Saturday, July 27, 2013

ባለስልጣናቱ ከባለሀብት ጋር ያቋቋሙት የንግድ ድርጅት እየተመረመረ ነው

የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራ ቡድን፤ በእነ ዳዊት ኢትዮጵያ መዝገብ ስር ተጠቃለው የሚገኙት ከፍተኛ ባለሀብቱ አቶ ማሞ ኪሮስ በሌላ መዝገብ ተጠርጥረው ከሚገኙ የጉምሩክና ገቢዎች ባለስልጣን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባቋቋሙት “ልማት ለእድገት” የተባለ ድርጅት ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገለፀ፡፡ ድርጅቱን የሚገምት የባለሙያዎች ቡድንም ተቋቁሟል፡፡ አቶ ማሞ በስራ አስኪያጅነት ይመሩታል የተባለው ይህ ድርጅት በተለያየ ጊዜ ከህግ አግባብ ውጪ እቃዎችን ከውጭ ሀገር ያስገባ እንደነበር ለፍርድ ቤት ያስረዳው የምርመራ ቡድኑ፤ እስካሁን ይህን የሚያስረዱ ሰነዶች መሰባሰባቸውንና 4 ምስክሮች መቆጠራቸውን ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት አመልክቷል፡፡ በእኚሁ ባለሀብት በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል የተባሉ 22 ኮንቴነር እቃዎች ሞጆ በሚገኘው ደረቅ ወደብ ተይዘው ምርመራ እየተከናወነ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

ከትላንት በስቲያ በዚሁ መዝገብ ስር የሚገኙትን የጉምሩክ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም ባለሀብቶችን ጉዳይ ችሎቱ የተመለከተ ሲሆን የምርመራ ቡድኑም ቀደም ሲል በተሰጠው የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውንና ይቀሩኛል ያላቸውን ስራዎች በዝርዝር በመግለጽ፣ ለ7ኛ ጊዜ የጠየቀው የምርመራ ጊዜ ተፈቅዶለታል፡፡ በዚህ መዝገብ ከአቶ ማሞ ኪሮስ በተጨማሪ አቶ ዳዊት ኢትዮጵያ፣ አቶ ማሞ አብዱ፣ አቶ አሸብር ተሰማ፣ ፍፁም ገ/መድህን፣ እንዲሁም አቶ አበበለኝ ተስፋዬ የተካተቱ ሲሆን በተጠርጣሪዎቹ ላይ የምርመራ ቡድኑ በተሰጠው የ10 ቀን ጊዜ ውስጥ ከታክስና ቀረጥ ስወራ ጋር በተያያዘ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ ሰነድ ተሰባስቧል፣ በ3 ኩባንያዎች ላይ የሚደረገው የኦዲት ስራም ተጠናቋል፡፡

በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አድርጐ መያዝ በሚለው በአቶ አሸብር ተሰማ ላይ የሰው ማስረጃ እየተሰባሰበና ክትትል እየተደረገ ነው፣ ምንጩ ያልታወቀ ሃብትን በተመለከተ በአቶ ዳዊት ኢትዮጵያ፣ በአቶ ማሞ አብዱ፣ በአቶ አሸብር ተሰማ እና በአቶ አበበልኝ ተስፋዬ ላይ ከክ/ከተሞች፣ ከባንክ፣ ከትራንስፖርት ቢሮዎች እንዲሁም ከክልሎች ማስረጃ ተሰባስቧል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል የምርመራ ቡድኑ በዚህ መዝገብ ይቀሩኛል ብሎ የ14 ቀን ቀጠሮ የጠየቀባቸው ስራዎች፡- የቀሪ ሁለት ኩባንያዎችን ኦዲት ማጠናቀቅ፣ የታክስ ልዩነት በመፍጠር እቃዎችን አስገብተዋል በተባሉት ላይ የዘጠኝ ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ በአቶ ማሞ ኪሮስ እና በባለስልጣናቱ ተቋቋመ ከተባለው ድርጅት ጋር በተያያዘ ተጨማሪ 5 ምስክሮችን ቃል መቀበልና ንብረቱን በባለሙያ አስገምቶ ሪፖርቱን መቀበል፣ የባለሙያ ምስክርነት ቃል መቀበል፣ በህገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መያዝን በተመለከተ ከአዋሣና ጐንደር የንብረት ግምት ሪፖርትና የምስክር ቃል ተጠናቆ እንዲመጣ መከታተል የሚሉት ናቸው። በመርማሪ ቡድኑ ሪፖርት ላይም ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት ያቀረቡት መከራከሪያ እንዲመዘገብላቸው በመጠየቅና የየግል ምክንያታቸውን በማቅረብ፣ የዋስትና መብታችን ተከብሮ ጉዳያችንን በውጭ ሆነን እንድንከታተል ይፈቀድልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የመርማሪ ቡድኑም በሰጠው ምላሽ፤ በሪፖርቱ እንደተገለፀው ቀሪ የምርመራ ስራዎች ስላሉ፣ ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ ያላቸውን ስልጣንና ሃብት በመጠቀም ምስክሮችና ሊያባብሉ፣ ሰነዶችን ሊያሸሹ ይችላሉ በዚህም ፍትህ ሊጓደል ይችላል በሚል የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል፡፡


የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ሲያደምጥ የቆየው ችሎቱም፤ የመርማሪ ቡድኑ ቀሪ ስራዎች እንዳሉት በመገንዘብ፣ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ከተጠየቀው የ14 ቀን ቀጠሮ ውስጥ 10 ቀን በመፍቀድ መዝገቡን ለሐምሌ 29ቀን2005 ቀጥሯል፡፡ በተጨማሪም ምርመራው በተገቢ ፍጥነትና ጥራት እንዲከናወን ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በእለቱ ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ አምባው ሰገድ አብርሃን መዝገብ 12 ተጠርጣሪዎች የተካተቱበት ተመልክቷል- አቶ አምባው ሰገድ አብርሃ፣ ተክለአብ ዘረአብሩክ፣ ያደሳ ሚደቅሳ፣ እሸቱ ግረፍ፣ ጌታሁን ቱጂ፣ መላኩ ግርማ፣ አስፋው ስዩም፣ ጌታነህ ግደይ፣ ዮሴፍ አዲዮ፣ በእግዚአብሔር አለበል፣ ዘለቀ ልየው እና መሐመድ ሃሰን ፡፡ የምርመራ ቡድኑ በዚህ መዝገብ በተጠረጠሩት ላይ በተሰጠው 10 ቀን ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት የዘረዘረ ሲሆን ለጠቋሚ የሚከፈልን አበል ለራስ በማድረግ የተጠረጠሩት አቶ አምባው ሰገድ አድራሻ ላይ የሚመሰክሩ ግለሰቦች አድራሻ መገኘቱን፤ ሞጆ፣ አዳማ፣ ድሬደዋ፣ ሚሌ የተላከው የምርመራ ቡድን እንደቅደም ተከተላቸው ከ2-8 እንዲሁም በ11ኛ ተጠርጣሪዎች ላይ ሰነዶች መሰብሰቡን፣ በአዋሽ መቅረጫ ጣቢያ በህገወጥ መንገድ ሲገቡ የተያዙ ካሜራዎችን በተመለከተ በአቶ እሸቱ ግረፍ እና በአቶ አስፋው ስዩም ላይ የሰነድ ማስረጃዎች መሰብሰባቸውን፣፣ ተገቢው ቀረጥ ሳይከፈልባቸው የገቡ እቃዎችን በተመለከተ የ3 ኩባንያዎች ኦዲት መጠናቀቁን፣ በድሬደዋ የተያዙ የኮንትሮባንድ ንብረቶችን ተመሳጥሮ መሸጥን በተመለከተ ጉዳዩ በሚመለከታቸው በአቶ ጌታሁን ቱጂ እና መሐመድ ሃሰን ላይ መረጃ ተሰባስቦ የምስክሮች ቃል መቀበሉን፣ በቦሌ በኩል በህገወጥ መንገድ የገቡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በተመለከተ በአቶ ዘለቀ ልየው ላይ የ1 ምስክር ቃል ማግኘቱን፣ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ይዞ መገኘትን በተመለከተ ከክፍለከተሞች ባንኮችና ክልሎች እንዲሁም ከትራንስፖርት ቢሮዎች ሰነድ መሰብሰቡንና ንብረታቸው ላይ ለመድረስም ክትትል እየተደረገ መሆንኑ ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የሚቀሩ ስራዎች ተብለው በመርማሪ ቡድኑ የተዘረዘሩት የጠቋሚ አበልን ለራስ አድርጐ መጠቀምን በተመለከተ በአቶ አምባው ሰገድ ላይ የ5 ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ምንጩ ያልታወቀ ሃብትን የዋጋ ግምት ማውጣት፣ ከቀረጥ ስወራ ጋር በተያያዙ ደጋፊ ሰነድ ማስረጃ ማቅረብና የ2 ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ የኦዲት ምርመራ ደጋፊ ሰነድ ማቅረብ እና የ2 ኩባንያዎችን ኦዲት ማጠናቀቅ፣ የቀረጥ ልዩነት መፍጠር በሚለው የ9 ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ በድሬደዋ የተያዙ ኮንትሮባንድ ንብረቶችን በተመለከተ የምስክሮችን ቃል መቀበል እና ክትትል ማድረግ፣ በቦሌ የገቡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በተመለከተ የ2 ምስክሮች ቃል መቀበል የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህን ቀሪ ስራዎች ለማከናወንም መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ የ14 ቀን ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ተጠርጣሪዎችና ጠበቆች በበኩላቸው፤ ተመሳሳይ የምርመራ ሪፖርቶች ናቸው የሚቀርቡት፣ የሚፈለጉት ሰነዶች በሙሉ ተሰባስበዋል የሚሉና ሌሎች የየግል ምክንያቶቻቸውን አቅርበው ጉዳያቸውን በዋስ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ የመርማሪ ቡድኑ በበኩሉ፤ በሰጠው ምላሽ የሚከናወኑት የምርመራ ስራዎች ተከታታይነት ያላቸው ናቸው፣ ቡድኑም በአግባቡ ጊዜውን እየተጠቀመ እየሰራ ነው፣ ተጠርጣሪዎች በዚህ ሁኔታ በዋስ ቢለቀቁ ምስክሮችን በማባበል፣ ማስረጃዎችን በመወሰር የፍትህ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈጥሩ ስለሚችሉ የዋስ መብታቸውን እቃወማለሁ ብሏል፡፡ የግራ ቀኝ የቃል ክርክሩን ሲያዳምጥ የቆየው ችሎቱም፤ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የምርመራ ስራው በተገቢው መንገድ ያከናውን ዘንድ የ10 ቀን ቀጠሮ ፈቅዶ መዝገቡን ለሐምሌ 29ቀን2005ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

ምንጭ፡ አዲስ አድማስ

No comments:

Post a Comment