ሐምሌ 29 ቀን 2005 ዓ.ም.
ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 26 ቀን የወያኔ ወታደሮች በሙስሊም ዜጎቻችን ላይ ያካሄዱትን የጅምላ ግድያ ኢሕአፓ በጥብቅ እያወገዘ ወንጀሉን ያዘዙትና ድርጊቱን የፈጸሙትም ባስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ይጠይቃል። በግፍ የታሰሩባቸው የሃይማኖት አባቶች (ኢማሞች) እንደፈቱላቸው ከዋቤ ከተማ ወደኮፈሌ ሲጓዙ በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የወያኔ ወታደሮች አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ የእሩምታ ተኩስ ከፍተው አንድ ህጻንን ጨምሮ በርካታ ዜጎቻችን የገደሉ ሲሆን በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ያቆሰሉ መሆናቸው ታውቋል። በሻሸመኔና በሌሎች ከተሞች በድርጊቱ ተበሳጭተው ሰላማዊ ተቃውሞ ያደርጉ በነበሩ ወገኖች ላይም የወያኔ ወታደሮች ተኩስ ከፍተው በርካታ ሰዎችን የገደሉ መሆናቸው ታውቋል። ባጠቃላይ በሁሉም ቦታዎች ከ 25 በላይ የሚሆኑ ወገኖቻችን መገደላቸው እንዲሁም የቆሰሉት ሆስፒታል የገቡ መሆናቸውና ሌሎች በሺ የሚቆጠሩ ተይዘው እስር ቤቶች ውስጥ የተወረውሩ መሆናቸው ታውቋል።
የወያኔ አምባገነነ አገዛዝ የተመሰረተውም ሆነ ህይወት አግኝቶ ተጠናክሮ እየቀጠለ ያለው ወገኖቻችንን በመግደልና በመጨፍጨፍ መሆኑን ያለፉት 21 የግፍ ዘመናት አሳይተውናል። የሕግ የበላይነትን ማስጠበቅ፤ የዜጎችን መብት ማክበር ፤ ሰላማዊ ለሆኑ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ መመለስ ወዘተ… በአምባገነኑና ዘረኛው አገዛዝ የሚታወቁ አይደለም። ወያኔ የሚያውቀው ቋንቋ፤ ግድያ እስራት ጭፍጨፋ ነው። ስለዚህም ነው 18 ወራትን ያስቆጠረው የሙስሊሙ ኅብረተሰብ በሰላማዊ መንገድ ለጠየቀው ጥያቄ መሪዎችን ጨምሮ በርካታ ሙስሊሞችን በማሰርና ንጹህ ዜጎችን በመግደልና በመጨፍጨፍ ወያኔያዊ መልስ እየተሰጠ ያለው። የሰሞኑ የወያኔ አገዛዝ አረመኔያዊ ድርጊት በጽኑ መወገዝ ያለበት ቢሆንም ድርጊቱን በማወገዝና ተቃውሞን በማሰማት ብቻ የወያኔ አረመኔያዊና ጸረ ሕዝብ ጭፍጨፋ ማስቆም አይቻልም። የሕዝብን ስቃይና በደል ለአንዴም ለሁሌም ማስቆም የሚቻለው ሁለገብ በሆነ መንገድ ታግሎ አገዛዙን ከስልጣን ማስወገድ ሲቻል ስለሆነ የአገር ፍቅር የሚሰማው ዜጋ ሁሉ ኃይሉን አስተባብሮ በአረመኔው አገዛዝ ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር እንደወትሮው አሁንም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የወያኔን አምባገነነ አገዛዝ በተባበረ ትግል እናስወግድ!
ኢሕአፓ
No comments:
Post a Comment