Tuesday, April 8, 2014

የሃይማኖት ነፃነት ከወዴት አለ?

በቅዱስ ዮሃንስ





በሀገራችን ኢትዮጵያ ጥንታዊው ሃይማኖቶች ማለትም ኦርቶዶክስ ክርስትናና እስልምና ለረጅም ዘመናት ሳይነጣጠሉ ተቆራኝተው በአንድነት የኖሩ መሆናቸውን የታሪክ ማኅደር በሰፊው ይመሰክራል፡፡ በሀገራችን አንድነት፤ በሕዝባችንም ነፃነት እንዲሁም በቤተ እምነቶቻችንን ጽናትና ጥንካሬ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ፈተናዎች ቢገጥሙም፤ በቆራጥ የሃይማኖት አባቶቻችን ጽኑ አመራር፣ ተጋድሎና መስዋዕትነት የተጋረጡባቸውን መከራ እያለፉ ሃይማኖቶቻችንን ጠብቀው፤ የሀገራችንና የሕዝባችንም አንድነትና ነፃነት ሳያስደፍሩ አቆይተውልናል፡፡ ፀረ-ኢትዮጵያዊና ፋሽስቱ ወያኔ ከሽፍትነት ወደ ገዥ ቡድንነት ተሸጋግሮ ሥልጣን ላይ ከወጣበት 23 ዓመታት ጀመሮ የጥፋት እጁን ዘርግቶ የሀገራችንን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣል እየተፍጨረጨረ ከሚገኝባቸው በርካታ አጀንዳዎች መካከል ከፍተኛውን እጅ የያዘው እነዚህን ታላላቅ እምነቶች ማጥፋት እንደሆነ ይታወቃል። ፋሽስቱ ወያኔ የሃይማኖትን ነፃነትን እየተጋፋና በገሃድ ጣልቃ እየገባ ይሄን የሃይማኖት መስመር ነው መከተል ያለባችሁ፤ ሃይማኖቱንም የሚመሩት ልሂቃን እኔ ካልኩት ውጭ አይሆኑም በማለት የሃይማኖት መሪዎችን እየቀባና እየሾመ፤ የሃይማኖት አመለካከትን /Doctrine/ በጉጅሌው ፓርላማ ሳይቀር እየተነተነ የቱ ልክ እንደሆነ የትኛው የተሳሳተ መስመር ውስጥ እንዳለ እየሰበከ ይገኛል።   


ታዲያ የሃይማኖት ነፃነት የት አለ?   



የሙስሊሙ ህብረተሰብ ግልፅና የማያሻማ የዕምነት ነጻነት ጥያቄ ካነሳ ድፍን ሁለት አመታት ተቆጠሩ። የጉጅሌው ወያኔ አገዛዝ አህባሽ የተሰኘውን ባዕድ መጣሽ የሀይማኖት አስተምህሮ በግድ ሊጫንብን አይገባም፣ ለሀይማኖት መሪነት የተቀመጠው መጅሊስ (የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት) አይወክለንም፤ መሪዎቻችን በመስጊድ ነፃና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንምረጥ ሲሉ በሰላማዊ መንገድ በጠየቁ ህዝበ ሙስሊሞች ላይ የፋሽስቱ ወያኔ አጋዚ ጦር በወሰደው እርምጃ ከአርሲ ገደብ አሳሳ እስከ አወልያ የንፁሃንን ህይወት አጥፍቷል። በአዲሳባ፡ ደሴና በሻሸመኔ ኢማሞቻችን/ መሪዎቻችን ይፈቱ እያሉ በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ባሰሙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የፋሽስቱ ወያኔ አጋዚ ጦር የግፍ ግድያ መፈጸሙን ማንስ ይዘነጋዋል? ልጆች፣ አባቶች፤ እናቶች፣ እህቶችና ወንድሞች በጉጅሌው ወያኔ ትዕዛዝ የጥይት ሰለባ ሆኑ። ፋሽስቱ ወያኔ በሺህ የሚቆጠሩ ለእምነታቸው ዘብ የቆሙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ በልዩ ልዩ እስር ቤቶች በጅምላና በተናጠል በማሰር የማሰቃየት ተግባር እየፈፀመ ይገኛል። አገዛዙ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በሌላ ዕምነት ተከታይ ወገኖቹ ጥርጣሬ እንዲፈጠር አንዴ የአሸባሪ ተልዕኮ ለማስፈፀም የመጡ ሌላ ጊዜ በአገሪቱ በሃይል የሸሪኣ ስርዓት ሊዘረጉ ነው በማለት ውዥንብር እየፈጠረም ይገኛል። ይህ በንጹሃን ደም የሰከረ የፋሽስት አገዛዝ ስልጣኑን ለማቆየት የህዝበ ሙስሊሙን እንቅስቃሴ አደጋ አድርጎ በመቁጠር ሙስሊሙና ክርስቲያኑን ለማጋጨት ሰፊ ቅስቀሳ ማድረጉን ዛሬም ድረስ አላቋረጠም። ግን ኧረ ግን ይህንን ጸረ ሃይማኖት አገዛዝ በእምነታችን ላይ እየፈጸመብን የሚገኘውን በደል ስለምን በተጠናከረ ሁኔታ መመከት ተሳነንን?  እስከ መቼ እየተገደልን፤ እምነታችንን እያስደፈርን መገዛትን መረጥን?    

በፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ የቤተክርስቲያን ህልውናም ከምንጊዜውም በላይ የከፋ አደጋ ላይ ወድቋል። ቤተክርስቲያን ካሳለፈቻቸው የመከራ ዘመናት ሁሉ አሁን ባለንበት ወቅት እጅግ የረቀቀ የጥፋት እና የተንኮል ሴራ ተደቅኖባታል፡፡ ወያኔዎች ያለምንም ይሉኝታ እና ፍራቻ የዘረጉትን የጥፋት ሴራ እየፈጸሙት ይገኛሉ።  ባስረጅነት ለመጥቀስ ያክል መናኝ ባህታውያን በጸሎት ተወስነው የሚኖሩባቸውን ታሪካዊ ገዳማት እንደ ታላቁ የዋልድባ ገዳምን በልማት ስም ይዞታውን በመቆጣጠር የቅዱሳን አባቶችን መካነ መቃብር አሳርሰዋል፣ ዝቋላ አቦ፣ አሰቦት ገዳም የመሳሰሉትን በእሳት እንዲቃጠሉ አድርገዋል፡፡ የጉጅሌው ወያኔ አገልጋይ ካድሬዎች በገዳማቱ የለኮሱትን እሳቱ ለማጥፋት ግንባር ቀደም የሆኑ እና በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰው ጥፋት እንዲቆም አቤት ያሉ ሰዎች በፋሽስቱ ወያኔ የደህንነት ሀይሎች ተደብድበዋል፣ ታስረዋል ፣ተገድለዋል፡፡ የወያኔ አገዛዝ ባንድ በኩል አገዛዙ በሀይማኖት ጉዳይ ታልቃ አይገባም እያለ ሲደሰኩር በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ካድሬዎችን የሀይማኖት ካባ እያለበሰ በየቤተ- ክህነቱ በመሰግሰግ የማምለኪያ ቦታዎችን ወደ ገንዘብ መሰብሰቢያ ተቋማነት እየቀየራቸው ይገኛል፡፡ በአንጻሩ ስለኢትዮጵያ አንድነት ቀን ከሌሊት የሚጽልዩ አባቶች እንደጠላት ተፈርጀው ለእስር፣ ለእንግልት እና ለግድያ ተዳርገዋል። ለህዝበ-ምእመኑ እና ለቤተክርስቲያኗ ነፃነት ክብር ደንታ የሌላቸው ወያኔዎች የእግዚያብሄርን ቤት የፖለቲካ እድሜ ማራዘሚያቸው በማድረግ ለህዝበ ክርስቲያኑ ያላቸውን ንቀት በገሀድ እያሳዩ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ህዝበ ክርስቲያኑ ስለምን ለእምነቱ ዘብ መቆምና መጋደል ተሳነው? እውነት እምነትን ከማስደፈር በላይ በደል ከወዴትስ አለ?   
      
የጉጅሌው ወያኔ አገዛዝ በአዲስ አበባ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ዛሬ በሙስሊሞች ላይ እየፈጸመ የሚገኘውን የሰብአዊ መብት ረገጣ በልደታ ማርያም መፈጸሙን ማንም ይዘነጋዋል ብየ አላስብም። በእምነታችን ጣልቃ አትግቡ የቤተክርስቲያኑ ንብረት ለቤተክርስቲያኑዋ መዋል አለበት የሚል ተቃውሞ ያሰሙ ምዕመናንን፤ የቤተክርስቲያኑዋ አስተዳደርን፣ ካህናቱን እና የሰበካ ጉባኤ አባላቱን  ከተቃዋሚ  ፓርቲዎች ጋር እያጣቀሱ አመጸኞች አገዛዙን በሀይል ለመጣል ድብቅ ዓላማ ያላቸው በማለት የተለመደ የሃሰት ወነጀላ አደረገ። ውንጀላውን ተከትሎ በ ህዳር 9 ቀን 1995 ዓ.ም የልደታ ምዕመናን በወያኔው ቴሌቪዥን አመፀኞች፣ ፀረ ሰላም ኃይሎች፣ ስልጣን ናፋቂ  ተቃዋሚዎች የሚመሩት መባሉን በመቃወም፤ ጥያቄያቸውን በሰላም ለማሰማት ለምህላ በቤተክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ የተሰበሰቡ ምዕመናንን አረመኔው የፋሽስቱ ወያኔ አጋዚ ጦር ቤተ እምነቷን ጥሶ በመግባት በቤተክርስቲያኑዋ የተሰበሰቡ ምዕመናንን በዱላ መደብደብ ያዙ። በቤተክርስቲያኗ የሚደበደቡት ምዕመናን ዋይታና እሪታ አሰሙ፤ የቤተክርስቲኑዋ ደውል ለድረሱልን ተደወለ። ቤተ ክርስቲያኗ በክርስቲያኖች ደም ጨቀየች። በፋሽስቱ ወያኔ አጋዚ ፖሊስ ከተፈነከተ ጭንቅላታቸው የሚወርደው ደም ያዞራቸው ምዕመናን በያሉበት ወደቁ። ለጸሎት የተለበሰ ነጠላ የደም ጃኖ መሰለ። በአጠቃላይ ሰላማዊ የሆነውን የምዕመኑን ተቃውሞ በደቂቃ ውስጥ ሽብር ነዙበት። ካህናት ጥምጣናቸውን እየፈቱ፣ የክህነት ልብሳቸውን እያወለቁ፣ ህፃናትና ሴቶች ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ሽማግሌዎች ጭምር ድብደባ እንግልት እና ፀያፍ ስድብ ወረደባቸው። በባዶ እግራቸው እየተደበደቡ፣ እግር የሚወጋ ኮረት በፈሰሰበት እንዲራመዱ፣ እንደሙቀጫ እንዲንከባለሉ፣ ተዘቅዝቀው ተደፍተው የውስጥ እግራቸውን ተገረፈ። ስለ እውነት ግን ይህንን በደል ማንስ ይዘነጋዋል? ወይንስ ግን በደል ይለመዳል?  

በአወልያ የተጠነሰሰውን ሰላማዊ ጥያቄን ከመመለስ ይልቅ የጉጅሌው ወያኔ አገዛዙ አንዴ አሸባሪ ሌላ ጊዜ የሸሪአ ስርዓትን በሀይል ለማቋቋም የሚጥሩ በማለት የክርስቲያን ተቆርቋሪ መስሎ ህዝቡን ለመከፋፈልና በትርምስ  የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየጣረ ነው።  ጉጅሌው ወያኔ በአወልያ የተቀጠረውን የሰደቃና የአንድነት በዓል ለማደናቀፍ፤ የሰላምና የህግ ያለህ ያሉትን ህዝበ ሙስሊም በጉልበት ጥሶ በርካቶችን ደብድቦና ገሎ በመቶ የሚቆጠሩትን አስሮ በለመደው ስልት  ለመዝለቅ ቢያስብም የአወልያ መዘጋት ተስፋ ያላስቆረጠው የዕምነት ነፃነታችን ይከበር፣ ድምፃችን ይሰማ ያለው ህዝበ ሙስሊም በአንዋር ተሰባስቦ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ማቅረብ ቀጠጥሏል። እንደ ልደታ ቤተክርስቲያን ሁሉ አንዋር መስጊድንም ባለቆመጥና ባለመሳሪያዎቹ የፋሽስቱ ወያኔ አጋዚ ጦር ቤተመቅደሱን ሁሉ እንደረመረሙት ያንኑ በመስጊድ ደገሙት። በአንዋርም የሙስሊሞች ዋይታ ሆነ፤ የንፁሀን ሙስሊሞች ደም ፈሰሰ። ብዙዎች ተደበደቡ ሺዎች ተግዘው በሰንዳፋ በሸዋሮቢትና በማይታወቅ እስር ቤት ጭምር በጅምላ ስቃይ ተፈፀመባቸው፤ አሁንም ድረስ የህዝበ ሙስሊሙ ሰቆቃው በመላ ሃገሪቱ ቀጥሏል። በርግጥ ከአርሲ ገደብ አሳሳ እስከ አወልያ የንፁሃኑን ህይወት በመቅጠፍ፣ ሺዎችን በማሰር፣ በመደብደብ፣ የፈጠራ ወንጀል በመፈብረክ፣ ትላንት የልደታ ማርያምን ምእመናን የእምነት ነፃነት ጥያቄ እንደጨፈለቁት ግን የሙስሊሙን ጥያቄ በአንዴ መጨፍለቅ አለመቻላቸውን እያየን ነው። ልደታ ማርያምን ዘግተው ቅዳሴ እንዳስተጓጎሉት አንዋርን ግን መዝጋት አልቻሉም።                  
      
አሁን እምነቶቹ ተከታዮች (ምዕመናን) ምን ይጠበቃል?   


የክርስትናም ሆነ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በጋራ የዋልድባም መደፈር፣ በአወልያ ተነስቶ እስከ አንዋር የቀጠለው የዕምነት ነጻነት የመብት ጥያቄ በጋራ ይመለከተናል በማለት መቀጠል አለባቸው። በዋልድባ ቅዱሱን ስፍራ አትረሱ ያሉ መነኮሳትን እየደበደበ በማሰር ፀያፍ ስድብ የሰደበ አገዛዝ ዛሬ በክርስትና ስም መነገድ አትችልም ሊባል ግድ ነው። የሚያደርገው ጸረ ሙስሊም የአፈና እንቅስቃሴና የግፍ ግድያ ሁላችን በጋራ በመነሳት ልናወግዘው ወቅቱ አሁን ነው። የእምነቶቹ ተከታዮች በክፉዎች ወያኔዎች ሐሳብ መከፋፈሉንና መበታተኑን ትተው እንደ ቀድሞ አንድነትን በማጠናከር ሀገሪቱን ከተኩላዎች መጠበቅና መታደግ ይኖርባቸዋል። የፋሽስቱ ወያኔ የግፍና የሰቆቃ አገዛዝ በቃኝ በማለት በድፍረት መናገር ይኖርበታል፤ ከዚህ የባሰ ምንም ሊመጣ አይችልምና፡፡ እዚህ ላይ ለኢትዮጵያዊያን ክርስቲያንና ሙስሊሞች ያለቻቸው አንዲት ሀገር ስለሆነች አንድነታቸውን በማጠንከር ክርስቲያኑ ለሙስሊሙ፣ ሙስሊሙም ለክርስቲያኑ ድጋፉን በመስጠት መተባበር አለበት፡ ፡    

በአጠቃላይ ለሙስሊሙም ሆነ ለክርስቲያኑ ያለችን አንዲት ሀገር ናት፤ እሷም ኢትዮጵያ  በቃ!፡፡ ያለን ዕድል የእኛን ኢትዮጵያ ለእኛ ለዜጎች እንድትመች ማመቻቸትና መጠቀም ነው፡፡ ለእኛ ነፃነት ሌላ እንዲታገልልን መጠበቅ የዋህነት ነው። በዚህም የማህበራዊ ሚዲያዎችን (ፌስቡክ፣ ኢ- ሜይል፣ የሞባይል ፅሑፍ አገልግሎት፣ … የመሳሰሉትን) በመጠቀም ለአምባገነኖች ጥቃት በር ባለመክፈት የተለያዩ የለውጥ እንቅስቃሴ መንገዶችን መተግበር ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ ለኢትዮጵያዊ ክርስቲያን በችግሩም ሆነ በደስታው ጊዜ ከጐኑ የማይለየው ከምዕራባዊያን ክርስቲያኖች ይልቅ አጠገቡ ያሉት ወንድምና እህቶቹ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ለሙስሊሙም ቢሆን የሚደርስለት ከማያውቃቸው የአረብ ሀገራት ሙስሊሞች ይልቅ ወንድምና እህቶቹ ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ይሄ ለሁላችንም የሚጠፋን አይመስለኝም፡፡ አሁን ግን ፋሽስቱ ወያኔና ክፉዎቹ ግብረአበሮቹ የዚህን አቅጣጫ ሊያስቀይሩ ሌት ተቀን እየሰሩ ነውና አንድነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክረን ማሳየትና የተሻለ ጊዜና ስርዓት እንዲመጣ ትግላችንን ከመቸውም ጊዜ በላይ ማጠናከር ያስፈልጋል፡ ፡ በሃይማኖትና ቋንቋ እንዲሁም በብሔር ለሚከፋፍሉ ዲያቢሎሶች በሩን መክፈት የለብንም፤ እየተፈፀመ ያለው በደልና ሰቆቃ በሁሉም ላይ ነውና ሁሉም ለመብቱ አንድ ሆኖ መተባበርና መነሳት ይኖርበታል፡፡ 

No comments:

Post a Comment