የመንግስት ጥቃት ቀድሞ ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት ነበር!
ቅዳሜ ነሐሴ 4/2005
‹‹እኛ ልጆቻችንን ይዘን ለዒድ በዓል ወጣን፣ እነሱ ግን በዒድ በዓላችን መሳሪያ ይዘውብን ወጡ፡፡››
ሐሙስ እለት የተከበረውን የዒድ በዓል አክብረው ይመለሱ የነበሩ ዜጎች ላይ መንግስት የወሰደው እርምጃ ቀድሞ ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት እነደነበር ታውቋል፡፡ በእለተ ሀሙስ የተከበረውን የዒድ አል-ፊጥር በአል ለማክበር በሰላት ማካሄጃ አደባባዮች የተገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ድብደባ ከቀላል የአካል ጉዳት አንስቶም እስከ ሞት የደረሰ ጉዳት በሰፊው ሙስሊም ማህበረሰብ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ ጥቃት በተለይ ሴቶች፣ እናቶች እና አባቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል፡፡
መንግስት ከዒድ በዓል ቀድም ባሉት ቀናት ‹‹ሰላም ወዳዱ ሙስሊም ማህበረሰብ›› በሚል ብሂል ሰፊ ፕሮፖጋንዳ በመስራት ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ ‹‹ተቋርቋሪ›› መሆኑን ለማሳየት ሲጥር ሰንብቶ ነበር፡፡ ከዒድ ቀደም ብሎ ባሉት ጊዜያትም የአንዋር መስጂድን እና የመካ ተራዊህ ሰላትን በቀጥታ በኢቴቪ በማስተላለፍ የሙስሊሙን ልብ ለመደልል ሞክሯል፡፡ ከዚያ በተጨማሪም እስከአሁን ባልታየ መልኩ ከፌዴራል ፖሊስ የ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› የመልካም ምኞት መግለጫም ተብሎ በሚዲያዎች ተበትኗል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን ባዶ ሽንገላዎች መሆናቸውን ለማረጋጋጥ ቀናት እንኳ አልዘገዩም፡፡
ሆኖም መንግስት በሚዲያው ይህን አይነቱን ጉዳይ እያቀረበ በተቃራነው አቅጣጫ ግን መንግስት ሙስሊሙ ላይ ጥቃት የሚፈጽምበትን ስልት እያሰላ ነበር፡፡ ከፍተኛ የመንግስት እና የደህንነት ሀላፊዎች በወታደራዊ የጦር ስታራቴጂ የአዲስ አበባ ስተዲየምና አካባቢውን በጦር ቀጠና በመክፈልና ሙስሊሙ ላይ ጥቃት መፈጸሚያ ስልት በመንደፍ ላይ ነበሩ፡፡ ከስታዲየም እስከ 7 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ርቀት ድረስ የሚገኙ አካባቢዎችና የውስጥ መንገዶችን ለዚህ ጥቃት በማመቻቸት ለዒድ አሰቃቂ ጥቃት የተዘጋጀው መንግስት በቴሌቪዥኑ ግን ሙስሊሙን ‹‹ሰላም ወዳዱ ማህብረሰብ እያለ›› እያፌዘበት ነበር፡፡
በእለተ ዒድ ግን የዒድ ሰላት መጠናቀቁን ተከትሎ ሙስሊሞች ተቃውሞአቸውን አጠናቀው ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱም ለጥቃት የተዘጋጁ ወታደሮች ከፍተኛ ድበደባ በሙስሊሞ ላይ መፈጸም ጀምረዋል፡፡ ዋና አውራ ጎዳናዎችና የቅያስ መንገዶች ላይ በማድፈጥ በሰላም ሲመለስ የነበረው ሙስሊም ያለ ልዩነት በጅምላ ጥቃቱ ሲፈጸምበት ታይቷል፡፡ በተለይ ሴት እህቶቻችን ላይ በማተኮር ሲፈጸም የነበረው ድብደባና እንግልት በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ በአካል ያየነውና የታዘብነውም ይህንኑ ነው፡፡ ድርጊቱን የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዮዎችም የፖሊስ አሰቃቂ ጥቃት ምን ያህል የከፋና በጅምላ የተወሰደ እንደነበር ለሌላው ኅብረተሰብ አመላካች ነው፡፡ የፖሊስ ጥቃት ነፍሰ ጡር እናቶች፣ የታዘሉ ህጻናትን፣ መራመድ የተሳናቸው አረጋውያንን ሁሉ ባካተተ መልኩ ነበር የተፈጸመው፡፡ በዚህ የመንግስት ድርጊት ተጎድተው ሆስፒታል በህክምና ላይ የሚገኙ ከመኖራቸውም በላይ ህይወታቸው ያለፈም መኖሩን በእለቱ ዘግበናል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ክፍል ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች ከፍተኛ ምስጋና የሚያሻው ትብብራቸውን ለተጎጂዎች ለግሰዋል፡፡
ይህ ጸያፍ የመንግስት ድርጊት ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ ያስተላለፈው መልእክት ግልጽ ነው፡፡ መንግስት በሚዲያ ከሚፈጽመው ሽንገላ በተቃራኒ ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ አክብሮት እንደሌለው በግልጽ አስመስክሯል፡፡ ሙስሊሞች የዒድ በዓላችንን በደስታ ከማሳለፍ ይልቅ በሕጻናትና በእናቶች ዋይታ ዒዳችን እንዲያልፍ፣ ሙስሊሞች ለአሰቃቂ ጥቃት ሰላባ እንዲሆኑ፣ አባወራዎች ዒድን በእስር እንዲያሳልፉ ምክንያት እና ሰበቡ መንግስት ነው፡፡ በደስታ ቀናችን የፈሰሰው ደማችን ቆጥቁጦናል፣ የቆሰለው አካላችን ክፍኛ ጠዝጥዞናል፡፡ ይህን መንግስት በዒድ እለት የፈጸመውን አሳፋሪ እና አሰቃቂ ድርጊት መቼም ቢሆን ልንዘነጋው አንችልም፡፡ በእርግጥም እንደተባለው ‹‹እኛ ልጆቻችንን ይዘን ለዒድ በዓል ወጣን፣ እነሱ ግን ለዒድ በዓላችን መሳሪያ ይዘውብን ወጡ፡፡›› ሰላማዊነታችን በፍርሀት ያርዳቸዋል፣ ዲሲፕሊናችን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያዋልላቸዋል፡፡ ሰላማዊነታችን ነው ድላችን፡፡
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment