የጉናው ሰው!!
አንዱዓለም አራጌ ማነው? ለሚለው ጥያቄ ላንባቢያንና ለውጥ ለማምጣት ለሚታገልለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሕይወት ታሪኩ ትንሽ ጨለፍ አድርገን ለመፈንጠቅ እንሞክራለን ወደ ፊት እንደ አስፈላጊነቱና እንደ አግባብነቱ በስፋትና በጥልቀት እናቀርባለን፡፡
የትውልድ አካባቢና የልጅነት ጊዜ
አቶ አንዱዓለም አራጌ በጎንደር ክ/ሀገር በደብረታቦር አውራጃ በፋርጣ ወረዳ ጉና ተራራ ሥር ወይንም ግርጌ ክምር ድንጋይ ከተባለ ቦታ በ65 ዓ.ም ጥቅምት 25 ቀን ተወለደ፡፡ የኢትዮጵያ አብዮት ሊፈነዳ ሁለት ዓመት ሲቀረው በምጥ ዋዜማ ማለት ነው፡፡ “ሰው አካባቢውን ይመስላል” እንደሚባለው አንዱዓለም አራጌ በክ/ሀገሩ ከራስ ዳሽን ተራራ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃነት ከሚጠቀሰው ጉና ተራራ ስር በመወለዱ ለኢሕአዴግ እንደ ጉና ተራራ ኮርቶና ከብዶ ታይቶታል፡፡ እናም አስሮ በሽብርተኝነት በመወንጀልአሞቱን ያፈሰሰ መስሎታል፡፡ አንዱዓለም አራጌ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ አይደለም፡፡ ለምንም ነገር የማይበገር፣ ችግር የማይፈታው፣ ለቆመለት ዓላማ ወደ ኋላ የማይል፣ ከሁሉም በላይ ቅጥፈትንና እብለትን አጥብቆ ይጠየፋል፡፡ ባጭሩ ትክለ ሰውነቱ ወይንም ስብእናው በቁም ነገር የታነፀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለቆመለት ዓላማና ላመነበት ነገር ያላንዳች ይሉኝታና ፍርሃት ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል፡፡ በዚህ አቋሙና ፅናቱም ነው ገና በለጋ እድሜው ሩጦ ሳይጠግብ፣ ሠርቶ ሣይደክም በተደጋጋሚ የእሥር ሰለባ ለመሆን የበቃው፡፡
አንዱዓለም አራጌ አሥራ አንድ ዓመት እስከሚሞላው ድረስ ክምር ድንጋይ ከወላጆቹ ጋር ቆይቷል፡፡ አባቱ የቤተ ክህነት ሰው በመሆናቸው ልጃቸው በፅኑ የግብረገብ ሥነ ምግባር ኮትኩተውና ገርተው ከማሣደጋቸውም በላይ የቤተክህነት ትምህርት እንዲማርላቸው በመሻት ካንድ ከታወቁ መርጌታ ልከውት በተመላላሽነት እየተማረ እንዳለ አዲስ አበባ የሚኖሩ አያቱ ክምር ድንጋይ ይሄዳሉ፡፡ እሳቸውም የቤተክህነት ሰው ነበሩና ንቃቱን፣ ጨዋነቱን፣ ትህትናውንና አርቆ አስተዋይነቱን በዚያች አጭር ጊዜ ቆይታቸው አስተዋሉና “ይኸ ልጅ ዘመናዊ ትምህርት መማር አለበት” ብለው ወደ አዲስ አበባ ይዘውት ይመጣሉ፡፡
ሕይወት በአዲስ አበባ
አንዱዓለም አራጌ ካያቱ ጋር አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ መስከረም መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመግባት ከ1-8ኛ ክፍል ድረስ ሁለት ጊዜ ደብል ወይንም አጥፎ በማለፍ በ6 ዓመት ውስጥ ስምንተኛ ክፍልን አጠናቀቀ፡፡ ዘጠንኛና አሥርኛ ክፍልን የተማረው ኮከበ ጽባህ ሲሆን የደረጃ ተማሪ ስለነበር 11ኛና 12ኛ ክፍልን የተማረውና ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የበቃው በሳንጅ ዮሴፍ ት/ቤት በመማር ነበር፡፡
አንዱዓለም አራጌ በከፍተኛ ውጤት አ.አ.ዩ በመግባት በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታውም በተለያዩ ክበባት በመግባት በኃላፊነትም ሆነ በአባልነት ካንድ ንቁ ተማሪ የሚጠበቅበትን ግዴታ ተወጥቷል፡፡ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በአራት ዓመት ቆይታው የት/ቤት ጓደኞቹ በሚያደርጋቸው ክርክሮችና በአቋሙ ፅናት እጅግ አድርገው ያደንቁት እንደነበር ዛሬ በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ አንዱዓለም አራጌ ከሚታወቅባቸው ቁም ነገሮች መሀከል ባገራችን ገና የሰላማዊ ትግል ፅንስ ሐሳብ በቅጡ ባልታወቀበት ወቅት እሱ ሰለሰላማዊ ትግል ይሰብክ ነበር፡፡ ይህንንም ሲያደርግ የአንጋፋ ሰላማዊ ታጋዮችን አርማ በማንሳትና መርሃቸውን እንደ ምርኩዝ በመጠቀም ነው፡፡ ማርቲን ኪንግ፣ ማንዴላ፣ ማኅተመ ጋንዲን ታሪካቸውን በማጥናትና የሄዱበትን መንገድ በመከተል በዩኒቨርስቲ ቆይታው መርሃቸውን መርሁ በማድረግ የትግል ብቃቱን እንዳዳበረ በቅርብ የሚያውቁት በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡
የአንዱዓለም አራጌ ልዩ ባህሪውና ተሰጥኦው ወይንም ትክለ ሰውነት ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው በሰላማዊ ትግል ገና ከወጣትነቱ ዕድሜው ጀምሮ ቆርቦ እያለ ገዥው ፓርቲ “ሽብር አራማጅ” ብሎ በመወንጀል ጥላሸት ሲቀባው ማየትና መስማት ያለንበትን ዘመንና ሥርዓት ምን ያህል አስጨናቂና አስከፊ እንደሆነ መገመቱ ከባድ አይሆንም፡፡ እያንዳንዳችንም ውለን ስለመግባታችን ዋስትና የለንም፡፡ ሁላችንም የሱ እጣ እንደሚጠብቀንና ጥላሸት እንደምንቀባም በርግጠኝነት መናገር እንችላለን፡፡
የሥራ ዓለም
አንዱዓለም አራጌ ከአ.አ.ዩ ትምህርቱን ጨርሶ ከወጣ በኋላ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ እየተቀጠረ ሠርቷል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የዓለም ባንክና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች መኅበር በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የፖለቲካ ሕይወቱ
አቶ አንዱዓለም አራጌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቆይታው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የፖለቲካ ሀሁን ከመቁጠር ጀምሮ በማዳበር ብስለቱን ያስመስከረ ቢሆንም በድርጅት ውስጥ ታቅፎ መታገል የጀመረው ግን በ1992 ዓ.ም የኢዴፓ መሥራች አባል በመሆን ነበር፡፡ በኢዴፓ ውስጥ በቆየባቸው ዓመታትም ከቋሚ ኮሚቴ አባልነት ጀምሮ ደረጃ በደረጃ አድጎ ም/ዋና ጸሐፊ በመሆን በከፍተኛ ኃላፊነት ሠርቷል፡፡ በመሆኑም በ1997 ዓ.ም ኢዴፓ /ቅንጅትን ወክሎ በተወለደበት ክ/ሀገር ፋርጣ ወረዳ ለተወካዮች ም/ቤት ተወዳድሯልለ፡፡ በምርጫው ውጤት ቅንጅት ቢያሽንፍም ከፍተኛ አመራሩና አባላቱ በተለያዩ እስር ቤቶች ሲታሰሩ እሱም አብሮ ቃልቲ እስር ቤት ለሁለት ዓመታት ቆይቷል፡፡ በሁለት ዓመት ቆይታውም የብረት ግድግዳ በመሆን ፅናቱን አስመስክሯል፡፡ ከእስር ቢለቀቅም ከፖለቲካው ወደ ኋላ አላፈገፈገም፡፡ አንድነት ፓርቲን በመቀላቀል የብሔራዊ ም/ቤትና የሥራ አሥፈፃሚ አባል በመሆን ለዋና ጸሐፊነት ተመርጦ ላንድ ዓመት በቆራጥነት አገልግሏል፡፡ ብቃቱን በማስመስከሩም በም/ሊቀመንበርነት የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ ሆኖ ተመርጦ በማገልገል ላይ እንዳለ ነው ርምጃው ያልጣመው ገዥው ፓርቲ ከግንቦት 7 ጋር በማገናኘት የሽብርተኝነት ጥላሸት በመቀባት መስከረም 3 ቀን 10 ሰዓት ላይ ከመንገድ የታጠቁ ኃይሎች ከመኪና አስወርደው ይዘውት የሄዱት፡፡
የቤተሰብ ሁኔታ
ወጣቱ ፖለቲካኛ አንዱዓለም አራጌ ባለትዳርና የሁለት ህፃናት አባት ነው፡፡ አንዱዓለም አራጌ ትዳር የመሠረተው ከእስር ከተፈታ በኋላ በ2000ዓ.ም ከዶ/ር ሰላም አስቻለው ጋር በሥርዓተ ተክሊል ነው፡፡ እንግዲህ ስለሱ ባጭሩ ይህን ያህል ካልን በመጨረሻ ፍ/ቤት ቀርቦ ቃሉን ሲሰጥ በተናገረው ሀሳባችንን እንቋጫለን “መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአፋና ሥራ እየሠራ ነው፡፡ እኔም አንዱ የዚህ ሰለባ ነኝ፡፡ ፍ/ቤት ነፃ ሆኖ የራሱን ሂደት ያያል የሚል እምነት ስለሌለኝ እስከመጨረሻው የሞት ፍርድ ድረስ ቢደርስብኝም ከመቀበል ሌላ የምከራከረውም ሆነ የምናገረው ነገር የለኝም”
ፍኖተ – ከነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል
አንዱዓለም አራጌ መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም፡፡
No comments:
Post a Comment