አቶ አስራት አብርሃም ይባላል፡፡ አቶ አስራት በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በስነ ፅሑፍ “ጎበዝ ተማሪ የመሆን ምስጢር”፣ “ከሀገር በስተጀርባ”፣ “መለስና ግብፅ” በቅርቡ ደግሞ “ፍኖተ ቃኤል” የሚሉ ስራዎችን ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዓረና ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆንና የመድረክ ስራ አስፈፃሚ በመሆን በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በቅርቡ ከነበረበት ዓረና/መድረክ የፖለቲካ ድርጅት እራሱን ያገለለ ሲሆን በዚህና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢቦኒ መጽሄት ጋር ያደረገውን አጭር ቆይታ እነሆ.
ኢቦኒ፡- ፖለቲካ ላንተ ምንድነው?
አቶ አስራት፡-ፖለቲካ ለእኔ አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም የለውም። ለምሳሌ በፊት የነበረኝ ምልከታ እና አሁን ያለኝ፣ በተለይ የፍልስፍና ትምህርት መማር ከጀመርኩ በኋላ “ፖለቲካ ላንተ ምንድነው?” ለሚለው ጥያቄ የተወሳሰበ መልስ ነው ሊኖረኝ የሚችለው። ሳይንሱ እንደሚለው ከሆነ የስልጣን ሳይንስ ነው ፖለቲካ! ስልጣን የመያዝና የማስጠበቅ ነገር ነው። ከእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ተነስቼ ፖለቲካን ሳየው አንዳንዴ ደስ ደስ የሚል ሌላ ጊዜ ደግሞ መጥፎ ነገር መስሎ የሚታየኝ ወቅት አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትልቅ ነገር የማሰብ፣ ትልቅ የመሆን፣ አገርን ወይም ወገንን ወደ ተሻለ የአስተሳሰብና የአኗኗር ደረጃ ለማድረስ የሚደረግ ትግል ይመስለኛል። የሰው ለሰው ግንኙነት ቀላልና ምቹ የማድረግ ጥበብ መስሎ የሚታሰበኝ ቀንም አለ።
ኢቦኒ፡- እንዴት?
አቶ አስራት፡- ፖለቲካው በደንብ ከገባህ በሁሉም ቦታ ላይ ነው የምታገኘው። ቤትህ ውስጥ ራሱ ልታገኘው ትችላለህ። ከባለቤትህ ጋርና ከልጆችህ ጋር የሚኖርህ ግንኙነትን ሁሉ ሊያጠቃልል ይችላል። ለምሳሌ በወሳኔ አስጣጥህ ይሳተፋሉ ወይ? በእነርሱና በአጠቃላይ የቤተሰብ የጋራ ውሳኔ ላይ ሃሳብ ይሰጣሉ ወይ? አንተስ እንደፊውዳል ጌታ ነው? እንደ ባርያ አሳዳሪ ነው? እንዴት ነው ራስህን የምታንፀባርቀው? ዴሞክራት ነህ? ሌበራል ነህ? እዚህ ላይ ሴት ልጅህ የወንድ ጓደኛዋን ወደ ቤትህ አምጥታ ብታስተዋውቅህ የሚኖርህ ምላሽ እንዴት ያለነው? ያንተ የብቻህ የሆነ ነገርስ ምንድነው? ትዳርህ ምን ሲሆን ነው ግድ የሚሰጥህ? ይህ ትዳር ቢፈርስ ግድ የለኝም የምትልበትስ ጊዜ የሚመጣው ምን ሲሆን ነው? በማንኛውንም ግንኙነት ውስጥ ቀይ መስመሮች አሉ፡፡ ጓደኝነት ምን ዓይነት ሲሆን ነው ቢቀጥል ጠቃሚ የሚሆነው? ቢፈርስ ግድ የማይኖርህስ መቼ ነው? በፍልስፍና መነፅር ስታየው ይህ ሁሉ ፖለቲካ ነው የሚሆነው።
ኢቦኒ፡- ወደ ፖለቲካው ህይወት እንዴት ልትገባ ቻልክ?
አቶ አስራት፡-በህፃንነትህ ቆሎ እየበላህ ካደክግና በዚያ ላይ ትምህርት ከጨመርክበት ፖለቲከኛ መሆንህ አይቀርም። ምክንያቱም በምቾት እና በተድላ ማደግ ስትችል በድህነት፣ በጉስቁልና ማደግህ ይቆጭሃል፣ ስትማር ያን ሁኔታ ተመልሰህ ማየትህ፣ ምክንያት መፈለፍግህ አይቀርም። በዚህ ጊዜ ዋነኛው ምክንያቶቹ መሪዎች ሆነው ነው የምታገኛቸው። በዚህ ጊዜ መሪዎቹን ከነስርዓቱ ለመቀየር ትነሳለህ፤ በዚህ ምክንያት ሳታስበው ፋኖ ትሆናለህ ማለት ነው።
ልጅም ስለነበርኩ ሊሆን ይችላል እስከ ህውሓት ክፍፍል ድረስ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ህወሓት ተከፋፈለ ሲባል ሁላችንም ነው የደነገጥነው፤ በኋላ ኢንፎርማሊ በሆነ መንገድ ስለጉዳዩ እዚያ የነበርነው የትግራይ ልጆች ስንነጋገር አንዳንድ ተማሪዎች “ስዬ አብርሃ እንደዚህ ነው፤ ገብሩ አስራት እንደዚህ ነው” የሚል ነገር ሲመጣ ግር ይለን ጀመር።
በተለይ ስዬ ላይ የሚነገረው ነገር እኔ በጣም ነው ቅር ያሰኘኝ ። የተንቤን ልጅ እንደመሆኔ ፤ልጅ ሆኔ ስለስዬ አብርሃ ጀግንነት እየዘፈንኩ ነው ያደኩት፤ ልጆች ሆነን ከስዬ እና ከኃየሎም ውጭ የምናውቀው ሰው አልነበረም። መለስ የሚባል ሰው በህወሓት መኖሩን እኔ ያወኩት የሽግግሩን ጉባኤ ሲመራ ነው። ስለዚህ እነስዬ፣ እነ ገብሩ አስራት ከህወሀት ወጡ ሲባል ከእኔ ልብም ህወሓት አብሮ መውጣቱ አልቀረም። በወቅቱ እኔ ስለህወሓት ምንንነት ላውቅ የምችልበት እድል አልነበረም። ስለህወሀት በጥልቀት ለማወቅ ጥረት ያደረኩት ከዚያ በኋላ ነው።
በዚህ አገር የፖለቲካ ልዩነት የሚመጣው ባለው ነገር ሳትስማማ ስትቀር ወይም ቅር የሚልህ ነገር ሲኖር ነው። እነርሱም ቢሆኑ አኩርፈው ነው ወደ ጫካ የገቡት። ዞሮ ዞሮ በዚያ ምክንያት የትግራይ ህዝብ ለምንድነው በህወሓት ብቻ የሚወከለው? የሚል ጥያቄ አንስተን መወያየት ጀመርን። የትግራይ ወጣቶች ድርጅት የመመስረት ሀሳብም በተወሰኑ ልጆች ተነስቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ትምህርቱም ኑሮውም ይጫነን ስለነበር እስክንመረቅ ድረስ ምንም ማድረግ አልቻልንም ነበር።
የእኛ ፍላጎት ታክሎበት አብዛኞቻችን ወደ ትግራይ ተመደብን። ይህን አጋጣሚ ተጠቅመን እየተንቀሳቀስን እያለን እነ ገብሩ አስራት ፓርቲ ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ መረጃ ደረሰን፡፡ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ሆነን ነው ዓረናን ወደ መመስረቱ የገባነው። በወቅቱ በኮሌጅ ማስተማር፣ የኮሌጅ ኃላፊ ሆኖ መስራት ብርቅ በነበረበት ወቅት ፓርቲውን ለመመስረት በውድድርና በስዕለት ጭምር ያገኘሁትን ስራ ሁሉ ትቼ ዋናው ጽ/ቤት መቀሌ ላይ ሲከፈት አደራጅ ሆኜ ገባሁ።
ኢቦኒ፡-ወደ ፖለቲካው ህይወት በመግባትህስ ምን አገኘህ?
አቶ አስራት፡-በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ በስለት ላይ የመራመድ ያህል ነው። ስለዚህ ከዚሁ ስለታሙ ጎዳና አገኛለሁ ብለህ የምታስበው ነገር በጣም ትንሽ ወይም ምንም ሊሆን ይችላል። ከዚህ በመለስ ግን ወደዚህ ፖለቲካ በመግባቴ ያገኘኋቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ምርጫዬ፣ ውሎዬ ከታላላቅ ሰዎች እንዲሆን አድርጎታል። ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ስዬ አብርሃ፣ አረጋሽ አዳነ፣ አቶ አውዓሎም ወልዱ፣ አቶ አስገደ ገብረስላሴ፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ ገብሩ አስራትና ሌሎች እነዚህን የመሳሰሉ መሪዎች ስብስብ ጋር ነው እውል የነበረው። ከእነዚህ መሪ ሊሆኑ ከሚችሉ ሰዎች ጋር መዋል ቀላል ነገር አይደለም፡፡
ሌላው ያገኘሁት ጥቅም በህወሓት ዙሪያ የፃፍኳቸው መፃሕፍት መረጃ ለማግኘት ቅርብ እንድሆን አድርጎኛል፡፡ በእርግጠኝነት ዓረና ውስጥ ባልገባ ኖሮ “ከአገር በስተጀርባም” ሆነ አሁን ያሳተምኩት “ፍኖተ ቃኤል” የሚታሰቡ አይሆኑም ነበር። ከአገር ውስጥና ከውጭ ከብዙ ጠንካራና ቅን ኢትዮጵያውያን ጋር አስተዋውቆኛል። ጥሩና ባለራዕይ የሆኑ የትግል ጓዶች አፍርቼበታለሁ። ከዓረና ብለይ እንኳ ከእነዚህ ጓደኞቼ ብዙ ብዙ መንገድ ለወደፊት አብረን የምንራመድበት መንገድ ተዘርግቷል፤ ሁላችንም የዚያ መንገድ ተጓዦች መሆናችን ስለማይቀር አብረን የምንጓዘው መንገድ ነው። በነገራችን ላይ ባለቤቴንም ያገኘኋት በዓረና ዋና ፅህፈት ቤት ስሰራ ነው። የዓረና አባል አይደለችም ነገር ግን ለእኔ ብላ በ2002 ምርጫ ወቅት ከእኔ ጋር በተንቤን በምርጫ ቅስቀሳው ላይ ተሳትፋለች፤ የመድረክ ታዛቢ ሆናም ስርታለች።
ኢቦኒ፡-እስካሁን ባደረከው ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት ተሳትፎ ይህን አበርክቼአለሁ የምትለውስ አለ? ያጣኸውስ?
አቶ አስራት፡-ቀዳሚው ነገር ስለትግራይ ህዝብ የሚነገረውና እውነታው ምን እንደሚመስል በጥቂቱም ቢሆን ለማሳየት ችያለሁ። በተለይ ለአዲሱ ትውልድ ሀገራዊ አጀንዳ ያስቀደመ ትግል ማድረግ እንደሚሻልና እንደሚያስከብርም ጭምር ምሳሌ ሆኜ በትንሹ ለማሳየት በመቻሌ በዚህ በእኩል በተወሰነም ቢሆን የተሳካልኝ ይመስለኛል።
ያጣሁት ነገርም የዚያው ያህል በጣም ብዙነው። ከሁሉም በላይ የእናቴን ህይወት ለማሻሻል ህልም ነበረኝ፣ አጠገቤ ሆና እንድትኖር እፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን ዓላማው ወደዚህ በመቀየሩ ምክንያት ለራሴም በዚህ ዕድሜዬ ሚስትና ልጅ ይዤ ከቤተሰብ ጋር ነው ተጠግቼ የምኖረው። የግል ኑሮዬ ጫና ያለበትና አስቸጋሪ ነው።
ኢቦኒ፡-ብዙውን ጊዜ በትግራይ የኢህአዴግ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ አለ ተብሎ አይታሰብምና አንተ በይበልጥ እዛ ስለምትንቀሳቀስ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
አቶ አስራት፡-እኔ ኢህአዴግን እንደ ትግራይ ህዝብ ከልብ አዝኖ የሚያማርረው ህዝብ አላየሁም፤ አንድም በሌሎች አካባቢ ያለውን ሁኔታ በደንብ ስለማላውቅ ሊሆን ይችላል። ልጆቻችንን የሰዋነው እንዲህ ዓይነቱን ስርዓት ለማምጣት ነበር እንዴ? ፍትህ የምትሰጡት እንዲህ ነው እንዴ እያለ የሚጠይቅ ህዝብ ነው። በዚህ ጊዜ ህወሓት እኔ እዚያው ባሉበት አግጄ ይዛቸው ነው እንጂ ደርጎቹ ተመልሰው ይምጡላችኋል በማለት ሲያስፈራሩት ተመልሶ ጸጥ ይላል፡፡ በዚህም ሳያበቃ የትግል ዘፈን፣ የትግል ዘመን እንጉርጉሮ እያሰማ ያሰፈራራል፡፡
ህዝቡ ደግሞ እውነታውን ባለማወቁ ደርግ ከሚመጣስ እናንተ ልጆቻችን እንደፈለጋችሁ አድርጉን ብሎ ዝም ይላል። ችግሩ የነበረው ተቃዋሚዎች ላይ ይመስለኛል። ምክንያቱም ህዝቡን በደንብ አልቀረቡትም፡፡ የድርጅት ስራ በደንብ ሳይሰሩ ህዝብ ለመስብሰብ ይሄዳሉ፤ ያኔ ህወሓት ደጋፊዎቹን አሰባስቦ አደራሾቹ ይሞሉና ስብሰባው እንዲታወክ ያደርጋል። ዓረና ይህን ነገር በጠንካራ አደረጃጀት ተሻግሮታል፡፡ በዚህም ምክንያት መድረክ ከሁለት ጊዜ በላይ በመቀሌ ከተማ እጅግ በጣም ደማቅ ህዝባዊ ስብሰባዎች አካሂዷል።
ኢቦኒ፡-አሁን በእናንተ የፖለቲካ ድርጅት “ዓረና ትግራይ” ውስጥ ያሉት አመራሮችና አባላት ከኢህአዴግ የተለየ ነገር ኖሯቸው ሳይሆን ከአቶ መለስ ጋር ባላችው የግል ጥላቻ እንደሚቃወሙና እንደሚንቀሳቀሱ ይነገራል፤ እዚህስ ላይ አንተስ ምን ትላለህ?
አቶ አስራት፡-ሁለት ነገር ለያይቶ ማየት ተገቢ ነው። ዋናው ጉዳይ ይህን እያለ ያለው ማነው የሚለው ነው። ይህን የሚለው ኢህአዴግ ነው። ነገር ግን ከኢህአዴግ የተለዩበት ዋና ምክንያት የሀገር ጉዳይ ነው። በኤርትራ ጉዳይ ምክንያት ነው ከአቶ መለስ ጋር እንዲጋጩ ያደረጋቸው። ይሄ ታሪክ ዘግቦታል ብዬ ነው የማስበው። በነገራችን ላይ በግል ጉዳይ ላይ ከአቶ መለስ ጋር እስከጥል የሚያድርስ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም። በፖለቲካ ከእርሳቸው ጋር እስከተስማማህ ድረስ መስረቅም ሆነ ሙስና መፈፀም ትችላለህ፡፡ በግል ህይወትህ አቶ መለስ ምንም የሚሉ ሰው አልነበሩም።
በፖለቲካው አመራራቸው ላይ ጥያቄ ያነሳህ ጊዜ ነው እርሳቸውም የሚነስቡህ። ስለዚህ ከአቶ መለስ በነበራቸው የግል ፀብ ነው የወጡት የሚለውን አልቀበለውም። ይህን ሀቅ እመሰክር ዘንድ ህሊናዬ ያስገድደኛል፤ ምክንያቱም በቅርብ ሁኔታውን ለማወቅ የተሻለ እድል ነበረኝና።
ኢቦኒ፡- ዓረና በትግራይ ያለው እንቅስቃሴስ ምን ያህል ነው?
አቶ አስራት፡-ይህን የምትጠይቀኝ አዲስ የሚሾመው የዓረና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምን ሊስራ ነው?! እንግዲህ ስራውን መሻማት እንዳይሆን እንጂ እኔ አውቀው እስከነበረ ድረስ እንቅስቃሴው ጥሩ የሚባል ነው። በራሪ ወረቀት በየጊዜው እያሳታመ ከአላማጣ እስከ ሁመራ ድረስ ይበትናል፣ አባላት ያደራጃል። ከ2002 ምርጫ በኋላ ተዘግተው የነበሩ ጽ/ቤቶች እንደአዲስ ተክፍተዋል። በሁመራ ዙሪያ የተከፈቱ አዳዲስ ፅሕፈት ቤቶች አሉ። አጠቃላይ እንቅስቃሴው አበረታች ሊባል የሚችል ነው።
ኢቦኒ፡- ፓርቲያችሁ መድረክን ከመሰረቱ 6 ፓርቲዎች አንዱ ነው፤ አብሮ በመንቀሳቀሱ ምን ያህል ውጤታማና ተጠቃሚ ነን ብላችሁ ታስባላችሁ?
አቶ አስራት፡-ዓረና ወደ መድረክ በመግባት ያገኘው ነገር ብዙ ነው። ቀዳሚው በፓርቲው ውስጥ በፕሮግራም ደረጃ የነበሩ ልዩነቶችን ወደ አንድ እንዲመጣና የሀሳብ አንድነት እንዲኖር ትልቅ አስተዋዕኦ አድርጓል። ምክንያቱም የዓረና የመጀመሪያው ፕሮግራም ላይ አንዳንድ መግባባት ላይ ያልደረስንባቸው ለወደፊት አባላት ከፈለጉ እንዲያሻሽላቸው የተውናቸው ነገሮች ነበሩ። በሁለተኛው ጉባኤ ግን የመድረክን መለስተኛ ፕሮግራም ለእኛ በሚስማማ መልኩ አሻሽለን ስለተቀበልነው የነበሩትን ልዩነቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲጠቡ ተደርጓል።
ሌላው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ የመስራቱ ጉዳይ፣ ክልላዊና አገራዊ አጀንዳዎቻችንን ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማድረስ፣ በመድረክ በእኩል ሀሳባችንን ለማስረፅ ጥረት አድርገናል። እንደዚሁም በብሄርና በህብረ ብሄር ፓርቲዎች መካካል የነበረውን ያለመግባባትና ያለመተማመን የሁለቱም ድልድይ በመሆን ጥሩ መቀራረብና አብሮ መስራት እንዲቻል የበኩላችንን አድርገናል። ያጣነው ነገር ብዙም የለም። ምናልባት ዓረና ወደ መድረክ ባይገባና መድረክ ባይፈጠር ከአንድነት ጋር የመዋሃድ እድል ወይም ራሱን ወደ አገራዊነት የማሳደግ ነገር ሊኖር ይችል ነበር። ይህ ግን ብዙም ልዩነት የለውም። አሁንም ከአንድነት ጋር በመድረክ ውስጥ እየሰራ ነው ያለው። ወደ ሚፈለገው ደረጃ አላደገም እንጂ መድረክ እንዲዋሃድ የዓረና ፍላጎት እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።
ኢቦኒ፡-አሁን ባለበት ሁኔታ መድረክ የሚጠበቅበትን ስርቷል ብላችሁ ታምናላችሁ? ወደፊትስ ከመድረክ ምን የተለየና የተሻለ እንጠብቅ?
አቶ አስራት፡-በእውነቱ ከሆነ መድረክ የሚገባውን ያህል ስራ ሰርቷል ብዬ አላስብም። የሚጠበቅበትን ስራ እንዳይሰራ ያደረጉት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች አሉት። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአስራርና የአደረጃጀት ለውጥ ለማምጣት አለመቻሉ ነው የከፋ የሚያደርገው። ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን አንጋፋነቱን አሳልፎ እየሰጠ ነው። የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንደሚባለው ሆኖ አንዴ 33 አንዴ ምንትስ እየተባለ ያለው መድረክ በተገቢው ሁኔታ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ነው። ወደ ስራ ሊገባ አልቻለም። ወደ ስራ ልገባ ነው ብሎ ይነሳና የሆነ ነገር ይፈጠራል፤ በዚያ ላይ ይቆማል። የሁሉንም ምክንያት ኢህአዴግን ማድረጉ ደግሞ የውስጥ ችግሩን እንዳያይ አድርጎታል።
ሌላው ከዚህ በኋላ ከመድረክ ምን እንጠብቅ ያልከው እኔም ከዚህ በኋላ እንደዜጋ የሚሆነውን መጠበቅ እንጂ ምን ሊያደርግ እንደሚችል አላውቅም። ከዚህ በኋላ የማድረግም ያለማድረግም፣ የመታገልም ያለመታገልም የተቀሩት የመድረክ አመራሮች መብትና ግዴታ ነው የሚሆነው። አሁንም ሀሳብ እየሰጠሁ ያለሁት እንደ አንድ ዜጋ እንጂ እንደመድረክ አመራር አይደለም፤ እንደዜጋ ስለመድረክ ሀሳብ ስሰጥ ደግሞ ስለሚመለከተኝ ነው። እየታገሉ ያሉት ህዝብን ለማስተደዳደር ነው። ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ ነገ አስተዳዳሪዎቼ ሊሆኑ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት አስተዳዳሪ ነው እንደዜጋ የሚያስፈልገኝ በሚለው ጉዳይ ላይ ስናገር ስለመድረክም መናገሬ አይቀርም፤ ወደፊትም መናገሬ የሚቀጥል ነው የሚሆነው።
ኢቦኒ፡- እስኪ ከፍልስፍና አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት ትግል አለ ብለህ ታምናለህ?
የፍልስፍና አንዱ ጥቅም አውቅህም ሳታውቅም የሰበሰብካቸው የእውቀት፣ የአስተሳሰብና የመረጃ ኮተቶች የሚያስወግድልህ ጥሩ መጥረጊያ መሆኑ ላይ ነው። አዲስ እውቀት፣ አዲስ አስተሳሰብ ለማነፅ የቆየውን ማስተካካል ወይም ማፍረስ ግድ ነው። ቀድሞ በነበረህ ላይ በላይ በላይ የምትቆልለው ከሆነ የእውቅት ድሪቶ ነው የሚፈጠረው። እንዲያውም እዚህ ሀገር ያለው አንድ ችግር ይህ ይመስለኛል፡፡ አንድ ሰው ከአያቱ የማይሻል ወይም የሚያንስ አስተሳሰብ እንደያዘ ዶክተር ወይም ፕሮፌሰር ሊሆን የሚችልበት የጉድ አገር ነው ያለነው። ትምህርት ማለት የአስተሳሳብ ለውጥ መሆኑ እዚህ አገር ተረስቷል። ማንበብና መማር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። መሸምደድና ማወቅ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ የፍልስፍና አንዱ ጥቅም Deconstruct ማድረግ መቻሉ ነው።
ወደ ጥያቄህ ልመለስና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትግል አንዳንድ ጊዜ ባልሆነ ነገር ላይ የሚጠፋ ነው። ጥራዝ ነጠቅነት በጣም ይበዛበታል። ከስልሳዎቹ የሚቀዳ አሁንም የእኔ ርዕዮተ ዓለም እንደዚህ ነው ያንተ ደግሞ እንደዚህ ነው ስለዚህ አንድ ዓይነት አይደለም የሚል ነገር ይበዛበታል። ዶ/ር መረራ ጉዲና ስለዚህ ነገር ሲናገሩ “እኛ በፊውዳል ስርዓት አራማጅነት የምንከሳቸው ሰዎች ናቸው እኮ ሊበራል አይደላችሁም የሚሉን” ሲሉ ሰምቼ ነበር፡፡ ለምሳሌ እኔ ከዚህ ወደ ሽሬ ለመጓዝ፣ በመቀሌ በእኩል ልሂድ ወይስ በጎንደር፤ በመኪና ልሂድ ወይስ በአውሮፕላን የሚለውን ለመወሰን ርዕዮተ ዓለም የግድ ላያስፈልገኝ ይችላል። ፖለቲካው እንደዚያ ነው። ተግባራዊ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ነው ማትኮር ያለበት።
በአገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ነው መስማማትና መቀናጀት ያለበት። እኛ ምን ዓይነት ሀገርና ህዝብ ነው ያለን፤ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይስ ነው የምንገኘው የሚለው ነገር ከርዕዮተ ዓለም በላይ ነው። እኛ ሀገር ግን ይሄ እየታሰበ ያለ አይመስለኝም፡፡
ኢቦኒ፡- ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች አሁን በሚከተሉት አካሄድ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ ብለህ ታስባለህ? ለምን?
አቶ አስራት፡-እዚህ አገር የተለያየ ግብ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ነው ያሉት። በአዲሱ መፅሐፌ ላይ እንደገለጽኩት የፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በስልጣን ላይ ካሉ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ፤ ተቃዋሚ ከሆኑ ደግሞ ስልጣን ለማግኘት ነው የሚታገሉት። ከዚህ አንፃር በእኛ አገር ብዙ ዓይነት ተቃዋሚዎች ነው ያሉት፡፡ ኢህአዴግ እንዳይወድቅ የሚሰሩ ተቃማዊዎች አሉ፤ በኢህአዴግ ያገኙትን የብሄራቸውን መብት ለማስጠበቅ የቆሙ ፓርቲዎች አሉ፤ የቢዝነስ ፓርቲዎችም ያሉ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ለምን የልማታዊ ባለሀብት መሆን እንዳልቻሉ ይገርመኛል። እውነተኛ ትግል የሚያደርጉትና ለለውጥ የሚታገሉት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ከገዥው ፓርቲ በሚደርስባቸው ጫና፣ በውስጣቸው በሚኖር ሽኩቻና በውስጠ ዴሞክራሲ እጦት የሚታመሱ ናቸው።
በተገቢው ጊዜ ተገቢ እንቅስቃሴ ማድረግ ተስኗቸዋል። ህዝቡን በተገቢ ሁኔታ ማደራጀት ቢቻል ኖሮ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች በእስር ባልማቀቁ ነበር፣ የህዝብ ድምፅ የነበሩት ጋዜጦችም ባልተዘጉ ነበር። ኢህአዴግ ሕገ መንግስቱን ሲጥስ መግለጫ ከማውጣት የዘለለ ስራ ስለማይሰራ ነው። ሁሉም ሰው ለመታሰር እራሱን ዝግጁ ቢያደርግ ዜጎች አለአግባብ የሚታሰሩ ከሆነ እኛንም እሰሩን ቢል መንግስት የታሰሩትን ይለቃል እንጂ ሁሉንም ህዝብ ማሰር አይችልም። በቃን ሰለቸኸን ስለዚህ ከእንግዲህ ከጫንቃችን ውረድልን ብሎ ሁሉም ህዝብ ጎደና ቢወጣ ኢህአዴግ ምንም ነገር ማድረግ አይችልም ነበር፤ የሚደረገው ትግል ብስልና ጥሬ እየሆነ ነው የተቸገርነው።
መታሰር የሚፈሩ እና የኢህአዴግን ፊት እንደ አየር ፀባይ እያጠኑ የሚታገሉም አሉ። እንዲህ ሆነህ ፖለቲካውን መምራትና ህዝብን በማደራጀት ለውጥም ማምጣት አትችልም። ስለዚህ እውነተኛ ትግል በልኩ እየተደረገ መስሎ አይታየኝም፤ ይሄ እንግዲህ ወደ ሰፊው ህዝብ ከተመለስኩ በኋላ እንደዜጋ ነው ሀሳቤን እየተገፅኩልህ ያለሁት።
ኢቦኒ፡-እስኪ በአጭሩ ከመድረክም ሆነ ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ከኢህአዴግ አለ የምትለው ጥሩ ነገር በንፅፅር ጥቀስ ብትባል ፤ ደካማ ወይም መጥፎ ጎንስ?
አቶ አስራት፡-የኢህአዴግን ጥሩ ነገር መናገር የኢቴቪን ስራ መሻማት ሊሆንብኝ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ እነ በረከት ስምዖንና እነ ሽመልስ ከማል በስራችን ለምን ገባ ብለው ሊቀየሙኝ ይችላሉ። ለማንኛውም ዓላማው ምንም ይሁን ምን አባይን ለመገደብ መነሳቱ ጥሩ ነገር መስሎ ነው የሚታየኝ! በፕሮፓጋንዳ መከራችንን በላን እንጂ! የኢህአዴግ ደካማ ጎን ወይም መጥፎነት ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም።
በአጭሩ ከብዙ በጥቂቱ የኢህአዴግ ትልቁ ስህተት የአገሪቱን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ባለቤትነት ያለውን ወደብ ማሳጣቱ ነው። ቀጥሎ የዘር ፖለቲካ የሚያራምድ መሆኑ ነው። በተጨማሪም ዴሞክራሲያዊ አይደለም። ወደ ተቃዋሚዎች ስትመጣ ብዙውን ጊዜ መናገር የምችለው ስለማውቀው ስለመድረክ ወይም ስለዓረና ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ መድረክ ከፕሮግራም አንፃር ጥሩ ነገር ነበረው፤ ወደ ስራ ለመተርጎም አስቸጋሪ ሆነ እንጂ! በዚህ አገር ያሉት እርስ በእርስ የሚቃረኑ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች ወደ አንድ ለማምጣት ጥረት ያደረገ ፓርቲ ነው። ችግሩ ደግሞ የአመራር ዳይናሚዝም የሌለው መሆኑ ነው። ስልጣን በጥብቅ ቁጥጥር ስር ሆና በአንጋፋዎቹ ዙሪያ ብቻ እንድትሽከረከር ነው የተደረገችው። የፖለቲካ ትግል የስልጣን ትግል ነው፤ ስልጣን ሳይኖርህ ዓለማህን ማስካት አትችልም። እኔ ለስልጣን አይደለም የምታገለው የሚል ፖለቲከኛ ፖለቲካ የገባው አይመስለኝም። ከቻልክ ራስህ ካልቻልክ ደግም ፓርቲህ ስልጣን እንዲይዝ ነው የምትታገለው።
ኢቦኒ፡- አዲሱ “ፍኖተ ቃኤል” የተሰኘው መፅሐፍህ ምን ላይ ነው ትኩረት ያደረገው? ለምን?
አቶ አስራት፤-አሁን በዚህ ወር ያሳተምኩት “ፍኖተ ቃኤል” የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሽርፍራፌ ገፆች የሚለው ነው። ይህ መፅሐፍ አሁን እኔ የደረስኩበትን የብስለት ደረጃ በትክክል የሚያሳይ ሆኖ ነው የሚሰማኝ። ብዙ ነገሮች ላይ በተለይ ፖለቲካው ላይ ለውይይት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች አሉበት። በተለይ ከመግቢያው ጀምሮ እስከ ሰባ ምናምን ገፅ ያለው አጠቃይ ስለተቃውሞው ፖለቲካ ጎራ ደካማ ጐንና ወደፊት ምን መደረግ አለበት በሚሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ የሚያተኩር ነው። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ስለህወሓትና ስለኢህአዴግ በተለይ ከመለስ በኋላ ስላለው ኢህአዴግ የሚያትቱ ፅሁፎች አሉበት።
መጨረሻ ላይ ክህደት በዘገልባ የሚል ሰፊ ርዕስ አለ፡፡ ይህ አንድ ራሱን የቻለ መፅሐፍ እንዲሆን ነበር የፈለኩት ፤ ነገር ግን የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑ ሰዎች ትብብር ማጣትና በመረጃ እጥረት ምክንያት በአንድ ምዕራፍ እንዲጠቃለል ግድ ሆኗል። ወደፊት በስፋት ሊጠና የሚችል ቁም ነገር የያዘ ጉዳይ ነው። አቅሙና መረጃው ያላቸው ሰዎች ይሰሩታል የሚል እምነት አለኝ። ይህ መፅሐፍ ዋና ትኩረቱ የተቃውሞ ጎራው ድክመት ሊወገድ የሚችልበት መንገድ መጠቆምና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሌለ፣ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ማሳየት ነው።
ኢቦኒ፡- የሰሞኑን የሚኒስትሮችን ሹምሽርስ እንዴት አየኸው?
አቶ አስራት፡-አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ ኢህአዴግ ሹም ሽር ሲያደርግ ይህ ሶስተኛው ሲሆን ስርዓቱን ለማስቀጠል እያደረገ ያለው ሙከራ አንዱ አካል ነው። ይህ ሹም ሽር ልዩ የሚያደርገው እነዚህ ከስልጣን የተሻሩት በሹመት ስም መሆኑ ነው። የነበራቸውን ስልጣን በሌላ ግን ደግሞ በማይረባ ስልጣን ተተክቷል፤ ጥቅሙም ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም። ለምሳሌ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ወርቅነህ ገበየሁን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሁን ትራንስፖርት ሚንስትር ሆነዋል፡፡ በእርግጥ እርሳቸው ባለፈው የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ወርክሾፕ ላይ እንዳየኋቸው ከሆነ ምክትላቸው አቶ ሀሰን ሽፋ ሳይቀሩ ውይይቱን በትኩረት በሚከታተሉበት ሰዓት እርሳቸው ከአይፎናቸው ጋር ይጫወቱ ነበር፡፡ መቼም ወደዚህ ቦታ ሲመጡ ከአውቶብስ ግፊያ ወይም ከታክሲ ሰልፍ የሚያድነን ብልሀት ይፈጥራሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በአንፃሩ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በክልላቸው ዜጎችን በማፈላቀል ባሳዩት ተነሳሽነት ይሁን በሌላ ምክንያት እድገት አግኝተው የትምህርት ሚንስትር ሆነው ተሹመዋል። እንዴት ነው ነገሩ፤ ቢያንስ በዚህ ቦታ የሚቀመጠው ሰው ለተማሪዎች አርአያ የሚሆን ሰው መሆን የለበትም እንዴ!
አቶ በረከት ስሞዖንም አቶ ደመቀ መኮንን አስከትለው ወደ ቤተ መንግስቱ ዘልቀዋል፡፡ አቶ ኩማም እንደዚሁ የአቶ አረከበ ዕጣ ደረሷቸው፤ ማዘጋጃ ቤቱን አስረክብና ወደዚህ ጠጋ በል ተብለዋል። ከዚህ በኋላ ቤተ መንግስቱ በአማካሪ እና በአጫፋሪ መጨናነቁ አይቀሬ ነው። ሰውዬውስ የስንቱን ምክር ነው የሚሰሙት! “ምክር፣ ምክር በዛ እኔ አላማረኝም” የሚል ዘፈን ቢኖር እንጋብዛቸው ነበር። እንግዲህ ምንም ጥርጥር ለውም፡፡ ከዚህ በኋላ ሀገሪቱን ተሰብስበው ነው የሚመሯት! ይሄ ነገር ግን ያለመተማመን ነው የሚያሳየው ወይስ የህወሀት ድራማ ነው?! የሚያስብል ነው፤ ይህን ጊዜ ራሱ የሚፈታው ነው የሚሆነው።
አሁንም እላለሁ፤ ይህ ነገር “ጉልቻ ቢቀያይር…” ነው! የኢህአዴግ መሪዎች የዘነጉት ነገር አንድን ስርዓት በህዝብ ፍላጎት እንጂ በአማካሪ ብዛት የማይቆም መሆኑ ነው! ጠንካራና የተደላደለ ስርአት መፍጠር የሚቻለው ነፃነትና ዴሞክራሲ በማስፈን መሆኑን አሁንም አልተገለፃላቸውም!
No comments:
Post a Comment