Monday, August 12, 2013

በደልን በጽኑ እንታገላለን፤ ምንዳችንም ከአላህ ነው!! (ድምፃችን ይሰማ)

ሰኞ ነሐሴ 6/2005

እኛ ሙስሊሞች እየከፈልን ያለነው መስዋእትነት መጠኑ ሊለካ የሚችለው ከያዝነው ዓላማ አንፃር ብቻና ብቻ ነው፡፡ ለዲን ያለንን ፍቅር ንፁህነት እና ደረጃውን በመጪው ዓለም የምናረጋግጠው እውነታ ቢሆንም በየትኛውም አለም ከታዩ ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር ግን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በተለየ መልኩ እጅግ ንፁህ የሚባል የዲን ፍቅር እንዳለን በበርካታ አጋጣሚዎች የታየ እውነታ ነው፡፡ የምናካሄደው ሰላማዊ ትግል የአላህን ውዴታ ከጅለንበት እንጂ ሌላ ምንም ተመኝተን፣ ማንንም ተመክተን አልገባንም፡፡ ይህ ሰላማዊ ትግል በኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክ ግዙፍ የተባለና የተቀነባበረ ጥፋትን የማምከን ዓላማ ባይኖረው ኖሮ በመላው ሃገራችን አሉ የምንላቸው ምርጥ የኢስላም ልጆች ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ባልገቡበት ነበር፡፡ ይህ ትግል የአላህን ውዴታ ከመከጀል ባይመነጭ ኖሮ በትግል ሂደቱ ዋና ተሰላፊ በሆነው ህዝብ እና በተለያዩ ዘርፎች የማስተባበር ሚና በሚወጡ ወገኖች ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ የሚያስብል ትንቅንቅ ባልተደረገበት ነበር፡፡ ይህ ትግል ጀነትን የምንከጅልበት ባይሆን ኖሮ እስካሁን በገጠሙን ግዙፍ የበደል ናዳዎች ተጨፍልቀን፣ በጥልቅ የክስረት ሸለቆዎችም ሰምጠን በቀረን ነበር፡፡ 

ዛሬ ላይ ስለደረሰብን በቃላት የማይገለፅ ኢ-ሰብአዊ እና ኢ-ኢትዮጵያዊ ግፍ ከማውራት ይልቅ ስለያዝነው መንገድ መናገርን ያስቀደምነው ይህ ትግል ዱንያን ግባቸው ያደረጉ ሰዎች ከሚሞቱለት አላማ እጅጉን የላቀ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያችን ካስተናገደችው ክስተት በምንም የማይፋቅ ጥቁር ክስተት ሆኖ ይቀርብ ነበር፡፡ በሃገራችን ያለፉ መንግስታትን የምንወቅስበት 1001 ምክንያቶች አሉን፡፡ ከፊሎቹ በእድሜ ዘመናችን ያየናቸው፣ ከፊሎቹም ሰለነሱ የሰማንላቸው ነበሩ፡፡ እነዚያ መንግስታትና አጫፋሪዎቻቸው ላደረሱት እያንዳንዱ በደል ወይ በህይወት እያሉ ዋጋውን ከፍለዋል፣ አልያም በድናቸውን እረፍት የሚነሳ ዘላለማዊ የህዝብ እምባ እና ሰቆቃ ላይለያቸው ተቆራኝቷቸዋል፡፡ ላደረሰው በደል ዋጋ ሳይከፍል ያለፈ በደለኛ የለምና! ይህ ቋሚ መርህ ነው፡፡ ባለጊዜዎቹ በደለኞችም ላደረሱትና ለሚያደርሱት እያንዳንዱ በደል ዋጋውን ሳይከፍሉ አይቀሩም፡፡ ዛሬ በደለኞች የጨቀዩበትና የንፁሃንን ደም ተራምደው ያመጡት የንፁሃን ጣር ላይ ያለች ህይወት ፈጣሪ ዘንድ ያላት ዋጋ የስልጣናቸውን ወንበር ብቻ ሳይሆን የቆሙበትን ምድርም የሚያንቀጠቅጥ ብርቱ ሃይል እንዳለው ለአፍታም አንጠራጠርም፡፡ ይህ ተከስቶ አይተናል፤ ዳግም የሚከሰትበት ወቅትም ሩቅ እንዳልሆነ እምነታችን ነው፡፡ 

በዚህ ሁሉ ዋይታ ውስጥ ግን በዳዮች ዛሬ የተረዱትን እውነታ ሳናነሳ አናልፍም፡፡ ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት ህዝብን በህዝብ ላይ ለማስነሳት መንግስት አስተዳደራዊ አቅም እና ብልሃቱ እንደተሟጠጠ በሚያሳብቅ መልኩ ሙሉ አቅሙን በሚዲያ ላይ አድርጎ መሰንበቱ ሁሉንም ‹‹ይህ ለምን ሆነ?›› ያስባለ ነበር፡፡ መንግስታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ ያልተወጣ መንግስት፣ የህዝብን ቅሬታ በመንግስታዊ አግባብ ማስተናገድ የተሳነው መንግስት፣ ከጥፋት ላለመታረም ሌላ ጥፋት በመደራረብ እይታው የተጋረደ መንግስት ባሳለፍናቸው ተከታታይ ሳምንታት እንዳየነው ሙሉ አቅሙን ‹‹ምን ብዬ ላውራ›› ብሎ ሚዲያ ላይ ከመዝመት ሌላ አሳሳቢ ጉዳይም አማራጭም እንደሌለው አሳይቶናል፡፡ እነዚህ የሚዲያ ጦርነቶች የህዝብን የኃያልነት ስልጣን ሊነጥቁ እንደማይችሉ ግን ሚሊዮኖች በመላው ሃገሪቱ በአይናቸው እንዲያዩት አስገድደዋቸዋል፡፡ ግና በዚህ የህዝብን አቅም እና አቋም በመጨረሻው ሰአት ላይ እንኳን ሊቀበሉ ያልፈቀዱ በዳዮች በታጋይ ሃየሎም አርዓያ አንደበት በወጣው የእውነት ብሂል የግዜያችን ምስክር መሆንን የመረጡ ይመስላሉ፡፡ ታጋይ ሐየሎም ‹‹ወደ ህዝቡ መተኮስ የጀመረ ውድቀቱን አፋጠነ›› ብሎ ነበር፡፡ ገዢዎቻችን አሁን ከዚህ እውነታ ጋር ፊት ለፊት እየተፋጠጡ ይመስላል፡፡ 


ዛሬ ላይ ያደረሳችሁት ጭፍጨፋ ገድላችንን እንዳናወሳ የማድረግ ቅንጣት ታክል አቅም የለውም፡፡ ልጅ አዋቂ ሳትሉ የጭካኔያችሁን ጣሪያ አሳይታችሁናል፡፡ ይህ ግን ለሳምንታት የነዛችሁትን የሀሰት ዲስኩር ተሻግረን ያንን አስደማሚ ሰላማዊ ተቃውሞ ከማድረግ አላገደንም፡፡ መስከረም 27 በቀበሌ ያካሄዳችሁት መንግስታዊ የመጅሊስ ሹመት በአደባባይ ቀብረነዋል፡፡ ህዝብ ይህን ተምሳሌታዊ ቀብር ሲያካሂድ እንዲሁ ‹‹የተቃውሞ መንገድን ለማሳመር›› እንደሚያደርገው አስባችሁ ከሆነ በእርግጥም የበደል ክምር እይታችሁን ጋርዶታል፡፡ አዎን! ይህ ተምሳሌታዊ ቀብር በእርግጥም ተፈፅሟል፡፡ ከዚህ በኋላ ከዚህ የሙት መንፈስ ጋር ሚሊዮኖች ግንኙነት የለንም፡፡ ከዚህ የሙት መንፈስ ጋር አብሮ ሊሰራ የሚችለው የኢ-ዴሞክራሲያዊ ቋንቋውን ሊረዳው የሚችል አካል ብቻ ነው፡፡ ያንን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ቋንቋ ለመናገር አንደበቱን የሚያላውስ ኅብረተሰብ የለንም፡፡ ኅብረተሰባችን ኢ-ፍትሀዊነትን አምርሮ የሚታገል መንፈሰ ብርቱ ነውና፡፡

እኛ የዛሬ የበደልን ግፍ ያስተናገድን አማኞች የዛሬውን ስቃያችንን አሳንሶ የሚያይ ህሊና ፈፅሞም አይኖርም፡፡ ግና ዛሬም ይህ የአላህ መንገድ መሆኑን ከማውሳት አንቆጠብም፡፡ ከአላህ ቃልም የበለጠ ማፅናኛ ከወዴት ይገኛል? - (213) أَمْ حَسِبْتُمْ أَنْ تَدْخُلُوا الْجَنَّةَ وَلَمَّا يَأْتِكُمْ مَثَلُ الَّذِينَ خَلَوْا مِنْ قَبْلِكُمْ مَسَّتْهُمُ الْبَأْسَاءُ وَالضَّرَّاءُ وَزُلْزِلُوا حَتَّى يَقُولَ الرَّسُولُ وَالَّذِينَ آمَنُوا مَعَهُ مَتَى نَصْرُ اللَّهِ أَلَا إِنَّ نَصْرَ اللَّهِ قَرِيبٌ (214) ‹‹በእውነቱ የነዚያ ከበፊታቸው ያለፉት ምእመናን መከራ ቢጤ ሳይመጣባችሁ ገነትን ልትገቡ ታስባላችሁን? መልእክተኛውና እነዚያ ከርሱ ጋር ያመኑት ‹‹የአላህ እርዳታ መቼ ነው?›› እስከመቼ ነው እስከሚሉ ድረስ መከራና ጉዳት ነካቻቸው፤ ተርበደበዱም፡፡ ንቁ! የአላህ እርዳታ ቅርብ ነው!› ተባሉም!›› ሱረቱል በቀራ አንቀጽ 114

እኛ የዛሬ የበደልን ግፍ ያስተናገድን አማኞች የዛሬውን ስቃያችንን አሳንሶ የሚያይ ህሊና ፈፅሞ አይኖርም፡፡ ግና ዛሬም ይህ ብቸኛ የትግል መንገድ መሆኑን ከማስታወስ ወደኋላ አንልም፡፡ እንኳንስ የዜጎችን ቅሬታ ለማድመጥ ጆሮ በሌላቸው በዳዮች ላይ በሚደረግ ተቃውሞ ቀርቶ የሰላሙን መንገድ እስልምናን ለመስበክ በመጣራቸው ብቻ ታላቁ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ደምተዋል፤ ተሰቃይተዋልም! እኛም እስከ ድል ዋዜማ መድማታችንን እንቀጥላለን፡፡ 

እኛ የዛሬ የበደልን ግፍ ያስተናገድን አማኞች የዛሬውን ስቃያችንን አሳንሶ የሚያይ ህሊና ፈፅሞም አይኖርም፡፡ ግና ዛሬም ድል ቅርብ እንደሆነች እናውቃለን፡፡ እንኳንስ እኛ አግርቶልን ከፊል በትራችሁን ቀምሰን የተረፍነው ቀርቶ ዛሬ በአሰቃቂ ሁኔታ በወህኒ የምታንገላቷቸው ሺዎችን ብትጠይቋቸው ‹‹ፅኑ ነን!፤ ፅናታችን በዳዮችን አንበርክኳል! ድላችንም ቅርብ ነች!›› ይሏችኋል፡፡ 

በሰላማዊ ትግላችን ምክንያት ከዘለፋ እስከ ነፍስ ግድያ ያስተናገድንና ያስተናገዱ፣ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ምንዳችንን አላህ አብዝቶ እንዲከፍለንና የከፈልነውን መስዋእትነትም ከንቱ እንዳያስቀርብን ኃያሉ ፈጣሪያችንን እንለምናለን! እርሱ የሚለምኑትን ሰሚና ተቀባይ ጌታ ነውና!

አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment