በምዕራብ ጎጃም ዞን በሜጫ ወረዳ ከባህር ዳር ከተማ 25 ኪሎ ሜትር አካባቢ ባችማ ቀበሌ ውስጥ አቶ ገብሬ ስንቴ ገደፋው የተባለ ግለሰብ ህይወት በጣም አስቸጋሪ ትሆንበትና ከነገ ዛሬ ቀን ይጣል ብሎ ተስፋ በማድረግ በሰው ቤት ተቀጥሮ ደፋ ቀና ይል ጀመር፡፡ ጊዜያት እየሄዱ ጊዜ ሲተካ እኔም እንደ እኩዮቼ በማለት ሚስት አግብቶ ልጅም ወለደ፡፡
የመጀመሪያ ልጁንም ብርቱካን ገብሬ
ሲል ሰዬማት፡፡ ብርቱካን ግን ከሶስት ዓመታት በላይ በህይወት ለመኖር አልታደለችም፡፡ በጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎችን የጫነች በፌደራል ፖሊስ በታጀበች መኪና ትገጫለች፡፡ አቶ ገብሬ ሁኔታውን ከስድስት ዓመት በኋላ ሲያስታውሱ ‹‹ድምጽ ሰምቼ ወደ መኪናው መንገድ ሄድኩ፤ የማይታመን ነገር ተመለከትኩ፤ በድህነቴ ለፍቼ የማሳድጋት አንዲት ልጄ አንገት ተቆርጦ ብዙ ርቀት ሂዷል፡፡ አካሏ ከሁለት ተለያይቷል፤ ከዚያ በኋላ የሆንኩትን አላውቀውም፡፡›› በማለት ሲናገሩ አሁንም ድረስ ፊታቸው ላይ አደጋው እንዳለ አድረገው ያስታውሳሉ፡፡
ሰኔ 6 ቀን 2000 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 3፡00 አካባቢ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ፌደራል ፖሊሶች አንድ ባለስልጣን አጅበው ይጓዙ ነበር፡፡ ብርቱካንን እንደገጩ በአካባቢው ወደ መራዊ ከተማ እየሄዱ የሚማሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መኪናውን ለማስቆም ሲሚክሩ ታጣቂዎቹ ‹‹እናንተንም እንዳንደፋችሁ›› በማለት አስፈራርተው ያልፋሉ፡፡ የአካባቢው ሰዎች ወደ ወረዳው ከተማ መራዊ ፓሊስ ስልክ ደውለው እነኚህ ወፍራም ባለስልጣን ወወንጀለኛ እንዲያዙ ቢናገሩም ከተማውን አልፈው ስለነበር ወደ አዊ ዞን እንጅባራ ይደውላሉ፡፡ አዊ ዞን ላይ ቢያዙም ከፖሊስ ጋር በምን መልኩ እንደተደራደሩ ሳይታወቅ ጉዟቸውን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ቀይሰው የመኪናዋን ታርጋም ቀይረው ጉዟቸውን ወደ ቻግኒ ከተማ ያደርጋሉ፡፡
የሜጫ ወረዳ የፖሊስ አካላት ወንጀለኛውን ለመያዝ ደፋ ቀና ሲሉ ከቆዩ በኋላ የሰውዬውን ማንነት ያውቃሉ፡፡ ከዚያም ምስኪኑን የሟች አባት ‹‹አርፈህ ተቀመጥ ልንረዳህ አንችልም›› ብለው ያሰናብቱታል፡፡ አባትም ሳይሰለች የልጁን ገዳዮች በህግ እንዲያዙለት በየቀኑ በየደረጃው ያሉ ባለስልጣናትን ደጅ መጥናት ቀጠለ፡፡ ግን የበለጠ መረጃዎቹን እያጠፉበት ሄዱ እንጅ አንዳች ነገር የፈየደለት አካል የለም፡፡ እንደ ደሃዋ መበለት ቢያንስ ሰልችቷቸው መልስ ይሰጡኛል ቢልም ቀናት ቀናት እየቆጠሩ ድካምና ልፋት ብቻ አተረፈ፡፡
የመራዊ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ በቁጥር መጤጣ/283/01 በቀን 17/10/2000 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ በሰጠው የህክምና ማስረጃ ሰኔ 06 ቀን 2000 ዓ.ም. ወደ ጤና ጣቢያው የመጣችሁ ህጻን ጭንቅላቷ የተፈረካከሰ፣ አንገቷ የተቆረጠ፣ እጆቿና ወገቧ የተሰባበረ ሲሆን ምንም አይነት እስትንፋስ እንደሌላት ለሜጫ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አሳወቀ፡፡
ፖሊስ ጽ/ቤቱ ግን በወቅቱ የሟችን አካል የሚያሳየውን ፎቶ ግራፍና ሌሎች ሰነዶችን ሁሉ አጠፋፏቸው፡፡ የሟች አባት ወደ ምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያና ፍትህ ቢሮ በተደጋጋሚ አመለከቱ፡፡
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ቢሮ በቁጥር ፍቢ/801/አበ.23/2001 በቀን 11/02/2001 ዓ.ም. ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በተጻፈ ደብዳቤ በትራፊክ ፖሊስ የተጀመረው ደብዳቤ ለምን እስካሁን እንደዘገዬና አደጋውን ያደረሰው ሰው ለምን እንደተለቀቀ በዝርዝር እንዲልክ ጠየቀ፡፡ በዚያው ዓመት እስከ የካቲት ወር ከተጓተተ በኋላ ፍትህ ቢሮ ብድጋሚ ለምዕራብ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ በቁጥር ፍቢ/1700/አበ.23/2001 በቀን 04/06/2001 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ‹‹የሰሌዳ ቁጥሩ ኢት 33- 3364 የሆነ ኮብራ መኪና ማንነቱ ባልታወቀ ሰው እተሸከረከረ ሳለ ሰው ገጭቶ ከገደለ በኋላ ማምለጡንና በዚህ ጉዳይ በሜጫ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ምርመራ ተጀምሮ ለውጤት ሳይበቃ በእንጥልጥላ ላይ መሆኑን›› ይገልጻል፡፡ ደብዳቤው አያይዞም ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ግለሰቡ በተደጋጋሚ ማመልከቱንና ምላሽ ያላገኘ ሲሆን በወረዳው ፖሊስ የተጀመረውን ምርመራ እንዲቀጥሉ በማድረግ ለቢሮው ሪፖርት እንዲያደረጉ ተገልጧል፡፡
ከዚያ በኋላ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥር አብክመፖ/መ/7/አደ/መ/80/02 በቀን 7/8/2002 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ከላይ የተጠቀሰውን ታርጋ ቁጥር በመጥቀስ ህጻን ብርቱካንን ገጭቶ እንዳመለጠ ዋና ሳጅን ደሳለኝ አባተ የተባለ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ፖሊስ ቢይዘውም እንዳልገጩ ሲነግሩት ሙሉ መረጃ ሳይዝ ሲለቃቸው ጉዟቸውን ወደ ፓዊ አቅጣጫ እንዳደረጉ ሪፖርት አድርጓል፡፡ ደብዳቤው አያይዞም ዳንግላ ከተማ ላይ ፖሊሶች ሊይዙት ቢሞክሩም ጥሰው እንዳመለጡ ይናገራል፡፡ በመጨረሻም የታርጋ ቁጥሩ በማን ስም እንደተመዘገበ በማጣራት እንዲተባበሩ ይጠይቃል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥር 1/ፌፖኮ211 በቀን 7/11/2002 የመኪናው ንብረትነት በቤኒሻንጉል ክልል መስተዳደር ምክር ቤት የተመዘገበ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ ቢሆንም ግን ለሟች ቤተሰቦች መፍትሄ አልተሰጣቸውም፡፡ የሟች አባት አቶ ገብሬ አሁንም ተሰፋ በለመቁረጥ ለሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አመለከቱ፡፡ ሰመጉም ምንም መፍትሄ ማምጣት ብቻ ሳይሆን መግለጫም ሳያወጣ እስከ 2004 ዓ.ም. ድረስ ቆየ፡፡ እንደ ሟች አባት እምነት የወንጀለኛው ማንነት በዚያው ቀን ታውቆ ነበር፡፡ ነገር ግን የመንግስት ከፈተኛ ባለስልጣን በመሆኑ ለስድስት አመት ተበድበስብሶ ቆየ፡፡
በወቅቱ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ባህር ዳር ላይ ስብሰባ ነበራቸው፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን በሙስና ወንጀል በቃሊቲ (በማዕከላዊ) የሚገኙት በዘመኑ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ ያረጋል አይሸሹም ባህር ዳር ሲመለሱ በጸጥታ ሀይሎች ታጅበው ሲሄዱ አደጋውን ያደረሱት የእርሳቸው መኪና አሊያም እርሳቸውን ያጀቡ ወታደሮች መኪና እንደሆነ በጊዜው ይታወቅ ነበር፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አቶ ያረጋል ወደ ማረሚያ ቤት ከተላኩ በኋላ በ2004 ዓ.ም. መግለጫ እንዳወጡ የሟች አባት ቢነግሩኝም መግለጫውን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ወንጀሉን የፈጸመው ግለሰብ በህግ ከተያዘ በኋላ በዚህ አመት እንደገና እንቅስቃሴ የተጀመረ ቢሆንም እስካሁን አቶ ገብሬ መፍትሄ አልተሰጣቸውም፡፡ የምራብ ጎጃም ፍትህ መምሪያ በዞ/ፍ/አቤ/መ/ቁ 92/05 በቀን 19/07/05 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ለሜጫ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት በአጭር ጊዜ የነበረው ሁኔታ እንዲገለጽልን ብሎ ቢጽፍም አቶ ገብሬ ፍትህ ለማግኘት አሁንም የማይረግጡት መስሪያ ቤት የለም፡፡
የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል ናቸው ቢልም ይህ የህገ መንግስቱ አንቀጽ ለሁሉም ዜጎች እኩል እንደማይሰራ ማረጋገጫ መሆኑን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያምናል፡፡
ሰላም
No comments:
Post a Comment