የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ሰባት የምሕንድስና ኃላፊዎች ከትራንስፎርመር ግዥ ጋር በተያያዘ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
ሐምሌ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል የኮርፖሬሽኑ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ማስፋፊያ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላና የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ብርሃኔ ይገኙበታል፡፡
የምሕንድስና ኃላፊዎችና በጨረታ ኮሚቴ ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ከተባሉት ሰባት ኃላፊዎች መካከል አቶ መኮንን ብርሃኔ፣ አቶ ፋሪስ አደምና አቶ ሚሊዮን ማቱሳላ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባካሄደው ምርመራ ሲሆን፣ የምርመራው ጭብጥ የሚያጠነጥነው በ1999 ዓ.ም. በተካሄደ የትራንስፎርመሮች ግዥ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡
በወቅቱ አምስት ሺሕ የሚደርሱ ትራንስፎርመሮች ግዥ ከተፈጸመ በኋላ በግንቦት 2000 ዓ.ም ውል ተፈርሞ ትራንስፎርመሮች አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ትራንስፎርመሮቹ የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ ነው በሚል ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወሳል፡፡
ግዥው የተፈጸመው ኮቡራ ከተባለው የህንድ ኩባንያ ሲሆን፣ ኩባንያው ያቀረባቸው ትራንስፎርመሮች ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው መግባባት ላይ ተደርሶ፣ ለደረሰው ጥፋት ክፍያ እንዲፈጸምና ለሥራ አፈጻጸም ዋስትና ያስያዘው ገንዘብ እንዲወረስ ውሳኔ ተላልፎ ነበር፡፡
ነገር ግን ቀደም ሲል በነበረው ውል የዋስትና ቦንድ እንዲወረስ የሚያደርግ ቅድመ ሁኔታ እንዲቀመጥ ባለመደረጉ ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን እንደቀረ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ የሪፖርተር ምንጮች ግዥው የተፈጸመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ቦርድ ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጪ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን በጥርጣሬ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው መካከል የተወሰኑት ማክሰኞ ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ ረቡዕ ቃላቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የህንዱ ኩባንያ ኮቡራ በወቅቱ በተፈጸመው ጥፋት ምክንያት፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጥቁር መዝገቡ ውስጥ መግባቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ጉዳዩ ከተፈጸመ አምስት ዓመታት ቢሆነውም፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተጭበርብሯል በተባለው ግዥ ዙሪያ ከአንድ ዓመት በላይ ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ፣ በግዥው ተሳታፊ ናቸው ያላቸውን ተጠርጣሪዎች ከለየ በኋላ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ መጀመሩ ታውቋል፡፡
EthiopianReporter
No comments:
Post a Comment