አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
ኢህአዴግ በሐይማኖት ጉዳይ ገብቶ በእሳት መጫወቱን ያቁም !!
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
አንድነት ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ሲታገልለት የኖረውን የዴሞክራሲ ጥያቄ በማንገብ የህግ የበላይነት የሰፈነባት፣ ዜጎች በማንነታቸው የማይጨቆኑባት፣ ሁሉም ዜጎች በእኩል ደረጃ መብትና ነፃነታቸው የተረጋገጠባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትፈጠር ዘንድ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ እየታገለ ያለ ፓርቲ ነው፡፡ ይህን ትልቅ ህዝባዊ ርዕይ እንዲሳካ የሚታገለው ፓርቲያችን ስርዓቱ በቤተሰብ ደረጃ ጭምር የዘረጋውን የአፈና አደረጃጀት በመቋቋም በሀገር አቀፍ ደረጃ አስተማማኝ ድርጅታዊ መዋቅር ዘርግቷል፡፡ አንድነት መዋቅሩን ይበልጥ ለማጠንከርና ለማስፋትም ድርጅታዊ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
አንድነት ሀገራችን የምትተዳደርበትን ህገ መንግስት አክብሮ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ መሆኑንና በአንፃሩ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ግን ህገ መንግስቱን በመደፍጠጥ የዜጎችን የማሰብ፣የመናገርና የእምነት ነጻነት በማፈን ላይ እንደሚገኝ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ግልፅ ነው፡፡
ፓርቲያችን ኢ-ህገመንግስታዊ የሆኑ የመንግስት እርምጃዎችን ያወግዛል፤ ኢ-ህገመንግስታዊ የሆኑ ህጎችም ተሽረው በሌላ እንዲተኩ ይታገላል፡፡ አንድነት የኢህአዴግ መንግስት ህገመንግስቱን ረግጦ በሐይማኖት ጉዳይ እጁን ማስገባቱን ያወገዘውም ለዚሁ ነው፡፡ ዜጎች የመረጡትን ሐይማኖት መከተል፣ መሪዎቻቸውን ሐይማኖታቸው በሚፈቅደው መሰረት የመምረጥና የዕምነት ተቋማቶቻቸውን ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ውጪ የማስተዳደር መብት እንዳላቸው አንደነት ፓርቲ በፅኑ ያምናል፡፡
ኢህአዴግ በሐይማኖቶች የውስጥ ጉዳይ በመግባት የዜጎችን የዕምነት ነፃነት ማፈኑ ኢ-ህገመንግስታዊ ከመሆን ባለፈም የሀገራችንን ሰላም የሚያደፈርስ በእሳት የመጫወት ድርጊት ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ሁሉን የመቆጣጠር አባዜ ተጠናውቶት በሐይማኖት ነጻነት ላይ ጣልቃ መግባቱ ለሰው ህይወት መጥፋት መንስኤ መሆኑ አንድነትን አሳዝኖታል፡፡ግድያው በየትኛውም ወገን የተፈጸመ ይሁን ህገ ወጥነት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ኢሰብአዊ ድርጊቶች በአጭሩ የሚቀጩበት መንገድ ካልተፈጠረም መጪው ጊዜ ከአሁኑ በበለጠ የተወሳሰበ እንደሚሆን አንድነት በመጠቆም መንግስት እጁን ከሐይማኖት ተቋማት የውስጥ ጉዳይ እንዲሰበስብ ይጠይቃል፡፡
ፓርቲያችን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላለፉት አስራ ስድስት ወራቶች ሲያነሱት የቆዩትን የዕምነት ነፃነት ጥያቄ መንግስት በአግባቡ መመለስ እንዳለበት ያምናል፤ መንግስት ህገ መንግስቱን እንዲያከብርም ይጠይቃል፡፡ መንግስት በሐይማኖት ጉዳይ መግባቱን በመቃወማችንና የዜጎች የዕምነት ነፃነት እንዲከበር በመጠየቃችን ኢህአዴግ አንድነትንና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በአክራሪነት በመፈረጅ ላይ ይገኛል፤ ይህ የፍረጃ አካሄድ በሀሰት ላይ የተመሰረተ ውንጀላ መሆኑን መላው ህዝባችን እንደሚገነዘበው አንጠራጠርም፡፡ ኢህአዴግ የመብት ጥያቄ ያነሱ ዜጎችን ጥያቄ ሳይመልስ ችግሩን በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ለማላከክ መሞከሩ እንደማያዋጣውም አንድነት ያምናል፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በቅርቡ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት/Millions of voice for freedom” በሚል መሪ ቃል የጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ በኢህአዴግ መንግስት የተነጠቁ የህዝብ መብቶችና ነፃነቶች እንዲመለሱ እንዲሁም ዜጎች በሀገራቸው በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ የሚጠይቅ ነው፡፡
ኢህአዴግ ህዝባዊ ንቅናቄያችን እንዳይሳካ የፓርቲያችንን አባላትና አመራሮች በማስፈራራት፣በማገትና በማሰር ከንቱ ሙከራ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የእስር ዘመቻውን አስገራሚ የሚያደርገው በመዲናችን አዲስ አበባም ጭምር እየተካሄደ መሆኑ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ ለህዝባዊ ንቅናቄው አሳትሞ ያሰራጫቸውን በራሪ ወረቀቶች ሲያሰራጩ የነበሩ አባላት በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በህገወጥ መንገድ ታስረዋል፡፡
አንድነት ፓርቲ መንግስት በሰሜን ጎንደር፣በደቡብ ወሎና በአዲስ አበባ የጀመረው ህገ ወጥ እስር እንዲቆምና በህገወጥ መንገድ ያሰራቸውን የፓርቲያችንን አባላት በአስቸኳይ እንዲለቅ ይጠይቃል፡፡
ፓርቲያችን የጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ እንዲሳካ አባሎቻችን፣ደጋፊዎቻችንና ህዝቡ እያደረጉ ያለውን መብትን የማስከበር እንቅስቃሴ እያደነቀ ወደፊትም ትግሉን በቆራጥነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሐምሌ 5 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment