድርገናል። ‹‹ህገ መንግስቱ ይከበር! ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ! የታሰሩት ይፈቱ! ድምፃችን ይሰማ! በእምነታችን ጣልቃ አትግቡ! ማስገደዱ ይቁም! አህባሽ አንሆንም! የመጅሊስ አመራሮች አይወክሉንም! የመጅሊስ አመራሮች ህገ-ወጥ ናቸው! የመጅሊስን አመራሮች አልመረጥናቸውም! ሀይማኖታዊ ጭቆናው ይቁም! ጥያቄያችን ይመለስ! የሀሰት ክስ አይገዛንም! የተነጠቁ መስጂዶቻችን ለሕዝብ ይመለሱ! የተባረሩ ኢማሞች ይመለሱ!›› እነዚህ ሁሉ ጠረጴዛው ላይ ተቀምጠው የዜጎች ጉዳይ ‹‹ይገደኛል›› የሚል አካል እየጠበቁ ነው፡፡ እኛ ሌላ አቋም የለንም!

አላሁ አክበር!

ማሳሰባያ፡ ፎቶዎቹ በተቃውሞው 20/ 2005 በተካሄደው የተነሱ መሆናቸው ይታወቅ!

No comments:

Post a Comment