ፍርሃትን ማንገስ የተለመደ የአምባገነኖች የመጨቆኛ መሣሪያ ነው። ፍርሃት ለተወሰነ ጊዜ ዜጎች ተዋርደው፣ ተረግጠውና ተቀጥቅጠው እንዲገዙ የማድረግ አቅም አለው። ሆኖም ግን ፍርሃት ያቆመው ሥርዓት ለመናድ ጊዜ አይፈጅበትም። ፍርሃት ያቆመው የበርሊን ግንብ በሰዓታት ውስጥ መፈራረሱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በአገራችንም ቢሆን በፍርሃት ለመግዛት ሞክረው ለጥቂት ዓመታት የተሳካላቸው አምባገነኖች ሁሉ አስከፊ ውድቀትን ወድቀዋል። የወያኔም ውድቀት ተመሳሳይ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለኝም።
በየእለቱ እየጠነከረበት ያለው የፍርሃት በሽታ ገዢውን መንግስት አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ ሊያስገባው እንደሚችል መገመት ይቻላል። በዚህም ምክንያት በሕዝብ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።በአሁኑ ወቅት በሙስሊም እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ገዢው መንግስት በከባድ ፍርሃት እየራደ የሚይዘው፤ የሚጨብጠው ማጣቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ይህንን ተጋፍጦ ለማሸነፍ በራስ የመተማመን ሃቅምን ማጐልበትና እስከ መስዋዕትነት መዘጋጅትን ይጠይቃል። በራስ መተማመን የጎደለው ማኅበረሰብ ችግሮቹን ፈትቶ ወደፊት ለመራመድ ያለው አቅም በእጅጉ የተወሰነ ስለሆነ ነው።
ስለዚህ በፍርሃት ላይ መዝመት የሚኖርብን ዛሬ ነው። በፍርሃት ምክንያት ወዳጅን አሳልፎ ለወያኔ መስጠት በፈጣሪም፣ በእውነትም፣ በሕዝብም በታሪክም የተነቀፈ አስፀያፊ ተግባር ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል። ከአሁን በኋላ ይህንን መታገስ ፈጽሞ አይኖርብንም። አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ራሳቸውን በወያኔ የድርጅት፣ የስለላ ወይም የመጨቆኛ ተቋም ውስጥ ያገኙ ወገኖቻቸን ሰልፋቸውን ፍትህና ነፃነትን ከተጠማው ሕዝብ ጋር ማድረግ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ። ይህ ከሆነ የኢትዮጵያችንን ትንሳኤ ለማየት ሩቅ ጊዜን ማለም አይኖርም። ለመጭው ትውልድም ነፃነትና ፍትህ የሰፈነባት ታላቋ ኢትዮጵያን በማስረከብ በታሪክ መዝገብ እራሳችንን ፅፈን ማለፍ እንችላለን።
ድል ለጭቁኑ ህዝብ!
ኢትዬጵያችን በክብር ለዘላለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment