Saturday, April 19, 2014

ግድብ እያፈረሱ ጎርፍ መከላከል አይቻልም !!!

ዘረኛዉ የወያኔ ዘገዛዝ በ2002 ዓም “አኬልዳማ” የዛሬ ሁለት አመት ደግሞ “ጂሀዳዊ ሀረካት” የሚባሉ ሁለት አስጸያፊ ድራማዎችን ሰርቶ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማታለል የሞከረዉ ወያኔ በያዝነዉ ሳምንት መግቢያ ላይ ደግሞ ሌላ “የቀለም አብዮት” የሚባል ቂላቅል ድራማ ሰርቶ ለለዉጥ የተዘጋጀዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ቀለብ ለመስለብ ጉድ ጉድ ማለት ጀምሯል። ይህ በኪነጥበብ የፈጠራ ስራዉ ሳይሆን እንደማሞ ቂሎ በተፈጥሮዉ አስቂኝ የሆነ የዉሸት ድራማ የሚያሳየን ወያኔ በስልጣን ላይ ለመቆየት የማያደርገዉ ምንም ነገር አለመኖሩን ብቻ ነዉ። ይህንን ድራማ ከአኬል ዳማና ከጅሀዳዊ ሀረካት የሚለየዉ አንድ ነገር ቢኖር በዚህ ድራማ ዉስጥ ዋና ዋናዎቹ ተዋናንያን የተለመዱት የኢቲቪ ካድሬዎች ሳይሆኑ ሳይማሩ ምሁር የሚል ስያሜ የተሰጣቸዉ ሁለት ወጣት ካድሬዎችና የዉሸት እመቤት በመባል የምትታወቀዉ አዛዉንቷ እሟሆይ ሚሚ ስብሀቱ መሆናቸዉ ብቻ ነዉ።

ወያኔ በአኬልዳማ ድራማ ጥላሸት ለመቀባት የሞከረዉ ግንቦት ሰባትን የመሳሰሉ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ለህዝቦቿ መብት መከበር በህይወታቸዉ የቆረጡትን የህዝብ ወገኖች ሲሆን፤ ጅሀዳዊ ሀረካት ደግሞ የአገርና የህዝብ ጠላት አድርጎ የሚያቀርበዉ የማምለክ መብታችን ይከበር ብለዉ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ያቀረቡትን የኢትዮጵያ እስልምና እምነት ተከታዮችን ነዉ። እንደተለመደዉ በዉሸት ታጅቦ ከሰሞኑ ብቅ ያለዉ ሦስተኛዉ የወያኔ ድራማ ደግሞ ከ85 በመቶ በላይ የሚያወራዉ ስለኢትዮጵያ ሳይሆን ዩክሬይን፤ ጆርጂያ፤ ሰርቢያና ኪርግስታን ዉስጥ ስለተካሄዱት ህዝባዊ የለዉጥ እንቅስቃሴዎችና ስለቀድሞዉ የቬኑዝዌላ መሪ ስለ ሁጎ ሻቬዝ ነዉ። የድራማዉ አቢይ መልዕክት ደግሞ የቀለም አብዮት ልማትን የሚጻረርና አገርን የሚጎዳ ስለሆነ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሞከር የለበትም የሚል ነዉ። በዚህ የሞኞች ድራማ ዉስጥ ምሁርና ተንታኝ ሆነዉ የቀረቡትን የጂማ ዩኒቨርሲቲዉን መርከብ ነጋሽንና የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የሰላምና የልማት ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆነዉን አቤል አባተን አደብ ገዝቶ የተከታተለ ሰዉ እነዚህ ወያኔዎች ሌላ ቢቀር የተማረ ሰዉ አጠገባቸዉ የለም እንዴ የሚያሰኙ ብዙ ነገሮችን መታዘብ ይችላል። በእርግጥም መርከብና ነጋሽና አቤል አባተ ኢትዮጵያ ዉስጥ ጭነት የተሸከመዉን አህያ እየመራ ወደ ገበያ የሚወስደዉ ገበሬዉ ሳይሆን በተቃራኒዉ ገበሬዉን እየመራ ወደ ገበያ የሚወስደዉ አህያዉ መሆኑን በማያወላዳ መልኩ አሳይተዉናል። እነዚህ ሁለት በጥንቃቄ ተመርጠዉ የመጡ የወያኔ ካድሬዎች እንዲህ ነበር ያሉት ።


በድራማዉ የመጀመሪያ ክፍል ዉስጥ የቀለም አብዬት ምዕራባዉያን መንግስታት በታዳጊ አገሮች ዉስጥ ጣልቃ ለመግባት የሚጠቀሙበት መሳሪያ ነዉ አንጂ የህዝብ ምሬት የወለደዉ ወይም አገር በቀል ክስተት አይደለም ሲሉ የከረሙት ምሁር ተብዬዎቹ መርከብ ነጋሽና አቤል አባተ በድራማዉ የመጨረሻ አካባቢ በማንኛዉም አገር ዉስጥ ሙሰኝነት ከነገሰ፤ ህብረተሰቡ ያለዉን መንግስት ዬኔ ነዉ ብሎ ካላመነ፤ ህዝብ በዲሞክራሲ ሂደቱ ዉስጥ ካልተሳተፈ፤ የፖለቲካዉ ስርዐት አግላይ ከሆነና በብሔራዊ ኤኮኖሚዉ ተጠቃሚ የሚሆኑት ጥቂቶች ብቻ ከሆኑ የቀለም አብዮት መከሰቱ አይቀርም እያሉ እራሰቸዉን የተናገሩትንቃል እራሳቸዉ መልሰዉ ሲያፈርሱት ይታያሉ። እነ አቤል አዙረዉ የማያዩ ጋሪ ፈረሶች ስለሆኑ ነዉ አንጂ እነዚህ አብዮት ያስሳሉ ያሏቸዉ ነገሮች ሁሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በግልጽ የሚታዩ ነገሮች ናቸዉ።

የእነዚህ ሁለት የወያኔ ቡችላዎች ጉድ በዚህ ብቻ አያበቃም። የሩሲያዉን አምባገነን ቪላድሚር ፑቲንንና ሟቹን የቬኑዝዌላ ፕሬዚዳንት ሁጎ ቻቬዝን አንደ ህዝብ መብት ተሟጋች ብሄራዊ ጀግና አድርገዉ ስስሏቸዉ ይታያሉ። ባጠቃላይ ይህ ምስቅልቅሉ የወጣ የወያኔ ድራማ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ምዕራባዉያን መንግስታት ለቀለም አብዮት የሚያስቧት አገር መሆኗን ይናገርና፤በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ የምዕራባዉያን የቀለም አብዮት ያልተሳካዉ እንደ ሌሎቹ አገሮች ለምዕራባዉያን የሚታዘዙና በሙሰኝነት የተጨማለቁ መሪዎች ባለመኖራቸዉ ነዉ ይላል። መቼም የወያኔ መሪዎች ሙሰኞች አይደሉም ሲባል አንኳን አንጡራ ኃብቱን የተዘረፈዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘራፊዎቹ የወያኔ መሪዎችም ቢሆኑ እዉነት ነዉ ብለዉ የሚቀበሉ አይመስለንም። ኢትዮጵያ ሙሰኝነት የነገሰባት አገር ናት፤ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠሩት እፍኝ የማይሞሉ የትግራይ ልህቃን ናቸዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በጉጂና በጌዲኦ፤ በቦረናና በጋሪ ወይም በኦሮሞና በጉሙዝ ብሄረሰቦች መካከል ግጭት ተፈጠረ ሲባል የተለመደ ነገር ነዉና የሚደነግጥ ሰዉ የለም። እንግዲህ እንደዚህ አይነቱን አፍንጫቸዉ ስር በየቀኑ የሚፈጸመዉን በደል ማየት የተሳናቸዉ ሚሚ ስብሀቱ፤ አቤል አባተና መርከብ ነጋሽ ናቸዉ በአስር ሺዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሰለሚገኙ አገሮች ሙሰኝነትና የብሄር ብሄረሰቦች ግጭት የሚነግሩን . . . ለካስ “ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነዉ” የሚሉት ተረት አለምክንያት እልተተረተም።

የወያኔ ፍርፋሪ ሆዳቸዉን ሞልቶ አይናቸዉን የሸፈነባቸዉ አቤል አባተና መርከብ ነጋሽ ቁልጭ ብሎ የሚታይ እዉነት ተሰዉሮባቸዉ ነዉ እንጂ የወያኔ አገዛዝ በነፃ ገበያና በሶሻሊዝም መካከል ግራ ገብቶት የተገተረ የምዕራባዉያን የቤት ዉስጥ ሰራተኛ ነዉ። ምዕራባዉያንም ቢሆኑ ወያኔ ሠላማዊ ሠልፈኞችን በጥይት ሲጨፈጭፍና ህዘብን እያሰረ ሲያንገላታ አፋቸዉን ዘግተዉ የሚመለከቱ የወያኔ የእንጄራ አባቶች ናቸዉ። የወያኔ መሪዎች የምዕራባዉያን የገንዝበና የዲፕሎማሲ ከለላ ባያገኙ ኖሮ ዛሬ እነሱም እንደ ደረግ አባላት ቦታቸዉ ስደት ወይም አስር ቤት ይሆን ነበር።

ለመሆኑ ለምንድነዉ የአምባገነን መሪዎች እርግጫ፤ አስርና ግድያ ሰለባ የሆኑት የአዉሮፓ፤ የኢሲያና የአፍሪካ ህዘቦች እራሳቸዉን ከአምባገነኖች ቀንበር ለማላቀቅ የሚያደርጉትን ሰለማዊ ትግል ወያኔ እንደ ወንጀል የሚመለከተዉ? ደግሞስ ዩክሬን፤ ሰርቢያ፤ ጆርጂያና በሌሎችም አገሮች ዉስጥ የተካሄዱት ሠላማዊ የቀለም አብዮቶች ሁሉ ደም ያፋሰሱ ፀረ ህዝብና ፀረ አገር እንቅስቃሴዎች ከሆኑ ወያኔ ዬትኛዉን የትግል ስልት ይሆን “ሠላማዊ ትግል” ብሎ የሚጠራዉ? መደራጀት፤ መሰብሰብና ሀሳብን በነፃነት መግለጽ ሽብርተኛ ካሰኘ፤ በሰላማዊ መንገድ መታገል እንደ ወንጀል ከታየ ወያኔ ህጋዊ የትግል ስልት ነዉ ብሎ የፈቀደዉ ዬትኛዉን የትግል ስልት ነዉ? ወይስ ወያኔ እየነገረን ያለዉ ረግጬ እገዛችኋላሁ፤ አፋችሁን ዘግታችሁ ተገዙ ነዉ።

“የቀለም አብዮት” የሚል ስያሜ የተሰጠዉ የሰሞኑ የወያኔ ድራማ የሚጀምረዉ በጠመንጃ ድምጽና በእሳት ቃጠሎ ነዉ። ይህ ደግሞ የቀለም አብዮት ሠላማዊ አለመሆኑን ለማሳየት ሆን ተብሎ የተሰራ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ነዉ። ለመሆኑ የ1997ቱን የወያኔ ጭፍጨፋ ጨምሮ ከሰርቢያ እስከ ዩክሬን ፤ ከቱኒዝያ እስከ ግብፅ በተካሄዱት ሠላማዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ታንክና የታጠቀ ኃይል እየላከ ደም ያፋሰሰዉ ህዝብ ነዉ ወይስ የየአገሩ አምባገነን መሪ? “ዘር ከልጓም ይስባል” ነገር ሆኖባቸዉ በዘር ተስበዉ በአንድ ወቅት ያይ የነበረዉመን አይናቸዉን አሳዉሮት ነዉ አንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ አናቱ ላይ ቁጢጥ ብለዉ የሚረግጡትን ጨካኝ አምባገነኖች ማባረር ወይም ማስወገድ የተፈጥሮ መብቱ መሆኑን ለእሟሆይ ሚሚ ስብሀቱ ማን በነገራቸዉ?። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ይህንን የህዝብ የተፈጥሮ መብት እየተዋጉ ነዉ የአገርንና የህዝብን ደህንነት ለማሰከበር የማናደርገዉ ምንም ነገር የለም እያሉ በህዝብና በአገር ላይ የሚዘብቱት። ህዝብን በጅምላ አስረዉ ሰቆቃ እየፈጸሙና ሠላማዊ ዜጎችን በዉድቅት ሌሊት ከመኖሪያ ቤታቸዉ ጎትተዉ በጥይት ደብድበዉ እየገደሉ የህዝብን ደህንነት ለማስከበር ነዉ ብለዉ ቢነግሩን እየዋሹ አድገዉ እየዋሹ ያረጁትን የወያኔ መሪዎች ቀርቶ የሰማይ መልዐክትንም አናምናቸዉም።

በቀለም አብዮት ድራማ ዉስጥ ሌላም አንድ እጅግ በጣም የሚገርምም የሚያሳዝንም በወያኔ ተራ ዉሸትና አዉቃለሁ ባይነት የተጀቦነ ድንቁርና አለ። እሱም በእዉቀት አልባ ጭንቅላታቸዉ የሚታወቁት ተራዎቹ የወያኔ ካድሬዎች ቀርቶ ልህቃን ነን ባዮቹም በሚገባ ያልተገነዘቡት ነገር ግን በነጋ በጠባ ሊተነትኑት የሚሞክሩትና እንዳላዋቂ ሳሚ በነጋ በጠባ ቆሻሻ የሚቀቡት የሊብራል ፍልስፍና አስተሳሰብ ነዉ። የወያኔ ካድሬዎች እንዲያዉቁት የምንፈልገዉ አንድ ቁም ነገር ቢኖር ሊብራሊዝም ወይም የልብራል ፍልስፍና ወያኔዎች እንደሚያመልኩበት እንደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ደደቢት በረሃ ዉስጥ ለዚያዉም በዘረኝነት በተጨማለቀ ሰዉ ተጽፎ መክኖ የቀረ የመላ መላ ድርሰት አይደለም። ይልቁንም ሊብራሊዝም በመቶዎች በሚቆጠሩ አመታት ዉስጥ በተለያዩ ሊቃዉንት እየዳበረ የመጣና አሁንም በመደባር ላይ የሚገኝ ህያዉ ፍልስፍና ነዉ።

በመሰረቱ ሊብራሊዝም በወያኔዎች መንደር ሌላ አዲስ ትርጉም ካልተሰጠዉ በቀር በሦስቱ የመንግስት አካላት መካከል የስልጣን ክፍፍልና ልዩነት መኖር አለበት የሚል፤ በእኩልነት፤ በነፃነት ፤ በሰብአዊ መብቶች፤ በነፃ ሜድያ፤ ነፃ ምርጫ፤ ነፃ ገበያና በግል ኃብት ዙሪያ እጅግ በጣም ጠንካራ አቋም ያለዉና እነዚህ መብቶችና ነፃቶች መከበር አለባቸዉ የሚል የፖለቲካና የኤኮኖሚ ፍልስፍና ነዉ። ሀሳበቸዉን በነፃነት የመግለጽ መብት የሌላቸዉ ጥራዝ ነጠቆቹ የወያኔ ካድሬዎች ምን እንደሆነ እንኳን የማያዉቁትን ሊብራል ፍልስፍናን የሚያወግዙት ሆዳቸዉን ለመሙላት ሲሉ ነዉ እንጂ የሊብራሊዝም ፍልስፍና ቢገባቸዉና ቢረዱት ኖሮ ትግላቸዉ ከወያኔ ጋር ይሆንና ሆዳቸዉንም አዕምሯቸዉንም መሙላት ይችሉ ነበር። ምንግዜም ቢሆን ሊብራልዝምና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፊቱ ላይ ቀርቦለት ሊብራሊዝምን አዉግዞ አብዮታዊ ዲሚክራሲን የሚያወድስ ለሰዉ ልጆች በጎ ነገር አስቦ የማያዉቀዉ ሳጥናኤል ብቻ ነዉ። ወያኔንም ከሳጥናኤል ተርታ የምንመድበዉ ልክ እንደ ጌታዉ እንደ ሳጥናኤል ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድም ቀን በጎ ነገር አስቦ ሰልማያዉቅ ነዉ።

ሊብራሊዝም ወይም የሊብራል ፍልስፍና አገሮች አታሪካዊ አመጣጣቸዉን፤ ባህላቸዉንና የሚገኙበትን ተጨባጭ ሁኔታ እያጤኑ ለክተዉ የሚለብሱት ልብስ ነዉ እንጂ በአንድ ወጥ ተሰፍቶ እየተነቀለ የሚተከል የእድር ድንኳን አይደለም። ለምሳሌ ብዙዎቹ የአዉሮፓ አገሮች፤ አሜሪካ ፤ ህንድ፤ አዉስትራሊያና ደቡብ አፍሪካ የሊብራል ፍልስፍናን የሚከተሉ አገሮች ናቸዉ፤ ሆኖም የእያንዳንዱ አገር ፖሊቲካና ኤኮኖሚ በዚህ ፍልስፍና ይመራ እንጂ የተዋቀረበት መንገድ ይለያያል። የወያኔ ጀሌዎች ግን ሊብራሊዝምን በጅምላ ማዉገዝ ነዉ እንጂ እንደዚህ አይነቱን መልካምና ጠንካራ ጎኑን አይነግሩንም ።

ወያኔ የቀለም አብዮት ብሎ ከሰሞኑ የለቀቀዉ ለዛቢስ ድራማ ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል ማስቀረት የማይችለዉን ኢትዮጵያ ዉስጥ መሰረታዊ ለዉጥ የመካሄዱንና ወያኔም የመደምሰሱን እዉነታ ለማስቀረት የሚሞክር የፍርሀት ድራማ ነዉ። ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሠላምና መረጋጋት እንዲኖር ከፈለገና አገራችን ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት የመበታተን አደጋ ተሰዉራ በዕድገት ጎዳና ወደ ፊት እንድትገሰግስ ከልቡ የሚመኝ ከሆነ ማድረግ ያለበት ሰዉ ሰዉ የማይሸት ድራማ እየሰራ መልቀቅ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ መብትና ነፃነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማክበር ብቻ ነዉ። ወያኔ የኢትዮጵያን የፖለቲካና የኤከኖሚ መዋቅሮች ብቻዉን ተቆጣጥሮ፤ አገርን በዘረኝነት ፖሊሲ እየመራና ከሱ ጋር የማይስማሙ ዜጎችን ከቤታቸዉ ጎትቶ እያወጣ የሚገድል ከሆነ በዚያ በቀለም አብዮት ድራማ መግቢያ ላይ ሊያሳየን የሞከረዉ የጥይት ፍንዳታና የእሳት ቃጠሎ ኢትዮጵያ ዉስጥ የማይከሰትበት ምንም ምክንያት የለም። ስለዚህ ወያኔ እሩቅ አገር እየሄደ ስለ ዩክሬን፤ ስለ ጆርጂያና ስለ ኪርጊስታን መንግስታት ሙስናና አምባገነንነት ከሚነግረን እኛ በግልጽ የምናየዉን የራሱን ቆሻሻ ማራገፍ ወይም እሱ እራሱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ ላይ ተጠራርጎ መርገፍ አለበት። ወያኔ ይህንን የማያደርግ ከሆነ ጥቁር ይሁን ነጭ ብርቱካናማ ወይም ጽጌረዳ ኢትዮጵያ ዉስጥ አብዮት መካሄዱ አይቀርም።

No comments:

Post a Comment