አብርሃ ደስታ #Abrha «ኢህአዴግ አንድ ነገር ይችላል» በሚል መነሻ በፌስቡክ ያሰፈረውን ጽሑፍ አነበብኩት፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ አብርሃ በጽሑፉ የነገረን ኢህአዴግ አጀንዳ መቅረፅ እንደሚችልና ይህም ከተቃዋሚዎቹ የተሻለ የፖለቲካ ጥቅም እያስገኘለት እንደሆነ ነው፡፡ ቀጥሎም ተቃዋሚዎቹ አጀንዳ መቅረፅ ላይ ትኩረት አድርግው መስራት እንዳለባቸው ይጠቁማል፡፡
አብርሃ እንደብዙዎቹ ጽሑፎቹ ሁሉ በዚህም ጽሑፍ ሃሳቡን በሚገባና ግልፅ በሆነ መልኩ አቅርቧል፡፡ ሆኖም ግን እሱ እንዳለው ኢህአዴግን በተሳካ ወይም ከተቃዋሚዎቹ በተሻለ አጀንዳ መቅረፅ ይችላል ባለው ሀሳብ አንዳንድ ልዩነቶች እንዳሉኝ መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡
...
ኢህአዴግ አብርሃ እንደጠቀሰው አጀንዳ መቅረፅ ሳይሆን አጀንዳ መንጠቅና ማስቀየስ ላይ የተካነ የፖለቲካ ድርጅት ነው ብየ አስባለሁ፡፡ በተለይ ኢህአዴግ ከምርጫ 97 ጀምሮ ተቃዋሚዎች የሚያነሷቸውን ሀሳቦችና የሚቀርጿቸውን አጀንዳዎች እየተከታተለ ሲነጥቅ አስተውለናል፡፡ ለአብነት የቅርብ ጊዜ አጀንዳዎችን ብቻ እንጥቀስ፡
(1.) ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ባካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ያነሳቸው መሰረታዊ የፖለቲካ፣ የሐይማኖት ነፃነት፣ የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስና በመረጡት ቦታ ሰርተው ሃብት የማፍራት መብትን የተመለከተ፣ የፀረ ሽብር ህጉንና የፖለቲካ እስረኞችን ወዘተ የተመለከቱ ጉዳዮችን አንስቶ የፖለቲካ መነቃቃት ፈጥሮ ነበር፡፡ ወዲያውኑ ኢህአዴግ በህዝቡ ደካማ ጎን ወይም አንገብጋቢ ችግሩ በመነሳት የቤት ምዝገባን ይፋ አደረገ፡፡ በዚህም የአዲስ አበባ ህዝብ ዓይንና ጆሮ የቤት ጉዳይ ላይ አተኮረ፡፡ ኢህአዴግም የተፈጠረውን የፖለቲካ መነቃቃት አስቀየሰ፡፡
(2.) ግብፅ በአባይ ጉዳይ መንግስቷንና የተቃዋሚ ፓርቲዎቿን ጠርታ በአንድ ላይ ተገናኝተው እንዲነጋገሩ አድርጋ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ እንደነ ዶክተር መረራ ጉዲና አይነት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የኛም መንግስት (ኢህአዴግ) ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መነጋገር እንዳለበት ማሳሰብ ጀመሩ፡፡ በተለይ መንግስት ከግብፅ ጋር ለመወያየት መቼም ዝግጁ መሆኑን በሚናገርበት ጊዜ፣ ተቃዋሚዎች መንግስት ከግብፅ ጋር ብቻ ሳይሆን ከኛም ጋር መነጋገር አለበት ሲሉ ማሳሰባቸውን ቀጠሉ፡፡ ኢህአዴግ ግን በኢቴቪ ክርክር ቢጤ አዘጋጅቶ «የአባይ ግድብ የማን ነው?» አይነት ጥያቄ ለተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች በማንሳት የእንነጋገር አጀንዳቸውን አፈርድሜ አበላው፡፡
(3.) የነፃው ፕሬስና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያውያን የስደት ኑሮና የሚደርስባቸውን እንግልት ማጋለጥ ጀምረው ነበር፡፡ መንግስትም አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሲሰጠው ቆየ፡፡ ዜጎች ስንትና ስንት መከራና እንግልት ሲደርስባቸው እያወቀ ለረጂም ጊዜ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የቆየው የኢህአዴግ መንግስት ድንገት ስደትን አጀንዳው አደረገ፡፡ ይህም ራሱ ኢህአዴግ የቀረፀው አጀንዳ ሳይሆን ዘግይቶም ቢሆን ከሌሎች የነጠቀው ነው፡፡ መንግስት ከዳያስፖራው የሚያገኘውን remittance እንጂ ስቃያቸው ግድ እንደማይሰጠው በአረብ ሐገራት የሚኖሩ ዜጎቻችንን ህይወት ማንሳት ይቻላል፡፡
(3.) ኢህአዴግ ከሐገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ሀገራትም ማስቀየሻወችን ይዋሳል፡፡ «የኛን የታላቁ መሪ ራዕይ» ማስቀጠልና እና የሰሜን ኮሪያን «ታላቁ መሪ ስራዎችን ማስቀጠል» ልብ ይሏል፡፡ ኢህአዴግ የመለስ ሞትን ተከትሎ ችግር ይገጥመዋል በሚል ትንታኔ ይሰጡ የነበሩ ሰዎችን ሃሳብ ያስቀየሰው «መሪያችን ሁሉን ነገር ትቶልን ስለሄደ የሚቀየር ነገር የለም፡፡ በእሳቸው ቦይ መፍሰስ ብቻ ነው የኛ ተግባር» እያለ አጀንዳውን ደቁሶታል፡፡
ስለዚህም ኢህአዴግ አጀንዳ ከመቅረፅ ይልቅ አጀንዳ መንጠቅና ማስቀየስ ይችላል፡፡
በበላይ ማናየ
No comments:
Post a Comment