አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፣ በመቀሌና በወላይታ ሶዶ ከተሞች ሠላማዊ ሠልፍና ህዝባዊ ስብሠባ ለማካሄድ የነበረው እቅድ በተለያዩ ጫናዎች መጨናገፉን የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገለፁ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጠበቁትን ያህል የህዝብ ድጋፍ ሲያጡ የራሳቸውን ድክመት ለመሸፈን መንግስትን ይወነጅላሉ ብለዋል፡፡
አንድነት ፓርቲ በ16 ከተሞች ሠላማዊ ሠልፍና ህዝባዊ ስብሠባ ለማካሄድ እቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ነጋሶ፤ በየከተማው የፓርቲውን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ሙከራዎች አጋጥመውናል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከመቀሌ እና ከወላይታ ሶዶ በስተቀር በሌሎች ከተሞች ሠላማዊ ሠልፎችና ህዝባዊ ስብሠባዎችን በስኬት ለማከናወን ችለናል ብለዋል፡፡ ሐምሌ 28 ቀን በመቀሌ ሊካሄድ የነበረው ሠላማዊ ሠልፍ የተጨናገፈው ለቅስቀሣ የምንጠቀምበት መኪና በመታገቱ ነው የሚሉት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ በከተማዋ ያሉ የፓርቲያችን አስተባባሪዎች በመታሠራቸውም እቅዳችን ሳይሳካ ቀርቷል ብለዋል።
“ሠልፍ ማካሄድ አትችሉም” የሚል ግልጽ ክልከላ ባያጋጥመንም፣ በተለያዩ መሰናክሎች ሳቢያ ፓርቲው በገዛ ፈቃዱ ሠልፉን መሠረዙን አቶ ዳንኤል ገልፀዋል፡፡ በወላይታ ሶዶ ከተማም በዚያው እለት ህዝባዊ ስብሠባ ለማካሄድ ታስቦ እንደነበር አስታውሰው፣ ስብሠባው የሚካሄድበትን አዳራሽ ከፍተን ለመግባት አልቻልንም የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ ቁልፍ ጠፍቶ የስብሠባው ሠአት ካለፈ በኋላ ነው የተገኘው ብለዋል፡፡ የታሠበውን ያህል ተሣታፊ ባለመገኘቱም ስብሠባው ስኬታማ አልሆነም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“አንድነት በተለያዩ ከተሞች ሠላማዊ ሠልፍ እና ህዝባዊ ስብሠባ በማድረጉ ኢህአዴግ ግራ ተጋብቷል” የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ በአርባምንጭና በወላይታ ሶዶ የቅስቀሣ መኪኖች እንዳይንቀሣቀሡ ጐማ በማስተንፈስ እንቅፋት ለመፍጠር ተሞክሯል ብለዋል፡፡ በባህርዳርም፣ በሠልፉ ተሣታፊ የነበሩ ባጃጆች ታርጋ ተፈትቶ እንደተወሰደባቸው ዶ/ር ነጋሶ ገልፀዋል፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች እየተካሄዱ ባሉት ሠላማዊ ሠልፎችና ህዝባዊ ስብሠባዎች ዙሪያ የመንግስትን አቋም እንዲገልፁልን የጠየቅናቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በህገመንግስት የተከበረላቸውን መብት እያጣጣሙ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚመሠረቱበት አላማ ለመቃወምና ሃሣባቸውን በሠላማዊ ሠልፍ ወይም በህዝባዊ ስብሠባ ለመግለፅ መሆኑን አቶ ሽመልስ ጠቅሰው፣ ይህም በህገመንግስት የተፈቀደላቸው መብት ነው ብለዋል፡፡
ነገር ግን አንዳንድ ተቃዋሚዎች ከአክራሪ ሃይሎች ጋር የፈጠሩት “ያልተቀደሠ ጋብቻ” ለህዝቡ ስጋት መሆኑን የተናገሩት አቶ ሽመልስ፤ መንግስትም በዚህ ሁኔታ ህገ መንግስቱ ሲጣስ ከዳር ቆሞ አይመለከትም ብለዋል፡፡ ተቃዋሚዎች በሰልፍና በስብሰባ ጥሪ የጠበቁትን ያህል ሠው ሣይወጣላቸው ሲቀር፣ የራሳቸውን ድክመት ለመሸፋፈን መንግስትን ተጠያቂ ለማድረግ ይሞክራሉ ያሉት አቶ ሽመልስ፤ መንግስት ጫና በማድረጉ ሠው ሊወጣልን አልቻለም የሚለው የተቃዋሚዎች ስሞታ መሠረት የሌለው ውንጀላ ነው ብለዋል፡፡
ምንጭ፡ አዲስ አድማስ
No comments:
Post a Comment