Tuesday, August 13, 2013

የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ወጣት ክንፍ ድርጅት (ኢወክንድ) ማዕከላዊ አመራር የተሰጠ መግለጫ


ነሐሴ 6 ቀን 2005ዓ.ም.  

የኢሕአፓ ወጣቶች ክንፍ ድርጅት (ኢሕአፓ ወክንድ) አራተኛ ጉባዔውን አካሄደ በሚል ርዕስ  የድርጅታችንን የኢሕአፓን ወክንድን ስምና አርማ በመጠቀም  በሥነ-ምግባር ጉድለት ከድርጅታችን ከኢሕአፓ ወክንድ የተባረሩ ጥቂት ግለሰቦች በህገ ወጥነት ያወጡት መግለጫ  በአንድ ድረ ገጽ ተለጥፎ ለማየት ችለናል። እነዚህ ህገ ወጥ ግለሰቦች በቃልም  ሆነ በጽሁፍ  የሚያሰራጩዋቸው ማናቸውም መግለጫዎች ድርጅታችንን ኢወክንድን በምንም መንገድ የማይመለከቱና የማይወክሉ መሆኑን አጥበቀን ለመግለጽ ተገደናል።  

የኢሕአፓ ኢወክንድ መወለድና የሚደርገው ድርጅታዊ እንቅስቃሴ የማይጥማቸውና እናት ድርጅታችንን ኢሕአፓን የሚጠሉ ግለሰቦች  የኢህአፓ ወክንድን  እንቅስቃሴን ለማደናቀፍና ለማዳከም በተለያየ መንገድ ደንቃራ ለመሆን ሲክቸልቸሉ ይታያል። ይህ ጸረ- ድርጅትና ጸረ – ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ለኢሕአፓ ወክንድ እንደ አዲስ ክስትት ወይንም ዱብ እዳ የሚታይ ሳይሆን  በትግል ተወለዶ በትግል የሚያድግ ድርጅት የሚጠብቀውና በጽናትም የሚታገለው ይሆናል።  

ይህ የድርጅትን ስም እንደ ሞርዶፋ እየቀደዱ ይዞ የመሮጥ ሥርዓት ዓልባ  ክስተት  ለወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ እጅ በመስጠት አመች ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ በአንድነት ሃይሎች ትብብር ቶሎ መምከን አለበት ብለን እናምናለን። በዚህ ደረጃ  የድርጅቶችን ስም በመንጠቅ ከፋፋይ መልእክት ያላቸውን   ህገ ወጥ ወረቀቶች ከማስተናገድ በመታቀብ እየተባበሩ ላሉ ድህረ ገፆች እና ማህበራዊ ፎረሞች ምስጋናችንን እናቀርባለን።  

ያለፈው ትውልድ ለሕዝብ መብትና ልእልና እንዲሁም ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት የፈጸመውን ገድል ለመድገም በሚደረገው ህዝባዊና ዴሞከራሲያዊ ትግል ኢሕአፓ ወክንድ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ምንጊዜም ዝግጁ ነው። 

ኢትዮጵያ  የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት የበርካታ ብሔር/ ብሔረሰቦች አገር ነች። ሕዝቦቿ መብታቸው ተረግጦ በሰላም በእኩልነትና በአንድነት መኖር ይፈልጋሉ። ለልማትና ብልፅግና በጋራ መስራትም ይሻሉ። ኢሕአፓ ወክንድ  ከእናት ድርጅቱ ከኢሕአፓ በወረሰው የትግል ተመክሮና ጽናት ፤ ዛሬም እንደትናትናው ለሁሉም የኢትዮጰያ ህዝብ የጋራ ጥቅም ፍላጎትና መብት መከበር ከጎናቸው ተሰልፎ መታገሉን ይቀጥላል።  ሕዝቡ ከወያኔ አምባገነን አገዛዝ ተላቆ የመብት ባለቤት እስኪሆን ድረስ የጀመረውን ትግል  ግንባሩን ሳያጥፍ በቆራጥነት ይቀጥላል። ኢሕአፓ ወክንድ ዓላማው አደረጎ የተነሳው የአብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር በመሆኑ ትግሉም የህዝብ ትግል ነው። ትግሉ ምንም እንኳን መራርና ውስብስብ ቢሆንም በመጨረሻ ግቡን እንደሚመታ  ጥርጥር የለውም። የሚካሄደው ሕዝባዊ ትግል ተጠናክሮ ግቡን አጠር ባለ ጊዜ እንዲመታ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ባጠቃላይም የህዝብ ወገን የሆኑ ሁሉ ያልተቋረጠ ትብብርና ድጋፍ እንዲሰጡትና በያቅጣጫው በሚደረገው ትግልም ሁሉም የየድርሻውንና የየችሎታውን እንዲያበረክት ዳግም ጥሪውን ያስተላልፋል። በኢሕአፓ ወክንድ ስም የሀሰት መግለጫ ለሚያወጡት ጋጠ ወጥ ግለሰቦች መድረክ መስጠት የሕዝብን ትግል የሚያዳክም መሆኑን በመረዳት መግለጫውን የለጠፈላቸው ድረ ገጽ  ባስቸኳይ እንዲያነሳ እንጠይቃለን። 

   
 ፀረ ድርጅትና ፀረ ዲሞክራሲ ሀይሎችን በጽናት እንታገል 
 ኢሕአፓ ኢወክንድ 
 ነሀሴ 2005ዓ.ም. 

  Tel : 202-291-5832              5309 Georgia Ave. NW 2nd Fl. Washington DC 20011

  e-mail: eprpylnew @gmail.com                 Website:   www.eprpyl.com 

No comments:

Post a Comment