ስም ምንድን ነው? መታወቂያ ነው፤ መጠሪያ ነው፤ ስም ማጥፋት ሲባል ስም አለ ማለት ነው፤ ከስምም አልፎ የገነነ ስም አለ ማለት ነው፤ ስለዚህም ሊጠፋ የሚችለው የገነነ ስም ሲኖር ብቻ ነው ማለት ነው፤ ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የገነኑ ስሞች ናቸው፤ አንድ ሰው እነዚህን የገነኑ ስሞች አጠፋህ ቢባል ሊገባን ይችላል፤ ዘለቀ ወርዶፋ፣ አየለ ተከስተ ስማቸው ጠፋ ቢባል፣ መጀመሪያ የሚቀርበው ጥያቄ እነማን ናቸው? ዱሮስ የገነነ ስም ነበራቸው ወይ? የሚል ይሆናል፤ ስለዚህ መሰላሉን ያልወጣውን ሰው ውረድ ቢሉት ትርጉም የለውም።
ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ስም ነው፤ ዘርፈሽዋል ማናለብህ ስም ነው፤ ክቡር ፕ
ሬዚደንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ስም ነው፤ ታደሰ ክፍሎም ስም ነው፤ ደራርቱ ቱሉ ስም ነው፤ ውቢቱ ማስረሻ ስም ነው፤ አዜብ መስፍን ስም ነው፤ ቴዎድሮስ ካሣሁን ስም ነው፤ አበበ ቶላ ስም ነው፤ ሚካኤል በላይነህ ስም ነው፤ ሐጎስ በየነ ስም ነው፤ … እነዚህ ሁሉ ስሞች በመሆናቸው አንድ ቢሆኑም ከእያንዳንዳችን ጋር ባላቸው ግንኙነት ይለያያሉ፤ አንዳንዶቹን እናውቃቸዋለን፤ በተለያዩ መንገዶችም ቢሆን ከኑሮአችን ጋር የተያያዙ ስለሆኑ፣ ያስደስቱናል ወይም ያስከፉናል፤ ስለዚህም ሲያስደስቱን እናወድሳቸዋለን፤ ሲያስስከፉን እንወቅሳቸዋለን፤ ዋናው ጥያቄ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፤ ውቢቱ ማስረሻ፣ ዘርፈሽዋል ማናለብህ፣ ታደሰ ክፍሎም፣ አበበ ዋቅቶላ ማን እንደሆኑና ምን እንደሆኑ አላውቅም፤ ስለዚህ የነሱን ስም አንሥቼ የምደሰትበትም ሆነ የምከፋበት ምክንያት የለኝም፤ የኔ አይደሉም፤ የሚያስደስቱኝና የሚያስከፉኝ የኔ የምላቸው ናቸው፤ የኔ የምላቸው እነማን ናቸው? ወድጄም ሆነ ተገድጄ ጭንቅላቴ ላይ በእግራቸው የቆሙ ሰዎች አሉ፤ እኔ የኔ ባልላቸውም እነሱ የራሳቸው፣ ዕቃቸው አድርገውኛል፤ የምነቅፋቸውም ራሳቸውን የኔ ሳያደርጉ እኔን የነሱ ስላደረጉኝ ነው፤ ስለዚህም የኔ የሆኑት ሁሉ ሳወድሳቸው አይከፍሉኝም፤ ስወቅሳቸውም አይከሱኝም፤ ሳወድሳቸው ደስ የሚላቸውና የሚኩራሩት ስወቅሳቸው ለምን ይቆጣሉ? የማወድሳቸውም ሆነ የምወቅሳቸው የራሴን ጥቅም እያሰብሁ መሆኑን ሳይገነዘቡት ቀርተው ነው? ወደአራት ዓመት ግድም ሲሆነኝ ገና ጣልያን ሳይገባ አንዲት እግራቸው የማይንቀሳቀስላቸው አሮጊት ጎረቤት ነበሩ፤ ጠዋት ተሸክመው በር ላይ ያስቀምጧቸዋል፤ እንደልባቸው ሲለፈልፉ ይውሉ ነበር፤ በደንብ የማስታውሰው ‹‹ሠይፉ ዘለቀ … ተለቀለቀ! መስፍን ስለሺ ይበቃል ለሺ!›› እያሉ በየዕለቱ ይጮሁ ነበር፤ መስፍን ስለሺ የአራዳ ዘበኛ ሀነው በፈረስ ይታዩ ነበር፤ ሠይፉ ዘለቀ በድቅድቂት የሚሄዱ ነበሩ፤በኋላ አንደሰማሁትና ትንሽ ትንሽ እንደማስታውሰው ለጣልያን ገብረው ውርደት ደርሶባቸው ነበርና የአሮጊትዋ ትንቢት የያዘ ይመስላል፤ ለማናቸውም ሴትዮዋ ተከሰሱ ሲባል አልሰማሁም።
ከስድሳ ዓመታት ያህል በፊት በኒው ዮርክ አንድ ሰው በስም ማጥፋት ክስ መሠረተ፤ ፍርድ ቤቱ ከሱን ሲመረምር ከሳሽ ፖሊስ መሆኑን ተረዳ፤ ፖሊስ የሕዝብ አገልጋይ ነው፤ ስለሆነም በፖሊስ ላይ ከተገልጋዮቹ ሰዎች ትችት ቢቀርብበት የስም ማጥፋት አይሆንም፤ በተጨማሪም ዜጎች ሁሉ የማይገረሰስ ሀሳብን የመግለጽ መብት ስላላቸው፣ የሕዝብ አገልጋይ የሆነው ፖሊስ ስም እንዳይጠፋ ተብሎ ሕገ መንግሥታዊውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መገደብ አይቻልም በማለት የኒው ዮርኩ ፍርድ ቤት በየነ፤ ፍርድ ቤቱ በብይኑ ላይ አንድ መሠረታዊ ሀሳብን አስገነዘበ፤ ስም ማጥፋት የሚባለው በተራ ሰው ላይ ወይስ በሕዝብ አገልጋይ ላይ የተፈጸመ መሆኑን መለየት እንደሚያስፈልግ አመለከተ፤ በአገራችንም አጼ ቴዎድሮስ ወንድምዋን የገደሉባት ሴት በሄዱበት ሁሉ እየተከተለች ንጉሠ ነገሥቱን ስትሰድብ፣ በሆነ ባልሆነው ሁሉ ገደል የሚጨምሩትና በእሳት የሚያቃጥሉት ንጉሠ ነገሥት ይቺን በንዴት የተቃጠለች ሴት ምንም አላደረጓትም! አጼ ምኒልክንም አሞካሽቶ ገጣጣ ያላቸው ምንም የደረሰበት አይመስለኝም፤–
በሰማይ የሚጠድቅ በምድር ያስታውቃል፤
ከከንፈሩ ተርፎ ጥርሱ ጣይ ይሞቃል፤
በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በያመቱ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ ንጉሠ ነገሥቱ በግጥምም በመፈክርም በጣም ይሰደቡ ነበር፤ አንድም ተማሪ በስም ማጥፋት ሲከሰስ አላየሁም፤ በሌላ መንገድ ቀጥተዋቸው እንደሆነም አላውቅም፤ ግን ብዙዎቹ ተመርቀዋል።
ከላይ የተገለጹት ሁሉ ስለግለሰቦች ነው፤ ሕጉ በግለሰቦች ላይም ቢሆን በኒው ዮርኩ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዳየነው፣ በኢትዮጵያም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 612 የማያስቀጡ ትችቶችና ንግግሮች በሚል ርእስ ስር ተደንግጓል፤ በኒው ዮርኩ ፍርድ ቤት የምንገነዘበው የከሳሹን የመክሰስ መብት የሚገድብ ሲሆን፣ በወንጀለኛ መቅጫው ሕግ ደግሞ የምንገነዘበው ሊከሰስ የታሰበውን ተከሳሽ ያለመከሰስ መብት የሚገልጽ ነው፤ ሁሉም በግለሰብ ደረጃ መሆኑን ልብ እንበል።
የመንግሥትን ስም ማጥፋት የሚባል የሌለ ነገር ነው፤ ካለማወቅ የመጣ የሥልጣን ድፍረት ነው፤ ከላይ እንደተገለጸው በስም ማጥፋት ክስ ለመመሥረት ከስምም የገነነ ስም ያስፈልጋል፤ መንግሥት ምን ስም አለውና ስሙ ይጠፋል? የአጼ ኃይለ ሥላሴ ስም ይጠፋል፤ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ስም ይጠፋል፤ የመለስ ዜናዊ ስም ይጠፋል፤ የመንግሥት ስም የሚጠፋው እንዴት ነው? ሦስቱም የተጠቀሱት ስሞች በአለፉት ሰባና ሰማንያ ዓመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተከታታይ የሚያያይዛቸው ሁኔታ ነበረ፤ ወይም ባህላዊ የፈረስ ስም እየሰጠናቸው ብንሄድ አባ ጠቅል፣ አባ ገልብጥና አባ ሰንጥቅ ልንላቸው አንችል ይሆናል፤ ፈረሱ አንድ ነው፤ ጋላቢዎቹ የተለያዩ በመሆናቸው እያንዳንዳቸው እንደየፍላጎታቸው ወይም እንደየተግባራቸው ለጋላቢዎቹ የወጣላቸው ስም ይለያያል፤ አባ ገልብጥ ከርፋፋ ነው ብንል በስም ማጥፋት ለመክሰስ የሚችለው ጋላቢው ነው ወይስ ፈረሱ? አባ ሰንጥቅ ተንጋሎ የተፋ ለራሱ ከፋ አንደሚባለው ያለ ጅልነት ያለበት ነው ብንል ከሳሹ ማን ሊሆን ነው?
ሕግን የጭቆና መሣሪያ ማድረግ የተጀመረው በወያኔ ዘመን ነው፤ ዓይን ባወጣ ውሸት ‹‹ሕገ መንግሥቱን ሕገ አራዊት በሏል›› በማለት ፍርድ ቤትን አሳምኖ (ለፍርድ ቤት አስረድቶ አይደለም) በሐሰት ማስፈረድ የተቻለው በወያኔ ዘመን ነው፤ ሕጋዊ የፖሊቲካ ፓርቲ ስብሰባዎችን ‹‹መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ መዶለት›› ተብሎ እንደማስረጃ በግልጽ የተሠራውን ቪዲዮ ለፍርድ ቤት አቅርቦ ማሳመንና ማስፈረድ የተቻለው በወያኔ ዘመን ነው፤ በሰላማዊና ሕጋዊ የፖሊቲካ ትግል መንግሥትን ለመለወጥ መሞከር መንግሥትን በኃይል እንደመገልበጥ ተደርጎ የታየውና ክስ የተመሠረተበት በወያኔ ዘመን ነው።
አንድ ነገር በጋዜጣ ተጽፎ አደባባይ ሲወጣ ከሦስት ነገሮች አንዱ ወይም ሁሉም ይከሰታሉ፤ አንዱ የተጻፈው ሐሰት ነገር ሊሆን ይችላል፤ ሁለተኛ አስተያየቱ የማይወደድ፣ ብዙ ሰዎች የማይቀበሉት ይሆናል፤ ሊሆን ይችላል፤ ሦስተኛ አንድ ግለሰብን በሰብእናው ወይም በሥራው የሚጎዳ ሊሆን ይችላል፤ እንግዲህ የተባለው ነገር ሐሰት ከሆነና ሐሰት ነው የሚለው ሰው እውነትን ይዞ ከሆነ ሐሰትን ለማጋለጥ ከባድ አይሆንም፤ ሐሰቱን ከእውነቱ ጋር አጋፍጦ ቀልጦ እንዲጠፋና እውነቱ ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ ነው፤ ትክክለኛ ዳኛ ካገኙ እውነትና ሐሰት በማስረጃ ይሸናነፋሉ፤ እውነቱ ከታወቀ በኋላ አደባባይ በወጣው ሐሰት ጉዳት ደርሶብኛል የሚለው ተራ ዜጋ ከሆነ ካሣ የመጠየቅ መብት ይኖረዋል፤ የሕዝብ አገልጋይ ከሆነ ግን ሆን ተብሎ ለመጉዳት በክፋት እንደተጻፈበት ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል፤ አንደኛው በዚህ ያልቃል።
ሁለተኛው የተነገረውን ወይም የተጻፈውን የአንድ ሰው አስተያየት በሕግ ወይም በግድ ማስለወጥ አይቻልም፤ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የግል አስተያቱን ወይም እምነቱን ለገለጸው ሰው ይመክትለታል፤ የእኔ አስተያየት ከአንተ አስተያየት ወይም የእኔ እምነት ከአንተ እምነት ይሻላል ብሎ በሕግ ክርክር ለማሸነፍ አይቻልም፤ ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት ሚል የሚባል የእንግሊዝ ፈላስፋ እንዳለው የዓለም ሕዝብ በሙሉ ተሰብስቦ አንዱን ሰው አስተያየትህ ወይም እምነትህ ትክክል አይደለም ብሎ ሊረታው አይችልም።
ሦስተኛ የተባለው ነገር ግለሰብን በሰብእናው ወይም በሥራው ግልጽ በሆነ መንገድ ከጎዳውና ጉዳቱ ከተረጋገጠ፣ የተባለው ጎጂ ነገር በአደባባይ የተነገረው ሆን ተብሎ ለመጉዳት መሆኑ፣ ወይም ባለማወቅ፣ ወይም በስሕተት መሆኑ ተለይቶ መረጋገጥ አለበት፤ ካሣውም ሆነ የወንጀል ጥፋቱ ከዚያ በኋላ የሚወሰን ይሆናል።
ይህንን ሁሉ ከአልን በኋላ የመንግሥትን ስም ማጥፋት ወደሚለው ስንመለስ ከባድ የአስተሳሰብ ችግር ይገጥመናል፤ መንግሥት ከሕዝብ የተለየ ህልውና እንደሌለው አያከራክርም፤ በአንድ መንግሥት ስር የሚተዳደረው እያንዳንዱ ሰው ወደደም አልወደደም፣ ተቀበለውም አልተቀበለውም በዚያ መንግሥት ስር በመሆኑ የመንግሥቱ አካል ነው፤ ባዕድ አይደለም፤ ስለዚህም ግለሰቡ በመንግሥት ላይ የሚያቀርበው ነቀፌታም ሆነ ሐተታ ጉዳት ያስከትላል የሚባለው ለማን ነው፤ አገር የሚባለው ውስጥ ግለሰቡ አለ፤ ሕዝብ የሚባለው ውስጥ ግለሰቡ አለ፤ መንግሥት የሚባለው ውስጥ ግለሰቡ አለ፤ ስለዚህም የመንግሥትን አመራር የሚነቅፈው ግለሰብ የመንግሥትን ስም አጠፋ ማለት ድርብርብ ስሕተቶችን ያሳያል፤ በመጀመሪያ ነገር መንግሥት ከግለሰቡ የተለየ ህልውናም ሆነ ስም እንደሌለው አለመገንዘብ ነው፤ ሁለተኛም ግለሰቡ መንግሥትን፣ ሕዝብን፣ አገርን ከዚህም ሁሉ ጋር ራሱን ለማሻሻል በበጎ ፈቃድ ለበጎ ዓላማ የሚፈጽመውን ተግባር ወደክፋት መለወጥ አግባብ የለውም፤ ሦስተኛ የመንግሥት ስም ማጥፋት ብሎ ክስ መመሥረት አንድ መንግሥትን ዘለዓለማዊ አድርጎ በመገመት ክፉ ስሕተት መፈጸም ነው፤ በደርግ ዘመን የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ይሰደብ ነበር፣ ዛሬ ደግሞ በወያኔ ዘመን የአጼ ኃይለ ሥላሴና የደርግ አገዛዞች ይሰደባሉ፤ መንግሥት ዘለዓለማዊ አይደለም፤ ባለመሆኑም ይወቀሳል፤ ይነቀፋል፤ ይለወጣል፤ ይህንን ማድረግ የመንግሥት ባለቤት የሆኑት ዜጎች መብትና ሥልጣን ነው።
የመንግሥትን ስም ማጥፋት የሚለው የስጋት መግለጫ ዘዴ የአምባ-ገነን አገዛዞችና ሎሌዎቻቸው የሚያቀነቅኑት ማታለያና ማደናገሪያ ነው እንጂ ሕጋዊ መሠረት የለውም፤በማኅበራዊ ጉዳይ የእውነት ምንጩ ሕዝብ እንጂ መንግሥት አይደለም።
ግለሰቡ ራሱን ለመጉዳት አስቦ ጉዳት የሚያደርሰው በራሱ ላይ ነው ማለት ዋናውን ዓላማ መሳት ነው።
ምንጭ፡ http://ecadforum.com/Amharic/
No comments:
Post a Comment