Tuesday, July 9, 2013

አዎ! ኢትዮዽያዊ ስሜት ይኑረን

አዎ! ብዙ ችግሮች አሉን። የትግላችን ዓላማም እነዚህ ዘርፈ ብዙ ችግሮች (በተወሰነ መልኩም ቢሆን) መመለስ ላይ ያተኩራል። አብዛኞቹ ችግሮቻችን በተናጠል የሚመለሱ አይደሉም። እናም ችግሮቻችንን ለማቃለል ሕብረታችን ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ሕብረታችን የአንድነታችን ምሶሶ መሆን አለበት። አንድነታችንም የእኩልነታችን መሰረት መሆን አለበት።

እኩልነታችን በየራሳችን እሴቶች መመስረት አለበት። የየራሳችን እሴት ሳይኖረን የጋራ እሴት ሊኖረን አይችልም። የየግላችን ሰፈር ወይ ጎጥ ሳይኖረን የጋራ ሀገር ሊኖረን አይችልም። ምክንያቱም ሀገር የየራሳችን የግል እሴት፣ ጎጥ ምናምን ድምር ዉጤት ነው።

ግን ችግሮቻችን ለማሸነፍ በእኩልነት የተመሰረተ አንድነት ያስፈልገናል። ስለዚህ እላቸዋለሁ፤ ኢትዮዽያዊ ስሜት ይኑረን። ይህ ማለት ግን የየግላችን እሴት ወይ አስተሳሰብ አሸቀንጥረን መጣል አለብን ማለት አይደለም።


ዜጎች የፈለጉትን አስተሳሰብ ይዘው ነው ኢትዮዽያዊ መሆን የሚችሉት። ኢትዮዽያዊ ስሜት ማዳበር የምንችለው ሁሉም ኢትዮዽያዊ ሰው በየምርጫው እንዲኖር ስንፈቅድለት ብቻ ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው 'ኢትዮዽያዊ ስሜት የለውም' ብለን ያሰብነው ሰው በማግለል አይደለም። ይህንን የአንድነት መንገድ የተሳሳተ ነው። ምክንያቱም ሰዎች እንደየአስተሳሰባቸው በነፃነት እንዲኖሩ ካልፈቀድንላቸው ሀገራዊ ስሜት እስርቤት ይሆንባቸዋል። ማናችንም እስርቤት አንመርጥም።

ስለዚህ ኢትዮዽያዊ ስሜት ይኑረን። ግን ኢትዮዽያዊ ለመሆን የራሳችሁን ማንነት አትጣሉ። የኔ ፍላጎት ማንነታቹ ኢትዮዽያዊ እንዲሆን ነው። ምክንያቱም የየራሳችን ማንነትም ቢሆን ኢትዮዽያዊ ማንነት ነው ብዬ ስለማምን ነው። ከዚህ የተለየ አመለካከት ብታራምዱም ያው ኢትዮዽያዊነታችሁ አልክድም። የተለያየ አመለካከት ይዘን ኢትዮዽያዊ መሆን እንችላለንና።

ኢትዮዽያዊ ነኝ። ስለ ኢትዮዽያዊነት ያለኝ አለመካከት ግን ከናንተ ሊለይ ይችላል። ኢትዮዽያዊ ለመሆን የተለያየ አመለካከት ማራመድ ፀጋ እንጂ ፈተና አይደለም። ለሀገር አንድነት ፈተና የሚሆነው የተለያየ ሓሳብ መያዝ ሳይሆን ለተለያዩ አመለካከቶች የምንሰጠው ጤናማ ያልሆነ የማጥላላት ተግባር ነው።

ስለዚህ ልዩነታችን ይዘን ኢትዮዽያዊ ስሜት ይኑረን።

It is so!!!

በአብርሃ ደስታ

No comments:

Post a Comment