Tuesday, April 8, 2014

የትምህርት ጥራት መውደቅ እስከ በነርሶች የሚማሩ “ዶክተሮች” …..The case of Adigrat University:

በሴቭ አድና

በሀገራችን ስላለው አሳሳቢና ትውልድ አምካኝ የሾቀ የትምህርት ጥራት ባወራን ቁጥር አንዳንድ ሰዎች አይ መጀመርያ ብዛት ይምጣና ከዚያ ቀስ ብሎ ጥራት ይመጣል የሚል መከራከርያ ሲያቀርቡ ስሰማ ይገርመኛል፡፡
አንድ ሰው ከታች ከመሰረቱ በቂ ነገር ሳይዝ ከመጣ እንዴት ነው እላይ የስተካከላል ተብሎ የሚጠበቀው በመጀመርያ ዲግሪ ትምህርቱ እውቀቱ ዜሮ፣ የማወቅ ፍላጎቱ የተገደለበት ሚስኪን፣ በራሱ የማይተማመን፣ የእውቀትንና የትምህርትን ዋጋም የማይገነዘብ፣ እንደማያውቅ እራሱ የማያውቅ ሁኖ የወደፊቱ ህልሙና አላማው ገደል ገብቶበትና “መማር ማለት ያለእውቀት ወረቀት ነው” ወደሚል ድምዳሜ የደረሰ የመከነ የነበረውን passion ሁሉ እንድያጣ የተደረገ ባለዲግሪ፤
ይኸው እውቀትም የሌለው፣ የማወቅ ተነሳሽነቱም የተቀማ ባለዲግሪ እሱም በተራው ሌላ የዲግሪ ተማሪዎችን በሚያስተምርበት ሁኔታ ሌሎች በርካታ አእምሮዎችን ከሱም በባሰ መልኩ በሚያቀጭጭበት ሁኔታ፤ ሀይስኩልም ቢያስተምር እንዲሁ መደደብና እውቀትን መጥላት የሚባሉ በሽታዎችን ለታዳጊዎች በሚያስተላልፍበት ሁኔታ……ሂደቱ እንዲህ እየቀጠለ እንዴት ነው በሂደት ጥራት የሚገኘው?

ይህ ሰው የማስተርስ ፕሮግራም ተብሎ ትምህርት ቢላክም በሶስት፣ አራት፣ አምስት ዐመት የትምህርት ሂደት ቀጭጮ የነበረውን እውቀቱና የማወቅ ሞራሉ በ 1 ዐመት የማስተርስ ፕሮግራም ይቃናል ብሎ እንዴት ይጠበቃል(ተጨማሪ 6 ወሯ ያው የ”ሪሰርች” ጊዜ ናት)? በየዩኒቨርሲቲው በራፍ የተኮለኮሉት የ”Research proposal and Thesis ስራዎችን እናማክራለን” የሚሉት ድርጅቶችስ ይሀንን የማስተርስና የፒኤችዲ ጥናት ወረቀቶች በ3ና 5 ሺህ እየቸበቸቡ አይደለም? እናስ መቸ ነው ይኸ ከታች መክኖ የወጣውን ሰው የሚቃናው?



ሰሞኑ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በነርሶችና በጤና መኮንኖች የሚማሩ “ዶክተሮች” እየተፈበረኩ አይቸ በድንጋጤ ክው ብየ ቀረሁ! በሁሉም የትምህርት ዘርፎች የትምህርቱ ጥራት በአስደማሚ ፍጥነት ቁልቁል እየተፈጠፈጠም የህክምና ትምህርት ቤቶች በተወሰነ መልኩ የመንግስትን ጫና ተቋቁመው ጥራታቸው በተወሰነ መልኩ አስጠብቀው ቆይተዋል፡፡ አሁን መንግስት በህክምና ትምህርት ቤቶችም ዘምቷል፡፡ እንደጂኦግራፊው፣ ኣካውንቲንጉ ወ.ዘ.ተ እሱም ይሙት ነው፡፡ ለ50ና 60 ተማሪ መማርያ ተብለው በተዘጋጁ የህክምና ትምህርትቤቶች በዚያ መሳርያና ሀብት፣ እንዲያውም የሰው ሀይላቸው ሶስትና አራት እጥፍ ሾቆ እያለ 400ና 500 እንዲቀበሉ እየተገደዱ ነው፡፡ በየዩኒቨርስቲውም ያለምንም በቂ መሳርያ፣ የሰለጠነ አስተማሪ፣ ላብራቶሪ ወይ ሌላ ሁኔታ አዳዲስ የህክምና ትምህርትቶች ያለምንም ቁጥጥር እየተከፈቱ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት ዐመታት እንኳ በ13 አዳዲስ ቦታዎች ያለምንም ዝግጅት፤ ያለ አስተማሪ፣ ላብራቶሪዎች፣ መፃሕፍቶች ወ.ዘ.ተ ተከፍተዋል፡፡ እንኳን ስፔሻሊስት ሊያስተምራቸው ጠቅላላ ሓኪም እንኳ ማየታቸውም እንጃ፡

በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያየሁትን ብትሰሙ በእውነት ታዝናላችሁ፣ ስለወደፊቱም በጣም ትፈራላችሁ፡፡ በስራ ጉዳይ ወደ ዐዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሂጀ የህክምና ትምህርት ክፍሉም አይቸ ነበር፡፡ የሕክምና ትምህርት(ሜድሲን) ጀምሯል፡፡ 2ተኛ ዐመትም አድርሷል፡፡ አስተማሪዎቹም ምንም ሀይ ባይ የሌላቸውና ምን እንደሚያስተምሩ የማይታወቁ ህንዶች፣ ኢትዮጵያውያን ነርሶችና የጤና መኮንኖች ናቸው፡፡ በፋካልቲው ውስጥ የነበሩት ሀኪሞች ደግሞ ሶስት ብቻ ሲሆኑ አዲስ ተመራቂ ጠቅላላ ሓኪሞች ናቸው፡፡ ባለው አስተዳደራዊ ብልሹነትና የህክምና ትምህርትን ለማስኬድ ስለማያስችል አንዷ ለቃለች፤ አንዱም ሰሞኑን እየለቀቀ ነው፡፡ ተማሪዎቹ ላብራቶሪ የሚባል ነገር አይተው አያውቁም፡፡ የሬሳ ክፍልም የለም፡፡ አይተውም አያውቁም፡፡ የትምህርቱ ክፍል ሓላፊዎች ከህክምና ሙያ ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸው ሲሆኑ በተደጋጋሚ በሐኪሞቹ ቢጠየቁም እነዚህን የጎደሉ ነገሮችን ለማሟላት ፍላጎቱም የላቸውም ፡፡ ሓኪሞቹ የሚለቁበትም አንድ ምክንያት ሰሚ በማጣታቸውና የዚህን በሰው ህይወት የመቀለድ ወንጀል ተባባሪ ላለመሆን ነው፡፡

አንድም ስፔሻሊስት ሐኪም አልተቀጠረም፡፡ ክሊኒካል አታችመንት ሲጀምሩ ማስተማር ያለበት በደምቡ ቢያንስ ስፔሻሊስት ሓኪም ነው፡ ፡፡ ሌሎች ሀገሮች ላይ ደግሞ ሳብ ስፔሻሊስት፡፡ እዚሁ አዲግራት ግን ያው በኤችኦና በነርስ ሊሰለጥኑ ነው ሓሳቡ፡፡ በነርስ፣ በHOና ምንነታቸው በማይታወቁ ሀይ ባይ የሌላቸው ህንዶች የሚሰለጥኑ “ዶክተሮች”!! እግዚኦ መሐረነ ፈጣሪ፡፡

በስንት ታላላቅ ስፔሻሊስትና ሳብስፔሻሊስቶችና እንዲሁም በተሻለ ሁኔታ እየተማሩ እንኳ ከትምህርቱ ስፋት ፤ትምህርቱ ከሚፈልገው ጥረት፣ የማተርያልና የሰው ሐይል አንፃር “የኢትዮጵያ ህክምና ጥራቱ ጥሩ አይደለም” እየተባለ በሚታማበት ወቅት እዚህ ደግሞ ይባስ ብሎ በነርስና ጤና መኮንን፣ በህንድ የሚሰለጥኑ “ዶክተሮች” እየተፈበረኩ ነው፡፡ ስልጣን ላይ ላሉት ዋናው ለሚድያ ፍጆታ ወይም ለፈንድና ለ“እዩልኝ” ቁጥር ማብዛት ነው፡፡ብዙዎቹን የህክምና ትምህርትቤቶች እንዲከፈቱ የገፋፋው በጊዜው የጤና ጥበቃ ሚ/ር የነበረው የባዮሎጂ ምሩቁ ዶ/ር ቴድሮስም ቁጥርን መጨመርና ይሀንን ያክል አስመረቅን ብሎ ዝናን ማካበት እንጂ ጥራቱ ግድ የሚሰጠው አልነበረም ፡፡
በመኸል ህዝቡ ተጎዳ፡ ትውልድም ለመሰ፣ ቀጨጨ!!እኒያ በጉብዝናቸው ተወዳድረው የህክምና ትምህርት መርጠው የገቡ ወንድሞቻችን እንዲህ ከነርስም ጤና-መኮንንም ምንነቱ በማይታወቅ ህንዳዊ ባለፎርጅድ ወረቀትም ሰልጥነው በእውቀትም ከነሱ በብዙ ያነሱ ሁነው ነገ “ዶክተር” ተብለው ሊወጡ ነው፡፡ እንግዲህ ሀገራችን ውስጥ እየሆነ ያለው ይህ ነው፡፡

በሌላ ሀገር የያንዳንዱ የትምህርት ጥራትና የሙያ ብቃት የሚከታተል፣ ስልጠና ለመጀመርም የሚፈቅድ በዚያ ሙያ ውስጥ ያሉ ታላላቅ ባለሙያዎች አንድ ላይ በመሆን የሚያቋቁሟቸው የሙያ ማህበራት ከመንግስት ጋር በመሆን ነው፡፡ እዚህ ግን ማንም የዩኒቨርሲቲ ሹም ተነስቶ ትንሽ ፈንድ ለማግኘት ብቻ የሰው ሀይል ቢኖርም ባይኖርም፣ ማተርያሎች ቢሟሉም ባይሟሉም የፈለገውን ትምህርት ያስጀምራል፤ የፈለገው ዲግሪም ያድላል!! የሙያ ማሕበራትማ እንዲቀጭጩና ብዙዎቹም እንዲጠፉ ተደርገው የለ እንዴ! ያሉትም ለስም ብቻ ነው!

ሰዎች፡ ይህ አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት፡፡ የዐዲግራቱ ምሳሌ በሀገሪቱ በመላ እየተከናወነ ያለ አሳዛኝ እውነታ ነው፡፡ እግዚሀር ይይላችሁ፡ አሁን ከላይ ያሉት ዶክተሮች በስራ ዐለም ወጥተው ሰውን እየገደሉ ነው ጥራት የሚመጣው! እረ ሰዎች እሪ እንበል!

No comments:

Post a Comment