ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት)
የተሰጠ መግለጫ
--------------------------------------------------------------
ፓርቲያችን አንድነት ህጋዊና ሰላማዊ መንገድ የሚታገል ፓርቲ በመሆኑ የሚያደርጋቸውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ኃላፊነት በተሞላበት ህጋዊ አግባብ ሲተገብር ቆይቷል፡፡ ፓርቲያችን “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት/Millions of voices for freedom” በሚል መሪ ቃል የጀመረውም ህዝባዊ ንቅናቄ የህዝባችንን መሰረታዊ ጥያቄዎችን ያነገበ ነው፡፡
የአንድነት ፓርቲ ህዝባዊ ንቅናቄ አካል የሆኑ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች በሚካሄዱባቸው ከተሞችም ስለሰልፉ ማወቅ ለሚገባቸው መንግስታዊ አካላት ህጉ በሚጠይቀው መሰረት በወቅቱ አስፈላጊው የማሳወቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ ተወጥቷል፡፡ የኢህአዴግን መንግስት አንድነት ፓርቲ የጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ ታላቅ ህዝባዊ ድጋፍ ማግኘቱ አስደንግጦታል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በየክልሉ ያሉ የመንግስት መዋቅሮችን በተለይም የፀጥታውን ዘርፍ በመጠቀም ህዝባዊ ንቅናቄያችንን በህገወጥ መንገድ ለማደናቀፍ መንቀሳቀሱ ነው፡፡
ፓርቲያችን ሰኔ 30 ቀን 2005 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ለማደረግ ቢያቅድም መንግስት የሰልፉ ቀን እንዲተላለፍለት አሳማኝ ጥያቄ በማቅረቡና ይህንንም ህግ ስለሚፈቅድለት ሰልፉን ለሐምሌ 7 , 2005 ዓ.ም አስተላልፏል፡፡ ኢህአዴግ ግን በአንፃሩ በጎንደር ከተማና በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ 9 የአንድነት ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን በህገወጥ መንገድ እንዲታሰሩ አድርጓል፤እነዚህ አባላት እስከ አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ወደ ሐምሌ 7 የተላለፈውን ሰልፍም ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡
አንድነት የሰጣቸውን የቅስቀሳ ተልዕኮ በመወጣት ላይ ያሉ አመራሮችንና አባላትን የማዋከብና የማገት ተግባር ተፈፅሟል፡፡ በተለይም አርብ ሐምሌ 5 ቀን 2005 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በመክበብ በርካታ አባላት የታገቱ ሲሆን ፖሊሶችም ከህግ አስከባሪ አካል በማይጠበቅ ሁኔታ ከፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ባልደረባ ላይ ካሜራ ነጥቀዋል፡፡ የኢህአዴግ ካድሬዎችና የመንግስት ሰራተኞች የጎንደር ነዋሪ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ እንዳይሳተፍ ቤት ለቤት በመዞር ቀስቅሰዋል፡፡
በደሴና በሀይቅ ከተሞችም የአንድነት አመራሮች በተደጋጋሚ እገታ የፈተፀመባቸው ሲሆን የትራፊክ ፖሊሶችም መደበኛ ስራቸውን በማቆም በመኪና የሚደረገውን ቅስቀሳ በተደጋጋሚ አደናቅፈዋል፡፡
የኢህአዴግ ካድሬዎችና የመንግስት ሰራተኞች የደሴ ነዋሪ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ እንዳይሳተፍ ቤት ለቤት በመዞር ቀስቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም በድንገት የስፖርት ዝግጅት እንዳለ በማወጅ ወጣቶችና የከተማው ነዋሪ በሰልፉ ላይ እንዳይሳተፉ ለማከላከል እየተሞከረ ይገኛል፡፡ በደሴ ከተማ የተለጠፉ ፖስተሮችን የመቅደድና በጭቃ የማበላሸት ድርጊትም ተፈፅሟል፡፡
ኢህአዴግ በጎንደርና በደሴ የሚደረገውን የቅስቀሳ ስራ በማደናቀፍ ሰልፉ እንዳይካሄድ ቢሞክርም የከተሞቹ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ከአንድነት አመራሮችና አባሎቸ ጎን በመቆም ቆራጥነታቸውን ማሳየታቸውን እናደንቃለን፡፡
አንድነት ይህን ሁሉ የኢህአዴግን ህገወጥ እርምጃ ተቋቁሞ በነገው እለት በጎንደርና በደሴ ከተሞች የጠራቸውን ታላቅ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች በቆራጥነት ለማካሄድ በያዘው አቋም ፀንቷል ፡፡ በመሆኑም መላው የጎንደርና የአካባቢው እንዲሁም የደሴና የአካባቢው ነዋሪዎች እስከአሁን እያሳዩ ባሉት ቆራጥ ፀንተው በነገው እለት በሚደረጉት ሰልፎች ላይ እንዲሳተፉ አንድነት ፓርቲ በድጋሚ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ በሁለቱም ከተሞች ለሰላማዊ ሰልፍ የሚወጡ ነዋሪዎች አበባና ሌሎች ወዳጅነትን የሚያንፀባርቁ ስጦታዎችን በየመንገዱ ለሚያገኟቸው ፖሊሶችና የፀጥታ አስከባሪዎች እንዲያበረከረቱና ወዳጃዊ ሰላምታ እንዲሰጡ እንጠይቃለን፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment