ሳስበው ሳስበው ስለ ‘መለሲዝም’ ሰበካ የተጀመረ ይመስለኛል። በመለስ ማመናቸው ችግር የለብኝም። ግን መለስ ፈጣሪያቸው መሆኑ እየነገሩን ነው። ብዙ ነገሮች በሱ ስም እየተሰየሙ ናቸው። እነሱ እንደሚነግሩን ከሆነ የኢህአዴግ ፖሊሲ የመለስ ነው፣ መለስ ወታደራዊ መሃንዲሳቸው ነበር፣ መለስ አንቀሳቃሽ ሞተራቸው ነበር፣ የኢህአዴግ ሓሳብና ተግባር የመነጨው ከመለስ ነበር፣ ባጠቃላይ መለስ ሁለመናቸው ነበር።
ለዚህም ነው የኢህአዴግ አባላት አውቀውም ሳያውቁም መለስ የተናገረውን እንደ ፓሮት የሚደግሙት። በራሳቸው ማየት ሳይችሉ መለስ በመራቸው ይጓዛሉ። ለዚህም ነው መለስ ያወጣውን ፖሊሲ መተግበር የማይችሉ። ፖሊሲው መተግበር ያልቻሉበት መንገድ ማየት ስለሚሳናቸው ፖሊሲው ጥሩ መሆኑ ተናዘው ችግሩ ያለው ግን አፈፃፀሙ ላይ መሆኑ ይለፍፋሉ።
ግን አንድ ትክክል ወይ ጥሩ የሆነ ፖሊሲ እንዴት ላይፈፀም ይችላል? ፖሊሲ’ኮ አፈፃፀም ነው። ፖሊሲ ከህልም የሚለይበት ዋነኛው መስፈርት ስለሚፈፀም ነው። ስለዚህ አንድ ፖሊሲ አፈፃፀም ላይ ችግር ካጋጠመው ፖሊሲው ትክክል አይደለም ማለት ነው። ግን የመለስ ልጆች ‘ፖሊሲው ስህተት ነው’ ብለው የማጋለጥ ዓቅሙና ድፍረቱስ አላቸው? አይመስለኝም። ምክንያቱም ፖሊሲው የመለስ ነው። ፖሊሲው ስህተት እንደሆነ መናገር ማለት መለስ እንደሚሳሳት መመስከር ነው። መለስ ደግሞ ፈጣሪያቸው ነው። ለዚህም ነው ከነ ስህተቱ ‘የመለስ ሌጋሲ ወይ ራእይ’ እያሉ የመለስን የተሳሳተ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅጣጫ ለማስቀጠል የሚባዝኑ።
ከኢህአዴግ አባላት የምስማማበት ነጥብ አለኝ፤ መለስ ሁለመናቸው ነው። እሱ የተናገረውን ያደርጋሉ፣ ይፈፅማሉ። ከነሱ ጋር የምስማማበት ነጥብ ይሄ ነው። ይሄንን ነጥብ ትርጓሜ እንስጠው።
የኢህአዴግ አባላት (እነሱ ራሳቸው እንደሚነግሩን) መለስ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ዕይታ ምንጫቸው ነው። አዎ! ነው። ይህ ማለት አባላቱ ምን መስራት እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው መለስ ይነግራቸው ነበር ማለት ነው። እነሱም ‘የታላቁ ባለራእይ መሪ’ ትእዛዞች ተቀብለው ይተገብሩ ነበር ማለት ነው።
የመለስና የአባላቱ ግንኙነት እንዲህ ከነበረ መለስ dictate ያደርጋቸው ነበር ማለት ነው። በእንግሊዝኛው አጠራር ሌሎችን dictate የሚያደርግ መሪ Dictator ይባላል። ስለዚህ ከተግባራዊ ትርጓሜው ተነስተን መለስን ስንገልፀው Dictator ነበር ማለት ነው። “Dictator’ ወደ አማርኛ ስንመልሰው ‘አምባገነን’ (ብትግርኛ ‘ዉልቀ መላኺ’) የሚል ትርጓሜ ይይዛል። ስለዚህ ‘ሁሉም ወይም አብዛኞቹ የፓርቲው ስራዎች የመለስ ነበሩ’ በሚል ከተስማማን ‘መለስ አምባገነን ነበር’ በሚልም መስማማት ይኖርብናል።
እኔ ‘መለስ አምባገነን ነበር’ ሲል ‘የሁሉንም አድራጊ እሱ ነበር’ እያልኩኝ ነው። እናንተም በራሳቹሁ ሚድያና አንደበት ተመሳሳይ ነገር እየነገራችሁን ነው። ስለዚህ ሓሳባችን አንድ ነው። ተስማምተናል። በመለስ ስራና ስያሜ ላይ ልዩነት የለንም።
(ስለ መለስ ላለመፃፍ ዕቅድ የነበረኝ ቢሆንም የመንግስት ሚድያዎች ግን ስለሱ እያስታወሱ አስቸገሩኝ)
It is so!!!
No comments:
Post a Comment