የጉጅሌው ወያኔ አገዛዝ ያረቀቀው የይስሙላ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 87 የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና የሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ሲሆን አገዛዙ ላለፉት 19 ዓመታት ራሱ ህዝብን በማጭበርበር ረጅም እድሜ ለመግዛት ይረዳው ዘንድ ያረቀቀውን የህገ መንግስቱን አንቀጽ በመጣስ በተለይም በመከላከያው አመራር ላይ የአንድ ብሄር የበላይነት በማስፈን ስልጣኑን ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጉጅሌው ወያኔ የመከላከያ ሚኒስተር ተብየ ሲራጅ ፈጌሳ ለወያኔው አሻንጉሊቱ ፓርላማ የ2006ን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ የሠራዊቱ የብሔር ተዋጽኦ እየተመጣጠነ መምጣቱን በመደስኮር ለማስረጃነትም ከአጠቃላይ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት የአማራ ብሔር ተዋጽኦ 29.46 በመቶ በመሆን በቀዳሚነት እየመራ ይገኛል ሲል የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተዋጽኦ 25.05 በመቶ በመሆን በሁለተኛ ደረጃ፤ የኦሮሞ ብሔር 24.45 በመቶ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል፤ የትግራይ ብሔር ተዋጽኦ ወደ 17.47 በመቶ በመውረድ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲል ዳግም ህዝብን ለማደናገርና ለአገዛዙ እንዲመች ተደርጎ በውሸት የተቀሸረ የቅጥፈት ሪፖርቱን አሰምቷል።
የጉጅሌው ወያኔ አገዛዝ በመከላከያ ሰራዊቱ የአመራሩ ክፍል የብሄር ተዋጽኦ እስካልተመጣጠነ ድረስ ታች ባለው የሰራዊት አባል የቁጥር ጋጋታ ብቻ ‹‹ተዋጽኦውን አሟልተናል›› ብሎ መደስኮር ዳግም አገዛዙ ለህዝብ ያለውን ንቀት ከማሳየቱ ውጭ ሌላ ምንም ትርጉም አይሰጥም። የመከላከያ ሰራዊቱ አመራር በአንድ ብሄር የተሞላና የብሄር ተዋጽኦን በማማከል የተገነባ አለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
የዛሬ ሁለት አመት ግንቦት ሰባት በኢትዮጵያ መላከያ ሰራዊት ዉስጥ የተዘረጋዉን የወያኔ የዘረኝነት መረብ አደረጃጀት በመረጃ በማስደገፍ ለህዝብ ማቅረቡ ይታወሳል። ግንቦት ሰባት በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ያለውን የወያኔን ዘረኝነት የሚያጋልጡ መረጃዎችን ከራሱ ከወያኔ ጓዳ እየፈለፈለ አዉጥቶ ለህዝብ የሚያቀርበዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን ዘረኝነት አያውቀዉም በሚል አስተሳሰብ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በየቀኑ ደሙን እንደ መዥገር የሚመጠዉን ወያኔን የመሰለ የጀርባ ላይ አጥንት ተሸክሞ መኖር የለበትም ብለን ስለምናምንና እንደዚህ ህዝብ በገዛ አገሩ “እኩል አደረግንህ” ብለዉ በሚነግሩት ከሀዲዎች ቅኝ አገዛዝ እየተገዛ መሆኑን ደግመን ደጋግመን ለማሳወቅ ነዉ።
No comments:
Post a Comment