Tuesday, July 2, 2013

ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ለአማራው ሲባል ከሆነ ዛሬ ይፍረስ!!

ለጠባቦቹ ጃዋሮች እየተዘጋጀ ካለ የመልስ ምት የተቀነጨበ ጽሁፍ ነው፡፡ ጠባቦች ብሄራችሁ ምንም ይሁን ምንም በአመዛኙ ሳያችሁ የዚህ አገር አንድነት ለአማራው ሲባል የቆመ ይመስላችሁዋል፡፡ እቺ ለናንተ እያዘጋጀሁት ካለ ጽሁፍ የቀነጨብኩላችሁ ነው፡፡ ፍርጥ ላድርግላችሁ አማራው ይሄ አገር ቢገነጣጠል የሚያጣው የተለየ ጥቅም የለም፡፡ ከአንድነቱም ያገኘው የተለየ ጥቅም አልነበረም ዛሬም የሚደርሰው የተለየ በረከት የለም፡፡

የትኛው ሀገሬ ኢትዮጵያዊነትን መርጦ ተቀበለውና ነው ኦሮሞው ዜግነቱ ተጭኖበት ነው የለበሰው የሚል የሰከረ መዝሙር ድሮም ዛሬም የምንሰማው፡፡ ለምን ጠባብ ጃፋሮች ኬንያዊው ኦሮሞ እንዴት ዜግነቱን እንዳገኘ አይነግሩንም፡፡ ዛሬም ነገም መላቅጡን ያጣ ዲስኩር፡፡ ይሄ እኮ ነው የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ የሚባለው፡፡ እቺ እኮ እንግዲህ አንዱ ግብጻዊ ወይም ፈረንጅ ጠባቦቹን የጋትዋቸው ምሁራዊ ትንታኔ መሆንዋ እኮ ነው፡፡

በግሌ ኦሮምያ ወይም ትግራይ ወይም ደቡብ ክልል የመገንጠል ጥያቄ ቢያቀርብና ቢገነጠሉ የሚሰማኝ የተለየ ስጋት የለም፡፡ አንድነትና መገንጠል በባህሪያቸው የሚያስገኙት ጥቅምና ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ ለአማራው ህዝብ የሚያስገኙት የተለየ ጉዳትም ጥቅምም የለም፡፡ በመሆኑም የትኛውም ብሄር ከአንድነት የሚገኝን የላቀ ጥቅምንና ጥንካሬን በመቀበል እንጂ በዚህ አገር ለአማራ ሲል አንድ የሆነ የለም፡፡ ካለም ዛሬ የመገንጠል መብቱን እንዲጠቀምበት አበረታታዋለሁ፡፡ አማራው ሌሎቹ ብሄሮች መጽውተውት ሳይሆን በአንድነቱ ውስጥ የሚጠበቅበትን አድርጎ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡

ኦሮምያ ለአማራ ክልል ሲባል ከሆነ በአንድነቱ የሚቆየው በግሌ እንዲህ አይነት ግንኙነት እንደሌለ ስለማውቅና አማራው ላቡን ጠፍ አድርጎ የሚኖር ህዝብ በመሆኑ አንድነቱ ዛሬ ቢፈርስ የህብረታችን መፍረስ ለአማራው አርሶ አደርም ይሁን ለሌላ ማንኛውም አማራ ከኦሮሞው የተለየ ፋይዳም ጉዳትም እንደማይኖረው ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ጃፋሮቹን ጠባቦች ይችን ታክል ብናስታውሳቸውስ፡፡

አማራው ጤፍና ሽሮ ተሰፍሮለት የሚኖር ይመስል አማራው ጠንካራ ሰራተኛ ያልሆነና ሰርቶ መኖር የማይችል ህዝብ ይመስል ኢትዮጵያዊ የሆኑት ለአማራው ሲሉ የሚመስላቸው ጠባቦች አማራው መንፈስ እንዳልሆነ ራሱን ማሳደግ ማልማት መከላከል የሚችልና በመገንጠልም በአንድነትም የተለየ በረከት የማይቸሩት እንደሆነ መንገር ያስፈልጋል፡፡

እንደ ህዝብ ለአማራው ሲባል አንድ የሆነ የሚመስለው ህዝብ የለም እንጂ ሲኖር ይህ ህዝብ ህገመንግስቱን ተከትሎ ቢገነጠል እደግፈዋለሁ፡፡ አማራ አንድነቱን ሲሻውና ሲፋለምለት አንድነት የሚያስገኘውን ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በማሰብ እንጂ በየትኛውም ብሄር ጫንቃ የለማና የኖረ ህዝብ ሆኖ አደለም፡፡

አማራው በተጋጋጠው ተራራውና መሬቱ ስርአቶች ድርቅ ሲልም ጦርነት እየበላው የኖረ ህዝብ እንጂ ምን ተረፈው፡፡ ከሌላው በሄር የተለየ ጥቅም ምንስ አግኝቶ ነው ይሄ ሚስኪን አርሶ አደር ይሄን ያህል የሚነተረከው፡፡ እቺ አገር ቀምሳዋለች የሚባለውን ግፍ ከአፍ እስከገደፉ እያጣጣመ የኖረ ህዝብ እንጂ የነዚህ ግፈኛ ስርአቶች ደቀ መዝሙር ማን አደረገው፡፡ እነዚያን አደገኛ ስርአቶችም ሲታገል የኖረ ህዝብ ነው፡፡

ጦርነቱ ነው መሰደዱ ነው መበዝበዙ ነው መገደሉ ነው መረሸኑ ነው ጠኔው ነው ስደቱ ነው የግዴታ ሰፈራው ነው የቱን ግፍ ነው ያልተጎነጨው? በዝባዦቹ ስርአቶች አማርኛንና ባህሉንም በመጠቀማቸው ሌላው ብሄር ስርአቶቹን ሳይሆን እንደነሱ ወገቡ እየተላጠ የኖረውን ጭሰኛ ደሀ የአማራ አርሶ አደር እንዲጠሉት ተደርጉዋል፡፡ እኮ ይሄ አንድነት የተለየ ምን ጥቅም ለአማራው ቸሮት ነው

ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን አንዳንድ ጠባቦች የአማራው ጉዳይ የሚያደርጉት፡፡ የሆነ ሆኖ አማራው እንደሌላው ብሄር ሁሉ ይሄን ግፍ ቀምሶ ሲያበቃ ለዚሁ ሁሉ የዳረጉኝ ስርአቶች እንጂ ሌሎች ወንድም ብሄሮች ናቸው ብሎ አያውቅም፡፡ አንድነቱም የህልውዬ ጠንቅ ነው ብሎ አያምንም፡፡ በዝባዦቹን ስርአቶች ግን ይፋለማል፡፡

እናም ለአማራው ሲባል አንድ የሆነ ብሄር ቢገነጠል ደስ ይለኛል፡፡ ይህ አገር ጠባቦቹ እንደሚሰበኩት ተገነጣጥሎ ቢያበቃ አማራው ተደምረው ፓርቹጋልና ቤልጅየምን የሚያክል አገር ወይም ከኔዘርላንድስ የሚበልጥ ህዝብ ኖሮት እንደ አገር መቆም ይችላል፡፡ በንጽጽርም ወደብ አልባ ሆነው ተገነጣጥለው ከሚፈጠሩት ሀገሮች ለወደብ የቀረበው መሆን ይችላል፡፡ አቦ አንድነቱ ለአማራው ሲባል የቆመ አናስመስል፡፡ የአማራ አርሶ አደርም ይሁን ሌላው አማራ ላቡን ጠፍ አደርጎ እንደሌላው ብሄር የሚኖር ህዝብ ነው፡፡

ሁሉም ብሄር ታሪካዊ ሂደቶች የፈጠሩትን ሁነቶች ተቀብሎ ሲያበቃ ቁምነገሩና ችግሩ ከዜግነታችን ሳይሆን አገር ከተመራበት መንግስታዊ ስርአት ነው በሚል ወደ ስርአት ለውጥ ትግል ገባ እንጂ ጎበዝ ኢትዮጵያዊነትን የመምረጥ እድል የተሰጠው ዜጋ የለም፡፡

ጃዋርን የመሰሉ ከየትኛውም ብሄር የተነሱ ጠባቦች ዜግነትን በምርጫ በዚህ አለም የትኛውም አገር ስለማግኘቱ አንድ ማረጋገጫ ሊያቀርቡልን አይችሉም፡፡ የሆነው በግዜ ሂደት ዴሞክራሲያዊ መንግስት በመመስረት በአንድ ሀገር ህዝቦች መሀል መተማመን መፍጠር ነው፡፡

አቦ ተውን አንድነታችንን የምንሻው የበለጠ ሁላችንንም ስለሚያዋጣን እንጂ አማሮች ልዩ ጥቅም የምናገኝበት ሆኖ አደለም፡፡

በዘሪሁን ካሳ

1 comment:

  1. ወንድ አባቴ ይሙት !! የጀግና ልጅ ።

    ReplyDelete