አዲሰ አበባ ፣ ሃምሌ 9 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለያዘቻቸው የልማት ውጥኖች ማሳኪያ የውጭ ምንዛሪ ወሳኝ ሲሆን ፥ አገሪቱ ይህን የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው መንገዶች አንዱ የወጪ ንግድ ነው ።
ሃገሪቱ ለዓለም ገበያ የምታቀርባቸውን የግብርና ፣ የኢንዱስትሪና የማእድን ምርቶችን በመተማመን በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግበራ መጨረሻ ላይ ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢዋን 10 ነጥብ 48 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ላይ ለማድረስ አቅዳለች።
ያለፉት ዓመታት እቅድ አፈፃፀም ሲታይ ግን ይህን የአምስት ዓመት ግብ ለመምታት በርካታ የቤት ስራዎች እንደሚቀሯት ነው የሚያሳየው።
ለአብነት ያህል በ2003 ዓመተ ምህረት 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ብታቀድም ያሳካችው 2 ነጥብ 75 ቢሊዮኑን ነው።
በ2004 ቢሆንም 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት አቅዳ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮኑ የአሜሪካን ዶላር አግኝታለች ።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመትም ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ አገኛለሁ ብትልም የዓመቱ መጨረሻ ወር ሳይካተት 2 ነጥብ 77 ቢሊዮኑን አግኝታለች።
የዓመታዊ እቅዶች አለመሳካት መንስኤው ምንድን ነው ?
የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ እንደሚሉት ፥ የየዓመቱ የወጪ ንግድ ገቢ ሲፈተሽ ከእቅድ አንፃር እየተሳካ አይደለም ።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተቀናጅተው እቅዱን ለማሳካት አለመረባረባቸውን ለአፈፃፀሙ አናሳነት ዋነኛ ምክንያት ነው ብለው ሚኒሰትሩ አስቀምጠዋል።
ከዚህ ባለፈ ግን ወደ ውጭ የምንልካቸው ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸው ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መውረዱ ተጠቃሽ ነው።
አምናና ዘንድሮ
ባለፈው ዓመት አንድ ቶን ቡና 5 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ቢያወጣም በአሁኑ ወቅት ግን ዋጋው ወደ 3 ሺህ 400 ዝቅ ብሏል።
ዘንድሮ ወደ ውጭ የተላከው ቡና መጠን ከአምናው ከ30 በመቶ በላይ ቢበልጥም ከገቢ አንጻር ግን ከ4 በመቶ በላይ ቀንሷል።
ይህ የዋጋ ቅናሽ በወርቅ ፣ አበባና ሌሎች ምርቶችም ላይ ተስተውሏል ።
በተቃራኒው በዓለም ገበያ የተሻለ ዋጋ ያላቸው ሰሊጥን የመሳሰሉ ምርቶች ደግሞ ከምርት አቅርቦት ውስንነት የተነሳ የሚፈለገውን ያህል ገቢ እንዳይገኝ ምክንያት ሆነዋል።
ሰሊጥ ብቻውን ዘንድሮ የ20 በመቶ የምርት ቅናሽ ተመዝግቦበታል።
የ5 ዓመቱ እቅድ ተስፋዎች
በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ በዓመት ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ 10 ነጥብ 48 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚደርስ ነው የተቀመጠው ።
አገሪቱ ልትቆጣጠራቸው የማትችላቸው ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው በቀሩት ሁለት ዓመታት ውስጥ በራሷ ልታስተካክል ሲገባት ላላስተካከለቻቸው ስራዎች ትኩረት እንደምትሰጥ ነው የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት ።
በእቅድ ዘመኑ ግንባታቸው የተጀመሩ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ፋብሪካዎች ወደ ማምረት ገብተው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ መላክ ይጀምራሉ ተብሎም ተስፋ ተጥሏል ።
እስካሁን የኢትዮጵያ ምርቶች ያልገቡባቸውን የኤዢያ ፣ ሩሲያ ፣ እስራኤልና የአፍሪካ ገቢያዎችን በአገባቡ በመጠቀም ለእቅዱ መሳካት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ታስቧልም ነው ያሉት ።
ሚኒስትሩ አቶ ከበደ እነዚህን የመፍትሄ እርምጃዎችን በመጠቀምም በአምሰት ዓመቱ እቅድ ላይ የተቀመጠውን ግብ ሙሉ በሙሉ ማሳካት ባይቻል እንኳን ዓመታዊ ገቢውን ከ8 እስከ 10 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማድረስ እንችላለን ብለዋል ።
No comments:
Post a Comment