ለኢትዮጵያው ፋሽስታዊ አገዛዝ እጅግ ከፍተኛውን የእውቀት፣ የአይነትና የገንዘብ እገዛ በማድረግ የሚታወቀው የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ አገዛዙ በሀገሪቱ እጅግ የገዘፈ የሰብአዊ መብት ረገጣ ያሰፈነ መሆኑን ምስክሮችን አስቀርቦ በማዳመጥና የአባላቱን የግል ትዝብት በመጨመር ከፍተኛ ትችት መሰንዘሩ ተሰማ።
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙትን የማእከላዊና ቃሊቲ ወህኒ ቤቶችን ጨምሮ በኦጋዴንና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች አገዛዙ እያደረሰው ያለውን አፈና፣ ግርፋት፣ ያለምክንያት ማሰር፣ ግድያና አስገድዶ መድፈር ምስክርነት በዝርዝር ያደመጠው የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ በገፍ እያፈሰስን ያለነው አመታዊ የገንዘብ እገዛም በትክክለኛው መንገድ እየዋለ ካለመሆኑም በተጨማሪ ለሙስና የተጋለጠ ነው በማለት አስረግጦ ተወያይቷል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የሰብአዊና የልማት ርዳታ ከሚወስዱት ሀገራት ቀዳሚዋ መሆኗን በአንክሮ የገለጸው ይህ የአወሮፓ ሕብረት ፓርላማ ውይይት፤ ይህ ሁሉ እገዛ ያላግባብ በዘፈቀደ ሲውል፣ ለሙስና ሲጋለጥና ከዚያም በላይ ከታለመለት ዓላማ ውጭ ለአገዛዙ የፖለቲካ ፍጆታ ለፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ማሰባሰቢያነት እንዲሁም ተቃዋሚዎችን ለማጥቂያነት ሲውል በአዲስ አበባ የሚገኙ የምራባዊያ ሀገሮች ዓለማቀፍ ተቋማትም ሆኑ ኤምባሲዎቻቸው ምንም አለማለታቸውና ነገሩን እንደቀላል መተዋቸው በጣም አሳፋሪ ነው ይህ ደግሞ ከአውሮፓ ሕብረት ህግና መመሪያ ተቃራኒ ነው ሲል አማሯል።
ምስክርነቱን ያደመጡና የምስልና የጽሁፍ ማስረጃዎችን የተመለከቱ አንዳንድ የፓርላማው አባላት እነዚህ ማስረጃዎች በኢትዮጵያው አገዛዝ ላይ ከፍተኛ ማእቀብ ለመጣል ከበቂ በላይ ስለሆኑ የኢኮኖሚ ማእቀብ መጣል ይገባናል ሲሉ የተደመጡ ሲሆን የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ከፍተኛ አመራሮችና ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው የፓርላማው አባላት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት የሰጡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የእርዳታ ገንዘብ አሰጣጥንና አጠቃቀሙን በተመለከተ በሕወሃት መራሹ ወያኔ ላይ አሳሪ ህግ ያጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የቀድሞ ከፍተኛ አማካሪና አሁን በስደት የሚገኙት አብዱላሂ ሁሴን እንዲሁም በስዊድን ጋዜጠኛና በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ የነበረው ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብዬ ለፓርላማው ምስክርነታቸውን የሰጡ መሆኑ ተያይዞ ተገልጿል።
No comments:
Post a Comment