Thursday, July 18, 2013

ኢህአዴግ በሩን እንዲከፍት የዓለም ባንክ አዘዘ! የማነቂያው ገመድ ከርሯል፤ “ትግሉ ይቀጥላል” ኦባንግ ሜቶ

ኢህአዴግ ለሚገዛት ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ዕርዳታ የሚሠጠው የዓለም ባንክ፤ ለዕርዳታና ልማት የሚልከው ገንዘብ ኢህአዴግ የሕዝቡን ሰብዓዊ መብት ለመጣስ ተጠቅሞበታል በሚል ሙሉ ምርመራ እንዲካሄድ አዘዘ፡፡ የባንኩ ውሳኔ ኢህአዴግን የማነቂያው ገመድ እንደሚያከረው ተገለጸ፡፡ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በተለይ ለጎልጉል በሰጡት መግለጫ “ይህ በጥናት ከምናካሂደው ትግል አንዱ ውጤት ነው፤ ገና ጅማሬ ነው፤ ጠንክረን እንሠራለን” አሉ፡፡

የዓለም ባንክ ለልማት ሥራዎች የሚሰጠው የእርዳታ ገንዘብ በኢትዮጵያ በተለይም በጋምቤላ ክልል የሚኖሩትን ዜጎች ሰብዓዊ መብት በመጣስ ላይ ውሏል በሚል ከዚህ በፊት ክስ ቀርቦበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ጉዳዩን ከ9 ወራት በፊት በዘገበበት ወቅት ተጠቂዎቹ ዜጎች ያቀረቡትን ማስረጃና የኢንስፔክተር ቡድኑ የሚያደርገውን ምርመራ በዝርዝር ሰፍሮ ነበር፡፡ በወቅቱ ምርመራውን ያደረገው የመርማሪ ቡድን (ኢንስፔክሽን ፓናል) በአካባቢው የሚገኙትን ተጠቂዎች ካነጋገረ በኋላ ለባንኩ የሥራ አመራር ቦርድ በሰጠው ሪፖርት በዕርግጥ የዕርዳታው ገንዘብ በሰብዓዊ መብት ረገጣ ላይ መዋሉን ይፋ አድርጓል፡፡

ይህ የኢንስፔክተር ቡድን ከፍተኛ ሥልጣን ያለው መ/ቤት ሲሆን የዓለም ባንክ ለአገራት የሚሰጠውን ገንዘብ በትክክለኛ ቦታ ላይ አለመዋሉን በመጥቀስ ክስ የሚያቀርቡ ወገኖችን ጉዳይ በመከታተልና ቦታው ድረስ የራሱን ምርመራ በማካሄድ ውጤቱ ተግባራዊ እንዲሆን የባንኩን እጅ የማስጠምዘዝ ዓቅም ያለው እንደሆነ ከዚህ በፊት ያካሄዳቸው የምርመራ ውጤቶች ይጠቁማሉ፡፡


ቡድኑ መረጃውን ይፋ ባደረገበት ወቅት ቢያንስ የ600 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ከዚህ ካለፈም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የማጣት ጭንቀት ውስጥ የገባው ኢህአዴግ አንገቱ መታነቁን ሲያስተውል የኢንስፔክሽን ቡድኑን ውሳኔ አጣጥሎት ነበር፡፡ በወቅቱ መግለጫ የሰጡት በጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ቢሮ አፈቀላጤ የነበሩት ጌታቸው ረዳ “ከኢንስፔክተር ቡድኑ ጋር አንተባበርም፤ ትብብር ማድረግ ካስፈለገንም ከዓለም ባንክ ጋር ይሆናል፤ … ይህ በኢህአዴግ ላይ የተነጣጠረ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ነው፤ … ኢንስፔክሽን ፓናል የራሱ የዓለም ባንክ ኢንስፔክተር (መርማሪ) ቡድን አይደለም፤ … ቡድኑ የራሱን ልብወለድ ዘገባ በዓለም ባንክ አሠራር ላይ ለመጫን ያደረገው ሙከራ ነው” በማለት ነበር ያጥላሉት፡፡

ከዚህ በኋላ የዓለም ባንክ በኢንስፔክተር ቡድኑ የውሳኔ ሃሳብ መሠረት ሙሉ ምርመራ እንዳያደርግ ኢህአዴግ እንደለመደው ውሉ ያልለየለት አካሄድ በመከተል ሲከላከል አምስት ወራት አስቆጥሯል፡፡ በመጨረሻም ለዛሬ ሐምሌ 11 (ጁላይ 18) ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ከአዲስ አበባ፤ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በመሆን የዓለም ባንክን አመራሮች ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው እያለ ባንኩ ከአንድ ቀን በፊት ሙሉ ምርመራ እንዲካሄድ ማዘዙ “ኢህአዴግን የማነቂያው ገመድ” እየከረረ መምጣቱን የሚጠቁም ነው፡፡ ከዚህም በላይ ባንኩ በራሱ ገንዘብ ማንም ሊያዝበት እንደማይችል ያሳየበትና ለኢህአዴግም እጅግ አሳፋሪ ውሳኔ መሆኑ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለው ኢንክሉሲቭ ዴቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል Inclusive Development International (IDI) እና ሌሎች ክፍሎች ይናገራሉ፡፡ በውሳኔው መሠረት አሁን የሚካሄደው ሙሉ የምርመራ ዘገባ ኢህአዴግ በእርግጥ የሚሠጠውን ገንዘብ ለሰብዓዊ መብት ረገጣ ማዋሉን ካረጋገጠ፤ ኢህአዴግ በትንሹ 600ሚሊዮን ዶላር ያጣል፤ ጉዳቱም እስከ ቢሊዮኖች እንደሚደርስም ይገመታል፡፡

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ከሚያካሂደው ሁሉን ዓቀፍ ትግል ይህ አንዱ ክፍል አንደሆነ የተናገሩት የንቅናቄው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ “እኛ በመሠረቱ ልማትን አንቃወምም፤ ሆኖም ግን በልማት ስም የሚሠጠው ዕርዳታ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለመርገጥ የሚውል ከሆነ ህወሃት/ኢህአዴግ ተጠያቂ መሆን ይገባዋል” ብለዋል፡፡ የግልጽነትና ተጠያቂነት ዕጥረት እንዲሁም የሙስና በሽታ እንዳጠቃው በራሱ መሪዎች የሚነገርለት ኢህአዴግ፤ የፈለገውን ነገር እንደፈለገው የማድረግ አምባገነናዊ አሠራሩ ራሱን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከተው አቶ ኦባንግ በተለይ ለጎልጉል በስካይፕ በሠጡት አጭር ቃለምልልስ አስታውቀዋል፡፡ እልህ አስጨራሽ ቢሆንም የጋራ ንቅናቄው በጥናትና በዕቅድ ከሚያካሂደው ሁሉን ዓቀፍ ትግል አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት የንቅናቄው ዳይሬክተር፤ “ይህ ገና ጅማሬ ነው፤ በተጠናከረ መልኩ በመንቀሳቀስ ጉዳዩን ዳር በማድረስ የተጎዱ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን መከራ” እንደሚታደጉ ጨምረው አመልክተዋል፡፡

ባንኩ የሚልከው የመርማሪ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በቅርቡ እንደሚንቀሳቀስና ኢህአዴግም ቡድኑ ለሚያደርገው ሙሉ ምርመራ በሩን ክፍት ማድረግ እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ የምርመራው ውጤት ከዚህ በፊት የተደረገውን ምርመራ የሚያጸና ከሆነ ኢህአዴግ ለልማት ሥራ እንዲያውለው በዕርዳታና ድጎማ ስም የሚያገኘው ገንዘብ እንዲሁም ሌሎች የእርዳታ ምንጮች እጅግ ከፍተኛ አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ ባንኩ ከዚህ በፊት በደቡብ እስያ አገር ላይ የወሰደው ዓይነት አስከፊም እርምጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ምንጭ፡ www.goolgule.com

No comments:

Post a Comment