ኢትዮጵያ ጉድ የማያልቅባት አገር ናት። ጉድ የማያልቅባት ከጉድም ጉድ የኾኑ ገዢዎች ስለሚፈራረቁባት ነው። ሕዝባቸውን አያከብሩም። ለዜጎቻቸው መብት እና ፍላጎት አይጨነቁም። ስለዚህ ጉደኛ የኾኑ ክስተቶችን በየጊዜው ያመጡብናል። ይፈጥሩብናል።
በሚቀጥለው እሁድ ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም ሠማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ላይ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ዕቅድ ካወጣ ሰንብቷል። በዚሁ ቀን መንግሥትም ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ። "ጽንፈኝነትን እና አክራሪነትን እንቃወማለን" የሚል መፈክር ለደጋፊዎቼ አስይዤ አዲስ አበባን በሠላማዊ ሰልፍ አጥለቀልቃታለሁ የሚል ዕቅድ አውጥቶ።
መንግሥት አስፈጻሚ፣ አድራጊ ፈጣሪ፣ ገዢ እና ገናዥ በኾነበት አገር ላይ መንግሥት ሠላማዊ ሰልፍ ይጠራል። ወለፈንድ ማለት ይኼ ነው። ራሱ ቤት ለቤት ዞሮ “ጽንፈኝት እና አክራሪነትን” ለመቃወም “ኑ ዉጡ!” ብሎ በሕዝብ ሀብት እና ንብረት ላይ ከቀለደ በኋላ መልሶ “ሕዝቡ ጽንፈኝነትን እና አክራሪነትን ተቃውሞ ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ፤ መንግሥት ሐላፊነቱን እንዲወጣ ጠየቀ” ብሎ ሊወስድ የሚፈልገውን ርምጃ ልብስ ማልበስ ይፈልጋል። የዚህ ሠላማዊ ሰልፍ ጥሪ የስትራቴጂው ዋና ነጥብ ይኼ ነው።
በእኔ እምነት ጽንፈኝትን እና አክራሪነትን የማይቃወም ሕዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራል ብዬ አላስብም። ጽንፈኝነት እና አክራሪነት መፍትሄ ያመጣል ብለው የሚያስቡ እና መስመሩን ዓላማቸው አድርገው የያዙ ጥቂቶች አይኖሩም የሚል ጅላጅል አስተሳሰብም ኾነ አቋም የለኝም። ሊኖሩ ይችላሉ። ካሉ እነዚህን ጥቂት ሰዎች ፈልጎ እና ፈልፍሎ የማውጣቱ ሥራ የመንግሥት ነው። አገሪቱ ትክክለኛ ለሕዝብ ሰላም የሚጨነቅ የደህንነት መሥርያ ቤት ካላት ሕዝብ ሳይሰማው እና ሳያውቀው መጨረስም ይችላል። ለጊዜው የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥት በሁለት እግሩ ቆሞ ሥራውን እንዲሠራ በቀረጥ እና በግብር ሐላፊነቱን ከተወጣ በቂው ነው። እንደገና ምን በወጣው ነው መንግሥት የቤት ሥራውን ባለመሥራቱ ለሚጨቁነው መንግሥት ደግፎ ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣው?
ነገሩ ወዲህ ነው። አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ከእውነተኛዎቹ ጽንፈኞች እና አክራሪዎች ይልቅ በአሸባሪነት እና በጽንፈኝነት መንግሥትን የሚተካከለው እና የሚወዳደረው የለም፤ ይህን ዓላማውን እንዴት ማሳካት እንደሚችል ስለሚያስብ ሕግን ከማስከበር እና ከማስጠበቅ ወጥቶ ሠላማዊ ሰልፍ ጠሪ ለመኾን በቅቷል። አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በፈለገበት በተመሳሳይ ቀን እኔም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እፈልጋለሁ ማለት እብደት ነው። ሐላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው። ሁለት የተለያየ ሐሳብ ያላቸውን ቡድኖች የሚከተሉ ደጋፊዎች በአንድ ቀን ወደ አንድ ቦታ እንዲወጡ ማድረግ ራሱን የቻለ የጽንፈኝነት እና የሽብር መገለጫ ነው።
መንግሥት ይህን ለምን ማድረግ ፈለገ?
እኔ ሲመስለኝ፦
1ኛ) በሠላማዊ ሰልፈኞቹ መካከል ግጭት እንዲፈጠር፤
2ኛ) ከግጭቱ በኋላ ሊፈጠር የሚችለውን አጋጣሚ በመጠቀም “ያልኳችኹ እውነት ነው” ብሎ ከዚህ በኋላ ማንኛውም ተቀዋሚ ፓርቲ ምንም ዐይነት ሠላማዊ ሰልፍ እንዳይጠራ ለማድረግ፤ ቀስ በቀስ የብዙ ሰዎችን ትኩረት በመሳብ ላይ ያለውን የሠላማዊ ሰልፍ ጉዳይ እግረ መንገድ እስከወዲያኛው ለማኮላሸት።
3ኛ) በሁለቱም ወገን ሠላማዊ ሰልፈኞቹ ምንም ዐይነት የገጭት አዝማማያ ሳያሳዩ በሰላም ሊያጠናቅቁ የሚችሉበት ክፍተት ከተፈጠረ፤ የተመረጡ እና የተመለመሉ ሰዎችን በሠማያዊ ፓርቲ ሰልፈኞች መካከል በማስረግ በኢሕአዴግ ደጋፊዎች ላይ ትንኮሳ እንዲያካሂዱ ማድረግ ናቸው።
ስለዚህ ይህ የሁለት ተቃራኒ ቡድኖች የሠላማዊ ሰልፍ ጥሪ ምን መኾን አለበት?
አሁንም እኔ ሲመስለኝ፦
መንግሥት ሐላፊነት በጎደለው አኳኋን ለሰላማዊ ሰልፈኞች ጥበቃ እና ከለላ በመስጠት ፈንታ፤ ራሱ የጫዎታው ተሰላፊ በመኾን ከላይ በጠቀስኳቸው ነጥቦች መሠረት ኹኔታውን ወደ ግጭት እንዲያመራ የሚያደርግ ከኾነ፤ ለሕዝብ ተቆርቋሪ የኾነ ሐላፊነት የሚሰማው ሌላ አካል ያስፈልጋል ማለት ነው። በዚህ የሠላማዊ ሰልፍ ፍጥጫ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን አላስፈላጊ የኾነ ግጭት ለማስወገድ ይህ አጅግ አስፈላጊ ነገር ይመስለኛል።
* ስለዚህ ሰማያዊ ፓርቲ የእሁዱን የሠላማዊ ሰልፍ ጥሪ ለሌላ ጊዜ አስተላልፌዋለሁ ማለት ይኖርበታል።
1ኛ) የመንግሥትን ሐላፊነት የጎደለው አካሄድ ለመቀልበስ፤
2ኛ) በሠላማዊ ሰልፍ ሰበብ ሊፈጠር የሚችልን አላስፈላጊ ግጭት ለማስወገድ፤
3ኛ) ቀጣይ የኾኑ ሰላማዊ ሰልፎች እንዲኖሩ ሩቅ አሳቢነቱን ለማሳየት
4ኛ) በሠላማዊ እና በሠላማዊ በኾነ መንገድ ብቻ መብትን እና ነጻነትን ለዜጎች ማሳየት እና በማስተማር እንደሚቻል ለማሳወቅ።
No comments:
Post a Comment