Tuesday, July 9, 2013
ምሁሩን የት ፈልገህ አጣኸው?
የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩበትም የችግሮቹን መነሻዎች ግን በርግጠኝነት ለመናገር ስንቸገር እና መላምት የሆኑ አስተያየቶችን ስንሰጥ እንስተዋላለን:: ከነዚህ አስተያየቶች መካከልም በዘላለም ክብረት የተፃፈ ፅሁፍ በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ አንብበናል:: ዘላለም በፅሁፉ ለመግለፅ የሞከረው የችግሩን መኖር ብቻ ነው:: የችግሩን መነሾ ለመዳሰስ ቢሞክር ኖሮ ፅሁፉን በተወሰነ መልኩ ችግርና መፍትሄ ጠቋሚ ሊያደርገው ይችል ነበር:: ያንን መነሻ በማድረግ የችግሮቹን መንስኤዎች ከማውቀው በመነሳት ለመዳሰስ እሞክራለሁ:: አስቀድሜ ግን ስለትምህርት ስርአቱ ጥቂት ላንሳ:-
የትምህርት ስርአቱ(Education system) ያሉት የትምህርት እርከን እንደሚከተለው የተከፋፈለ ነው::
ሀ) የመጀመሪያ ደረጃ (ከ1ኛ - 8ኛ ክፍል) ይሆንና በ8ኛ ክፍል ክልላዊ መመዘኛ (ፈተና) ይጠናቀቃል::
ለ) መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ (Lower (Junior) Secondary) (ከ9ኛ - 10ኛ ክፍል) ሲሆን በዚህ የትምህርት እርከን ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ቀድሞ በክልላዊ ቋንቋ ሲማሯቸው የነበሩትን ትምህርቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚማሩ ሲሆን በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ ሰፋ እና ጠንከር ያለ ነው:: በዚህ እርከን ውስጥ ያለፉ ተማሪዎች ለማጠናቀቅ ሃገር አቀፍ መመዘኛ ወይም ፈተና ይፈተናሉ::
ሐ) ሁለተኛ ደረጃ (High School)
በዚህየትምህርትእርከንውስጥሁለትየተለያዩአቅጣጫዎችአሉ::
1. የመሰናዶ ትምህርት (ከ11ኛ - 12ኛ ክፍል)
እዚህየምናገኛቸውተማሪዎችበ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና አመርቂ ውጤት ያመጡት ሲሆኑ በድጋሚ እንደምርጫቸው ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ እና ማህበረሰብ ሳይንስ የትምህርት መስኮች ይሰማራሉ:: ይህንን የትምህርት ደረጃ ያጠናቀቁት በድጋሚ ሌላ ሃገር አቀፍ ፈተና ይወስዱና ያለፉት ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመደቡ ያላለፉት ደግሞ ወደሚፈልጉት የትምህርት መስክ (ለምሳሌ ወደ ኮሌጆች ወይም የሙያ ትምህርት) ተሰማርተው ተጨማሪ እውቀት ይዘው ወደስራ ይሰማራሉ::
2. የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ (TVET)
ወደዚህ የትምህርት መስክ የሚሰማሩት ተማሪዎች በ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና አመርቂ ውጤት ያላመጡት/ወይም አምጥተው በፍላጎታቸው የገቡት ሲሆኑ እንደየዝንባሌያቸው ወደሚፈልጉት የሙያ ዘርፍ ገብተው የሙያ ስልጠና ይወስዳሉ::
መ) የዩኒቨርሲቲ ትምህርት(Higher (tertiary) Education)
እዚህ የሚገቡት ተማሪዎች የመሰናዶ ትምህርትን ያጠናቀቁና በተጨማሪ ሌላ ሃገር አቀፍ ፈተና ወስደው አመርቂ ውጤት ያመጡት ናቸው:: በዚህ የትምህርት ደረጃም ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ በየደረጃው እንዲማሩ ይደረጋል::
ይህ እንግዲህ የትምህርት ፖሊሲው የትምህርት እርከኖች አጠቃላይ ይዘት በአጭሩ ነው:: ሙሉው የትምህርት ፖሊሲው በዘላለም ክብረት ፅሁፍ ላይ ስለተያያዘ ማንበብ ይቻላል:: በተያያዘ አፈፃፀሙንም ለአፍታ አጠር አድርገን እንየው::
የትምህርት ፖሊሲውን ለማስፈፀምና ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ አካላት የየራሳቸው ድርሻ አላቸው:: ከነዚህም ውስጥ:-
ሀ) ትምህርት ሚኒስቴር
ለትምህርት ስርአቱ አጋዥ ፍጆታዎችን የማቅረብ፣ ስልጠናዎችን መስጠት/ማሰጠት እና በቅርብ መቆጣጠር እንዲሁም አፈፃፀሙን መገምገም ወይም ማስገምገም፣ የፖሊሲ ግምገማ በማድረግ ማሻሻያ ካስፈለገ ማድረግ/ማስደረግ የዚህ መስሪያ ቤት ትልቁ ድርሻ ነው::
ለ) የክልል፣ ዞን እና ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤቶች
እነዚህ ባለድርሻ አካላት በየእርከኑ ላሉት የትምህርት ስልጠናዎች፣ የመምህራን ምደባዎች፣ የመምህራን እድገት ውሳኔዎች ሃላፊነት ሲኖርባቸው ለትምህርቱ ጥራትና ብቃት በድጋሚ ወሳኝ አካላት ናቸው::
ሐ) የትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን
ለትምህርት ጥራቱ መጓደል ወይም መጨመር ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ:: የመምህራን ክትትል፣ የተማሪዎች ክትትል፣ ከወላጆች ጋር የሚኖርን ግንኙነትና ክትትል በተመለከተ አፈፃፀሙን መገምገም እና አፋጣኝ እርምጃዎችን የመውሰድ ሃላፊነት መወጣት የሚገባቸው ናቸው::
መ) መምህራን
የትምህርት ስርአት የጀርባ አጥንት መምህራኑ ናቸው:: መምህራን በሚያስተምሩት መጠን የትምህርትን ውጤት እንለካለን:: የመምህራን ብቃት ካለም በተዘዋዋሪ የትምህርት ጥራት አለ ማለት ያስደፍራል:: የተማሪዎችም ውጤት በመምህራኑ የማስተማር ብቃት ላይ ያነጣጠረ ይሆናል:: መምህሩ ብቃት እስከሌለው ድረስ የፈለገውን ያህል ጥሩ የሆነ የት/ት ፖሊሲ ወይም አቅርቦት ቢኖር የት/ት ጥራት ሊኖር አይችልም::
ሠ) በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ያለው አስተዳደራዊ አካሄድ ከላይ ከጠቀስኳቸው ጋር በተወሰነ መልኩ ስለሚገናኝ አልፌዋለሁ::
ታዲያ የትምህርት ጥራቱ ለምን አጠያያቂ ሆነ?
የትምህርት ጥራት የለም የሚል አጠቃላይ መደምደሚያ መስጠት እጅግ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው:: ደካማ የሆኑ ተማሪዎች እንዳሉን ሁሉ እጅግ ጠንካራና ምስጉን ተማሪዎችም እንዳሉን መዘንጋት የለብንም:: የሆነሆኖ በሁሉም የትምህርት እርከኖች ላይ ሃሳብ ማንሳት ቢቻልም ለጊዜው ከሁለተኛ ደረጃ አንስቶ ያለውን ለመዳሰስ እንሞክር::
1)የስርዓተ ትምህርቱ ቀረጻ እና አተገባበር
በትምህርት ፖሊሲዉን ንዑስ አንቀፅ 3.1.2. ላይ ሥርዓተ ትምህርት ሲዘጋጅም ሆነ ሲተገበርና ሲገመገም ኀብረተሰቡ በሰፊው የሚሳተፍበት ሥርዓት በመቀየስ በየደረጃው የትምህርት ባለሙያዎችን መምህራንን ቁልፍ የሆኑ የልማትና አገልግሉት ሰጪ ድርጅቶችንና የምርምር ተቋሞችን እንዲሁም ተጠቃሚ ኀብረተሰቡን ባቀፈ ሁኔታ ይከናወናል ይላል:: ነገር ግን ይህ የተተገበረው (ባለኝ መረጃ)በ ቅርቡ ለተደረገው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ላይ ብቻ ነው:: የሚመለከተው የመንግስት አካል የካሪኩሉም ክለሳ ወይም የፖሊሲ ለውጥ ሲደረግ ቢያንስ መምህራንን በስፋት ያካተተ እና በየደረጃው ሰፊ ውይይት የተካሄደበት ቢሆን የተሻለ ይሆናል:: ጥቂት መምህራንን አሳትፎ ብዙሃኑን ያሳተፈ ማለት ስህተት ነው::
2)የፕላዝማ ጉዳይ
መንግስት የትምህርት ፖሊሲዉን ለማስፈፀም ከጀመራቸው ስልቶች ውስጥ አንዱ ትምህርትን ወጥ በሆነ መልኩ በፕላዝማ ቴሌቭዥን አማካኝነት ማስተላለፍ ነው:: መርሃ ግብሩ ሲጀመር መምህሩን እንዲተካው ተደርጎ ሳይሆን መምህሩን እንዲያግዘው አካሄዱም ሃገራዊ ወጥነት እንዲላበስ ታስቦ ነበር:: ነገር ግን በተሳሳተ መንገድ በተሰራጨ አስተሳሰብ ይህ የአፈጻፀም ዘዴ ግቡን እንዳይመታ ተደርጓል:: ለዚህ ተወቃሽ ሊሆኑ የሚችሉት በፖለቲካው መስክ የተሰማሩት የመንግስት ተቃዋሚዎ ችናቸው:: ለፖለቲካ ፍጆታ በሚል የፕላዝማው ትምህርት መምህሩን እንዲተካ ታስቦ እንደተቀየሰ ተደርጎ በመምህራኑ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለማሳደር ተሞክሯል:: በዚህም የተነሳ በርካታ መምህራን ቸልተኛ እንዲሆኑ የራሱን አስተዋፅዖ አድርጓል::
3)ወጥነት የሌለው የመብራት ሃይል አቅርቦት አለመኖር
የፕላዝማው ፕሮግራም ሲዘጋጅ መብራትን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም ቀጣይነቱ እጅግም አጥጋቢ አልሆነም:: በዚህም የተነሳ መብራት ከጠፋ መምህራን ክፍል ትተው እንዲወጡ ተማሪዎችም ሳይማሩ እንዲዉሉ የተደረጉባቸውን ት/ቤቶ ማጣቀስ ይቻላል:: ጀነሬተር የተገጠመላቸውም ቢሆኑ ውጤታማነታቸው የታሰበውን ያህል አልሆነም:: ነገር ግን ፕሮግራሙ ሲቀረፅ ይህን ታሳቢ ያደረግ ሆኖ መብራት በሚጠፋበትም ግዜ መምህሩ የፕላዝማ ፕሮግራሙ ካቆመበት እንዲቀጥል የታለመ ነበር:: ነገር ግን መምህራን ላይ በተፈጠረው የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ በርካታ መምህራን በየቀኑ ሌሰን ፕላን ሳያዘጋጁ እንዲሁም ለትምህርቱ በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ ስለሚመጡ መብራት ሲጠፋ መቀጠል ስለማይችሉ ትምህርቱ ይቋረጣል::
4)የአመራር ብቃት
ይህ ከላዕላይ እስከ ታህታይ ያለውን መንግስታዊ መዋቅር ይመለከታል:: አመራሮች ሲሾሙ ካላቸው ፖለቲካዊ ታማኝነት እንጂ ብቃትን ያገናዘበ እንዲሆን የታለመ አይደለም:: ለዚህ ማሳያ ሊሆን የሚችለው እራሱ ት/ት ሚኒስቴር ሲሆን በውስጡ የያዛቸው ኤክስፐርቶች አብዛኞቹ ማለት በሚያስችል ደረጃ የጅማ እና ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ትምህርት ምሩቃን ናቸው:: ይህ ሊስተካከል የሚገባው ሲሆን በትምህርት አስተዳደር መስክ የተመረቁ ለምሳሌ ያህል የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አስተዳደር ምሩቃን ላይ ያነጣጠረ ምደባ ቢደረግ ለውጥ ማምጣት ይቻል ይሆናል:: መንግስት የራሱን ፖለቲካዊ አቅጣጫ ለማስፈፀም በሚኒስትር ደረጃ የሚፈልጋቸውን ሰዎች አድርጎ ኤክስፐርቶችን ግን በሙያው ብቁ የሆኑትን መመደብ ቢችል ችግሮችን በቀላሉ መቅረፍ ይቻላል:: ይህ በክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ሳይቀር አንገብጋቢ ችግር ሆኖ ይስተዋላል:: የአመራር ብቃት ያላቸው መምህራን በርዕሰ መምህርነት ቢመደቡ፣ የተሻለ ብቃት ላስመዘገቡ ምስጋና ቢቸራቸው ውጤታማነቱን ማሳደግ ይቻላል:: ከላይ እንዳልኩት እነዚህ ነገሮችም በከፊል በከፈተኛ ት/ት ዘርፍም ይታያሉ:: ለምሳሌ የሃይል አቅርቦት፣ አመራርን በተመለከተ::
5)የተማሪዎች ቸልተኝነት
ይህ ችግር በየእርከኑ ባሉ በርካታ ተማሪዎች ላይ ይታያል:: ከጥቂት ተማሪዎች በስተቀር ቤተ-መፅሃፍትን አዘውትሮ የመጠቀም፣ የትምህርት ግዜን በአግባቡ የመጠቀም ዝንባሌም ከግዜ ወደ ግዜ እየቀነሰ እንደመጣ ለመረዳት ሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤቶችን ወይም ዩኒቨርሲቲዎችን ማየት ይቻላል:: የከፍተኛ ት/ቱ እንዳለ ሆኖ በየእርከኑ የሚወጡ ተማሪዎችን በተመለከተ በት/ት ፖሊሲዉ ንዑስ አንቀፅ 3.2.8. ላይ እንደተመለከተው ከየሳይክሉ የሚወጡ ተማሪዎች አስፈላጊዉን የሙያ ስልጠና የሚወስዱባቸው ተቋማት እንዲኖሩ እንደሚደረግ ይገልፃል:: በየደረጃውም ከአንደኛ ደረጃ የሚወጡ ተማሪዎች እንደየእድሜያቸው ስልጠና ወስደው ወደ ግብርና፣ እደ-ጥበብና ኮንስትራክሽን በጀማሪ ባለሙያነት እንዲሰማሩ እንደሚደረግና የሌሎቹንም እርከኖች በተመሳሳይ ይገልፀዋል:: ነገር ግን የማሰልጠኛ ተቋማቱ ቁጥር አነስተኛ ከመሆናቸው በተጨማሪ ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ወደ ተጠቀሱት የሙያ ዘርፎች ለመሰማራት ያላቸው ተነሳሽነት እጅግ አናሳ ነው::
እንግዲህ ከላይ ባሉት እና ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች ውስጥ ያለፉት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ሊኖራቸው የሚችለውም ተፎካካሪነት እጅግ አጠያያቂይ ሆናል:: አሁን አሁን እያስተዋልን እንዳለነው ይህ ችግር ስማቸውን እንኳ አስተካክሎ ለመፃፍ የሚቸገሩ ተማሪዎች እንዲኖሩን እያደረገ ይገኛል:: የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የራሱ የሆነ ድርሻ ቢኖረውም ዋነኛ አላማው ግን ተማሪውን ቀጣይ ለሚሰማራበት የስራ መስክ ብቁ የማድረግ እንጂ ከታች መማር የሚገባዉን ትምህርት ማስተማር አይደለም:: ከስር ጀምሮ እየተበላሸ የመጣው ትውልድ ሲመረቅ ለሚያሳየው ድክመት ዩኒቨሪሲቲዎች ተጠያቂ ሲሆኑም እናስተዉላለን:: ነገር ግን ተጠያቂነቱ በከፊል እንዳለ ሆኖ ትልቁ ድርሻ ያለው ግን ከታች ባሉት የት/ት እርከኖች ላይ ነው:: የስምን አጻጻፍ ዩኒቨርሲቲ እንዲማር መጠበቅ የዋህነትም ነው::
ተማሪው ሲመረቅ የት ይግባ?
ይህ በትምህርት ፖሊሲውም ላይ በግልፅ የተቀመጠ ሲሆን ሃገራችን አሁን ባላት አቅም ይህን ሁሉ ምሩቅ ወደመንግስት ሰራተኝነት የመለወጥ አቅሙ የላትም:: እናም ትውልዱ በትምህርት መስክ ባገኘው እውቀት የራሱን የስራ እድል በራሱ እየፈጠረ መስራት ይጠበቅበታል:: ለዚህ ደግሞ ተማሪዎች የራሳቸውን ልዩ ችሎታ እና ዝንባሌ አውቀዉና ተረድተው እንዲማሩ ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ እገዛ ማድረግ የሚገባቸው መምህራን ቢሆኑም ይህንን የሚያደርጉ ጥቂቶች ብቻ ናቸው:: ይህ ባለመደረጉም ተማሪዎች ሲመረቁ የት መቀጠር ወይም ምን መስራት እንዳለባቸው እንዳይረዱ እንቅፋት ሆኗል:: ዝንባሌያቸውንም ሳይረዱት ተመርቀው ስራ አጥ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል:: ዘላለም ክብረት ያነሳትም ተማሪ የሙያ ዝንባሌዋን ባለማወቋ የተነሳም ነው እናቷን ለማስደሰት ብቻ መመረቅን እንደ አላማ አድርጋ የተማረችው:: እንዲህ አይነት ችግሮች የተከሰቱት ወደድንም ጠላንም በመምህራን የስራ ድርሻዎች በአግባቡ አለመፈፀም ነው:: ማስተማር ማለት ተዘጋጅቶ ክፍል መግባት ብቻ ሳይሆን ተማሪውን መንገድ ማሳየት፣ መምራት እና መቅረፅም ጭምር ነው::
ኮብል ስቶን ስህተት ነው?
ይህ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚተች የስራ ዘርፍ ነው:: ሆኖም መንግስት የራሱን የስራ ድርሻና እቅድ ከማስፈፀም አኳያ ይህን የስራ እድል ፈጥሮ ስራ ያጣችሁ ተደራጁና ይህን ስሩ ሲል ይስተዋላል:: ይህ በምንም መልኩ ቢታይ ስህተት የለውም:: መንግስት የመሰረታዊ ልማት ዝርጋታን በተመለከተ ያስቀመጠውን ግብ ለማሟላት አሉኝ የሚላቸውን የስራ እድሎች በመፍጠር ሊያሰራ ይችላል:: በየአመቱ ለሚመረቁ በ2 ወይም3 አስር ሺህዎች ለሚቆጠሩ ምሩቃን ሃገራችን የስራ እድል ይኖራታል ወይም ትፈጥራለች ብሎ መጠበቅ የዋህነት ይመስለኛል:: ስህተቱ የሚፈጠረው ተማሪው ችሎታዉን እና ዝንባሌውን ሳያውቅ እንዲመረቅ ስለተደረገ "ህክምና ተምሬ ድንጋይ አልጠርብም" ወይም "አካውንቲንግ ተምሬ ድንጋይ አልጠርብም" ወይም "ኬሚስትሪ ተምሬ ኑሮ ዘዴ ሰፈር ለሰፈር እየዞርኩ አላስተምርም" ወደሚል እንዲገባ አድርጎታል:: ይህ የስራ መስክ እንደ አንድ የስራ ዘርፍነት ተከብሮ መያዝ ሲገባው ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ብቻ ተማሪዎች ወደ ስራው እንዳይሰማሩ ማድረግ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ሊሆን አይችልም:: "ድንጋይ ለመጥረብ ለምን ይህን ያህል መማር አስፈለገ?" ለሚለውም ጥያቄ በማህበር ከመደራጀት ጋር የሚያያይዘው ነገር ያለ አይመስለኝም:: ሃገራችን በዚህ ሰአት እያፈራች ያለችውን የሰው ሃይል ጥራቱ ቢጠበቅና ተማሪዎቹ ተነሳሽነትን እንዲሁም ዝንባሌን ያገናዘበ ትምህርት ቢማሩ ወደ ጎረቤት ሃገራትም ሄዶ ስራ የማግኘት እድሎችን ማግኘት ይችሉ ነበር:: ከዚህ በተጨማሪ ሃገራችን እየገነባቻቸው ባለችው ትላልቅ ግድቦች ላይ የተማሩ እና የተሻለ እውቀት ያላቸው ምሩቃን በተሻለ ገቢ ሁሉንም አይነት ስራ (የቀን ስራ እያልን የምንጠራውንም ጭምር) እንዲሰሩ ቢደረግ ከስራ ጥራት እና የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ የራሱ ድርሻ ሊኖረው ይችላል:: በየአመቱ ከሚመረቀው የተማረ የሰው ሃይል አንፃር ሲታይ እንደድሮው አካውንቲንግ ተምሮ የቢሮ ስራ ብቻ ወይም የታሪክ ትምህርት ተምሮ አስተማሪነት መቀጠርን ብቻ መጠበቅም የዋህነት ነው::
እናም ዘላለም ክብረት ያነሳቸውን አሳሳቢ ጉዳዮች ለመፍታት እና ፈልጎ ያጣውን ምሁር ለማግኘት ቁልፉ ያለው ከታች ከሁለተኛ ደረጃ ላይ ያሉት መምህራን የተማሪዎቻቸውን የሙያ ዝንባሌ በማወቅ እና እንዲለዩት እገዛ በማድረግ ሃላፊነታቸውን ሲወጡ ወይም እንዲወጡ ሲደረግ ነው:: ከላይኛው እርከን ያሉትም መምህራን ለሰልጣኙ አስፈላጊውን እውቀት በመስጠት ረገድ ያለባቸውን ሃላፊነት በትክክል ሲወጡ ነው:: አመራሩም ፓለቲካን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ከመንግስት ስራ ነጥሎ ማየት ችሎ ለትምህርቱ ልዩ ትኩረት ሲሰጥ ነው:: ምሁሩንም ጠመኔ ወይም ወረቀት ይዞ ብቻ ሳይሆን ድንጋይ እየጠረበ ወይም አካፋና ዶማ ይዞ ወንዞችን እየገደበም ያማረረውን የመብራት ሃይል ችግር ሲያቃልል ወይም ትራክተር እየነዳ ያማረረውን የምግብ እህል ውድነት ችግር ሲዋጋም ልታገኘው ትችላለህና እዛም ፈልገው:: ሳጠቃልል የትምህርት ጥራቱ ጉድለት የአፈጻፀም እንጂ አጠቃለይየ ትምህርት ፖሊሲው አይደለም:: የተለየ እይታ ያለው ካለም (ነገር ግን ፖሊሲን ከአፈፃፀም ለይተን) በአንድ ወገንተኝነት ሳያነጣጥር ከነባራዊው ሁኔታ ጋራ እያገናዘብን መፍትሄ ጠቋሚ እንዲሆን እንወያይበት:: የዛሬ ሃያ ወይም ሰላሳ አመት በነበረው የህዝብ ብዛት እና የተማረ የሰው ሃይል ብዛት ጋር እያወዳደርን አዲሱን ትውልድ ለሙያ ፍቅር እንዳይኖረው ባናደርግ እንዲሁም ዝንባሌውን ለይቶ እንዳያውቅ መጋረጃ ባንፈጥርስ? አበቃሁ!!!
----
ጸሐፊውን ለማግኘት jhnb4775@gmail.com ላይ ይጻፉላቸው፡፡
----
የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብበታገደው በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡
በታዬ ዘሐዋሳ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment