Written by ናፍቆት ዮሴፍ
“መረጃው የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ነው” የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት
ዘንድሮ ብቻ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት በዳኝነት ሙያ ያገለግሉ የነበሩ መቶ ዳኞች ስራ መልቀቃቸውን ምንጮች ገለፁ፡፡ ከ86 በላይ ዳኞችም የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው መልስ እየተጠባበቁ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ የኔነህ ስመኝ በበኩላቸው፤ መረጃው የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ “እንደማንኛውም መስሪያ ቤት አንዳንድ መልቀቂያዎች ይገባሉ፤ ይስተናገዳሉ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በተጠቀሰው መጠን ዳኞች ስለመልቀቃቸውም ሆነ መልቀቂያ ስለማስገባታቸው የማውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡
ዳኞቹ በደሞዝ ማነስ ፣በጥቅማጥቅም ማጣት፣በእርከን እድገት አለመኖርና በስራቸው ላይ በሚደርስባቸው ጣልቃ ገብነት ከስራ ለመልቀቅ መገደዳቸውን ምንጮቹ ገልፀው፣ በቅርቡ የገቡ መልቀቂያዎች ከሶስት ወር በፊት እንደማይስተናገዱ እየተነገራቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “በክልላችን የዳኛ ደሞዝ ከፖሊስ ደሞዝ ያንሳል” ያሉት አንድ ስራ የለቀቁ ዳኛ፤ የፖሊስ የስራ ሂደት 2800 ብር ደሞዝ ሲያገኝ ዳኛ ግን 2639 ብር ብቻ እንደሚያገኝ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የዳኝነት ስራ የህሊና ስራ እንደመሆኑ አንድ ዳኛ ለአድልኦና ለጉበኝነት እንዳይጋለጥና ፍትህ እንዳያዛባ ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩለት ይገባል ያሉት ምንጮቹ፤ በክልሉ ይህ ስለማይመቻች ፍትህ ከማዛባት ስራውን መልቀቅና መቸገር ይሻላል በሚል ዳኞች ስራ እንደለቀቁና ሌሎችም ለመልቀቅ ማመልከቻ እያስገቡ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ም/ቤቱ የዳኞች በብዛት መልቀቅ ስላሳሰበው ስብሰባ ካደረገ በኋላ ዳኞች በስራቸው ላይ እንዲቆዩ ጭማሪ ይደረግላቸው ብሎ መወሰኑን የጠቆሙ ሌላ ሥራ የለቀቁ ዳኛ፤ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላሉት 500 ብርና ከዚያ በላይ ሲጨመርላቸው ታች ሆነው ብዙ ለሚሰሩትና ለሚደክሙት ግን በ150 ብር ጭማሪ ብቻ መሸንገላቸው ዳኞችን አበሳጭቷቸዋል ብለዋል፡፡ ይህም ለመልቀቃቸው ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ፍ/ቤቱ በየአመቱ ከስልጠና ማዕከል የሚወጡ ዳኞችን እንደሚቀበል የገለፁት ምንጮቹ፤ እነዚህ ዳኞች ሲቀጠሩ በፍ/ቤት ሁለት አመት የማገልገል ግዴታ እንዳለባቸውና ሁለት አመቱን ሳይጨርሱ ከለቀቁ 50 ሺህ ብር እንደሚቀጡ ጠቁመው፤ ሙያተኛው ላይ የሚደረግ ጫና መቆም አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “ከሙያው ስነ-ምግባር የተነሳ ዳኛ ትርፍ ስራ መስራት አይችልም” ያሉት እነዚሁ ዳኞች፤ በዚህ የተነሳ የዳኛው ህይወት ከኑሮ ውድነቱ ጋር መጣጣም አልቻለም ብለዋል፡፡ በሌላው የመንግስት መስሪያ ቤት የተለያዩ ማበረታቻዎችና የደሞዝ እርከን ጭማሪ እንደሚደረግ ጠቁመው፣ በፍ/ቤት አካባቢ ይህ አይነት አሠራር የለም፣ አስር አመት የሰራም ሆነ ዛሬ የተሾመ ዳኛ እኩል ደሞዝ ነው ያላቸው ብለዋል፡፡
No comments:
Post a Comment