አቶ አበባው አያሌው፣ የታሪክ ባለሙያ
ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበርካታ ድንቅ የሆኑ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች ሙዚየም መሆኗን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡
ኢትዮጵያ የሰው ልጆች ታሪክ መነሻ አገር ተደርጋም ተደጋግማ ትነሣለች፡፡ በተጨማሪም ለአፍሪካ ሕዝቦች ሥልጣኔ መሠረት ለሆነው የዓባይ ወንዝ መነሻ ናት፡፡ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተለይታ የምትታወቅበት የበርካታ የታሪክ፣ የባህልና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤትም ና
ት፡፡
ይህን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅባቸውን በርካታ ቅርሶቿን በተመለከተ ባለፈው ቅዳሜ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በተደረገ ስብሰባ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች እንክብካቤና ልማት ማኅበር›› በሚል ስያሜ የታሪክና የቅርስ ተቆርቋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የተካተቱበት ማኅበር በይፋ መቋቋሙን የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ መንግሥቱ ጎበዜ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አቶ መንግሥቱ እንደገለጹት፣ ማኅበሩን ለማቋቋም ዋነኛው ምክንያት በአገሪቱ ያሉ ድንቅ፣ መተኪያና መሰል ሌላቸው ቅርሶች እየጠፉና ጉዳት ላይ እየወደቁ መሆናቸውነው፡፡ በአደጋ ላይ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ተገቢውን ዕውቅና እንዲያገኙ፣ ሙያዊ የሆነ ጥበቃና እንክብካቤ ተሰጥቷቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፈው ተገቢው ጠቀሜታ እንዲሰጡ ለማድረግም እንደሆነ አውስተዋል፡፡
በማኅበሩ ምስረታ ይፋ መሆንን በተበሰረበት ስብሰባ ላይ ከታሪክና ከቅርስ ሙያ ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎች የጥናት ወረቀት አቅርበው ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል ዕውቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ በኢትዮጵያ በሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች የሚገኙበትን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ሙያዊ ትንታኔ የታከለበት ጥናት አቅርበው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ ዘጠኝ ቅርሶች እንዳሏትና በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ አገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን አግኝተው በዩኔስኮ የተመዘገቡ ታሪካዊ ቅርሶቻችንም ሆኑ ሌሎች በርካታ ቅርሶቻችን ተገቢውን ትኩረት ከማጣት የተነሳ ለጉዳትና ለአደጋ እየተጋለጡ መሆናቸው የጠቀሱት ፕሮፌሰር ባሕሩ፣ በተጨማሪም በልማትና በጥበቃ ስም በርካታ ቅርሶቻችን ለጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ በልማት ስም ታሪካዊ የሆኑ ቤቶች የመፍረስ ዕጣ ፈንታ እንዳጋጠማቸውና ከዚህም የተነሳ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ በከተማዋ የሚገኙ ታሪካዊ ቤቶችና ቅርሶች ላይ አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ ቅርሶችን በመጠገንና በመንከባከብ ስምም በአገራችን በሚገኑ ድንቅ የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶቻችን ላይ ውድመት እየተፈጸመ እንደሆነም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እንደማሳያ በመውሰድ ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል፡፡
የቅርስ ጉዳይ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ መሥሪያ ቤቶች፣ የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት በቅርስ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ኅብረተሰቡን በማስተማር ለታሪኩና ለቅርሱ የሚቆረቆር ትውልድ እንዲፈጠርና እንዲሁም እንደ ሌሎች አገሮች ቅርሶቻችን ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቷቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉና አገራችን በእነዚህ ሀብቶቿ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚመለከታቸው ክፍሎች ሁሉ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በኢዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት አቶ አበባው አያሌው በምስል አስደግፈው ባቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ ቅርሶቻችን የተጋረጠባቸውን አደጋና ጥፋት አስመልክተው ታዳሚዎችን ያስቆጨ ጥናት ነበር ያቀረቡት፡፡ አቶ አበባው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ መንግሥቶች፣ አብያተ ክርስቲያናትና ሕንፃዎች ተገቢው የሆነ ትኩረት በማጣታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈራረሱና በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ዘመናትን ባስቆጠሩ የብራና መጻሕፍት፣ ቅዱሳን ሥዕላትና ቅርሶች ላይ በተለያየ አቅጣጫ እየደረሰ ያለው ጥፋት ከራሳቸው ከቅርሶቹ ባለቤቶች ጀምሮ፣ በሕገወጥ ደላሎችና ቅርስ አቀባባዮች አማካይነት ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ቅርሶች በዝርፊያና በሽያጭ አውሮጳ እየተሻገሩ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ለኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክና ቅርሶች ካለው ፖለቲካዊ አመለካከት የተነሣ ለታሪካዊ ቅርሶች ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ አይደለም፤›› ያሉት አቶ አበባው ይሄም ቸልታ በአገሪቱ ቅርሶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩንም አክለው ገልጸዋል፡፡
አቶ አበባው በጥናታቸው ኅብረተሰቡ ለማንነቱ ለታሪኩ ቋሚ ዋቢ የሆኑት ታሪካዊ ቅርሶቹን በመንከባከብና በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለው በመግለፅ ቅርሶቻችን ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉና ለዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊና ተመሳሳይ ጥቅሞች እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ማድረግ እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡
ከጥናት ወረቀቶቹ ከቀረቡ በኋላ ከስብሰባው ተሳታፊዎች አስተያየትና ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል በአብዛኛው የቀረበው አስተያየት አገራችን የበርካታ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም ከቅርሶቿ ተገቢውን ጥቅም እያገኘች አለመሆኗንና እንዲያውም አገሪቱ ዘመናትን ካስቆጠሩ ከበርካታ ቅርሶቿ ይልቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀው በራብና በድርቅ እንደሆነ በቁጭት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በተጨማሪም በኅበረተሰብ መካከል ለታሪካዊ ቅርሶች ያለው ግንዛቤ እጅግ አናሳ መሆኑና ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ለታሪክና ለቅርሶቻችን ተገቢውን ትኩረት አለመስጠታቸው ቅርሶች ለአደጋ መጋለጥና መጥፋት ምክንያት መሆናቸውን በውይይቱ ጊዜ ተነስቷል፡፡
ቅርሶቻችንን በተመለከተ ኅብረተሰቡን በማስተማር ረገድ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ ትምህርት መሰጠት እንዳለበትና ለዚህም መንግሥት፣ የሃይማኖትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን አግኝተው የተመዘገቡ ቅርሶቻችን የማንነታችን የታሪካችን ሕያው አሻራ መሆናቸው ታውቀው ተገቢውን የሆነ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከቅርሶቻችን ተጠቃሚ የምንሆንበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት የስብሰባው ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከእኛ ያነሰ ታሪክና ቅርስ ያላቸው አገሮች ያላቸውን ታሪክ አስውበው በማቅረብና ቅርሶቻቸውን በመንከባከብ ለቱሪስት መስህብነት አውለው በርካታ ጎብኚዎችን በመሳብ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ሲያገኙ፣ እኛ ይህን ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር የተመዘገቡ በርካታ ቅርሶች እያሉን የቱሪስት ድርቅ የመታን አገር መሆናችን አሳዛኝ ነው ያሉ አስተያየት ሰጪዎችም ነበሩ፡፡
አገሪቱ ያላትን ረዥም ዘመን ታሪክ፣ ቅርሶችና መስህቦቻችንን በማስተዋወቅና የአገሪቱን ገጽታ በመለወጥና በመገንባት ረገድ ኃላፊነት ያለበት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የአገሪቱ ታሪካዊ ቅርሶችን በመንከባበከብ፣ በመጠበቅና በማስተዋወቅ ረገድ የሚገባውን ያህል ሚና እንዳልተጫወተ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ትውልዱ በራሱ ወይም በማንነቱ፣ በታሪኩና በቅርሶቹ እንዲኮራ፣ እንደዚሁም እነዚህ የማንነቱ ሕያው አሻራ የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶቹን እንዲጠብቅ፣ እንዲንከባከብና ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ረገድ እየተጫወቱት ያለው ሚና እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩልም የበርካታ ቅርሶች ባለቤት የሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ቅርሶች በትምህርትና ሙያዊ በሆነ መንገድ ተጠብቀው ለጥናት፣ ለምርምርና ለጥቅም እንዲውሉ ለማድረግ በራቸውን ክፍት ማድረግ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል፡፡ ከትምህርትና ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ በየገዳማቱ እየተበላሹ፣ እየጠፉና እየተዘረፉ ወደአውሮፓ በሚሻገሩ የብራና መጻሕፍትንም በተመለከተ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት በተቀናጀ መልኩ መሥራት እንዳለባቸው በውይይቱ ላይ የተገኙ የሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡ ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment